
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብቻ ሳትሆን የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገርባትና የሰፊ ባህል ባለቤት ነች። በደም ተሳስረው ለዘመናት አብረው የኖሩት የኢትዮጵያ ህዝቦች የሃይማኖት፣ የቋንቋና የባህል ልዩነቶቻቸውን አክብረው ዛሬም በፍቅርና በመከባበር ይኖራሉ። አክብረው በአንድነት ያቆዩዋቸውን እሴቶቻቸውን አጠናክሮ መቀጠልም ሰላማዊ የሆነ ማህበራዊ መስተጋብርና ጠንካራ ሀገራዊ መግባባትን እንደሚፈጥር ምሁራን ይናገራሉ። የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም ሃሳቡን ያጠናክራሉ።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ አካሉ አስፋው ባህላዊ እሴቶች የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብቻ ሳይሆኑ የሀገር ሀብት እና የአንድነት መሰረት እንደሆኑ ያስረዳሉ። እርሳቸው እንዳሉት እነዚህን የሀገር ሀብቶች ተፈጥሯዊ ባህሪያቸው ሳይበረዝ ለትውልድ ማስተላለፍ ቀጣይዋን ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ለመገንባት አበርክቶው ከፍ ያለ ነው። ይሁን እንጂ ያለንበት የቴከኖሎጂ ዘመን ዜጎች በተለይም ወጣቶች ባህላቸውንና ማህበራዊ እሴቶቻቸውን እንዲያውቁ እምብዛም እድል አይሰጣቸውም።
በተለይ በከተማ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቱባው ባህል ከሚከወንበት ሥፍራ እራቅ ያሉ በመሆኑ ለባዕድ ሀገራት አስተሳሰቦችና ባህሎች ተጋላጭ የሚሆኑበት አጋጣሚ ይሰፋል። ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት ወግና ልማድ እንዲያፈነግጡና ባህላዊ ተቀባይነት የሌላቸው ተግባራትን እንዲፈጽሙ ያደርጋቸዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን ባህል የሚያጎናጽፋቸውን የመቻቻል፣ የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የአንድነት እሴቶችን በውል ሳይረዱ እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል። በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ክዋኔ ማግኘታቸው ከተማዋ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መገኛ እንደመሆኗ አንዱ የሌላውን ባህል እንዲያውቅና በጋራ እንዲያከብር እድል ፈጥሯልም ብለዋል።
አቶ አካሉ እንደሚያስረዱት እንደ አሸንዳ፣ ሻደይ፣ ሶለልና ኢሬቻን የመሳሰሉት ባህሎች በአዲስ አበባ መከበራቸው በህዝቦች መካከል መቀራረብን ያጠናክራል፤ ማህበራዊ ትስስርና አንድነትን ይፈጥራል። እያንዳንዱ ሰው ሲከወን ያየውን ባህል የእኔ ነው የሚል ስሜት እንዲኖረው ያደርጋል።
በከተማ የሚኖረው የየአካባቢውን ባህል ለማወቅ ቦታው ድረስ መሄድ አይጠበቅበትም ያሉት አቶ አካሉ፤ ይልቁንም ህዝቦች የብዝሃ ባህል ባለቤትነታቸውን የሚያረጋግጡት ሁሉንም በቅርበት በማወቅ እና አንዱ የሌላውን ባህል እንደራሱ ማየትና መንከባከብም ሲችል እንደሆነ ይናገራሉ። ህብረተሰቡ ለባህላዊ መገለጫዎች እኩል ዋጋና እውቅና በመስጠት መቀራረቡን ፣ፍቅሩንና አንድነቱን በአደባባይ መመስከር ይኖርበታል። ይህ ሲሆን ባህሎች ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለማቀፋዊ እውቅና አግኝተው ሀገሪቱ ከቱሪስት ዘርፍ የምታገኘውን ጥቅም ሊያረጋግጡ ይችላሉ።
ብዝሀነትን አክብራ በምትኖር እንደ ኢትዮጵያ ባለች ሀገር ለአንዱ ባህልና እሴት እውቅና በመስጠት የሁሉንም ህዝቦች ባህል ማጎልበት የህዝቦችን ማህበራዊ ግንኙነት ማጎልበት ይችላል። አብዛኛዎቹ ባህላዊ እሴቶች አንዱ ሌላውን እንዲገፋውና እንዲያርቀው የሚያደርጉ ሳይሆኑ ፍቅርና ወንድማማችነትን ፣ መቻቻልና አንድነትን የሚያጎለብቱ በመሆናቸው ተፈጥሯአዊ ባህሪያቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ማድረግ ያስፈልጋል። የሀገራችን ባህሎች በርካታና የየራሳቸው አውድና መገለጫ ያላቸው ሲሆን ማህበራዊ ፋይዳቸውም ይለያያል።
ኢትዮጵያ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ የመሰረቷት ሀገር እንደመሆኗ አንዱ የሌላውን ባህል ማወቁ ጠንካራ ማህበራዊ ግንኙነትን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ባለሙያው ያስረዳሉ። ሀገር በሚባለው ትልቅ ማዕቀፍ ውስጥ የሚኖር እያንዳንዱ ዜጋ የእኔ ነው የሚለው ሀገሩን ወይም ምድሩን ብቻ ሳይሆን ህዝቡንም ጭምር ነው፤ ህዝቡ ለሚከተለው ባህልም ባለቤት ነው። እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ በመያዝ ባህሎችን በጋራ ማክበርና እውቅና መስጠት ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባት እና በሰዎች መካከል ፍቅርና መተሳሰብን ለመዝራት ይረዳል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር መምህር ዶክተር አለሙ ካሳ በበኩላቸው ‹‹ባህላዊ ክዋኔዎች በማህበረሰቡ ውስጥ ማገልገል የጀመሩት ዛሬ አይደለም፤ ሰዎች ማህበራዊ ህይወትን መስርተው መኖር ከጀመሩ ወዲህ ደስታቸውን፣ ሀዘናቸውን ፣ ምስጋናቸውን፣ ጀግንነታቸውንና አንድነታቸውን ሲገልጹባቸው ቆይተዋል›› ሲሉ ይገልጻሉ። ባህሎች፣ወጎችና ልማዶች ማህበረሰብን ቅርጽ የማስያዝ ሚና እንዳላቸውና እያንዳንዱ ሰው የሚኖርበትን አካባቢ ወይም ሀገር መስሎ እንዲወጣ እንደሚያደርጉም ይናገራሉ።
እንደ ዶክተር አለሙ ገለጻ የማንነት መገለጫ የሆኑት ባህሎቻችን አሁን አሁን የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ማግኘታቸውና ከነበሩበት ተፈጥሯዊ አውድ ወጥተው ወደ ከተማ መምጣታቸው አዲስ ነገር ሊሆን ይችላል። ይህ መሆኑ ግን አንዱ አካባቢ የሚገኘውን ባህላዊ ክዋኔ ሌላው የማህበረሰብ ክፍል እንዲያውቀው እድል ይፈጥራል ። ትውልድ ጅረት ነው አይቆምም ፤ ኢትዮጵያም እንደ ጅረት በሚፈሱት ትውልዶቿ መቆሚያ የሌላቸው ባህሎችና ልማዶች የሚፈሱባት ሀገር ስለሆነች አንዱ ብሄረሰብ የሌላውን ብሄረሰብ ባህል እያከበረ እርስ በእርስ በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩባት ሀገር መሆን ይኖርባታል ።
እንደ ዶክተር ዓለሙ አባባል ባህላዊ ክዋኔዎችን አድማጭ ተመልካቾች ወዳሉበት ቦታ ማድረስ አንዱ ብሄረሰብ ለሌላው ብሄረሰብ ባህላዊ እሴቶች ባይተዋር እንዳይሆን ይረዳዋል ። መተዋወቅና ተግባቦትንም ይፈጥራል። ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድነትን የሚፈጥርና የኢትዮጵያን አጠቃላይ ስዕል የሚያሳይ ይሆናል።
እንደ ምሁሩ ማብራሪያ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሚኖሩባት አዲስ አበባ ከተማ ባህላዊ ትዕይንቶች መቅረባቸው ነዋሪዎቹ በርቀት የሚያውቁትን በቅርብ በማግኘት ዕውቀት እንዲያገኙ ያግዛቸዋል። ህዝብ ምንጊዜም ቋንቋው፣ ባህሉና ጥቅሙ እስከ ተከበረለት ድረስ የትም ቦታ በሰላም ይኖራል ይላሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያውያን ተሰደው በሚሄዱበት ሀገር እንኳን ትንሽ ቁጥራቸው በዛ ሲል ባህላቸውን ለማሳየት ይሞክራሉ። ምንግዜም የቡድኖች መኖር አደባባይ ወጥቶ እራስን የመግለጽ፣ ማንነትን የማሳወቅ፣ ተሰሚነትና ዕውቅናን የማግኘት ፍላጎትን እንደሚያሳድር ዶክተር አለሙ ያስረዳሉ።
‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን የሌሎች ሀገራትን አመጋገብ ፣ አለባበስ አጠቃላይ ባህላዊ ክዋኔዎች መገናኛ ብዙሃን እቤታችን ድረስ እያመጡ ሲያሳዩን በአድናቆት እንመለከታለን፤ ከዚህ በላይ ግን የማናውቃቸውን የሀገራችንን ባህሎች ለማወቅ ብንሞክር በርካታ ማህበራዊ ፋይዳዎችን እናገኛለን›› ሲሊም ይናገራሉ።
የህዝቦች መተዋወቅ ለብሄራዊ አንድነትና መግባባት እገዛ እንደሚያደርግ፣ መተዋወቅን አንድነትን፣ ፍቅርን፣ መፈቃቀድን፣ መቻቻልን እንደሚያመጣ እንዲሁም የተለያዩ ባህሎች ህዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ ሲወጡ ትልቅ የመተዋወቂያ መድረክ እንደሚሆኑም ይገልጻሉ። የህዝቦች መቀራረብና የባህል መመጋገብ እንደሚፈጠርና አንዱ የሌላውን ባወቀ ቁጥር መጫወቻ ሜዳው ስለሚሰፋ መገፋፋት አይኖርም ይላሉ ዶክተር አለሙ።
አቶ በለጠ ሞላ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው ። ባለቤታቸው የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጅ ሲሆኑ፤ እርሳቸው ደግሞ የአማራ ብሄረሰብ ተወላጅ ናቸው። አቶ በለጠ ‹‹ኢሬቻ ለሰላም›› በሚል መልዕክት በተካሄደው ሩጫ ላይ ከባለቤታቸውና ከልጃቸው ጋር ተሳታፊ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።
እርሳቸው እንደሚሉት በሃይማኖታዊ አስተምሮም ሆነ በሳይንሳዊ ምልከታ የሰው ልጅ መነሻው አንድ ነው። በሂደት ግን በመልክዓ ምድራዊ ተጽዕኖም ይሁን በተለያዩ ምክንያቶች የሰው ልጅ በቡድን መኖር በመጀመሩ የየራሱን ቋንቋ፣ባህልና ልምድ እየፈጠረ እንደመጣ ይናገራሉ።
የሰው ልጅ በቋንቋና በባህል መለያየቱ መሰረታዊ አንድነቱን እንደማያጓድል የተናገሩት አቶ በለጠ ፤ ለዘር ለሃይማኖትና ለባህል ድንበር በማበጀት ልዩነቶችን ማጉላት ማህበራዊ አንድነትን ከማላላት ያለፈ ምንም ትርጉም እንደማይኖረው ይናገራሉ። ሰው መለያየትና ጥላቻን ከሚያመጡ መጥፎ አስተሳሰቦች ይልቅ በሰላምና በፍቅር ለመኖር የሚያስችሉ እሴቶቹን ዋጋ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ይመክራሉ። በዚህም ምክንያት የኢሬቻ በዓልን አስመልክቶ በተዘጋጀው እሩጫ ላይ በመሳተፍ አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
አቶ በለጠ አሁን በሀገራችን የሚታዩ ችግሮችን በፍጥነት ማስወገድ ያልተቻለው ሰዎች ይዘዋቸው ለመጡት ማህበራዊ እሴቶች ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠታቸው እንደሆነ ያምናሉ። በሀገራችን ህዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት መልካም እንዲሆን ሰዎች ባህላዊም ሆኑ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችና እሴቶችን ዞር ብለው መመልከት ያስፈልጋቸዋል ይላሉ።
አቶ በለጠ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ባህላዊ እሴቶች ሰላምን አንድነትንና ፍቅርን በማጎልበት ረገድ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ እንደነበር በማስታወስ፤ አሁንም እሴቶቻችን ማህበራዊ አንድነታችንን ለማስቀጠል ሚና ስላላቸው ይህ የእከሌ ነው ሳንል ልናከብራቸው እንደሚገባ ያስረዳሉ። ባለቤታቸውና እርሳቸው ከተለያየ ብሄረሰብ እንደመጡ የተናገሩት አቶ በለጠ፤ የሁለቱንም ብሄረሰቦች ባህል ጠንቅቀው ለማወቅ እንደረዳቸው ገልጸዋል።
አንድ ሰው የሌላውን ብሄረሰብ ቋንቋና ባህል ሲያከብር ሌሎችም የእርሱን ሊያከብሩለት እንደሚችሉ የተናገሩት አቶ በለጠ ፤ በሁሉም ጉዳዮች መደጋገፍና አብሮ መቆም አንድነትን ያጠናክራል ብለዋል። ኢሬቻ፣ ሻደይና አሸንዳ በአላት በአዲስ አበባ ከተማ ሲከበሩ የብሄሩ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ሊያከብሯቸው የሚገባው የሀገር ቅርስ እንደሆኑ በአጽንኦት ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያ እያንዣበበ ያለውን መጥፎ ድባብ ለማስወገድም ባህሎቻችን መድሀኒት ሊሆኑን እንደሚችሉ አቶ በለጠ ገልጸዋል። እንዲህ አይነት ህዝብን የሚያገናኙ መድረኮች ፍቅርና አንድነትን ያሰፍናሉ፤ መላመድና መቀራረብን ያዳብራሉ ብለዋል።
ለአብነትም ሰላም ፣ፍቅርና አንድነት መገለጫው የሆነው የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ብሄረሰብ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ባህል መሆኑን ጠቅሰዋል። በዓሉ በሰው ልጆችና በተፈጥሮ መካከል ስላለው ግንኙነት ፣ ስለእንስሳትና እጽዋት ስለዝናብ ፣ ስለ አዝርዕት፣ ስለመልክዓምድር፣ ስለአየር ንብረት ፣ ስለሀገር፣ ስለ መላው የሰው ልጆችና ስለዓለም ፈጣሪ የሚመሰገንበትና ሰዎችም ቃላቸውን የሚያድሱበት ነው። ይህ ባህል በሀገር ውስጥ ስላሉ ብሄር ብሄረሰቦች ደህንነት ፈጣሪ የሚለመንበት በመሆኑ ሰዎች በፍቅርና በሰላም እንዲኖሩና እንዲቀራረቡ የሚያደርግ መሆኑን አቶ በለጠ አስረድተዋል።
በተመሳሳይም የመስቀል በዓልም በብዙ ብሄረሰቦች ዘንድ በድምቀት እንደሚከበር ያስታወሱት አቶ በለጠ፤ ይህ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴት ለሌሎች ብሄረሰቦችም ቅርሳቸው እንደሆነ መታሰብ አለበት ብለዋል። ዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት የመዘገበው የመስቀል በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለበት ግማደ መስቀል መገኘት ጋር ተያይዞ የደስታ መግለጫ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህ ክብረ በዓል ላይ በርካታ ህዝብ ተገኝቶ ታሪኩን ይዘክራል፤ ደስታውንም ይገልጻል። መስቀል ፣ የፍቅር ፣ የደህንነት ፣የሰላም ፣ የአንድነት የብርሀንና የበርካታ በጎ ተግባራት መገለጫ ተደርጎ ይታሰባል። በአጠቃላይ በሁሉም የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ፍቅርንና አንድነትን የሚሰብኩ መሆኑ ህዝቦችን በፍቅር ለማስተሳሰር ይጠቅማሉ።
በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት በረሳ አሰፋ በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበሩት የተለያዩ አካባቢዎችን የሚያንጸባርቁ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በአላት በብሄር ብሄረሰቦች መካከል መቀራረብን በመፍጠር አንድነትን የማጉላት ሚና እንዳላቸው ይናገራል። ኢሬቻም ሆነ መስቀል በመልካም አስተሳሰብ ላይ የተመሰረቱና ትውልድን የሚገነቡ ሀገርን የሚያደረጁ በመሆናቸው የአንድ አካል ጉዳይ ብቻ ተደርገው መታየት የለባቸውም ይላል። ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ከሁሉም በላይ ሰላም እንደሚያስፈልጋት የገለጠው ወጣት በረሳ፤ የሀገራችን ህዝቦች የመልካም ባህሎቻችንን ፍልስፍና በመከተል እርስ በእርሳቸው ይቅር ተባብለው አዲሱን ዓመት የሥራና የብልጽግና ማድረግ እንደሚገባቸው መልዕክቱን አስተላልፏል።
ብሄር ከብሄረሰብ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ሲኖረው ሀገሪቱ ሰላም ትሆናለች ያለው ወጣቱ፤ ወደ ሰላም የሚወስዱንን ባህላዊ እሴቶች በሙሉ በማክበር አንድ መሆን ወቅቱ የሚፈልገው ጉዳይ እንደሆነም አስረድቷል። በተለይም በአዲስ አበባና አካባቢዋ የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦች እንደ መስቀልና ኢሬቻን የመሳሰሉ በዓላትን በጋራ የማክበር ዕድል ስላላቸው በርካታ ቱሩፋትን በመውሰድ በማህበራዊ ህይወታቸው ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ተናግሯል።
ኢሬቻ ፍቅር፣ ሰላም ፣ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ብሩህ ተስፋን የሚፈነጥቅ ባህላዊ እሴት መሆኑን የተናገረው ወጣት በረሳ ፤ ሁሉም ሰው የበዓሉ ታዳሚ በመሆን ስለሰላም በጋራ ሊዘምር እንደሚገባ ምክረ ሀሳቡን ሰጥቷል።ኢሬቻ ሁሉም ብሄረሰብ ተቃቅፎና ተደጋግፎ በፍቅር እንዲኖር በር የሚከፍትና አቃፊነትን የሚያስተምር በመሆኑ በአዲሱ ዓመት ሰዎች በእርቅ በፍቅርና በሰላም እንዲኖሩ ወጣቱ ጥሪ አቅርቧል።
የተለያዩ በዓላት በከተሞች አካባቢ እንዲከበሩ ማድረጉም በተለይም አዲሱ ትውልድ የማያውቃቸውን ሀይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቹን እንዲያውቅ ዕድል እንደሚፈጥርም ወጣት በረሳ ተናግሯል።
ወጣቶች በተለይም የነገው ትውልድ ተረካቢዎች ከወላጆቻቸው ፍቅርና አንድነትን በመውረስ መጪዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት የአባቶቻቸውን አደራ መቀበል አለባቸው ብሏል። በመሆኑም እንደ ኢሬቻ ለመሳሰሉ ችግር ፈቺ ባህሎች ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልጿል። እነዚህን የሰላም መንገዶች በመከተልም ሀገራችንን ከተደቀነባት ሥጋት ማውጣት የወጣቱ ኃላፊነት እንደሆነም ጠቅሷል።
ኢሬቻ የመቻቻል ፖለቲካን መፍጠር ፣ የጋራ አንድነትን መመስረትና አዲሲቷን ኢትዮጵያን መገንባት የሚችሉ ዜጎችን መቅረጽ የሚያስችል ባህላዊ ትምህርት ቤት ነው። የክረምቱን ማብቃትና የብርሃን መፈንጠቅን ተከትሎ በየዓመቱ የሚከበረው የኢሬቻ ክብረ በዓል ለፍጡራን በተለይም ለሰው ልጆች መልካም በረከትን ይዞ እንደሚመጣ የሚታመነው ሰዎች የገቡትን ቃል ኪዳን ሲፈጽሙ እንደሆነ ወጣት በረሳ አስረድቷል። አያይዞም ወጣቶች የኢሬቻን ተልዕኮ በማንገብ በህዝቦች አንድነትና ፍቅር ፣በሀገራቸው ሰላምና ደህንነት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው መክሯል።
አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት ፤የተለያዩ ባህሎች ከሚከበሩበት አውድ ወጥተው በከተሞች አካባቢ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ መከበራቸው ከሚኖራቸው ባህላዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳቸውም የጎላ ነው።አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ መስቀልና ኢሬቻ በአሮጌው ዓመት ማብቂያና በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ላይ የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችን ናቸው።
ከዚህ አንጻር የሽግግር በዓል ናቸው ማለት ይቻላል። ከክረምቱ ባሻገር የሚታየው ህይወትን የሚያድሰው የምድር ልምላሜና ነፋሻ አየር ተስፋ ሰጪ ነው። በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ የሚገዳደሩ በርካታ ችግሮች ቢከሰቱም ከፈተናውና ከውጣ ውረዱ በኋላ የተሻለ ዘመን እንደሚመጣ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ።ከባህሎቻችን ያገኘናቸውን የፍቅር ፣ የመቻቻልና የአንድነት መንፈስ በማጠናከር ለሀገራችን ሰላምና ብልጽግና ማዋል እንደሚያስፈልግ ክብረ በዓላቱ ያስተምራሉ። ግለሰቦች፣ ብሄረሰቦችም ሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መገፋፋትና ጥላቻን ትተው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሀገራቸውን ለማሳደግ በሚያስችሉ ሃሳቦች ላይ ብቻ ቢያደርጉ ሰላምን ያተርፋሉ።
አዲስ አበባ ከተማ እንደአፍሪካ መዲናነቷ እና የዲፕሎማቶች መቀመጫም እንደመሆኗ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መገለጫ የሆኑ በዓላት በከተማዋ መበራከታቸው የቱሪስቶችን ቁጥር ለመጨመር ፣ ባህሉንም ለዓለም ህዝብ በማስተዋወቅ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በተጨማሪም የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያሳድጋል። ዜጎችም ባህላዊ አልባሳት፣ጌጣጌጦችና የተለያዩ ነገሮችን አዘጋጅቶ በመሸጥ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
በዚህ ረገድም ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጠራል። በተለይ የወጣቶች ተጠቃሚነት የጎላ ይሆናል። ወጣቶች ከባህላዊ እሴቶች የሚያገኟቸውን ቱሩፋቶች ጥቅም ላይ በማዋል እርስ በእርስ የመከባባር፣ የመፋቀርና የእኩልነት ስሜትን እንዲያዳብሩ ያግዛቸዋል። የሁሉንም አካባቢዎች የሚያንጸባርቁ ባህሎች በአደባባይ መከበራቸው በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እያበበ ስለመሆኑም አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል። የማንነት መገለጫ የሆኑ የባህል እሴቶች ሳይበረዙና ሳይሸራረፉ ከትውልድ ትውልድ ማሸጋገሩ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ካለፉት የበዓል አከባበር ክንውኖች መረዳት ይቻላል።በመሆኑም ጠብቆና አክብሮ ማስቀጠል ከዜጎች ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2012
ኢያሱ መሰለ