«ሰዎችን ከሃገር ለማፈናቀል ካልሆነ በቀር በዚህ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ጭማሪ በፍጹም አግባብ ሊሆን አይችልም፡፡ መንግስት ያደረገው ነው ብለን አናስብም፤ እንዲያውም መንግስት ጉዳዩን ያውቀዋል የሚል ዕምነትም የለንም» የሚሉት አዲሱን የኪራይ ቤቶች ጭማሪ አስመልክቶ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ጥሩውሃ ሲራጋ ናቸው፡፡ አቶ ጥሩውሃ አራት ኪሎ አካባቢ ካሉት የመንግስት ኪራይ ቤቶች ሥር የሚተዳደሩ የንግድ ቤቶች መካከል የቃል ስቴሽነሪና ኮምፒውተር አክሰሰሪ ባለቤት ሲሆኑ በአንድ ሺህ ሁለት መቶ ሃምሳ ብር ተከራይተው ነበር የንግድ ሥራቸውን የሚያካሂዱት፡፡ ይሁን እንጂ ከጥር 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በአዲሱ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ተመን መሰረት 10ሺ300 ብር ለመክፈል ውል እንዲሞሉ መጠየቃቸውን ይናገራሉ፡፡
ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት አገሪቱ ችግር ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ሰዓት እንዲህ ዓይነት ዜጎችን ለችግር የሚያጋልጥ የተጋነነ ጭማሪ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ጥያቄ እንደፈጠረባቸው የሚገልጹት አቶ ጥሩውሃ፤ «ጭማሪው ፍጹም ከአቅም በላይ በመሆኑ በጣም አስደንግጦኛል፣ ስጋት ውስጥ ነው ያለሁት» ይላሉ፡፡ እናም “ዕቅዱ ጤናማ አይመስለኝም፤ ጤናማ የሆነ ሰው ይህን ያስባል ብዬ አልገምትም፡፡ መንግስትም ሊያደርገው አይችልም፤ እንዲያውም መንግስት የሚያውቀው አይመስለኝም፡፡ የማይታወቅ ከሆነ ደግሞ መንግስት በአፋጣኝ ችግራችንን ሊያውቅልንና ምላሽ ሊሰጠን ይገባል» ይላሉ፡፡
እዚያው አራት ኪሎ አካባቢ የሚገኘው መሰረት ካፌ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ትርንጎ ከበደ በበኩላቸው፣ «ጭማሪ አይደረግብን የሚል ተቃውሞ የለንም፣ ከአሁን ቀደም እንከፍል ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በጣም ከፍተኛና ከምንሰራው ሥራ ጋር የማይመጣጠን፤ ከአቅማችን በላይ የሆነ ተመን መሆኑ ነው ቅሬታ የፈጠረብን» ይላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በወር የሚከፍሉት የቤት ኪራይ አንድ ሺህ አንድ መቶ ብር መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ትርንጎ፤ «አሁን ግን በወር 46ሺ700 ብር እንድንከፍል ነው የተተመነብን» በማለት የተደረገው ጭማሪ የተጋነነ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ወይዘሮ ትርንጎ እንደሚሉት፤ የአገር ጉዳይ በመሆኑ ጭማሪ አይደረግ የሚል አመለካከት የላቸውም፡፡ ሆኖም ጥያቄያቸው፤ ግብር የሚከፍሉ፣ የሰራተኛ ደመወዝን ጨምሮ በርካታ ወጪዎች ስላሉባቸው ጭማሪው ከገቢያችን ጋር የተመጣጠነ መሆን ይገባዋል የሚል ነው፡፡ በመሆኑም ተመኑ አቅማቸውን ባገናዘበ መልኩ እንዲሻሻልላቸው ለኮርፖሬሽኑ የቅሬታ ደብዳቤ ማስገባታቸውንና ቅሬታቸውም ተገቢውን ምላሽ ያገኛል የሚል ተስፋ ያላቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
«የተመን ጭማሪው እንዲሁ ሁለትና ሦስት እጥፍ ተብሎ እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፤ የተጨመረብን ከአንድ ሺህ እስከ ሁለት ሺህ በመቶ ነው፤ ይህ ደግሞ ጤናማ ያልሆነና ሰውን ወደ አልተፈለገ ነገር ውስጥ እንዲገባ የሚገፋፋ ነው» የሚሉት ደግሞ ሙሉጌታ ፍቃዱ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው፡፡ አቶ ሙሉጌታ፣ ፎቶ ቪው በሚባል ፎቶ ቤት ውስጥ ካሜራ ባለሙያ ሲሆኑ፤ ኮርፖሬሽኑ ያወጣው አዲስ የንግድ ቤቶች የኪራይ ተመን ከአገራዊ ለውጡ ጋር አብሮ የማይሄድና አሁን ባለው የመንግስት አካሄድ ይደረጋል ተብሎ የማይታሰብ ነው ይላሉ፡፡ «ከለውጡ በተቃራኒ ህዝቡን ለማነሳሳትና ወደ አልሆነ አቅጣጫ ለማስገባት ለሌላ ዓላማ ታስቦ ካልሆነ በቀር መቼም አሁን ያለው መንግስት እንዲህ አይነቱን አሰራር እንደማይደግፈው እርግጠኛ ነኝ» ብለዋል፡፡
ምክንያቱም አሁን አገሪቱ ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ማናቸውም ሥራ በእጅጉ በተዳከመበትና ብዙ ሰዎች ሥራ ፈተው በተቀመጡበት ሰዓት ነጋዴውን እንዲህ ዓይነት የተጋነነ ክፍያ እንዲከፈል የሚያስገድድ ተመን ማውጣት ሰዎችን ጫና ውስጥ የሚከትና ችግሩን የሚያባብስ ነው፡፡ ስለሆነም መንግስት ጉዳዩን በሚገባ አጢኖ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፤ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
እኛም እነዚህን ቅሬታዎች ይዘን ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ደውለን ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጠን ጠየቅን፡፡ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክብሮም ገብረመድህን፤ «ህብረተሰቡ የተጋነነ ጭማሬ የተደረገበት የመሰለው ከዛሬ አርባ ዓመታት በፊት ከነበረው የቤቶቹ ተመን ጋር አነጻጽሮ ስለሚያየው ነው እንጂ የኪራይ ዋጋ ተመን ማሻሻያው ምንም የተጋነነ አይደለም፣ በጥናት ላይ ተመስርቶ የተሰራ ነው» ይላሉ፡፡
ኃላፊው እንደሚሉት፤ እስከ አሁን ድረስ ህብረተሰቡ ለመንግስት ኪራይ ቤቶች የሚከፈለው የኪራይ ዋጋ በ1967 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 47/67 በተተመነው መሰረት ነው፡፡ በዚህም በተለያዩ ምክንያቶች አዋጁ እስካሁን ድረስ ሳይሻሻል በመቆየቱ በግል ባለሀብቶችና በሌሎች ተቋማት ከሚከራዩት አኳያ ሲታይ የመንግስት ኪራይ ቤቶች ደንበኞች ነጻ ሊባል በሚችል መልኩ በጣም ዝቅተኛ ዋጋ እየከፈሉ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ለአብነትም በከተማዋ ውስጥ እጅግ ታዋቂ የሆኑ ትልልቅ ሆቴሎችና የንግድ ቤቶች ሳይቀሩ አንድ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደር ግለሰብ ከሚከፍለው የቤት ኪራይ ባነሰ ዋጋ ሲከራዩ መቆየታቸውን ያነሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመዲናዋ ከሚገኙ 6ሺ635 በኮርፖሬሽኑ ሥር ከሚተዳደሩ የንግድ ኪራይ ቤቶች 279ኙ በካሬ ከአንድ ብር በታች ነው የሚከራዩት፡፡ እንዲሁም ከእነዚህ ቤቶች መካከል ሁለት ሺህ ሃምሳ ሰባት የሚሆኑት በካሬ ከአስር ብር በታች፣ 3ሺ880 የሚሆኑት ደግሞ በካሬ ከስድሳ አምስት ብር በታች ኪራይ የሚከፈልባቸው ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ቤቶቹ ንብረትነታቸው የህዝቡ በመሆናቸው የቤቶቹ ባለቤት የሆነው ሰፊው ህዝብ ይህን ያህል ዓመታት ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ «ስለሆነም ያኔ የነበረውና አሁን ያለው የአገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ በእጅጉ የተለያየ በመሆኑ አሁንም ያኔ በነበረው ዋጋ እንክፈል ማለት ትልቅ ስህተት ነው፣ ፍትሐዊነትም የለውም» ይላሉ፡፡ በመሆኑም እስካሁን ድረስ አዋጁ ባለመሻሻሉ ይህን ያህል ጊዜ ህብረተሰቡ ከገዛ ሀብቱ ተጠቃሚ ሳይደረግ ቢቆይም መንግስት ከያዘው የለውጥ አቅጣጫ አኳያ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ “ጊዜው አሁን ነው» ይላሉ ኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ፡፡
እንደ ሃላፊው ገለጻ፤ ብቸኛ ተጠቃሚ ሆነው የቆዩት አካላት እንደሚሉት ከደንበኞች አቅም በላይ የሆነ የተጋነነ ዋጋ ለማስከፈልና ህብረተሰቡን በመንግስት ላይ ለማሳመጽ ሳይሆን፤ የተመን ጭማሪው የወጣው ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ማምጣትና ሁሉንም ህብረተሰብ ተጠቃሚ ማድረግ የለውጡ አንድ አካልና የመንግስት ፍላጎት በመሆኑ ነው፡፡ ያም ሆኖ ትክክለኛና ሊያሳምን የሚችል ቅሬታ ያለው ደንበኛ ካለ ኮርፖሬሽኑ ቅሬታውን ተቀብሎ ለመፍታት በዝግጅት ላይ መሆኑን ኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2011
በይበል ካሳ