እንዲህም አለ!
በአበባ በመሃል ለሽርሽር እንደሚውል ሰው በእሬሳ ሳጥን ተከቦ እየሳቁ መዋል እንዴት ዓይነት ስሜት ይሰጣል ብሎ መጠየቅ ግድ ይላል። ኢትዮጵያውያን ከሕይወት ባልተናነሰ መልኩ ለሞት የምንሰጠው ትኩረት እንዲሁ ቀላል በማይባልበት በዚህ ዘመን የእሬሳ ሳጥን አሳምሮ፣ እሬሳ ገንዞ በህይወት ካለው ሰው ባልተናነሰ መንገድ የሟች የቀብር ስነስርዓት እንዲያሸበርቅ፣ ሳጥኑ ለእይታ ማራኪ ሆኖ እንዲያብረቀርቅ ለማድረግ የሚደረግ ግብግብ በአዕምሯችሁ ሳሉት። መስከረም ወር በአደይ አበባ እንደሚፈካ ሁሉ የእሬሳ ሳጥን በአበቦች ህብረትና ውበት ድምቅ ሲል ምን ይሰማዎት ይሆን?
አቶ ብርሃኑ ከበደ እና አቶ በቀለ ጉርሜሳ በዚህ ሥራ በርካታ ዓመታትን አስቆጥረዋል። ቀባሪዎች እንዳይከፉ ሟችም እንዳይጎሳቆል ይጠበባሉ፤ ይጨነቃሉ። ለሥራው ውበትና ድምቀት ያለ የሌለ እውቃታቸውን ይጠቀማሉ። ከሳጥኑ ዲዛይን ጨምሮ እስከ ቀብር መርሐ ግብር ደፋ ቀና ይላሉ። አለፍ
ሲል የሟች ቤተሰቦች በእነርሱ ሥራ ደስተኛ እንዲሆኑ የማይፈላሰፉት ነገር የለም። በቀጣይም ከዚሁ ሥራ ጋር የተቆራኘ ሕይወታቸው እየተጠናከረ እንደሚሄድ ተስፋ ያደርጋሉ። አጃኢብ ነው አይደል? በቀለ ጉርሜሳ አስክሬን በመገነዝ፤ ቀብር አስፈፃሚ በመሆን የሟች ሳጥን ወይንም ሙሉ መርሐ ግብር በማስፈጸም ያለፉት 15 ዓመታትን አሳልፏል። በእርግጥ ይህን ስራ በ1991 ዓ.ም ሥራውን ለመልቀቅ ወስኖ ወደ አምቦ ሄዶ ነበር። ግን ሥራው አሪፍ ብር ስለሚያስገኝ ጨክኖ መተው አልፈለገም። በዚህ ሥራው ቤተሰብ ያግዛል። ቀደም ሲል ምንም አልነበረውም። 1980 እስከ 1983 ዓ.ም በውትድርና የቆየ ሰው ሲሆን ለዚህ ስራው ድፍረት ሳይሰጠኝ አይቀርም ይላል። በአሁኑ ወቅት ሦስት ልጆች ወልዷል፤ በጉዲፈቻ ደግሞ ሁለት ልጆች አሉት። ታዲያ ልጆቹን የሚያሳድገው በዚሁ ሥራ ነው።
ክፍለሀገር ወደ ዘመዶቹ ሴሄድ ሱፍ ግጥም አድርጎ ነው። ግን የሚሰራው ሥራ ሲያውቁ በጣም ይገረማሉ፤ ለእርሱ ግን ብዙም ራስምታት አይሆንበትም ሕይወት ተላምዷልና። በአሁኑ ወቅት አምቦ ከተማ ላይ የቤት ቦታ አለው። ወጣ ብሎ ደግሞ ቤት ሰርቷል። በአሁኑ ወቅት በየሳምንቱ 500 ብር ደመወዝ አለው። አንዳንዴ ደግሞ አስክሬን ሲገንዝ በስራው ሰዎች ስለሚደሰቱ እስከ 3000 ብር ‹‹ቲፕ›› ይሰጡታል። ብቻ በዚህ ሥራ የሚያገኘው ገቢ ጥሞታል ኑሮውን በዚሁ መግፋት ይሻል።
አቶ ብርሃኑ ከበደ ላለፉት 30 ዓመታት በአማኑኤል ቀብር አስፈፃሚ ድርጅት ውስጥ ሲሰራ ቆይቷል። በመገነዝ፣ ቀብር በማስፈጸም፤ ሙሉ የቀብር መርሐ ግብር በማስፈፀም ልምድ አለው። እርሱ በዚሁ ሥራ ሙሉ ሕይወቱን እየመራ ሲሆን፤ ሥራው አሪፍ ገቢ ያለው ስለመሆኑ ይናገራል። ታዲያ ብርሃኑ ከበደ እና በቀለ ጉርሜሳ በዚህ ስራቸው ስለገጠመኞቻቸውና ስለ ስራቸው
ሁኔታ በጥቂቱ እንዲህ አቅርበናል።
ኑ ቅበሩልን!
ሥራውን ለማግኘት ብዙም መጥራት ወይንም ሰው መለማመጥ አያስፈልግም። ብቻ ኑ! ቅበሩልን ብለው ስለሚደውሉ፤ አሊያም ደግሞ እሬሳውን ገንዙልን ወይንም እጠቡልን የሚሉ በርካቶች ናቸው። ብቻ የእኛ ሥራ ቆንጆ የቢዝነስ ካርድ ማዘጋጀት እና ማሰራጨት ነው ይላሉ። ከዚህ በዘለለ የት አካባቢ ሰው ሞተ፣ ማንስ ቀበረው ብለን አንጨነቅም። ሰዎች በራሳቸው ኑ! ቅበሩልን ብለው ይደውላሉ። በዚህ ሥራ በመሃል ገብቶ የሚደልል ሆነ የሚያታልል ያለመኖሩ ብቸኛው ሥራ ሳያደርገው አይቀርም ይላሉ።
ግን አሁን አሁን የእሬሳ ሳጥን ለማሻሻጥ ኃይለኛ ድለላ ስለመጀመሩ መሸሸግ አልፈለጉም። ሥራ ቀዝቅዟል! በአሁኑ ወቅት የሥራ ሁኔታ ተቀዛቅዟል። ቀድሞ በቀን እስከ አምስት ሳጥን ይሸጥ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ሥራው በመቀዝቀዙ በቀን እስከ ሦስት ሳጥንም ላንሸጥ እችላለን። እናም ሥራ ተቀዛቅዟል። ግን ይህ ለምን ሆነ ብለን ስናስብ ብዙ ነገሮች ለማሰብ ተገደናል ይላሉ። አንደኛው ለጤናው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት የሟች ቁጥር ቀንሷል። ወይንም ደግሞ ቀብር አስፈፃሚዎች በየቦታው እየተበራከቱ ሊሆን ይችላል የሚል መላምት አላቸው። የሆነው ሆኖ ሥራው ስለመቀዛቀዙ፤ ገቢ ስለመቀነሱ ይመካራሉ። በሥራቸው ቀንቷቸው ገቢያቸው እንዲጨምር ይፀልያሉ ነገር ግን ሰው ይሙት ብለው አይመኙም። በእርግጥ የእነርሱ ገቢ ሰዎች ሲሞቱ ነው፤ ፀሎታቸው ደግሞ ሰው እንዳይሞት! ነገሩ ግራ አያጋባ ይሆን?
አመስጋኞች
አንዳንድ ሰዎች በቀብር አስፈፃሚዎች ከመርካታቸው የተነሳ ከፍ ያለ ምስጋና የሚያቀርቡ አሉ። አንዳንዶቹም ከቀብር በኋላ ይመጡና በቤተሰባችን ላይ የደረሰውን ሃዘን ሊካፈሉ የመጡ እንግዶችን አላስከፋችሁም፤ ስትቀብሩም በጥሩ ሁኔታ ነበር፤ አስክሬኑም አልተንገላታም፤ ሥራችሁን በጥሩ ሁኔታ ስለሰራችሁ እናመሠግናለን ብለው እጅ ይነሳሉ። በዚያውም ልክ ደግሞ የሚሳደቡና የሚደባደቡ አሉ።
ለመቀበሪያ 50ሺ ብር
አንዳንድ ሰዎች ከሕይወታቸው ይልቅ ለሞታቸው የሚጨነቁ አሉ ይላሉ። አንዳንድ ሰዎች የሚቀበሩት ከአሜሪካ በተገዛ ሳጥን ሲሆን እስከ 50ሺ ብር ወጪ ያደርጋሉ። ብቻ ከሠርግ በላይ ድምቅ የሚል ቀብር መኖሩን ነገራሉ። የጋጋታው እና የወጪው ብዛት ሟች ዳግም ነብስ ዘርቶ የሚኖር እንጂ እስከ ወዲያኛው የተሰናበተ አይመስልም ይላሉ። ብቻ መቀበሪያ ሳጥን ከ1ሺ500 እስከ 50 ሺ ብር ወጪ ያደርጋሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሳጥን መግዣ ሲያጡ እናያለን እናም ሰው ነንና ሳጥን በነፃ እንሰጣለን ይላሉ።
መቀበሪያህን ምረጥ!
አቶ ብርሃኑ ከበደ እና አቶ በቀለ ጉርሜሳ በዚህ ስራቸው ብዙ ነገሮችን ታዝበዋል። ከእለታት በአንዱ ቀን አንድ አባት ከታማሚ ልጁ ጋር ወደ እሬሳ ሳጥን መሸጫው ስፍራ ጎራ ይላል። እስተናጋጆቹም በችኮላ ምን ፈልገህ ነው ብለው ይጠይቁታል። ሳጥን ፈልጌ ነው ይላል። የሞተው ትልቅ ነው ትንሽ ነው ሲሉም ይጠይቁታል። የሞተ ሰው የለም፤ ግን በቅርቡ የሚሞት ሰው አለ ሳጥኑ የሚገዛውም ለእርሱ ነው ሲሉ አጠገባቸው ያለውን ልጃቸውን በጣታቸው አመለከቱ። በዚህ ወቅት ግራ የተጋቡት ሳጥን ሻጮች እንዴት ተብሎ ይህ ሊሆን ይችላል። ሟች እንዴት መቀበሪያውን ሳጥን መርጦ እንዲገዛ ይደረጋል፤ እንዴትስ በሥነ ልቦናው ትቀልዳላችሁ ሲሉ ቆጣ አሉ።
ታዲያ አባት የዋዛ አልነበሩም። ሆስፒታል ሄጃለሁ ለማሳከምም ሞክሬያለሁ ግን በቅርቡ እንደሚሞት ተነግሮኛል፤ ቢቆይ አንድ ወር ነው። ስለዚህ እራሱ የመቀበሪያውን ሳጥን ይምረጥ ብዬ ነው ሲሉ ይመልሳሉ። ፡ በዚህ ጊዜ በቁም ሳለ የመቀበሪያ ሳጥኑን እንዲመርጥ የተፈረደበት ሰው አይኑ እየተቅለሰለሰ፤ ልቡ እየፈራ ውስጡ ተስፋ ቢስ ሆኖ በመጨናነቅ ስሜት ሁሉንም ሳጥን እያየ በቃ አንዱ ይሁን ይላል። በዚህ ጊዜ ልባችን በጣም ተሰብሯል። ታዲያ ይህን የመሰለ ጭካኔ አይተን አናውቅም ሲሉ መቀበሪያው እንዲገዛ የተፈረደበት ሰው ከህሊናቸው ይመላለሳል።
በፌስታል ይቀበር!
ከዕለታት በአንዱ ቀን ደግሞ አንድ ወንድሙ የሞተበት ግለሰብ በጠዋቱ ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ሆኖ የእሬሳ ሳጥን ለመግዛት ይመጣሉ። ታዲያ መጀመሪያ የጠየቀው ሳጥን ሳይሆን የለበሰው ልብስ ዋጋ ውድነትን ማስረዳት ነበር። የለበስኩትን ልብስ ዋጋው 14 ሺ ብር ነው። በጣም የተከበሩ ሰዎች የሚለብሱት ነው ብሎ ከተናገረ በኋላ በጣም ጥሩ የእሬሳ ሳጥን እንደሚፈልግ ይናገራል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ጥሩ ምርጫ ይኖረው ዘንድ ሳጥኑን በዝርዝር ነገሩት። መጀመሪያ 50ሺ ብር ሳጥኑን ተመለከተ ግን አልተስማማም። ከዚያን 35ሺ ብር ዋጋ ያለው ሳጥን አሳዩት፤ ይህንንም ተቃወመ። በመቀጠል 10ሺ፣ አምስት ሺህ እያለ እስከ 1ሺ500 ብር ድረስ አስመረጡት። በዚህ ሁሉ አልተስማማም። በመጨረሻ ትንሽ እና ርካሽ የሚባለውን ሳጥን 500 ብር እንደሆነ ተነገረው፤ ይህንንም በክፉኛ ተቃወመ።
ታዲያ በዚህ ጊዜ እርር ያለው ብርሃኑ ከበደ ለምን አስክሬን ሳጥን ትፈልጋለህ፤ ‹‹በፌስታል ቅበረው›› ይለዋል። በዚህ ጊዜ ሰውየው ሽጉጥ መዞ ካልመታውህ ብሎ ከስውር ኪሱ መዘዝ ያደርጋል። ይህኔ ጓደኞቹ በፍጥነት ጎትተው እንዲወጣ አደረጉት። በመጨረሻም ሳጥኑን በ5000 ብር ገዝተው ሰውየውንም አባብለው መሄዳቸውን ያስታውሳል፤ ግን ዛሬም የሰውየው ድርጊት ዛሬ ከፊቱ ውል እያለበት በንዴትም በአግራሞትም በዓይነ ህሊናው ይመላለስበታል።
ገጠመኞች
በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ቀብር ለማስፈጸም ይሄዳሉ። ታዲያ በዚህ ጊዜ ሞቶ የነበረው ሰው የበዓድ አምልኮ ተከታይ ሰው ነበር። እኝህ ሰው በቤተሰቦቻቸውም ሆነ በተከታዮቻቸው ዘንድ በእጅጉ የሚፈሩ፣ የሚከበሩና መንፈሳቸው ደግሞ ሁሉን አድራጊ ተደርጎ የሚቆጠር ነው። ታዲያ ሰውየው አስክሬናቸው በግቢ ውስጥ ተቀብሮ ኖሮ ወደ ቤትክርስቲን የሚሄደው ሳጥን ውስጥ የኮባ ግንድ ተደርጎ ሰው ሲያለቅስ መዋሉን መቀበሩንም ያስታውሳሉ።
ከዚህም ሌላ አያሌ ነገሮች አጋጥሟቸዋል። በአንድ ወቅት አንዲት ሴት በቤቷ ሳለች ትሞታለች። ታዲያ ባለቤቷ አላመነም ነበርና ወደ እነርሱ ደውሎ ይሄዳሉ። የሰውየው ሃሳብ ወደ ሀኪም ቤት አዋስዱኝ የሚል ነበር። ሞታለች ለምን ሆስፒታል ትሄዳለች ብለው ቢከራከሩም ሰሚ አላገኙም። ታዲያ ታክሲ
ውስጥ ሬሳ ጭነው ወሰዱ። ሆስፒታል ደርሳ መሞቷን አረጋገጠ፤ ከዚያ አስክሬኑ ወደ ቤት ተመለሰ። በአንድ ወቅት ደግሞ እጅግ ወፍራም ሰው አጋጠማቸው። የአስክሬን ሳጥኑ አልበቃ አለ። በዚህ ጊዜ ሌላ መላ መዘየድ ግድ ይል ነበር። የሟች ባለቤት ወደ ውጪ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ የሟች አስክሬን ወገብ አካባቢ በጨርቅ እንደመቀነት ስብስብ ተደርጎ ታስሮ ሳጥኑ እንዲበቃ ተደረገ።
ሌሎች ደግሞ እሬሳ ስለሚፈሩ የሳጥኑን ልኬት በአግባቡ ስለማያውቁ እስከ ሦስት ሜትር የሚረዝም ሳጥን ይፈልጋሉ። ግን ይህን ያክል የሚረዝም ሰው የለም። ባለጉዳዮች ግን ይከራከራሉ። ብርሃኑ እና በቀለ ግን በእኛ ይሁንባችሁ እያሉ ለእሬሳው የሚበቃ ሳጥን ይሰጧቸዋል። አስክሬን ማጠብም ሆነ የሟችን ቤተሰቦች ማጽናናት ብሎም የሞተን መሸከም እንደ አስፈሪ ወይንም ደግሞ ባልተለመደ ሁኔታ ክስተት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ይልቁንም የአስክሬን ማጠብም ሆነ መገነዝ እንደማንኛው ሥራ የሚታይ ነው። የእሬሳ ሳጥን ማለት እንደማንኛውም ነገር ከእንጨት አሊያም ከብረት የሚሰራ ብሎም ማንኛውም እቃ ማስቀመጫ ሳጥን አስክሬን የሚቀመጥበት ነው።
ታዲያ ይህንን መፍራትም ሆነ መደናገጥ አያስፈልግም። ኑሯቸውን ሳጥን በመሸጥ፣ አስክሬን በመገነዝ አሊያም ደግሞ በመቅበር የሚተዳደሩትን መፍራትም ተገቢ አይደለም። ስለዚህ ሰዎች እንዳማረባቸው ኖረው እንዳማረባቸው ለመቅበር የተዘጋጀን አጋዦች መሆናችንን ልብ ሊሉ ይገባል ባይ ናቸው።
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር