አቶ ጁነዲን ሳዶ በኢህአዴግ የአስተዳደር እና ፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ ከነበራቸው ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። አቶ ጁነዲን ሳዶ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት እና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር በመሆን አገልግለዋል። የቀድሞውን ኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲ ድርጅት ወይም በአሁኑ ስሙ ኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲን ወክለው በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ ከፍተኛ ውሳኔዎች ላይ ተሳትፈዋል። ከዚያም በስደት ወደኬንያ፣ አሜሪካ እና የተለያዩ አገራት ቆይተው አሁን ወደሀገራቸው ተመልሰዋል።
ከረጅሙ የሕይወት እና የፖለቲካ
ልምዳቸው በመጨለፍ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን መልክ ነበረው አሁንስ ምን ዓይነት ጉዳዮች ትኩረት ይሻሉ የሚለውን አካፍለውናል። መልካም
ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አቶ ጁነዲን ሳዶ ማን ናቸው? የትስ ተወለዱ? ከሚለው እንጀምር።
አቶ ጁነዲን፡- እኔ የተወለድኩት አርሲ ዞን ውስጥ ነው። ያደኩትም እዚያው ነው። የልጅነት ፍላጎቴ በትምህርቴ ዘልቄ ፋርማሲ ትምህርት እና በሁለተኛ ደረጃ የሕግ ትምህርትን ለመከታተል ሃሳብ ነበረኝ። የፖለቲካን ሕይወት አስቤውም አልሜውም አላውቅም፡፡ የደረስኩበትን የሥልጣን ደረጃም እደርሳለሁ ብዬ አልሜም አላውቅም።
አዲስ ዘመን፡- የወጣትነት ሕይወትዎ ምን መልክ ነበረው?
አቶ ጁነዲን፡- ነብሴን ሳውቅ እና አንደኛ ደረጃን ሳጠናቅቅ ታላቁ የኢትዮጵያ አብዮት የፈነዳበት ወቅት ነው። በ1966 ዓ.ም የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ዘመኑ ከባድ የፖለቲካ ነውጥ የታየበት ነበር። ደርግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ከባድ ውሳኔዎች እና አዋጆች ሲወጡ ሕዝቡ በሬዲዮ ያደምጥ ነበር።
ማታ ማታ ሁል ጊዜ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ ዜና በአማርኛ ሲነበብ እኔ አማርኛ ለማይችሉ በርካታ የአርሲ ሰዎች እንደአስተርጓሚም አገለግል ነበር። ይህ ፖለቲካው ላይ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡ በእኔ ላይ ብቻ ሳይሆን በዘመኑ ትውልድ ላይ። አርሲ ሁሩታ ሆኜ ስምንተኛ ክፍል ስገባ ደግሞ ዴሞክራሲያ የተሰኘችውን የኢህአፓ ልሳን ጋዜጣ ማንበብ ጀመርኩ።
በሌላ ጎኑ ደግሞ የተማሪዎችን ንቅናቄ ወሬ በሩቁ እሰማለሁ። ከዚያ አሰላ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስገባ የኢህአፓ ወጣት ሊግን ተቀላቅዬ መንቀሳቀስ ጀመርኩ።
በወቅቱ ደርግ ላይ ጫና ለማሳደር ታልሞ ትምህርት እንዲቋረጥ ስናደርግ እኔም ዘጠነኛ ክፍል ትምህርት እስከማቋረጥ የደረሰ ትግል አድርጌያለሁ። ቀይ ሽብር እየተጠናከረ ሲመጣ እና የደርግ እርምጃ አሰቃቂ ሲሆን ግን በ1971 ዓ.ም ፖለቲካውን ትቼ ወደትምህርቴ ትኩረት አደረግኩ። የተቋረጠውን ትምህርት በመከለስ ጠንካራ ተማሪ መሆን ችያለሁ። ወደአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1973 ዓ.ም ገብቼ በጂኦሎጂ ተመረቅኩ።
አዲስ ዘመን፡- በጂኦሎጂነት ሙያዎ የት ሰርተዋል?
አቶ ጁነዲን፡- ከዩኒቨርሲቲ በኋላ ቀጥታ ወደሥራ በማምራት ውሃ ልማት ተመደብኩ። ከድሬዳዋ ልጆች ጋራ ለሦስት ቤት ተከራይተን መኖር ተጀመረ። አብዛኛውን ጊዜ ግን በመስክ ሥራ ከኤርትራ ከተሞች ጀምሮ እስከ ደቡብ ኢትዮጵያ ጫፍ እና የአማራ ክልልን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች እየተዘዋወርኩ ሰርቻለሁ።
ከጀርመኖች ጋር ፕሮጀክት ላይ ስሰራ ደግሞ ጥልቅ የጂኦሎጂካል ካርታ ጥናት እና ጂኦፊዚክስ ምርመራ ላይ በመሳተፍ ሰፊ ልምድ አገኘሁ። በወቅቱ ምናልባትም ኤርትራ ነፃ እስክትወጣ ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ የቀይ ባህር ዳርቻ የከርሰምድር ባለሙያ ብቸኛው ነበርኩ።
ከዚያም ከሌላ የውጭ አገር ኩባንያ ጋር አሰብ ላይ ስሰራ ጥሩ ነገር በማሳየቴ ምን እናድርግልህ ስባል ተጨማሪ የትምህርት ዕድልን ጠየቅኩ። ወደእንግሊዝ እንድሄድ ዕድሉ ተሰጠኝ። በእንግሊዝ ሁለት ዓመት ቆይታዬ ኢስት አንግሊያ ዩኒቨርሲቲ በኢንቫይሮንመንታል ሳይንስ እና በርኒንግሃም ዩኒቨርሲቲ በከርሰምድር ውሃ ኢንጂነሪንግ እና ሃይድሮሎጂ ትምህርት ሁለተኛ ዲግሪዎቼን አገኘሁ።
ስመለስ ደግሞ ውሃ ልማት ቀጠልኩና ከዚያም አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ቢሮ ገባሁ። የተለያዩ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በመምራት እና እስከአሁን ያልተተገበረውን የሱሉልታ ሲቢሉ ግድብ ጨምሮ ጥናት በማድረግ በቢሮው አምስት ዓመታት ሰርቻለሁ። በመቀጠል ግን የኦሮሚያ ክልል ሰዎች ይፈልጉሃል ተባልኩና ፍላሚንጎ አካባቢ ጀርባ ወደቀድሞው ኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር ሕንፃ አመራሁ። ለሁለት ሰዓታት ከጠበቅኩ በኋላ እነ ኩማ ደመቅሳ እና ሀሰን አሊን ጨምሮ የተለያዩ ባለሥልጣናት ወደተቀመጡበት ቢሮ ግባ ተባልኩ። በወቅቱ ማን እንደጠራኝ ባለማወቄና በመደንገጤ ሊያስሩኝ ይሁን እያልኩ ስጨነቅ ነበር። ስገባ ግን ተቀብለው ካናገሩኝ በኋላ ለኦሮሚያ ክልል ውሃ ቢሮ ኃላፊነት እንደተመረጥኩኝ ነገሩኝ።
በወቅቱ እኔ ውሎዬ መስክ ላይ የሆንኩ የሙያ ሰው እንጂ ኃላፊነት አይገባኝም ብዬ ተናገርኩ። ባለሙያ ባለመኖሩ ውሃ ቢሮውን ማቋቋም እንዳለብኝ አስረድተው ወደ ኃላፊነት መጣሁ። በወቅቱ አዲስ አበባ ላይ እያለሁ ያየኝ አቶ ተፈራ ዋልዋ ነበር ለኦሮሚያ ሰዎች እኔን የጠቆመው። እናም በኦሮሚያ ለአምስት ዓመት የክልሉን ውሃ ሴክተር እና ማዕድን ሴክተር በአግባቡ በማዋቀር ሰርቻለሁ። በክልሉ ካሉት ቢሮዎች ቀልጣፋ ተቋም ማድረግ ችዬ ነበር።
በመጨረሻ ግን ሥራዬን ሲመለከቱ ወደፖለቲካው ሊያስገቡኝ የሚያንዣብቡ ሰዎች ይበዙ ጀመር። ይህ ነገር ሲገባኝ ለዶክትሬት ትምህርት አመለከትኩና ለትምህርቴ የሚሆን ገንዘብ ከዓለም ባንክ እንዳገኘሁ ወደእንግሊዝ ሄድኩ።
አዲስ ዘመን፡- እንዴት ወደፓርቲ አባልነት ተቀላቀሉ?
አቶ ጁነዲን፡- ኃላፊነት ላይ ስትወጣ የፖለቲካ ሥራ መስራትህ አይቀርም። ነገር ግን የፓርቲ አባል አልነበርኩም። ለትምህርት እንግሊዝ እንደሄድኩ እና ለሁለት ወራት እንደተማርኩ ግን የትምህርቱ ፈንድ ለዩኒቨርሲቲው ባለመድረሱ ቢያንስ የማረጋገጫ ደብዳቤ ከኢትዮጵያ ማምጣት እንዳለበት ተገለጸልኝ። በወቅቱ ደግሞ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦርነት ተነስቶ ነበር። ደብዳቤው ከመንግሥት ቢሮዎች እንዲጻፍ ለማድረግ በርካታ ባለሥልጣናት ጋር ብደውል የሚያነሳም አልተገኘም።
በዚያው ቀልጬ ጥገኝነት ሳልጠይቅ ወደሀገሬ ተመልሼ መጣሁ። ተመልሼ አቶ ኩማ ቢሮ ገብቼ ለምን እንደመጣሁ ጉዳዩን ሳስረዳ የውሃ ቢሮው እየተዳከመ በመሆኑ መልሼ እንዳደራጅ እና ሌላ ጊዜ ትምህርቱን እንድቀጥል ተነገረኝ። ተመልሼ እየሰራሁ ፈንድ አግኝቼ ወደእንግሊዝ ዳግም ላመራ ስል 1993 ዓ.ም ላይ አትሄድም ተባልኩ።
ጊዜው ጭቅጭቅ የበዛበት እና ኢህአዴግ የተሰነጣጠቀበት ወቅት ነው። እነ አቶ ኩማ ከነስዬ አብርሃ ጎን ተቆጥረው ከኃላፊነት ተነስተው ነበር። እናም የኦሮሚያን ኢኮኖሚ ዘርፍ እንድመራ ተመደብኩ። ሁሉም ኃላፊዎች የፓርቲ አባል ስለነበሩ እኔ ብቻ ስብሰባ አልገባም እና የሥራ ጫናው እኔ ላይ መብዛት ጀመረ። የጸጥታ፣ የኢኮኖሚ ዘርፉንም ሆነ ሌላውን እኔ እመራ ነበር። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ እያለን 1993 መጨረሻ 27 ቀናት ኦህዴድ ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ስብሰባ ተቀመጠ።
ከስድስት ቀናት የስብሰባው ውሎ በኋላ የፓርቲው አባል ባልሆንም ገብተህ ተካፈል ተባልኩ። ቀጥሎ በዚያው ዓመት ጳጉሜ ወር ላይ ኦህዴድ ሁለተኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ነቀምት ላይ ሲያካሂድ እንድገኝ ተጋብዤ የኦህዴድ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንድሆን ተጠቆምኩ። በወቅቱ መመረጥ ስላልፈለግኩ ጥያቄዎች ሲነሱ መመለስ አልፈለግኩምና ዝም አልኩ።
በኢህአዴግ ታሪክ በወቅቱ መንግሥት ፈርሶ እንደአዲስ የሚገነባበት እና የፌዴራልም የክልልም መንግሥታት በጣም ደካማ የሆኑበት ጊዜ እና በቡድን የመጠቃቃት ሁኔታ የሰፈነበት ጊዜ ነበር። እነ አባዱላ ገመዳ እና ሌሎችም በእኔ ላይ በተነሱ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ላይ መልስ ከሰጡ በኋላ ግን ምርጫ ተካሂዶ በስብሰባው ምናልባትም በኢህአዴግ ታሪክ የመጀመሪያው በሚባል ሁኔታ የፓርቲው አባል ከመሆኔ በፊት የማዕከላዊ ኮሚቴ ብቻ ሳይሆን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆኜ ተመረጥኩ።
አዲስ ዘመን፡- በፓርቲው ውስጥ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተሳትፈዋል እናም የቀድሞው ኦህዴድ እና የአሁኑን ኦዲፒን ምን ያመሳስላቸዋል? ምንስ ልዩነት አላቸው?
አቶ ጁነዲን፡- በመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፣ ኦቦ ለማ እና ሌሎችም በኦዲፒ ውስጥ ሥልጣን ላይ የሚገኙ ሰዎች ከእኔ በፊት የፓርቲ አባል የነበሩ እና አንዳንዶቹ ኢህአዴግ ወደከተማ ሲዘልቅ ለአባልነት የተመለመሉ ሰዎች ናቸው። ስለሆነም የቀድሞዎቹ የኦህዴድ ሰዎች ናቸው አሁን ኦዲፒ ውስጥ ያሉት።
ምናልባት አመለካከት፣ አሠራር እና የፖሊሲ አካሄዶች ላይ ልዩነት ቢኖርም አዲስ ሰው ግን አልመጣም፣ ነባር ታጋዮች ናቸው። በሌላ በኩል የድርጅቱ አርማ ይቀየር እንጂ መተዳደሪያ ደንቡ ላይ መሠረታዊ ለውጥ አለው ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ኢህአዴግም መተዳደሪያ ደንቡን ስላልቀየረ አሁንም የኦህዴድ መተዳደሪያ ደንብ ነው ያለው።
በፖሊሲ አቅጣጫ ደግሞ አዲሱ ኃይል ጊዜ አግኝቶ የጠሩ ግልጽ ፖሊሲዎችን አላወጣ ሊሆን ይችላል፤ እስከአሁን ያሉት ፖሊሲዎችግን የቀድሞዎቹ ናቸው። በአንጻሩ ትችቶችም የሚሰነዘሩት ኦህዴድ ስሙን እንጂ የቀየረው ተግባሩን አልቀየረም የሚል ነው። ካድሬውም ያው ነው፤ እስከታች ቀበሌ ድረስ ተመሳሳይ ኦህዴድ ነው ያለውና የሰው ኃይሉ ተመሳሳይ ነው ይባላል።
አሁን ላይ ቀበሌ ሥራ አይሰራም፤ ወረዳዎችም አንዳንዶቹ ሥራ በአግባቡ አይከናወንባቸውም፤ አንዳንዶቹ እስከጭራሹ ቆመዋል። ቁልፍ ተቋማት የሆኑት ዞን አስተዳደሮች እና ከተማ መስተዳድሮች አካባቢ በአንድ ጎን ውጤታማ አይደሉም ወይም «ፓራላይዝ» ናቸው የሚል ጉዳይ ይነሳባቸዋል። ይህን ለመቀየር ጊዜ ያስፈልጋል።
ልዩነቱ ላይ ምናልባት መድረኩን ክፍት እናድርግ የሚለው ይለያቸዋል። ኦዲፒ ሁሉን አቀፍ በመሆኑ ሁሉም ፓርቲዎች አገር ውስጥ ይግቡ የሚል አካሄድ አለው። የሥነምህዳሩን ማስፋት እና አካታች የመሆኑ አዲስ ነገር ነውና ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- የቀድሞው ኦህዴድ በህወሃት የሚታዘዝ ፓርቲ ነው የሚል ትችት ይቀርብበት ነበር፤ ይህ ምን ያህል ይስማሙበታል?
አቶ ጁነዲን፡- ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በነበሩበት ጊዜ ምንም የማያወላዳ የህወሃት የበላይነት አለ። ይህ በፖሊሲ ደረጃ ነው። የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ላይ የተወሰነው አቅጣጫ አራቱም መሪ ፓርቲዎች እንዲሁም ታዳጊ ክልሎችም ተቀብለው ነው የሚተገብሩት። የበላይነት ያሰኘውም ይሄ ነው።
ይሁንና በየቀኑ የምትጋጭባቸው ጉዳዮች ይኖራሉ ወይም የማትስማማባቸውና እየጎረበጡህ የምትወስዳቸው ነገሮች ይኖራሉ። ነገር ግን በአጠቃላይ ቀድሞ ኦህዴድም ይሁን ብአዴንም ይሁን ደኢህዴን ከላይ የሚሰጠውን ነጥብ ነው ይዘው የሚተገብሩት። በጣም መጠነኛ የሆኑ ልዩነቶች እና እዚህ ግባ የማይባሉ በሕዝብ ፊት ሊታዩ የማይችሉ በየክልሉ አዋጆች ልታወጣ ትችል ይሆናል ይሁንና ከዋናው አጥር ግን ልትወጣ አትችልም።
አዲስ ዘመን፡- ይህን ያነሳሁበት ምክንያት በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ተጽእኖ ይደረግ ነበር የሚል መረጃ ስላለ ነው። ለአብነት እርስዎ የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት የክልሉን ዋና ከተማ ከአዲስ አበባ እና አዳማ እንዲቀየር የተወሰነው ውሳኔ ላይ በቀጥታ የህወሃት ተጽእኖ ነው ስለሚባል ነው።
አቶ ጁነዲን፡- አንድ መጠነኛ ነገር ሊታይ የሚችለው አሁን ኦሮሚያ ክልል ያለበትን ሕንፃዎች ለግብርና ሚኒስቴር እንድንሰጥ ደብዳቤ ከወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተጽፎልን ነበር። ያንን ደግሞ እኔ አልተቀበልኩም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተነጋገርኩና ሕንፃውን በማስቀረት ይልቁንም ሌሎች ቢሮዎች አሁን የተገነቡትንም ጥንስሱ ያኔ ነው የተጀመረው።
ፊንፊኔን በሚመለከት በቀጥታ ከላይ በትዕዛዝ መልክ የሚወርዱ ነገሮች አልነበሩም። ኦሮሚያ ክልል ቢሮዎች ወደአዳማ ሲሄዱ ግን ሁሉም አልነበረም የሄዱት። ከ20 በላይ ቢሮዎች ውስጥ ወሳኝ የማይባሉ ስምንት ቢሮዎችን ብቻ ሲሄዱ ሌሎቹ አዲስ አበባ ውስጥ ነው እንዲቀሩ የተደረገው።
ይህንን የወሰነው ደግሞ የኦህዴድ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነው እንጂ አቶ መለስ ወይም የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አልነበረም። ነገር ግን እንደ እምነት ይህን አጀንዳ ህወሃት ይዞ ሊሆን ይችላል። ወደሌላ ከተማ እንድንሄድ የሚፈልጉ ሰዎች ከኢህአዴግ ውስጥም ሊኖሩ እንደሚችል የታወቀ ነው።
በአንድ ወቅት እንደውም አቶ መለስ በሻይ ሰዓት ላይ እኔ እንደውም ጅማ ድሮም የንጉስ አባጅፋር መቀመጫ ስለነበረች ጅማ ቢሄዱ ብዬ ነበር ያሰብኩት ብሎ ሲናገር ሰምቼዋለሁ። አዳማን ግን የመረጠው ከእኔ በፊት አቶ ኩማ በነበሩበት ጊዜ የኦህዴድ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነው የተወሰነው። እኔም ገልማ አባገዳ እና የጨፌ ኦሮሚያን ሕንፃ ያሰራሁት ዋና ከተማው አዳማ ነው ስለተባለ ነው።
ምርጫ 97ን ተከትሎ ግን የነበረው የፖለቲካ አየር ስለተቀየረ አቶ መለስ ደውሎላቸው ነው ከአዳማ የጠራቸው እንደሚባል ከሕዝቡ ሰምተናል። የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ከአዳማ ወደ ፊንፊኔ እንዲመለስ የወሰንነው ግን እኔና አቶ አባዱላ ገመዳ በስልክ ተነጋግረን ነው።
እንደውም ውሳኔው ላይ የኦህዴድ ሥራ አስፈጻሚም ተሰብስቦ አልወሰነም። በተዘዋዋሪ መንገድ ጫናዎች ይኖሩ ካልሆነ በስተቀር በቀጥታ ይህን ግቡ የሚል ነገር አልነበረም ማለት እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በእርስዎ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንትነት ወቅት ፈታኝ ጊዜ የሚሉት የትኛውን ወቅት ነው?
አቶ ጁነዲን፡- ፈታኝ ጊዜ የነበረው ሦስት ዓመታትን ነው። ከአቶ ኩማ በኋላ ነው እኔ ኦሮሚያን ለአራት ዓመታት የመራሁት፤ ሁሉም ፕሬዚዳንቶች አምስት ዓመታትን ነው የሚመሩት። በ1993 ዓ.ም መንግሥት ሲዳከም በነበረው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት የተማሪዎችም ተቃውሞ ተነስቷል። በተለይ የምዕራብ ኦሮሚያ ተማሪዎች በተደጋጋሚ ሰልፍ ይወጡ ነበር። በመሆኑም በ1994 ዓ.ም በአንድ በኩል ይህን የማርገብ ሥራ ነበር።
ጉልበት ሳንጠቀም ወደሕዝቡ በመሄድ እና ቀበሌዎች እና ወረዳዎች ጭምር እያደርኩ አረጋግቻለሁ። ሰው የማይሄድበት እና ኦነግ ያለበት የሚባሉ አካባቢዎች ጭምር ገብቼ ሕዝቡን በመቅረብ እና ሕዝቡን መላ በመጠየቅ አልፌዋለሁ። በወቅቱ ግን ጠመንጃ ወደተማሪ እንዳይተኮስ በእኔ ስር አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ፖሊስ አዛዥ በነበሩበት ወቅት በደብዳቤ አግደን ነው የሰራነው። ከመቃወማችን በፊት በግብርና እና በትምህርት አቅም መፍጠር አለብን እያልኩ ሕዝቡን አወያይቼ እያረጋጋሁ ወቅቱን አልፌዋለሁ።
በሌላ በኩል በሁለቱ ሐረርጌዎች እና አርሲ ቆላ ውስጥ ረሃብ ተከስቶ ነበር። ይህ ረሃብ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ቁጥር የተመዘገበበት ነው። 13 ሚሊዮን ሕዝብ የተራበበት ዘመን በ1994 እና 1995 ዓ.ም ነው። በወቅቱ ኦሮሚያ ላይ ብቻ ሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ ተርቧል። ይህ በ1977 ከነበረው ጋር ቢነጻጸር ትልቅ ቁጥር በመሆኑ ለማዕከላዊ መንግሥትም አስደንጋጭ ሆኖ ነበር።
ሆኖም አጥጋቢ ሥራ ሰርተን አብዛኛው ሰው ሳይሞት ረሃቡ ታለፈ። ከምግብ ዋስትና፣ ሰፈራ፣ ውሃ ማቆር በመተግበር እና መረጃዎችን በወቅቱ በመቀያየር እንዲሁም እርዳታ ድርጅቶችን አስተባብሮ በማስገባት የሚደነቅ ሥራ በመሰራቱ ችግሩ ታለፈ። በሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ 300ሺ ሰዎች እንዲሰፍሩ በማድረግ አሁን ጥሩ ውጤት ላይ ይገኛሉ።
ሌላው ፈታኝ የነበረው ወቅት የምርጫ 97 ወቅት ነው። በወቅቱ ኢህአዴግ የተሳሳተበት ጉዳይ ተቃዋሚዎችን የት ይደርሳሉ? ማን ይመርጣቸዋል? የሚል የመናቅ እንድምታ ነበረው። የኢህአዴግ ደረት ትንሽ አበጥ ያለበት ሁኔታ ነበርና ለተቃዋሚዎች ትኩረት አልተሰጠም።
ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ከኢህአዴግ ቀደም ብለው ሕዝቡ ውስጥ ገብተው የቅስቀሳ ሥራ ሰርተዋል። በኢህአዴግ በኩል ደግሞ በተቃራኒው ምርጫ ስናስብ ልማት እንደሌለ ልማት ስናስብ ደግሞ ምርጫ እንደሌለ ነበር የምንሰራው፤ አሁን ልማቱ ላይ ትኩረት አድርገን እያሳየን ከዚያ በሙሉ ኃይል ወደምርጫ እንገባለን ተባለና የረባ የፖለቲካ ሥራ ሳይሰራ ምርጫ ተቃረበ።
በወቅቱ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ኢህአዴግም ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ለተቃዋሚዎች እንክፈተው በሚል የክርክር መድረኩም ተመቻችቶ ነበር። ከሌሎች ምርጫዎች የተለየ በመሆኑ ብዙ ፓርቲዎችም ይወዳደሩ ነበር። መጨረሻ ላይ ኢህአዴግ ሲመጣ መድረኩ በተቃዋሚዎች ተይዞበት ስለጠበቀው ከባድ ሁኔታ አጋጠመው።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ በምርጫው ቅስቀሳና ክርክሮች ምን ያህል ተሳትፈዋል?
አተ ጁነዲን፡- እኔ በማላውቀው ሁኔታ የኦህዴድ ምርጫ ኮሚቴ ውስጥ አልነበርኩም፤ ተከራካሪም አልነበርኩም። የመንግሥት ሥራ ብቻ እንድሰራ ነው የተፈቀደልኝ፤ ይህ እስካሁንም ለእኔ ግልጽ አይደለም። ምርጫው ሲቃረብ ግን አንድ ጊዜ ከአጋሮ ተጠርቼ ከበረከት ጋር ምርጫ ክርክር እንድገባ ተደረገ። በተለያዩ መድረኮች ግን ተቃዋሚዎች ኢህአዴግን እያሸነፉ ነበር የሚወጡት።
የኢህአዴግም አሠራር በመመሪያ እና በተዋረድ በመሆኑ በቀላሉ ሕዝቡ ውስጥ ገብቶ ተወዳዳሪ ቅስቀሳ ማድረግ አልቻልንም። እናም በጉልበት ገብቼ የኦሮሚያ ልማት ማህበርን የዕርዳታ ድርጅት መኪና ይዤ ወደ ጭናቅሰን ለቅስቀሳ በእራሴ አመራሁ።
ከጭናቅሰን ጀምሮ ባሌን፣ አርሲን እና ሸዋ የተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ቦታዎች ተንቀሳቅሼ ቀሰቀስኩ። እናም ምርጫውን ኦሮሚያ ላይ እንድናሸንፍ ሰፊ ሥራ ሰራሁ። በምርጫው እስከማስታውሰው ድረስ ልክ አማራ ክልል ላይ 75 በመቶ ተቃዋሚዎች እንዳሸነፉት ኦሮሚያ ክልል ላይ 50 በመቶ ተቃዋሚ አሸንፈው ቢሆን ኖሮ ኢህአዴግ በሙሉ ተዘርሮ ይወድቅ ነበር። እናም ይህ ጊዜ ለእኔ ፈታኙ ወቅት ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ከእርስዎ የሥልጣን ዘመን ጋር በተያያዘ የሃይማኖት ጉዳይ ይነሳል። አንዳንዶች ፖለቲካን ለሃይማኖት ተጠቅመዋል፤ መስኪዶች በብዛት እንዲገነቡ አድርገዋል ብለው ይተቹዎታል።
አቶ ጁነዲን፡-ይሄ ልክ አሜሪካኖቹ እንደሚሉት የአንድ ሚሊዮን ዶላር ጥያቄ ነው። ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ የሚነሱብኝ ጉዳዮች የፖለቲካ ሥራ ነው የተሰራባቸው። የፖለቲካ ሥራውን የሰሩት ሰዎች ደግሞ ከፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ ከኢህአዴግም ከኦህዴድም ውስጥ ናቸው። በ2004 ዓ.ም ታኅሣሥ ወር ላይ የሙስሊሞች ጥያቄ ተነሳ። እናም የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ጥር ላይ ነበርና ስብሰባውን እንኳን አሳልፉን ተብሎ ጉዳዩ በሽምግልና ተይዞ ሲለመኑ ነበር።
በሌላ ጎኑ በወቅቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መታመም ጋር ተያይዞ ውስጥ ውስጡን መቧደን እና አንዱ አንዱን ማጥቃት የተጀመረበት ጊዜ ሆነ። እኔም የዚያ ጥቃት አንዱ ሰለባ ሆንኩ። ሙስሊሞቹ ወገን ወሃቢዮች ናቸው እያለ ለመንግሥት የሚነግርብን እሱ ነው እያሉ ስም የማጥፋት ድርጊት ያራምዳሉ።
ሌሎቹ ደግሞ አሃበሽ የሚባል ባዕድ ሃይማኖት እንዲገባ ያደረገው እሱ ነው ይላሉ። መንግሥት አብረን እየሰራን እኔን ከመከላከል ይልቅ የተመረጡ ካድሬዎች እና የደህንነት ሰዎችን አሰማርቶ አሃበሽን ያስገባው እሱ ነው ብለው የውሸት መረጃ በውስጥ ያቀብላሉ። ይህን በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ለመምታት ነበር።
አንድም እኔን ከመንግሥት ውስጥ ማስወገድ በተመሳሳይ ደግሞ ወሃብያ የሚላቸው ማስወደድ ነበር እቅዱ። የእኔ አካሄድ እስከመጨረሻው ድረስ ድምጻችን ይሰማ የሚሉትን ማቀራረብ ነበር። እኔም ድምጻቸው ይሰማ የሚለውን ነው ሰላማዊውን አካሄድ ነው የተከተልኩት። ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር በነበርኩበት ወቅት ከሥራዬ ውጪ ጉዳዩ መንግሥትና ሕዝብን ማጋጨት የለበትም በሚል ሼሆችን፣ ወጣቶቹንም ሆነ አክቲቪስቶቹን ሰብስቤ እኔ አሃበሽን እንዳላስገባሁ ተነጋግረን ይቅርታ ተባብለን ነው የተለያየን። ነገር ግን ወቅቱ መጠነኛ አብዮች የነበረበት ነበርና ባለቤቴንም አስረው ጉዳዩ ለፖለቲካ ፍጆታ ዋለ።
መስኪድ አሰራ ስለሚባለው እኔ በሕይወቴ እስከአሁን ያሰራሁት አንድ መስኪድ ብቻ ነው። እናቴ ስታርፍ አርሲ የተወለድኩበት ቦታ ላይ በአርሲ ባህል «በጌጌሳ» ገንዘብ አሰባስቤ ነው የሰራሁት፤ በልመና። ከግለሰቦች በተጨማሪ የሳውዲ መንግሥት ግንባታውን ረድቷል። ለኤምባሲውም ደብዳቤ የጻፍኩት በወቅቱ በኃላፊነቴ ሳይሆን እንደ አንድ ግለሰብ ልሙጥ ወረቀት ላይ በጻፍኩት ደብዳቤ ነው።
ከዚህ ውጪ አይደለም መስኪድ ላሰራ በመስኪድ ግንባታ ከእኔም ጋር የተነጋገረ ማህበረሰብም የለም። አሁን ሳስበው የፖለቲካ ጥቃት እንጂ ምንም ዓይነት ወንጀል አልሰራሁም። የሀገሬንም ጥቅም ባለሁበት ቦታም አንድም ቀን አሳልፌ ሰጥቼ አላውቅም። አቶ መለስ ከመሞቱ ጋር ተያይዞ ጡንቻቸውን እያሳደጉ የመጡ ኃይሎች እኔን ለማስወገድ ያሴሩት ሴራ ውጤት ነው ውዥንብር የፈጠረው።
አዲስ ዘመን፡- እነማን ናቸው እነዚያ ኃይሎች
አቶ ጁነዲን፡- የደህንነት መስሪያ ቤቱ ነው። ምንም ጥርጥር የሌለው የደህንነት መስሪያ ቤቱ ነበር የተሳሳቱ መረጃዎችን በሕዝቡ መካከል ሲያሰራጭ የነበረው። በግል ከአቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር አንስማማም። ይህነው የሚባል የተጣላንበት ጉዳይ የለም። ምናልባት ኦነግ ነው ብሎ ሊያስብ ይችላል። ለ14 ዓመታት ያህል ኦነግ ነው ብሎ ይከታተለኝ ነበር። እርሱ የኦሮሞ ብሔርን ማየት አይፈልግም፤ ከሆንክ አንተ ኦነግ ነህ ማለት ነው ለእርሱ።
ኦነጎች በበኩላቸው መንግሥት ውስጥ በመሆኔ የሚቀሰቅስብን እና የሚያስቸግረን እሱ ነው ብለው እኔን የሚጠሉበት ሁኔታ አለ። ይሁንና አቶ ጌታቸው አሰፋ ኦነግ ነው ብሎ ፋይል ከፍቶብኝ ስልኬን እያስጠለፈ በርካታ ችግር አድርሶብኛል።
እኔ ሥልጣኔም ሥራዬም የተደበቀ አልነበረም፡፡ ሙስናውንም አልወደውም በዚህ ምክንያት ጥርሳቸው ውስጥ የገባሁ ሰዎች ይኖራሉ። በግሌ የሰራሁት ነገር የለኝም። አሁን ምንም ሀብት የለኝም። በፖለቲካው ችግር እና በተነሳብኝ የሃሰት ክስ ምክንያት ችግር ውስጥ በመውደቄ አገር ለቅቄ ለመሰደድ ተገደድኩ።
አዲስ ዘመን፡- ወደስደት ከመግባትዎ በፊት አወጣጥዎ እንዴት ነበር? ምክንያቱም የስለላ መረብ ሰዎችም አወጣጣቸው ላይ ተሳትፈውበታል ስለሚባል ነው።
አቶ ጁነዲን፡- እኔን ምክንያት አድርገው ባለቤቴን ስላሰሯት ከፍተኛ ብስጭት ውስጥ ገብቼ ነበር። የመጨረሻው ልጄ ከእናቱ ተለይቶ የማያውቅ ገና የአራት ዓመት ሕፃን ነበር። ባለቤቴን ፍቷትና እኔን እሰሩኝ ብል ማንም ሊሰማኝ አልቻለም። ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ በወቅቱ ያረፉበት እና ውዥንብር ስለነበር ማንም ሊያናግረኝ አልቻለም።
አራት ወር ሙሉ ብዙ ባለሥልጣናትም እያናገርኩ በግሌ ተከራከርኩ። ለኢህአዴግ ጽሕፈት ቤትም ደብዳቤ ጽፌ ባለቤቴን እንዲለቋት እና እኔን ግን ከፈለጉ ገምግመው እርምጃ እንዲወስዱ ነገር ግን ቤቴን እንዳይበትኑ ጠየቅኩ። ከፈለጋችሁ ከፓርላማ አባልነቴ ልልቀቅ ብዬ ጠየቅኩ። ባለቤቴ እንኳን ያኔ አሁንም ምንም ዓይነት የፖለቲካ ንክኪ የላትም። አቶ ጌታቸው አሰፋ በበኩሉ አሻፈረኝ ብሎ የሌለ ወንጀል ፈጠረ።
እናም እርሷን ባለመልቀቃቸው በጣም ተናድጄ በሽታም ላይ ወደቅኩ። 11 ኪሎ ግራም እስክቀንስ ድረስ በጣም ታምሜ ነበረ። በጊዜው አቶ ኃይለማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ነበርና እንድታከም ደብዳቤ ተጽፎላቸው ተፈቀደልኝ። ለህክምና ታይላንድ ነው በቀጥታ የሄድኩት። እዚያ ስደርስ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሄ ሥርዓት እስካለ ድረስ ሀገርም የለኝም መንግሥትም የለኝም ብዬ ወሰንኩ።
ታይላንድ ለአንድ ወር በህክምና ቆየሁና ወደዱባይ አመራሁ። ዱባይ ሁለት ወር ቆይቻለሁ። እዚያ ተራ ሥራ እየሰራሁ ኑሮን ለመግፋት አስቤ ነበር። ፓስፖርቴ የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት በመሆኑ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት እዚያ መኖሩ ሲታወቅ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ግጭት ሊፈጠር ስለሚችል ዱባይ ላይ የሥራ ፈቃድ ሊሰጡኝ አልፈለጉም።
በመሆኑም ወደግልጽ ስደት ፓስፖርት ለኢትዮጵያውያን ወደማትጠይቀው ኬንያ አመራሁ። በኬንያ 12 ወር ቆይቻለሁ። በወቅቱ ትንሽ ከተማ ውስጥ ተደብቄ ነበር። ኬንያ ውስጥ ብዙ ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል። ታስረው መጥተውም ደብዛቸው የጠፉ አሉ። እኔ የት እንዳለሁ አቶ ጌታቸው አሰፋ ቢያውቅ ስለሚያስረኝ የምጠቀመው ስልክ እንኳን ኢንተርኔት የሌለው ነበር።
በኋላ ከኬንያ ወደአሜሪካ አቀናሁ። እናም እንኳን የደህንነት ሰዎች ሊደግፉኝ ቀርቶ ሲያሳድዱኝ የነበሩት እነሱ ነበሩ። አሜሪካ ስገባ ይህ ሁሉ የደረሰብኝ ለበጎ ነው በማለት እራሴን ወደሃይማኖቴ በመመለስ እንደገና ውስጤን ለማየት ቻልኩ፡፡ ለሰዎችም ይቅርታ ማድረግ ጀመርኩ።
አሁን ጌታቸው አሰፋን ባገኘው ቀድሞ እንደምናደድበት አልናደድበትም፡፡ ይልቁንም ሰላም እለዋለሁ። እርሱም አሁን ችግር ውስጥ ነው። እኔ በተነጻጻሪ ከተማው ውስጥ በሰላም እንቀሳቀሳለሁ። ይህም ሥልጣን ዋጋ እንደሌለው ያሳያል ዋናው የትም የማይሄደው ሀገር እና መንግሥት ነው። አሁን ከስደት ተመልሼ ሀገር ውስጥ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡– ከአሜሪካ የተመለሱት በምን መልኩ ነው?
አቶ ጁነዲን፡- ውጪም ሆኜ የኢትዮጵያን ፖለቲካ እከታተል ነበር። በተለይም ኦሮሚያ ክልል ቄሮ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እከታተላለሁ። በተወሰነ መልኩ መረጃዎችንም አገኝ ነበር። ከለውጡ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ እና አቶ ለማ መገርሳ አሜሪካ በሄዱበት ወቅት አግኝቻቸዋለሁ። ሀገሬ መመለስ እፈልጋለሁ ስላቸው ዶክተር ዐብይ ዝግጁ ከሆንክ አሁኑኑ እንድትመጣ ነበር ያለኝ።
እኔ ግን አምስት ዓመት አሜሪካ ስላልሞላኝ የመኖሪያ ፈቃድ ባለማግኘቴ በወቅቱ ልመለስ አልቻልኩም። እነሱ ሲመለሱ ግን እኔ ዝግጅት ማድረግ ጀመርኩ እና ከአንድ ወር በኋላ በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ሊሴ ፓሴ በጥቂት ቀናት ውስጥ ተዘጋጅቶልኝ ወደሀገሬ ተመለስኩ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን መቀመጫዎትን አዲስ አበባ ላይ ካደረጉ በኋላ ምን ዓይነት ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ?
አቶ ጁነዲን፡- ከአሜሪካ ከመጣሁ ድፍን አንድ ዓመት ሞልቶኛል። የተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ ለመሰማራት እያቀድኩ ነው። ቢሮ ከፍቼም በመስራት ላይ እገኛለሁ። ይሁንና ምንም ዓይነት ገንዘብ ስለሌለኝ አቅም ካላቸው ሰዎች ጋር እየተባበርኩ ለመስራት ነው ሃሳቤ። ባለሀብቶችን ማሰባሰብ እና ማሳመን የሚጠይቅ ሥራ ላይ ተሰማርቻለሁ። ሰፋ ያሉ ፕሮጀክቶች አሉኝ፤ በትምህርት፣ በአገልግሎት፣ በአምራች ዘርፉ እና በሌሎችም ዘርፎች ላይ ሕዝቡን በሚያሳትፍ መልኩ ወደልማቱ ለመግባት ዝግጅት እያደረግኩ ነው። ጥናቶችን በማቅረብ ዳያስፖራዎችን እና ባለሀብቶችን ገንዘብ በማሰባሰብ እኔ ሃሳብ እያቀረብኩ ለመስራት ነው እቅዴ። በዚህ ረገድ ያለቁ ጥናቶች አሉኝ የተቀሩ ደግሞ በመጠናት ላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ስለ ሥራ ሲታሰብ ሰላም ያስፈልጋል። እናም አሁን ላይ በየቦታው የሚታዩ ግጭቶችን በተመለከተ ካለዎት ልምድ በመነሳት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ ጁነዲን፡- ለውጥ በሚኖርበት ጊዜ ግጭቶች ይጠበቃሉ። ግጭት ባይኖር ነበር ጤነኛ የማይሆነው። እዚህም እዚያም የሚፈነዳዱ ነገሮች በአግባቡ ከተያዙ ወደትክክለኛ መፍትሄ ሊመጡ ይችላሉ። ዋናው ነገር መንግሥት ጠንካራ መሆን መቻል አለበት።
ጠንካራ የሚሊተሪ አቅም ወይም የፖሊስ አቅም ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ጥንካሬ በንግግር ቃላት፣ በተግባር ማሳየት፣ በመዋቅር እና በፍትህ ይገለጻል። የመሪዎች ንግግር ሕዝቡ ቁጭ ብሎ በያመቸው ሊመነዝረው የሚችለው በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
በሁለተኛነት መንግሥት የሚችለውን እሰራለሁ የማይችለውን አልችልም ማለት አለበት። የሃሰት ቃል እየተገባ ከሄደ የሕዝብ አመኔታ እና አክብሮቱ ይታጣል። በዚህ ረገድ ሥራዎችን እና ንግግሮችን ማገናኘት ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል በእኔ እምነት ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ያለው የመንግሥት መዋቅር በአግባቡ እየሰራ ነው የሚል እምነት የለኝም። ማዘጋጃ ቤቶች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በአግባቡ ኅብረሰተቡን እያገለገሉ አይደለም። ሕዝቡ ሰላም እንዲሆን አገልግሎቶቹን በአግባቡ ማግኘት አለበት።
በሌላ በኩል በየቦታው ችግሮች ሲነሱ ከማሳደር ይልቅ በወቅቱ መፍታት ያስፈልጋል። መንግሥት ቆፍጣና ሆኖ የእራሱን ሰዎች በአግባቡ ማሰማራት ካልቻለ ሕዝቡ አያከብረውም። ከዚህ ባለፈ ግን እንደ አጠቃላይ ሕግ የበላይነት ላይ ማወላዳት አያስፈልግም። እኔም በነበርኩበት ጊዜ ቀድሞ ፍርድ ቤቶች ነፃ አልነበሩም። አሁን ግን ለሰላምና ለዜጎች መብትም ሲባል ፍርድ ቤቶችን ከግለሰቦች እና ከፓርቲ ነፃ ማድረግ ይገባል።
በሌላ ጎኑ የተንሰራፋውን ሙስና መቀነስ ይገባል። ባለሥልጣኑን ባቻ ሳይሆን ፖሊስንም በዋናነት ከሙስና ማራቅ ያስፈልጋል። ደህንነቱን በበኩሉ የሚፈራ ሳይሆን ለሕዝብ ተወካዮች ተጠሪ ማድረግ ያስፈልጋል። የግለሰቦች መጠቀሚያ ሳይሆን አሠራሩ ግልጽ የሆነ ተቋም መድረግ ይጠይቃል። እነዚህም ሁሉ ማስተካከል ከተቻለ የተረጋጋ አገር መመስረት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– ከመንግሥት ባሻገር ሕዝቡስ ምን ዓይነት መንገድን ቢከተል ነው ሀገር የምትጠናከረው ይላሉ?
አቶ ጁነዲን፡- እኔ ሙሉ ሰው የምባለው ሁሉም አካሌ ሲኖር ነው። ኢትዮጵያም ሙሉ የምትሆነው ከብሔር ብሔረሰቦቿ ጋር ነው። አንዱን በኢኮኖሚም ሆነ በማህበራዊ ጉዳይ አግልሎ ሌላው ሊያድግ አይችልም። በዚህ ረገድ አንዱ ለአንዱ ስጋት መሆን የለበትም።
ሜቴክ ገንዘብ ስለዘረፈ የትግራይ ሕዝብ አብሮ መጨፍለቅ የለበትም የሚል አስተሳሰብ ይዘን መጓዘ ያስፈልጋል፡፡ ጥቂት የኦዲፒ ባለሥልጣናት ካጠፉ ኦሮሞ ሕዝብን በአንድ ላይ መፈረጅ ኢትዮጵያዊነትን ያላላል። እናም ሁሉም አካታችነትን ሳይለቅ ሁሉም ተከባብሮ ሲኖር ነው ጥንካሬ የምናገኘው።
አዲስ ዘመን፡- በየቦታው ክልል እንሁን የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው። ከፖለቲካ ልምድዎ በመነሳት ከክልል አወቃቀር ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት አካሄድ ያዋጣል ይላሉ?
አቶ ጁነዲን፡- ክልል የመሆን ጥያቄ ችግር የለውም። ደቡብ ላይ 56 ብሔረሰቦች አሉ። በቁጥር አነስ ያሉትን በተለይ ደቡብ ኦሞ አካባቢ ያሉትን አንድ ላይ አድርጎ ክልል ማድረግ ይቻላል። እንደነ ሲዳማ እና ሌሎቹንም ተለቅ ያሉት ደግሞ ለብቻቸው ክልል መሆን ይችላሉ። ክልል መሆን ኢማዕከላዊነትን አያሳይም። ወደፊት እኮ ክልሎችም መልሰው ሊዋሃዱ /Re union/ ሊደረግ ይችላል።
ነገሩን ባናገነው እና ክልሎች መብዛታቸውን እንደችግር ባናየው ጥሩ ነው። ዋናው አደረጃጀቱን የማስተካከል እና ሕዝቡ አንዱ ሌላውን የመቀበል እና የመገባባቱ ጉዳይ ነው። የአንዱ እሴት የሌላውም እንደሆነ ስንቀበል ነው ኢትዮጵያ አንድ ሆና እንድትቀጥል የሚረዳት።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ጁነዲን፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2012
ጌትነት ተስፋማርያም