የፖሊስ ማርሽ ባንድ ሃይማኖታዊ ለዛ ያላቸውን ዜማዎች በማቅረብ የታዳሚውን ቀልብ መሳብ አልከበደውም። ካህናቱ እንደተለመደው ሁሉ የያሬድን ዝማሬ ከነሽብሻቦው ሲያቀርቡ አምሽተዋል። ዲያቆናትም የነጮቹን አፍ ባስከፈተ ሁኔታ መዝሙራቸውን ከትርኢት ጋር አጅበው በዓሉን አድምቀውት አምሽተዋል። የንግስት እሌኒ ተምሳሌት የሆነች እንስትም በኢትዮጵያ ባንዲራ አጊጣ የመስቀሉን መገኘት በሚያስረዳ ሁናቴ አጭር ድራማ ላይ ተውናለች።
በመድረኩ ደግሞ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትርያርኮች፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ እምነት አባት እና የሩሲያ ኦርቶዶክስ ተወካዮችን ጨምሮ በርካታ እንግዶች በመሃል አውራ ጎዳናው ላይ የሚካሄደውን በቀለማት ያጌጠ ትርኢት እስከመጨረሻው ተከታትለዋል። ይህ ሁሉ በመስቀል አደባባይ ትናንትና የደመራ በዓል በተከበረበት ወቅት የነበረ እውነታ ነው።
በደመራው ስነስርዓት ላይ ከተላለፉ መልዕክቶች መካከል አንድነትና ፍቅር ዋነኞቹ ነበሩ። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፣ ነገረ መስቀሉ ቂምና በቀልን አስወግዶ ፍቅርን የሚያድል መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ምስጢሩን በአግባቡ ተቀብሎ ሲተገብሩት እና በጎውን ተግባር ሲፈጽሙት መሆኑን ተናግረዋል።
“ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሁሉም በአንድነት እና በፍቅር በመኖራቸው ይህችን ሀገር ጠብቀው ለእኛ አቆይተውልናል” ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፤ ይህን ሲያደርጉ ግን በመከባበር እና በፍቅር እንደሆነ አስታውሰዋል። ይህ ፍቅር እና መከባበር እንዲሁም ይቅርታ ደግሞ በመስቀሉ ስር ተትረፍርፎ እንደሚገኝ በማወቅ እንደ አባቶች አንድ መሆን እንደሚገባ አስረድተዋል። ይሁንና በቤተክርስቲያኗ ላይ ጥቃት በማድረስ እና አንድነትን በመሸርሸር እኩይ ተግባር ላይ የሚሳተፉ መኖራቸውን በማንሳት ጥፋተኞቹ ደግሞ ከዚህ ተግባራቸው መገታት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
እኩልነትን ከአንድነት፣ ነጻነትን ከወንድማማችነት ጋር እንደሚሄድ አውቃችሁ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች ከስድብ እና ፉከራ እንዲሁም መዘላለፍ ተቆጥባችሁ በአስተዋይነት እና በአርቆ አሳቢነት ህዝቡን አገልግሉ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። ህዝቡም ሰላሙን እና አንድነቱን ጠብቆ በመተሳሰብ እንዲቀጥል አባታዊ ምክራቸውንም አስተላልፈዋል።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹእ አቡነ መልከጼዴቅ በበኩላቸው፤ የደመራው በዓል ሲከበር መስቀል የፍቅር እና የሰላም ተምሳሌት መሆኑን ተገንዝቦ በአንድነት እና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል ብለዋል። በረከተ መስቀሉ እንዲደርሰን ከጥፋት ሳይሆን ከሰላምና ከፍቅር ጋር ሆነን ልናከብረው እንደሚገባ ነው የገለጹት።
የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቸው፤ ቤተክርስቲያኗ ለሰላምና ለፍቅር መጎልበት ያበረከተችውን እና እያከናወነች ያለውን ስራ አድንቀው፤ ከቤተክርስቲያኗ ጎን በመቆም ለማገዝ መንግስት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ረገድ ባለፉት ወራቶች ማስረጃ ያልነበራቸው የቤተክርስቲያን ይዞታዎች ወደምዝገባ እንዲሄዱ መደረጉን እና አስፈላጊው ማስረጃዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረው፤ በቀጣይ ጊዜያት ደግሞ 137 ጥያቄዎች በመኖራቸው እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች በመፍታት ዳግም ለመገናኘት ያላቸውን ፍላጎት ለምዕመናኑ አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2012 ጌትነት ተስፋማርያም