እድሜ እየገፋ ጉልበታቸው ቢደክምም አሁንም ከወጣት እኩል የመሥራት ወኔ አላቸው፤ አቅም፣ እውቀትና ፍላጎት ጭምር። ትልልቅ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ድርጅቶች ላይ ሳይቀር ስልጠና በመስጠት ይታወቃሉ። 52 ዓመታትን በውሃ ሀብት ዙሪያ እየሰሩ አሳልፈዋል፤ የዛሬው የህይወት እንዲህ ናት አምድ እንግዳችን አቶ ፋንታ ፈይሳ። በበጎ ተግባራቸው የሚታወቁ፣ ሀገር ወዳድ መሆናቸውን ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል። የአንገትና የጣት ወርቅ መሸለማቸው የዚህ ተግባራቸው አንዱ ማሳያም ነው። እናም ይህ ተሞክሯቸው ለብዙዎች በአርአያነት ያስተምር ዘንድ የህይወት ተሞክሯቸውን እንሆ አልን።
ኢዶሳ
የልጅነት ህይወታቸው በፈተና የታጠረ እንደነበር ይናገራሉ። በቤተሰብ ውስጥ ተንደላቅቀው አላደጉም። ይልቁንም ‹‹እንደ ተልባ በእሳት የተቆላሁበትና ችግር ያነደደኝ ጊዜ ነው። በልቼ የጠገብኩበትን ቀን አላስታውስም። ለዚህ ሁሉ ችግር ዋናው ምክንያት የአባቴ መሞት ነው።›› ይላሉ ስለልጅነታቸው ሲያወሱ።
አባት ከሞተ በኋላ በአካባቢው ባህል መሰረት ሚስት በውርስ ለሌላ ዘመድ ወይም ወንድም ትሰጣለች። የእርሳቸውም እናት በባህሉ ውስጥ የማለፍ ግዴታ ይጠብቃቸው ነበር። ነገር ግን “እኔ ራሴን ማስተዳደር እችላለሁ፤ የባለቤቴን ንብረት ይዤ ልጆቼን ላሳድግ” በማለት አሻፈረኝ አሉ። ሆኖም ማንም ሊቀበላቸው አልቻለም። እንደውም ፈላጊያቸው በዛና እኔ ልውረስ እኔ በሚል ቤተሰብ ከቤተሰብ ተበጣበጠ። በግዳጅ እወርሳለሁ ያለውም ሰው ተገደለ። ከዚያ የአቶ ፋንታ እናት በነብስ ግድያ ተይዘው ወህኒ ወረዱ። ይህ ሁኔታ ደግሞ ለያኔው ህጻን ኢዶሳ እናትም አባትንም አሳጣው። የነብሰገዳይን ልጅ ማንም አይፈልገውምና አባትም እናትም የሌለው ተንከራታች ሆነ። በተለይ አጎቱ ጋር በነበረበት ጊዜ ስቃዩ ይበረታ እንደነበር አይረሳውም።
የትናንቱ ኢዶሳ የዛሬው አቶ ፋንታ ሲናገሩት፤ “ባዕድ ሰው እኔን አስተምሮኛል፤ መሸሸጊያም ሆኖኛል። በእርግጥ እኔም ብሆን በጉልበቴ እሰራ ነበር። በሰራተኝነት ተቀጥሬ ከብት እያገድኩ ዓመታትን አሳልፌያለሁ። “ይላሉ። እናታቸው ሲፈቱ ደግሞ የአባታቸው ንብረት ተሸጦ አገልግሎት ላይ ውሏልና የትውልድ ቀያቸውን ትተው ወደ እናታቸው ተጠጉ። ሆኖም ይህም ጊዜ ጥሩ እንዳልሆነላቸው ያስረዳሉ። ምክንያቱም እናት ኑሮን ለመግፋት ሲሉ ሌላ ትዳር መስርተው በቤት ውስጥ የእንጀራ አባት ተፈጥሯል። ከእርሱም ጋር ስለማይስማሙ በዚያ ማደሪያቸውን እያደረጉ ለሚበሉት፤ ለሚጠጡትና ለትምህርት ቁሳቁስ ማሟያ የሚሆናቸውን ገንዘብ ለማግኘት እየተላላኩ፤ እየተሸከሙና ከብቶች እየጠበቁ ያሳልፋሉ።
የወላጅ እንክብካቤ ማጣት ከነበራቸው የልጅነት ባህሪ አላቆ ነጭናጫና ተንኮለኛ አድርጓቸው እንደነበር የሚያነሱት ባለታሪኩ፤ በልጅነታቸው ከማንም ጋር ተስማምተው ሰርተው እንደማያውቁ ይናገራሉ። በወንጭፍ ሰዎችን ይደበድቡ፤ መንገድ ዳር ሆነው ይሳደቡ እንደነበርም አይረሱትም። በሀይለኛነታቸውም የሚናገራቸው ሰው እንዳልነበረ አጫውተውኛል።
አቶ ፋንታ የልጅነት መጠሪያቸው (ትምህርት እስኪገቡ ድረስ) ኢዶሳ የሚል ነበር። ይሁንና በወቅቱ በአማራ ስም መጠራት የበለጠ ክብር ያስገኛል ተብሎ ስለሚታመን ስማቸው በፋንታ ተተክቷል። ከዚህ በተጨማሪ ፋንታ አባሻረው የሚባሉ ብልጥና አዋቂ፤ የንጉሡ ምስለኔ የሆነ አማራ በአካባቢው ይገኙ ስለነበርና አክስታቸውም ያንን ሰው አግብታ ስላለች እንደእርሱ እንዲሆንልኝ በሚል ፍላጎት ስማቸው በፋንታ ተቀይሯል።
አቶ ፋንታ ይህ መሆኑ ባያስከፋቸውም የአባታቸው ስም በ”ገቢሳ” ማለትም በእንጀራ አባታቸው ስም መቀየሩ አስቆጥቷቸው ነበር። ምክንያቱም እንጀራ አባታቸው ብዙ ነገራቸውን ወስዶባቸዋል፤ ከልጅነት ጨዋታ አላቆ የሰው ፊት እንዲገርፋቸውና በሰው ቤት እየሰሩ እንዲማሩ ያደረጉ ሰው ናቸው። ስለዚህ በምንም ተኣምር አባትነትን ሊተኩ አይችሉምና “የወላጅ አባቴ ስም እንዲመለስ” ብለው በብዙ መንገድ ታገሉ።
መልሱን ያገኙት ግን አንደኛ ወጥተው ሽልማት ተቀበል ሲባሉ ‹‹አልቀበልም መጀመሪያ የአባቴን ስም መልሱ›› ካሉ በኋላ ነው። በወቅቱ መምህሮቻቸውና ተማሪዎች በጣም ይወዷቸው ነበርና እንዲህ መሆን የለበትም በማለት አብረዋቸው ተሟገቱ። በዚህም የአባታቸው ስም በትክክለኛ ወላጅ አባታቸው እንዲቀየርላቸው ሆነ። አቶ ፋንታ ፈይሳም ተብለው ከዚያ በኋላ መጠራት እንደጀመሩ ይናገራሉ።
አቶ ፋንታ በልጅነታቸው በጣም ወተት የሚወዱ ናቸው። በዚህም ወተትን ለማግኘት መስረቅን ልማዳቸው አድርገው ነበር። ይህ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ እናታቸው ቅቤ ለማውጣት ሲሉ ወተት ለማንም አይሰጡም። በዚህም ሁልጊዜ ከእናታቸው ጋር ይጣሉ እንደነበር ያስታውሳሉ። አቶ ፋንታ በአጭር ርቀት ፈጣን ሯጭ፤ በመሰናክልም ሆነ በመደበኛ ዝላይም ወረዳውን ሳይቀር ወክለው በመጫወት አሸናፊ ነበሩ። በእግር ኳስም ቢሆን ሥራ ላይ እያሉም የአጥቂ ቦታን በመያዝ ውሃ ልማት ዋንጫ እንዲያገኝ ያደረጉ ናቸው።
ትውልዳቸው በኦሮሚያ ክልል ከደንቢዶሎ 27 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ቄለም ወለጋ ዞን አዋገላን ወረዳ አዋሞይ ቀበሌ አዋባጡራ መንደር ውስጥ ነው። ችግር ሲበዛ ያስተምራል፤ አማራጭ መንገድንም ያመላክታልና የልጅነት ህይወቴ ዛሬ ችግር አዲስ ነገር እንዳይሆንብኝ፤ እንዴት በቀላሉ ማለፍ እንዳለብኝ አስተምሮኛል ይላሉ።
ራስን ማብቃት
ከብት በመጠበቅ፤ ከትምህርት ቤት ያገኙትን እውቀት የመማር ዕድሉን ላላገኙት በማስተማር፤ የባላባት ልጆችን በማስጠናትና በመላላክ ባገኙት ገንዘብ ነበር ራሳቸውን ለትምህርት ያበቁት። ያኔ ለመማሪያ የሚያስፈልጋቸውን ደብተር፣ እስክሪብቶና አልባሳት ግዛልኝ የሚሉት አንድም ሰው አልነበራቸውም። ለመማር ደግሞ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ምክንያቱም ካልተማሩ ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን ካሉበት አዘቅት ውስጥ ማውጣት አይችሉም። እናም እርሳቸው እንደሚሉት፤ በችግር እየተቆሉም ቢሆን ትምህርታቸውን እስከ 12ኛ ክፍል መከታተል ችለዋል።
የተማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ቤተሰብ ካለበት ብዙ ባይርቅም በሥራ እየደከሙ ነበር የሚማሩት። ይህም ሆኖ ውጤታቸው ያማረ ነው፤ ደረጃቸውንም ተነጥቀው እንደማያውቁ ይናገራሉ። ደሚዶሎ ከመሄዳቸው በፊት የቄስ ትምህርት ለመቅሰም አንበላና ሞጆ ቡሔ ቡራዮ የሚባል ቦታ ላይ ሄደው ፊደል የቆጠሩት እንግዳችን፤ ዘመናዊ ትምህርትን ሀ ያሉት በደንቢዶሎ ከተማ ላይ ቤቴል መካነ ኢየሱስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ቀጥለው አፄ ሰይፈአርድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ስምንት ከተማሩ በኋላ ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በደንቢዶሎ አፄ ዘርዓያቆብ ትምህርት ቤት ተምረው አጠናቀቁ።
ከ12ኛ ክፍል በኋላ ምንም እንኳን ውጤታቸው ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባቸው ቢሆንም መቀጠል ግን አልቻሉም። በሰው ቤት ተቀጥሮ መማሩ ከበዳቸው። በዚያ ላይ ዩኒቨርሲቲ ቢገቡ ለአንዳንድ ወጪዎች ማንም ሊሸፍንላቸው አይችልም። ስለዚህ ያላቸው አማራጭ በ12ተኛ ክፍል ውጤታቸው ተወዳድሮ መቀጠርና ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ማገዝ ነው። በዚህ ሁኔታ በውሃ ልማት ተቀጠሩ። ረጅም ዓመታትንም በዛው አሳለፉ።
በሥራ ምክንያት አዲስ አበባ ተዛውረው ከመጡ በኋላ ግን የመማር ጥማታቸውን ለማርካት በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመሩ። እዛም በኢኮኖሚክስ ትምህርታቸውን አጥንተው በማዕረግ ተመረቁ። አቶ ፋንታ ከልጅነት ጀምሮ በችግር ቢፈተኑም የደረጃ ተማሪ ነበሩ። ከአንድ እስከ 12ኛ ክፍል ሲማሩም አንደኛ በመውጣት የተለያዩ ሽልማቶችን ያገኙም ነበር። የተማሪዎች ፕሬዚዳንትም ሆነው ተማሪዎችን ያስተዳድሩ እንደነበርም አይረሱትም።
አቶ ፋንታ ሥራ ላለማቋረጥና ከተማሪዎች ላለማነስ ሲሉ ትምህርታቸውን ይከታተሉ የነበረው በማታ ትምህርት ሲሆን፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለመያዝ ሰባት ዓመታት ፈጅቶባቸው ነበር። በውሃ ላይ በሚሠሯቸው ሥራዎች ስፔሻላይዝድ ለማድረግም የተለያዩ ኮርሶችን በኬኒያ፣ ታንዛንያና ደቡብ አፍሪካ ወስደዋል። ሰርተፊኬትም አግኝተዋል።
በመንፈሳዊ ትምህርትም ቢሆን እንዲሁ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንድፈሀሳባዊ ጥናት ወይም በባይብሊካል ቲወሬቲካል ስተዲ በሚል መስክ በኢገስት ወይም ኢትዮጵያ ስኩል ኦፍ ግራጂዮት በተባለ የግል ኮሌጅ ተም ረዋል።
የካቲት 66 በተባለ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር ባለ ኮሌጅ በመግባት በፖለቲካ ሳይንስ ትምህርትም ዲፕሎማ ይዘዋል። በቢሸፍቱ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት እንዲሁ በውሃ ማኔጅመንት ላይ በመማር ሰርተፊኬት አግኝተዋል። በዓለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የተዘጋጁ ስልጠናዎችን ወስደዋል። ለእነዚሁ ተቋማት ስልጠና ሰጥተዋል።
52 ዓመትን በውሃ ልማት
‹‹ውሃ የጠራኝ ገና ከጅምሩ ነው። በ12ተኛ ክፍል ውጤቴ ስወዳደር በቀጥታ ያለፍኩት ትምህርት ሚኒስቴርና ውጭ ጉዳይ ቢሆንም በውሃ ልማት ተጠባባቂ ስለነበርኩ ውጤት ሲታወቅ ከሁለቱ ቀድሞ የተነገረው ውሃው ነው። እናም አንድ ጓደኛዬ በውድድሩ ያለፈ ቢሆንም የተሻለ ነገር አግኝቶ አሜሪካ ሲሄድ ሄጄ እንድጠይቅ ነገረኝ። ስጠይቅም ይህንን ማድረግ ትችላለህ በሚል ከባድ ከባድ ነገር ይጠይቁኝ ጀመር። የምላከውም ጠረፍ እንደሆነ ገለፁልኝ። የሚበላው እንኳን የሌለው ሰው ምን ምርጫ ይሰጣል በሚል አደርገዋለሁ አልኩና ገባሁ›› ይላሉ ወደ ውሃ ልማት ሥራ እንዴት እንደገቡ ሲያወሱ።
አቶ ፋንታ ባሌ፣ ሮቤ፣ አርሲ፣ ሐረርና ኡጋዴንን በውሃ ሀብት ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን የሠሩ ሲሆን፤ ብዙ ለውጥ ያመጡ ተግባራትንም ለዓመታት ከውነዋል። ለሪፖርት ዋና መሥሪያ ቤት ሲመጡ ደግሞ በዚሁ የሚያስቀራቸው አንድ ዕድል ገጠማቸውና በባለሥልጣን ደረጃ እንዲሠሩ ሆነ። ዕድሉ የልጅነት ብቃታቸው የሰጣቸው ሲሆን፤ ለእግር ኳስ ዋንጫ የቀረበው ውሃ ልማት ብዙ ተጨዋቾች ስላልነበረው እንዲካተቱ አደረጋቸው።
እንግዳችን ግን ምንም እንኳን ከእነርሱ እኩል ልምምድ ባያደርጉም አቅሙ ነበራቸውና በቴስታና በእግራቸው በመቷት ኳስ ሁለት ጎል በማስቆጠር ዋንጫው እንዲወሰድ አደረጉ። ይህንን ሁኔታ ሲከታተሉት የነበሩት የወቅቱ የውሃ ልማት ኃላፊም አስጠርተው ካነጋገሯቸው በኋላ ሊሸኟቸው ሲሉ ከምስጋና ባለፈ ከእነርሱ ጋር ይቆዩ ዘንድ የቡድኑ ልመና በረታ። በዚህም የሥራ ቆይታቸው በባለሥልጣን መሥሪያቤቱ እንዲሆን ተፈቀደ።
36 ዓመታትን በመንግሥት ቅጥርና ቀሪውን በመጠጥ ውሃና ፍሳሽ የምክር አገልግሎት ፈቃድ በማውጣት የተለያዩ ጥናቶችን ሲሰሩ የቆዩት አቶ ፋንታ፤ ተቋማትን እየወከሉ በማማከር ሥራ ተሰማርተው የውሃ ሀብቱን አጠናክረዋል። ዛሬ ድረስ በውሃ መስኖና ኢነርጂ እየሰሩ የውሃ ጥማቴ ገና አረካም ይላሉ። በውሃ ላይ ብዙ የሚሰሩ ነገሮች እንዳሉም ይናገራሉ። ስለዚህም ውሃ ሕይወት ነው የሚባለውን በአባባል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በህይወት እየኖርኩ ስላየሁት አሁንም ሌላውም ሰው ህይወትነቱን እንዲያረጋግጥ ለማድረግ እሰራለሁ ብለውናል።
በ52 ዓመት ጉዟቸው በፌደራል ደረጃ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን፣ ውሃ ልማት ባለሥልጣን፣ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን እየተዘዋወሩ የሠሩ ሲሆን፤ ውሃን ሳይለቁ ወደክልል ቢሮም ተዛውረው በኦሮሚያ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ውስጥ በህብረተሰብ ተሳትፎና የባለድርሻ አካላት ድርጅት ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር የዘርፍ ሃላፊ በመሆን 16 ዓመታትን አሳልፈዋል።
እናም በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ከህብረተሰብ ተሳትፎ ባለሙያነት እስከ ቡድን መሪነት፤ በአፈር ጥናት ምርምር ቴክኒሽያንነት፣ ከገንዘብ ያዥነት እስከ በጀትና ፕሮግራም አስተዳደር ሃላፊነት ደረጃ ሰርተዋል። ሶሾሎጂስት፣ ኢኮኖሚስት በመሆንም ተቋሙን አገልግለዋል። ከዚያ ባሻገር ስለውሃ ጥቅም ለህዝብ አስተምረዋል፤ ቅስቀሳም አድርገዋል፤ በተለይም ህዝቡ የዕገሌ ውሃ ነው ከሚለው አስተሳሰብ እንዲላቀቅና የእኔ ነው እንዲል ከማድረግ አኳያ የሕግ ማዕቀፍ ከማዘጋጀት ጀምሮ በርካታ ተግባራትንም ከውነዋል።
በውሃ ብክነት ዙሪያም እንዲሁ ማህበረሰቡ በእኔነት ስሜት እንዲጠቀም ከማድረግ አንፃርም ማዕቀፍ እንዲበጅ ካደረጉት መካከል አንዱ መሆናቸውን ይናገራሉ። በተለይ ግን ሠራሁት የሚሉት በውሃ ተቋማት ዙሪያ የሚፈጠሩ የሙስና ሥራዎች እንዲጠፉና በድጎማም ሆነ በመንግሥት እነዚህ ተቋማት ሲገነቡ ምን ወጣ ምንስ ገቢ ሆነ የሚለውን ለመረዳትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚረዳ የሕግ ማዕቀፍ ላይ ተሳትፈው ብዙዎቹን የገጠራማ የውሃ ሥራዎች በማዕቀፍ እንዲመሩ ማድረጋቸውን ነው።
በተለይም አማራ፣ ቤኒሻንጉልና ደቡብ በዚህ የመተዳደራቸው ምንጭ እርሳቸው መሆናቸውንም ያነሳሉ። በቀጣይ ደግሞ ሐረርና ድሬደዋን ጨምሮ በአዳጊ ክልሎች ላይ ይህ የሕግ ማዕቀፍ ተግባራዊ ይደረግ ዘንድ ሥራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠሩ መሆናቸውን አጫውተውናል።
ውሃን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ የተቀጠሩት ዋቢሸበሌ ፕሮጀክት ላይ ሲሆን፤ መረጃ ሰብሳቢ ባለሙያም ነበሩ። በ12ኛ ክፍል ውጤታቸውም ነበር ተወዳድረው የገቡት። ከዚያ ግን ፍቅሩ ላቀባቸውና ከዚህ ዘርፍ ሳይወጡ 52 ዓመታትን አሳለፉ።
እንጦጦ አውራጃ የሚባለውን እንዲያስተዳድሩ ተሾመው እንደነበር የሚናገሩት ባለታሪኩ፤ ከአራት ኪሎ እስከ እንጦጦ ማርያምና ከፈረንሳይ እስከ እንጦጦ ያሉትን 33 ቀበሌዎችን ሲመሩ ለአንድ ዓመት ተኩል መቆየታቸውንም አውግተውናል። በዚህ ሥራቸው ደግሞ የተለየ በጎነታቸው የታየበትና ህዝብ ሳይቀር የአንገትና የጣት ወርቅ ቀለበት ያበረከተላቸው ጊዜ እንደነበር ያስታውሳሉ። ግን እንደእርሳቸው ህዝብ መቅረብ ወቅቱ አይፈቀድምና ከዚህ እንዲያነሷቸው ጠየቁ። በዚያ ላይ ያላቸው ባህሪ ተበዳይና በዳይ የማይለይ መሆኑ ከህዝቡ ጋር እንዳያቀያይማቸው ፈርተዋል። እናም ባለሙያነቴ ይሻለኛል በማለት ለሾማቸው አካል ጥያቄያቸውን አቀረቡ።
ወቅቱ ስልጣን እንቢ የማይባልበት ቢሆንም እርሳቸው ውሏቸው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ጋር በማድረጋቸው ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቷል። ህዝቡ በጣም እንዲወዳቸውና ቦታ እንዲሰጣቸው አድርጓልናም የፈለገው ይሁንለት በሚለው የህዝብ ሀሳብ ወደ ነበሩበት የውሃ ሥራ እንዲመለሱም ተደርጓል።
ሌላው አቶ ፋንታ የሰሩበት ዘርፍ መምህርነት ነበር። በዚህም ለሁለት ዓመታት አገልግለዋል። ይህ የሆነው ግን 11ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በደንቢዶሎ በሚማሩበት ወቅት ሲሆን፤ ያስተማሩበት ትምህርት ቤትም ደንቢዶሎ ብሔራዊ የውትድርና ማሰልጠኛ ይባላል። በእንግሊዝኛና ሂሳብ ትምህርት የተሻለ አቅም ስለነበራቸው ሁለቱን ኮርሶች በመስጠትም ነው ያሳለፉት።
አሁን የተለያ ስልጠናዎችን በውሃ ዙሪያ ይሰጣሉ፤ የሕግ ማዕቀፎችንም ያዘጋጃሉ። በጎ አድራጎት ድርጅቶችን በማስተባበርም በርካታ ሥራዎች በውሃ ተቋማት ዙሪያ እንዲሰሩ አድርገዋል። በዓለም አቀፍ የሰላም ፌደሬሽን አማካኝነት በሰሯቸው ትልልቅ ሥራዎችም የድርጅቱ የሰላም አምባሳደር በሚል ሰርተፊኬት ሰጥቷቸዋል። አሁንም በዚያ አምባሳደርነታቸው እያገለገሉም ነው።
ማህበራዊ ኃላፊነት
በየትኛውም ክልል ያለው ማህበረሰብ የውሃ ተቋማቱን የመንግሥት ነው፤ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅትም ሲሰራው የእነሱ ነው እያለ ጥበቃ አያደርግለትም። በዚህም በተለያየ መልኩ ገንዘብም ሆነ የሰው ጉልበት ይባክናል። ስለሆነም ከዚህ ችግር ለማላቀቅ የሚያስችሉ ሥራዎችን በመሥራት ህዝብንም ሆነ መንግሥትን አገልግለዋል።
‹‹ለአገሬ እንደምኞቴ አልሠራሁም›› የሚሉት እንግዳችን፤ አገሬ ከሌሎች ያደጉ አገራት እኩል በውሃ ልማት፣ ሀብት አጠቃቀምና ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍ ብላ ማየት እፈልጋለሁ። በዚህም የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶ እንዲሰራበት በማድረግ ለዓመታት ሠርቻለሁ። አሁንም እየሰራሁ እገኛለሁ ብለውናል። ይህንን ሊያግዙ የሚችሉ የውጭ ተራድኦ ድርጅቶችም ለአገሪቱ እጃቸውን እንዲዘረጉ በማድረግና ማህበረሰቡ ይህንን የመጣ ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀምበት ከማድረግ አኳያም ብዙ እንደሰሩ ይናገራሉ።
በተለይ ኤርትራና ትግራይ እንዲሁም ኦሮሚያ ላይ የውሃ ሀብት በአግባቡ ተግባር ላይ እንዲውል ከማድረግ አንፃር የተሻለ እንደሰሩም አጫውተውናል። አሁን በሌሎችም ላይ ይህ ምልከታ እንዲኖር የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ ላይ እንደሆኑም ነግረውናል። ይህ መለያ ባህሪያቸው ከውሃ ጥገና ጀምሮ ከህዝቡ ጋር በቅርበት እንዲሰሩ እንዳበረታታቸው የተለየ ስምም እስከመስጠት እንዳደረሳቸውም አውግተውናል። ዛሬ እነዚህን ተግባራት የፈፀምኩባቸው ቦታ ላይ ቢኬድና ፋንታ ቢባል ማንም አያውቀኝም የሚሉት ባለታሪኩ፤ ለአብነት ሮቤ አካባቢ ገመዳ በሚል ቅጽል ስም እንደሚጠሯቸው አጫውተውናል።
የወተት ነገር
አቶ ፋንታ የወተት ፍቅር ከልጅነታቸው እስከ ልጃቸው ስም ያደረሳቸው ነው። ባለቤታቸው በተከታታይ በቢሯቸው በመንገድ ስታልፍ ልባቸው ተመኝቷት ከጠየቋት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የጋበዟት የሚወዱትን ወተት ነው። ስለዚህም ወተት ሚስትና ልጅ ሰጥቶኛል ይላሉ። የመጀመሪያ ልጃቸው ስምም በኦሮምኛ ‹‹አነን›› በአማርኛ ደግሞ ወተቴ ያሉትም ለዚህ ይመስላል።
አቶ ፋንታ አሁን የስድስት ልጆች አባትና የአምስት የልጅ ልጆች አያት ናቸው። በቅርቡም ቅድመ አያት እሆናለሁ ብለውናል። ዛሬ የገዳ ሥርዓትን ጨርሰው የመጨረሻውን እርከን ማለትም ‹‹ገደሞጂ›› ላይ የደረሱ በመሆናቸው ከስራቸው በተጨማሪ ሰዎችን ያስታርቃሉ፤ ይመክራሉ፤ ለእጮኛ ፍለጋም ሽምግልና ይላካሉም።
ምስክርነት
አቶ ፋንታ ብዙ ጊዜ ተዘዋውረው ጥናቶችን በሚያቀርቡበት ወቅት ይህ ለምን አልሆነልኝም፤ ይህ ካልተደረገልኝ አልሄድም የሚል ነገር አያውቁም። ሥራ የሚሰሩበትን ብቻ አሽትተው መሄድ ነው የሚፈልጉት። በተለይ ይህን ያህል አበል ለምን ይከፈለኛል፤ መኪና ሳይመደብልኝ በራሴ ትራንስፖርት ተንቀሳቅሼ አልሰራም። ጥቅማጥቅምና የደመወዝ ጭማሪም ይደረግልኝ ብለው ጠይቀው የማያውቁ እንደሆነ በሥራ ጉዳይ የሚያውቋቸው አቶ መርጋ ረጋሳ ይናገራል። ከዚህ መለያ ባህሪያቸው በተለይ ወጣቱ ብዙ መማር እንዳለበትም ያስረዳል።
አቶ መርጋ እንደሚለው፤ ድርጅታችን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን፤ ብዙ ሰዎች ተቋማትንም ሆነ ራሳቸውን ወክለው ሲመጡ ብዙ ገንዘብ እንደሚያገኙበት አስበው ነው የሚመጡት። ክልሎች ላይ የሚሰሩ ሰዎችም ቢሆኑ እንዲሁ ትልቅ ነገር ይጠብቃሉ። እርሳቸው ግን ከትራንስፖርት ጀምረው በራሳቸው ወጪ ተንቀሳቅሰው ነው የሚሰሩት፤ ይዘጋጅሎት ተብለው እንኳን አትቸገሩ የሚሉ ናቸው። ከፍተኛ የጥናት ባለሙያ ናቸው፤ በዓለም ደረጃ የሚታወቁ ጥናቶችን ያቀርባሉ፤ ትልልቅ ስልጠናዎችንም ወስደው ላላወቀ የሚያሳውቁም ናቸው። ሆኖም የፕሮቶኮል ጉዳይ የማያስጨንቀውና ለሥራ ብቻ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ሰው እንደእርሳቸው አልገጠመኝም። እናም ማንኛውም ሰው ከእርሳቸው ይህንን ባህሪ ቢወስድ መልካም ነው ይላል።
መልዕክተ ፋንታ
‹‹ታሪክ የህዝብ ነው። እያንዳንዱ ነገር በግለሰብ ደረጃ ቢደረግም ህዝብ ካልወደደውና እንዲታወቅ ካላደረገው እንዲሁም ካልኖረበት ሊነግረው አይችልም። እናም እኔም ህዝቡ ደግፎኝ ያቅሜን ለአገሬ አበርክቻለሁ። ሆኖም ግን አሁንም አረካሁምና ለአገሬ ለውጥ እተጋለሁ›› የሚሉት እንግዳችን፤ የአገሬ ልጆች እኔ ተምሬ በአገኘሁት ልክ እንዲማሩ ፤ የውሃ ጥማታቸው እንዲረካ የማድረግ ድርሻዬ ከፍተኛ ነው ብዬ ስለማምን ገና ያልሠራሁት ብዙ አለኝ። ሌሎችም እኔ ብዙ የምሠራው አለኝ ማለት አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ።
ህይወት በተለያየ ጊዜ የተለያየ ትምህርት ታስተምራለች። ስለዚህም እኔም በሞትና በህይወት መካከል ሆኜ ብዙ ተምሬያለሁ። በተለይም ለአገር ሳይሰሩ ማለፍ ዘላለም እንደሚያስቆጭ ከነበረኝ የልጅነት ጉዞ ተምሬያለሁ። እናም ወጣቱም ሆነ መሥራት የሚችል ሁሉ ጊዜው በሥራ እንጂ ባልባሌ ማለፍ እንደሌለበት ከእኔ ቢማር ደስ ይለኛል ።
የጊዜን ዋጋ ማንኛውም ሰው መገንዘብ ያለበት አለበት ቦታ ላይ ቆሞ ነው። እርምጃ ከተጓዘ በኋላ መቆጨት መልስ አያመጣም። እናም ለዛሬ ዛሬ መሥራትን ልምድ ማድረግ ይገባል። ለአገር አሻራን ማሳረፍ ደግሞ ለዘላለም የማይጠፋ ተክልን ማብቀል ነውና ይህንን ማድረግ የሁልጊዜ ተግባር ሊሆን ያስፈልጋል።
የሥራ ፍቅር ካረጁም በኋላ ስንቅ ነው፤ መዝናኛም ይሆናል። ለዚህም እኔ ምስክር ነኝ የሚሉት አቶ ፋንታ፤ የዲስክ መንሸራተት ገጥሞኝ እንኳን መሥራቴ ሰዎች ከፍ ያለ ክብር እንዲሰጡኝ አድርጎኛል። ሥራው እንደ ሥራ ሳይሆን እንደመዝናኛ የሆነልኝም ለዚህ ነው። አይከብደኝም፣ አይጨንቀኝም ይላሉ። እናም ሌሎችም በተለይ ወጣቱ በሥራው ሁሌም መደሰትና መጠንከር እንዳለበትም ይመክራሉ።
ሁሌም ጠንካራ ለመሆን ከገንዘብ ይልቅ አገርን፤ ከገንዘብ ይልቅ ሥራን፤ ከገንዘብ ይልቅ ህሊናን ማስቀደም ያስፈልጋል። የምንናገረውን በተግባር ማዋል ላይም በርትቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ባህሪያዊ ለውጥ ለአገር ገፅታ ግንባታ ብሎም ለራስ ክብር ያለው ዋጋ ከፍተኛ ነውና ይህንን አቅም ማጎልበት እንደሚገባም ይገልፃሉ። ስለ አቶ ፋንታ ብዙ መናገር ቢቻልም ገደብ አለብንና ምክራቸው በተግባር ይዋል በማለት አበቃን። ሰላም!
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው