አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያ የአባይ ውሃ አጠቃቀም የሚመሰረተው በዓለም አቀፍ ሕግ መርሆች ማለትም ፍትሃዊና ምክንያታዊ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምን በማስፈን መሆኑን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተባበሩት መንግስታት 74ኛ ጉባኤ ላይ ተናገሩ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በካሊፎርኒያ እየተካሄደ ነው። በወቅቱ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባደረጉት ንግግር፤ የአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የምትሰራው ግድብ ውሃ አጠቃቀም በተፋሰሱ አገራት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ጉዳት እንደማያደርስ ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እንደገለጹት፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ 65 ሚሊዮኑ ኤሌክትሪክ አያገኝም። በአባይ ወንዝ ላይ የሚካሄደው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለሕዝቡ ኤሌክትሪክ በማድረስ ቢያንስ እራት በመብራት መመገብ እንዲችል እድሉን ለመስጠት ነው። የአባይን ውሃ መጠቀማችን በአካባቢው እህትማማች አገራት መካከል ድንበር ተሻጋሪ ትብብሮች እንዲጠናከሩ የተለየ እድል ይሰጣል እንጂ የመጠራጠር እና የውድድር ምንጭ ጨርሶ ሊሆን አይገባም።
‹‹ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዘው ያሉ የቴክኒክ ጉዳዮች ለባለሙያዎቻችን መተው አለብን።›› ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ የቴክኒክ ባለሙያዎቻችን ሳይንሳዊ እና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ምክረሃሳብ እንዲያቀርቡ ልናበረታታቸውና ሙሉ ድጋፋችንን ልንሰጣቸው ይገባል ›
ብለዋል። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ፣የሱዳን እና ግብጽ ሚኒስትሮች በካይሮ ካደረጉት ውይይት በኋላ በመስከረም መጨረሻ እና በጥቅምት ወር በካርቱም ተመልሰው እንደሚገናኙ አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ እንዳስረዱት፤ በአባይ ወንዝ ላይ ከትብብር ውጪ ሌላ አማራጭ የለም። በኢትዮጵያ በኩል ተፋሰሱን ያካተተ እና ህጋዊ የሆነ ባለብዙ ወገን ማዕቀፍ እንዲመሰረት ቁርጠኛ ፍላጎታችን ነው። በተለያየ ጊዜ ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶች እና ድርድሮች ኢትዮጵያ ለስምምነት ያላትን ቁርጠኛ አቋም ያንጸባርቃል። በዚህ ረገድ ከ13 ዓመታት ድርድር በኋላ እውን ለመሆን የበቃው የናይል የትብብር ማዕቀፍ የመጀመሪያው እና እውነተኛ አካታች የባለ ብዙ ወገን ስምምነት ነው ማለት ይቻላል።
እንደ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከሆነ፤ የአባይ ተፋሰስ አገራት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ግንኙነት ያዳበሩ ናቸው። እንዳይነጣጠሉ ሆነው በስልጣኔያቸው እና በታላቁ የአባይ ወንዝ ተሳስረዋል። የጋራ ልማታቸው ዘር የተዘራው ከሺዎች ዓመታት በፊት ነው። የሕይወታችን የዕውነታችንና የዕምነታችን ምንጭ በሆነው አባይ የተሰራው እና በዘመናት መካከል የተፈተነው ግንኙነታችን የሕዝባችንን ሕይወት ለማሻሻል የገባነውን ቃል በአዲስ ኃይል ለመተግበር የሚያግዘን ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ዋነኛ ፍላጎት ሕዝቦቿን ከድህነት ማላቀቅ ነው። ዜጎቿ የተመቻቸ ኑሮ ባለቤት እንዲሆኑ ነው እየሰራን ያለነው። ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የያዝነው አላማ መሰረተ ልማትን መገንባትና ብሔራዊ ሀብቶቻችንን በአግባቡ መጠቀምን የሚጨምር ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2012