የአፍሪካ ምዘና ባለሙያዎች ማህበር የ25ኛ ዓመት በዓሉን በአዲስ አበባ ከተማ ያከብራል

አዲስ አበባ፡- የአፍሪካ ምዘና ባለሙያዎች ማህበር (African evaluation Exellence) የ25 ዓመት በዓል ከሰኔ 9 እስከ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ከ300 በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ሙያተኞች በተገኙበት በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚከበር ተገለጸ።

የኢዮቤልዩ በዓሉን አስመልክቶ የአፍሪካ ምዘና ባለሙያዎች ማህበር ፣የኢትዮጵያ ምዘና ባለሙያዎች ማህበር እና የኢፌዴሪ ፕላንና ልማት ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የፕላንና እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጥሩማር አባተ በመግለጫው እንደተናገሩት፤ ፕሮጀ ክቶችና ፕሮግራሞች ምን ያህል ማህበረሰባችን ላይ ለውጥ አምጥተዋል የሚለውን ለማወቅና አጀንዳ 2063ን እንደ አህጉር ከመተግበር አንጻር ሀገራት የእርስ በርስ ልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ የምዘና ሥርዓቱ መጠናከር አስፈላጊ ነው።

መድረኩ በተለይም ወጣቶች የሚሳተፉበት በመሆኑ ልምድና እውቀትን የሚያገኙበት፣ ባለፉት 25 ዓመታት በነበረው የማህበሩ ጉዞ ከተስተዋሉ ውጤታማ ሥራዎችና ተግዳሮቶች የሚማሩበት መድረክ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቅሰዋል። የምዘና ባሕልን ማሳደግ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን ለመንግሥት ተቋማት መስጠት የሚያስችል እንደሆነም ጠቅሰዋል።

አፍሪካውያን በብዙ ነገሮች ክህሎት እንዳላቸው የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ መሥራት እየቻልን እና አቅሙ እያለን እድሎችን ለሌሎች አሳልፈን መስጠታችን ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።

እንዲህ ዓይነቱ መድረክ አፍሪካውያንን የበለጠ እንዲቀራረቡ፣ ልምድ እንዲለዋወጡ፣ አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ እድል ይፈጥራል ብለዋል። አፍሪካ በሃምሳ ዓመታት ልትደርስባቸው ያሰበቻቸውን የጋራ እቅዶች በመደጋገፍ እና በመረዳዳት መንፈስ በራሷ ልጆች እውን እንድታደርግ ያግዛል ነው ያሉት።

የአፍሪካ ምዘና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ሚሼል ዱዩድራጎ በመግለጫው እንደተናገሩት፤ ተቋሙ ባለፉት 25 ዓመታት ጉዞው በአቅም ግንባታ፣ በእውቀት ልውውጥ እና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ ከማው ጣት አንጻር ያከናወናቸው ተግባራት ትልልቅ ጉዳዮች ናቸው።

ተቋሙ የአፍሪካ ምዘና ማእከል በመሆን አቅጣ ጫዎችን ያመላክታል፤ እስከ ዛሬ ከሠራቸው ሥራዎች በተጨማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ምዘና ሥርዓት የሚያ ወራ መጽሐፍ ማሳተሙን ተናግረዋል።

የትኛው ሀገር ከየትኛው የተሻለ የምዘና ሥርዓት ያከናውናል ለሚለው መደበኛ መለኪያ የለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በብሔራዊ ምዘና ደረጃ የትኛው ሀገር የተሻለ አሠራር ዘዴን ይከተላል የሚለውም በቀጣዩ የልምድ ልውውጥ መድረክ የሚታይ እንደሆነ አንስተዋል።

የምዘና ዓላማ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆን እውቀትና አሠራርን እያመነጩ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሆነ ጠቁመው፤ ምዘና መፍረድና መቅጣት ሳይሆን ማመላከት መማርና ወደ ጥሩ ውጤት መቀየር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ምዘና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ደረጃ ማሞ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ማህበሩ 523 አባላት ያሉት መሆኑን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ 53 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው ብለዋል።

ማህበሩ ፖሊሲ በማርቀቅና በተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎች የመንግሥት ተቋማትን እያገዘ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በየዓመቱ ሀገራዊ ኮንፈረንሶችን እያደረገ አሠራሩን የሚያጠናክሩ ግብዓቶችን የሚሰበስብ ፣ የዳሰሳ ጥናቶችን የሚያደርግ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

ምዘና እንደ ግምገማ አይደለም ያሉት ፕሬዚ ዳንቱ፤ በአመዛኙ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ድጋፍ የሚታይበት እንደሆነና ይህም የመንግሥትን ፕሮግራም እና ፕላን ለማገዝ እንደሚጠቅም አስረድተዋል። ማህበሩ ከፕላን እና ልማት ኮሚሽን ከተለያዩ የመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት እና ከአፍሪካ ምዘና ባለሙያዎች ማህበር ጋር ተቀራርቦ እየሠራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ሳምንት የሚደረገው የሦስት ቀናት ኮንፈረንስም እስከ አሁን በተሠሩ ሥራዎች ላይ የታዩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ምን እንደሆኑ የሚታይበት፤ ኢትዮጵያ የራሷን ልምድ የምታካፍልበት እና ከሌሎች አፍሪካ ሀገራትም ልምድና ተሞክሮ የምትወስድበት እንደሚሆን ተናግረዋል።

ሰኞ በሚጀመረው ኮንፈረንስ የመንግሥታት መሪዎች፣ መዛኞች ፣ ፖሊሲ አውጪዎች ፣ እና የልማት ባለሙያዎች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፤ የአፍሪካ ክትትልና ምዘና ትራንስፎርሜሽን ባሳየው ለውጥ ላይ በማተኮር ምክክር የሚደረግ መሆኑ ተመላክቷል።

በኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You