ገና በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛል። ታታሪነት እና አመለ ሸጋነት ደግሞ መለያዎቹ እንደሆኑ የሚያውቁት ይመሰክራሉ። በሙያው ለሌሎችም የስራ ዕድል ፈጥሮ የእራሱንም ገቢ እያሳደገ ነው። ሰዎችን አምረው እንዲታዩ በየቀኑ አዳዲስ የልብስ ስፌት ጨርቆችን እና ውብ ዲዛይኖችን አጣጥሞ እያመረተ ያቀርባል።
ብዙዎች ከልጅነቱ ጀምሮ ያደገበትን ሙያ ፈልገው ከረጅም ርቀት ተጉዘው እርሱ ጋር ይመጣሉ። እርሱም በሙያውም ሆነ በስነምግባሩ አያሳፍራቸውም፤ በወቅቱ እና በጥራት ሰርቶ ያስረክባቸዋል። ከባለቤቱ ጋር በስራ ቦታ የሚሳልፈው ወጣቱ አብዛኛውን ጊዜም ሌሊቱን ሙሉ ልብሶችን ሲያዘጋጅ ያድራል። ሙያውን ከዕለት ዕለት በማሳደግ ሰፊ ደንበኞችን በመሳብ ላይ ይገኛል። የዛሬው እንግዳችን ሙሉ ስሙ መሃመድ ሱሌማን ይባላል።
ለእናትና አባቱ ብቸኛ ልጅ ሲሆን የተወለደው አዲስ አበባ ውስጥ ነው። አባቱ በስራ ምክንያት ሱዳን አገር ስለሄዱ እርሱም ገና በሶስት ዓመቱ ነበር ወደሱዳን ያመራው። በቅጡ እንኳን አፉን ሳይፈታ ወደሱዳን በመሄዱ በአረብኛ ቋንቋ ነበር እንደገና አፉን የፈታው። በሱዳን እንደልጅነት ወጉ እየተጫወተ ካደገ በኋላ ትምህርቱንም እዚያው ጀመረ። በካርቱም እስከስምንተኛ ክፍል እንደተማረ ግን አባቱ ወደሳዑዲ አረቢያ ለስራ ሊሄዱ ሲነሱ እርሱ ደግሞ አዲስ አበባ ከእናቱ ጋር ለመኖር ተመለሰ።
በአዲስ አበባም ልደታ አካባቢ መቀመጫውን አድርጎ ትምህርት እንዲጀምር እናቱ አስመዘገቡት። ይሁንና አረብኛ እንጂ አማርኛ ቋንቋን በወጉ ስለማይናገር ትምህርቱን እንዴት እንደሚቀጥል እርግጠኛ የሆነ ሰው አልነበረም። በኋላም ሁለት የክፍል ደረጃዎችን ቀንሶ ከስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ጋር ተቀላቅሎ እንዲማር ተደርጎ ደጃዝማች ባልቻ ትምህርት ቤት ዕውቀት መሸመቱን ተያያዘው።
መሃመድ በልጅነቱ አሮጌ ልብሶችን እየቀዳደደ መስፋት እና የተበላሹትንም መጠገን ይወድ እንደነበር ያስታውሳል። እናቱም ይህን ፍላጎቱን በመረዳታቸው ገና ተማሪ ሳለ በትርፍ ሰዓቱ የልብስ ስፌት ትምህርት ቤት አስገብተውት ነበር። አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ ከሚገኘው የልብስ ቅድ ሙያ ትምህርት ቤት የተወሰኑ ወራትን እንደተማረ ግን ሳይገፋ በመቅረቱ አቋረጠው።
አባቱ ከሳዑዲ አረቢያ እርሱን ለማየት አዲስ አበባ ሲመጡ ግን አንድ መላ ዘየዱ። ከትምህርት መልስ የሚያገኘውን ጊዜ አልባሌ ቦታ እንዳያሳልፍ በሚል መርካቶ አካባቢ የሚገኙ ዘመዶቻቸው ጋር የልብስ ስፌት ስራ እያገዘ እና ሙያን እየተማረ እንዲውል አደረጉት። መሃመድ ግማሽ ቀን ትምህርት ቤት ከቆየ በኋላ ቀሪውን ጊዜ መርካቶ ዲፕሎማቲክ የተሰኘው ልብስ ስፌት ሱቅ አነስተኛ ስራዎችን እየሰራ መዋል ጀመረ።
የእጅ ስፌት ስራ እና የልብስ ተኩስ ስራዎችን ሲያከናውንም በአንድ ሙሉ ሱፍ ልብስ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ይከፈለዋል። ስራውን በመጠኑ ሲለምድም በመጀመሪያው ሳምንት ያገኘው ገቢ 22 ብር ከ50 ሳንቲም እንደነበር አይዘነጋውም። እንዲህ እንዲህ እያለ ከልብስ ስፌት ሙያ ጋር ያለውን ዝምድና ማጠናከሩን ተያያዘው።
12ኛ ክፍልን ሊያጠናቅቅ ሁለት ወራት ሲቀረው ግን በጉርምስናው ባህሪ ምክንያት ከቤት ተጣልቶ ወጣ። ያለምንም በቂ ምክንያት ከሞቀው ቤቱ የወጣው መሃመድ እራሱን ለመቻል ግን ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አዕምሮው ነግሮታል። እናም የጀመረውን ስራ ሳይለቅ ቤት ተከራይቶ መኖር ጀመረ። በሳምንት የሚያገኛትን ገቢ እያብቃቃ ለወጪው መሸፈኛ አዋላት።
አራት ዓመት ዲፕሎማቲክ ልብስ ስፌት ውስጥ ሰርቷል። የሚሰራበት የልብስ ስፌት ድርጅት ባለቤት ወንድም ደግሞ አምባሳደር ልብስ ስፌት አለውና ክፍት ቦታ ሲያገኝ ወደዚያው ተሸጋገረ። በወቅቱ የኮት እና ሱሪ ስፌቶችን የተወሰኑ ክፍሎች መስራት ስለለመደ እራሱን እንደ ሙሉ ልብስ ሰፊ መቁጠር ጀምሯል።
በአምባሳደር ልብስ ስፌት ኮሌታ እና የእጅ ክፍሎቹ የቀሩት ኮት ልብስ በማዘጋጀት የልብስ ስፌት ስራው ውስጥ በቋሚነት ተቀጥሮ መስራቱን ቀጥሏል። በወቅቱ ሌሊትም ጭምር እየሰራ እስከ 12 ያላለቁ ኮቶችን በመስፋት በሳምንት 300 ብር ያገኝ እንደነበር ያስታውሳል።
መሃመድ በአምባሳደር እያለ በልምድ ላይ ልምድን እያካበተ ዕውቀቱንም እያሳደገ ጥሩ የእጅ ሙያን ይዞ ነበር። በጎን ደግሞ በትርፍ ሰዓቱ ለጓደኞቹ እና ለቤተዘመድ የሚሆኑ ሙሉ ልብሶችን እያዘጋጀ በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ ያገኛል። ዘጠኝ አመታትን በአምባሳደር እንደሰራ ግን ጥቂት ጥሪት በመቋጠሩ የእራሱን ልብስ ስፌት ሱቅ ለመክፈት ተነሳሳ።
ፒያሳ አካባቢ በሶስት መቶ ብር ኪራይ አነስተኛ ሱቅ በመከራየት ስራውን “ሀ” ብሎ ጀመረ። ከመንግስት የተበደረውን ገንዘብ በመያዝ በአምስት ሺ ብር የልብስ መስፊያ ማሽንም ገዛ። በወቅቱ ግን የገንዘብ አያያዙ ደካማ ስለነበር ስራውን ማሳደግ አልቻለም።
ይባስ ብሎ በሱቁ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የተወሰነ ንብረትም ወደመና ከነአካቴው ስራውን ለመዝጋት ተገደደ። የገዛውንም ማሽን በአነስተኛ ዋጋ ሸጦ ድጋሚ ለመቀጠር ወደመርካቶ አቀና።
በመርካቶ ተቀጥሮ አዲስ ስራ ሲያገኝ ግን በዲዛይነርነት ነበር። ጥቂትም ቢሆን የሚያውቀውን የልብስ ዲዛይነርነት ሙያ ከኢንተርኔት በሚያገኘው መረጃ በማጎልበት አዳዲስ የልብስ ስፌት አይነቶችን ለስፌት ሙያተኞች ማቅረቡን ሥራ አለ። ለሁለት ዓመታት በዲዛይነርነት ተቀጥሮ ሲሰራ ደግሞ ትዳርም መጣና ሕይወት ወደሁለት ጉልቻ ተቀየረች።
ከትዳር በኋላ መመካከር እና ጥቂት ገንዘብ መቆጠብ ሲችል የእራሱን ስራ መጀመር እንዳለበት ይወስናል። ለዚህም እንዲረዳው ተቀጥሮ እየሰራ የልብስ መስፊያ ማሽን በመግዛት ቅድመ ዝግጅቱን አጠናከረው። ከቀድሞው ስህተቱ በመማር ምን አይነት የገንዘብ አጠቃቀም መከተል እንዳለበት ወስኗል። በመቀጠል ያደረገው ደግሞ ጉርድ ሾላ አካባቢ በመሄድ በ2ሺ 500 ብር የስራ ቦታ መከራየት ነበር። ከስድስት ዓመታት በፊት ቀድሞ የገዛትን አንዷን ማሽን ይዞ እየሰራ ማሜ የተሰኘውን የልብስ ስፌት ድርጅት ከፈተ።
በመጀመሪያ ሰሞን ከተለያዩ ልብስ ሰፊዎች የተቀበላቸውን የትርፍ ሰዓት ስራዎች በመያዝ በሱቆቹ ይደረድራቸው ነበር። ቀድሞ በሙያው የሚያውቁት ሰዎች ደግሞ የተለያዩ ስራዎችን ይዘውለት ይመጡ ጀምሯል። እናም ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል ነውና መሃመድም ከየአቅጣጫው የሙሉ ልብስ ትዕዛዞች እየበዙለት እየተጠናከረ መጣ። አንዳንዴም ሌሊትም ጭምር በመስራት ለደንበኞቹ በዕለቱ ያደርሳል። ጥራቱን የጠበቀ እና ደንበኛው በሚፈልገው ሁኔታ የተዘጋጀ ልብሶችን በማቅረብ በጥቂት ወራት በአካባቢው ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ቦታዎች ተፈላጊነቱ ጨመረ።
ለሰባት ወራት ብቻውን እንደሰራ ግን የሚመጡለት የልብስ ስፌት ስራዎች በመብዛታቸው የተነሳ ቀድሞ የሚያውቃቸው የልብስ ስፌት ሙያተኛ ጓደኞቹን ጭምር እያመጣ ያሰራ ጀመር። እያንዳንዱ ልብስ ሰፊ የሚከፈለው በሰራው የልብስ ልክ ነው የሚለው መሃመድ እርሱም በወቅቱ እንደየስራቸው ልክ በመክፈል አስቸኳይ ትዕዛዞችን ጭምር በወቅቱ ያደርስ እንደነበር ያስታውሳል። ቀጥሎ ደግሞ አንድ ቋሚ ሰራተኛ በመቅጠር ስራውን ማስፋፋቱን ተያያዘው። ይህ ሁሉ ሲሆን ስራው አልጋ በአልጋ አልነበረም።
ከሁሉም በላይ ግን ለመሃመድ ፈታኝ የሆኑበት ጉዳዮች የመብራት መጥፋት፣ የሰራተኛ እጥረት እና የስራ ቦታው ርቀት ነበሩ። መብራት በየጊዜው ሲጠፋ ስፌት ማሽኑም የሚሰራው በኤሌክትሪክ ነውና ስራውም ይጓተትበታል። በሌላ በኩል በርከት ያለ ትዕዛዝ ሲመጣ የልብስ ስፌት ሙያተኛ እጥረት ውጥረት ውስጥ ይከተው ነበር። መሃመድ እንደሚያስረዳው ወጣቱ በብዛት ወደዚህ ሙያ የመሳብ እድሉ ስለቀነሰ የልብስ ስፌት ሙያተኛ ማግኘት ከባድ ነበር። በርግጥ ችግሩ ከቀን ወደቀን ከባድ እየሆነ በመምጣቱ መንግስትም ጭምር ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ነው የሚናገረው።
በሌላ በኩል ግን ለመሃመድ ፈታኝ የነበረው ከቤቱ ሩፋኤል ሰፈር እስከ ጉርድ ሾላ ያለው ርቀት ነበር። በተለይ መርካቶ ሄዶ ጨርቆችን እና ተጨማሪ ግብዓቶችን ገዝቶ ስራ ቦታ ሲደስር ግማሽ የስራ ቀን ያልፋል። ጥቂት እንደሰራ ደግሞ ወደቤት የመመለሻው ሰዓት ስለሚደርስ ፈታኝ ነበር። ይሁንና መሃመድ ሁለት እና ሶስት ቀናትን በስራ ቦታው ሌሊትም እየሰራ ስለሚያሳልፍ ችግሩን ተቋቁሞ ማለፍ ችሏል።
መሃመድ ፈተናዎቹን በጥንካሬው በማሸነፍ እድገቱን አፋጥኗል። አሁን ላይ በልብስ ስፌት ድርጅቱ ውስጥ ባለቤቱን ጨምሮ አምስት ሙያተኞች እየሰሩ ይገኛል። ስራ በበዛ ወቅት ደግሞ በትርፍ ጊዜው የሚሰራ አንድ ጊዜያዊ ሙያተኛ አለው። በአንድ ማሽን የተጀመረው ስራ በአሁኑ ወቅት ስድስት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የልብስ ማሽኖች ከፍ ብሏል። ስራ ከመጣለትም በወር እስከ 60 የወንድ ሙሉ ልብሶችን ያዘጋጃል። የወንድ ሙሉ ልብስ መሃመድ በአማካይ ከ2ሺ 800 ብር እስከ 3ሺ ብር ይሸጣል። የጨርቅ ሱሪ ለደንበኞቹ ካዘጋጀ ደግሞ በ700 ብር ለገበያ ያቀርበዋል።
ቀንም ሌሊትም እየሰራ የሚውልባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው። ሶስት እና አራት ቀን ወደቤቱ ሳይሄድም ስራ ቦታ ሊያሳልፍ ይችላል። እንዲህ እንዲህ እያለ መሃመድ ለበርካቶች መድመቂያ የሆኑ አልባሳትን በወቅቱ በማዘጋጀት አምርቶ ለገበያ ያቀርባል።
ነገን ዛሬ በሚሰራው ስራ አማካኝነት በበለጠ የተሻለ እንደሚያደርገው የሚያስበው መሃመድ ወደፊት በርካታ ሰራተኞች ያሉት ጋርመንት እንደሚኖረው ውጥን ይዟል። ለዚህ ግን የመንግስት አካላት ተገቢውን የመስሪያ ቦታ በመስጠት ቢተባበሩት ከእርሱ አልፎ ለበርካቶችም የስራ ዕድል መፍጠር የሚችል አቅም እንዳለው ይናገራል። በሙያው ደስተኛ የሆነው ወጣት መሃመድ ከልጅነት ጀምሮ ያዳበረውን የልብስ ስፌት ሙያ ተጠቅሞ ህልሙን እያሳካ ይገኛል።
ይበል በሚያሰኘው ስራው አማካኝነት የብዙ ሰዎችን አመኔታ እና ውጤታማ የንግድ ትስስር አግኝቶበታል። ለእርሱ ስራ ማለት ዛሬም ነገም፣ ቀንም ሌሊትም የሚተገብሩት የሕይወት ትልቁ ክፍል ነው። ማንኛውም ሰው ሰለቸኝ ሳይል የከመረውን ስራ መከወን እና ወደ ንግድ መለወጥ ከቻለ ትርፋማ የማይሆንበት መንገድ አይኖርም የሚለው ደግሞ ምክሩ ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2012
ጌትነት ተስፋማርያም