መከራና ደስታ
ሀብትና ድህነት
ስቃይና ምቾት
የሚፈራረቁበት
ኑሯችን ነው እንጅ
ቀኑን ‘ሚያሳጥረው
የሚያስረዝመውም
ቀን በራሱ ጊዜ
የሚረዝም የሚያጥርበት
ምንም ኃይል የለውም፤
የሚረዝም የሚያጥረው
የሚቀያየረው
እኛ ያለንበት
ሁኔታው ነው እንጅ
ቀኑን ሚያሳጥረው
ቀኑን ሚያስረዝመው
ቀን ምን ቁመት አለው
ለቀን ጉልበት ሚሰጥ
ህይዎትን የሚያመር
ህይዎት የሚያጣፍጥ
ቀኑን ሚያስረዝመው
ቀኑን ‘ሚያሳጥረው
ኃያሉ ኑሮ እንጅ
ቀንማ በራሱ
‘የሚያጥር ‘የሚረዝምበት
ሚንቀሳቀስበት
ምን ህዋሳት አለው፡፡
ዕድሜ እየቆጠረ
ዕድሜ እየሰፈረ
እሱ ዕድሜ የሌለው
የሰው ልጅ ከሌለ
ብቻውን ማይኖር
በህይዎት ብርሃን
ህያው ሆኖ የሚኖር
ቀን ራሱን ችሎ
ምንስ ህላዌ አለው
ሁኔታው ነው እንጅ
ኑሯችን ነው እንጅ
ቀኑን ሚያስረዝመው
ቀኑን ‘ሚያሳጥረው
ቀንማ ለራሱ
ሁነት ተከትሎ
የሚያጥር የሚረዝም
የኑሮ ጥላ ነው!
(“ልሳነ ነፍስ” በሚል ርዕስ ለህትመት በዝግጅት ላይ ከሚገኝ የራሴ የግጥም መድበል የተወሰደ ግጥም ነው)
ውድ አንባቢያን በእርግጥ ጊዜንና ዕድሜን በተመለከተ የእኔ ዕምነት በዚህ ግጥም ውስጥ እንደተገለፀው ነው።በእኔ ዕምነት ያለንበት የኑሮ ሁኔታና እኛ ለነገሮች ያለን አመለካከት እንጅ ጊዜን ጨምሮ ማንኛውም ኑባሬ በእኛ ላይ ኃይል የለውም።ምክንያቱም በነፃ ፈቃድ ‹‹Free Will›› ይሉታል እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎቹ በእጅጉ አምናለሁ።ነፃ ፈቃድ ማለት በአጭሩ ሰዎች የፈለጉትን ዓይነት ህይወት ለመኖር “ምርጫው የእነርሱ ነው” የሚል እሳቤ ነው።
ይህ አስተሳሰብ በበርካታ የዓለማችን ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች የሚታመንበት ከመሆኑም በላይ በፍልስፍናውና በሥነ ልቦና ሳይንሱም አበክሮ የሚደገፍ ነው።ለአብነት ታላቁ መጽሐፍ የሚባለው መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው በልቡ ያሰበውን እንዲሁ ደግሞ ይሆናል” በማለት ስለ ነፃ ፈቃድ እውነታነት አስረግጦ የሚናገር ሲሆን፤ የመጽሐፍ ቅዱስ መነሻና መድረሻ የሆነው መምህሩ ኢየሱስ ክርስቶስም “እውነት፣ መንገድና ህይወትም እኔ ነኝ” ቢልም ሰዎች ፍላጎታቸው ከሆነ ግን ሞትን ቢመርጡ እንኳን በምርጫቸው ጣልቃ እንደማይገባ “እነሆ እሳትና ውሃ ቀርቦላችኋል፤ እጃችሁን ወደ ፈለጋችሁት መስደድ ትችላላችሁ” በማለት በቃሉ አረጋግጧል።
በሌላ በኩል የሥነ ልቦና ሳይንሱ ከዚህ በቀጥታ የተቀዳ በሚመስል መልኩ መልካምም ይሁን ክፉ በአንድ ሰው ህይዎት ውስጥ የሚፈጠሩና የተፈጠሩ ነገሮች ሁሉ በራሱ ምርጫ የሚፈጠሩ መሆናቸውን በጥናትና በምርምር ሳይቀር በማስደገፍ ረጅም ርቀት ሔዶ ርግጠኛ ሆኖ ይከራከራል።ይህንንም “የስበት ህግ” በማለት ይጠራዋል።“እኛ ማለት የምናስበውን እና የምናምነውን ነን” የሚለው እሳቤም በፍልስፍናው ዓለም ለዘመናት የታወቀ ነው።እናም ህይወታችንን የምናሳምረውም የምናበላሸውም እኛው ራሳችንን ነን ብዬ አምናለሁ።
ሆኖም ከዚህ በተቃራኒው ዓለም በዕድል በሚያምኑ ሰዎች የተሞላች ናት።በተለይም በእኛ ሀገር “ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚችለው ጊዜ ነው” የሚል በከፍተኛ ደረጃ የሚታመንበት፣ ለዘመናት የቆየ፣ ሥር የሰደደ አስተሳሰብ አለ።ከፈጣሪ በላይ ጊዜ ይመለካል ቢባል ብዙም የሚጋነን አይሆንም።“ጊዜ የጣለውን ጊዜ ያነሳዋል”፣ “ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል”፣ “የቀን እንጅ የሰው ጀግና የለውም”፣ “ቀን እስኪያልፍ የአባትህ ባሪያ ይግዛህ”፣ “የእኔም ጊዜ ይመጣል”…የሚሉ አባባሎቻችንም ይህ አስተሳሰብ ምን ያህል በህብረተሰቡ ውስጥ ሰርፆ የገባ መሆኑን በደንብ የሚያሳዩ ህያው ምስክሮች ናቸው።
ምን ይሄ ብቻ አንድ የህብረተሰብ ሁለንተናዊ መገለጫ የሆኑት የጥበብ ውጤቶቻችንም በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የጊዜን አድራጊ ፈጣሪነት ሳይሰብኩ የማያልፉ ናቸው።“ጊዜ ጌታ፣ ጊዜ ንጉሥ” የሚል ዜማ በሚደመጥበት ሀገር ከፈጣሪ በላይ ጊዜ ይመለካል ቢባል ምን ማጋነን ይሆናል።የሙዚቃ ነገር ከተነሳማ የቱ ተነግሮ የትኛው ይቀራል።“አቤት ጊዜ”፣ “ወይ ጊዜ”፣ “በጊዜ”፣ “አይሻለሁ በጊዜ” …።“የምን ሃሳብ የምን ትካዜ፣ ሁሉ ሊሆን በጊዜ” የሚለውን ብቻ ቃላቱ ሳይለወጥ በሦስት ታዋቂ ድምፃውያን ዘፈኖች ውስጥ ማዳመጤን አስታውሳለሁ።ስለ ጊዜ ኃያልነት የማይቀነቀንበት የዘፈን ሥራ የለም የሚለው ይቀላል።በሥነ ጽሁፎቻችንና በፊልሞቻችን ያለውም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
ብቻ በእኛ ሀገር ጊዜ ያልሆነው ነገር ምን አለ? ጨቋኞችና አንባገነንነኖች ጊዜያቸው ካልደረሰ ከስልጣናቸው ነቅነቅ አይሉም፣ ህዝቡም የቱንም ያህል ግፍና በደል ቢበዛበት፣ በጭቆና መዳፍ ሥር ሆኖ በባርነት ቀንበር ቢማቅቅ፣ በፍትህና በዕውነት ጥማት ቢሰቃይ ጊዜውን ይጠባበቃል እንጅ ታግዬ ነፃነቴን ላስከብር የለም።ምክንያቱም ጊዜው ካልፈቀደ ምንም ባደርግ አንባገነኖችን ማውረድ አልችልም ብሎ ያምናልና።እናም አንባገነኖች ከስልጣን የሚወርዱት በጊዜ ነው።ፍትህና ነፃነትም የሚገኘው በጊዜ ነው።
ጀግና የሚኮነው በጊዜ ነው፤ ጀግና ራሱ ጊዜ ነው።ድህነት ቢበዛ፣ ችጋር ቢበረታ በጊዜው ካልሆነ ከድህነት መውጣት አይቻልም።ምክንያቱም ጊዜው ካልፈቀደ ከድህነት ለመላቀቅ ጠንክሮ መሥራት በከንቱ መልፋት ይሆናል፤ ሀብት የሚገኘው በጊዜ ነዋ¡ ስኬታማ ለመሆን ጊዜ ያስፈልጋል።ደስተኛ ለመሆን ራሱ ጊዜው መፍቀድ አለበት።ዛሬ ቀኑ ደብሮኛል ብለው ቀኑን ሙሉ ሲቆዝሙ የሚውሉ ሰዎች አጋጥመዋችሁ አያውቁም? እኔ ግን “ዛሬስ ቀኑ ረዘመብኝ በጣም ደብሮኛል”፣ “ዛሬስ ምን ሆኜ ነው? ቀኑ በጣም አጠረብኝ!”፣ “የዛሬው ቀንስ ርዝመቱ፣ ተገትሮ ዋለ ሲያስጠላ!” የሚሉ አስተሳሰባቸውና ኑሯቸው በቀን ቁጥጥር ሥር የዋለ መዓት ሰዎችን አውቃለሁ።
ይህም ያለንበት የኑሮ ሁኔታና እኛ ለነገሮች ያለን አመለካከት እንጅ “እንዴት ቀን በራሱ ሊያጥርና ሊረዝም ይችላል?” የሚል ጥያቄንና ግርምትን ስለፈጠረብኝ ነበር በአንድ ወቅት በመግቢያው ላይ የተቀመጠችውን ግጥም በማህፀነ ህሊናዬ ፀንሸ የወለድኳት።
እዚህ ጋ ማሳየት የፈለኩት ዋናው ቁም ነገር አስተሳሰባችንና ነገሮችን የምንመለከትበት የህሊና መነፅር እንጅ ጊዜን ጨምሮ ማንኛውም ውጫዊ ኑባሬ የእኛን ዕጣ ፋንታ የመወሰን አቅም የለውም የሚለውን እንጅ ጊዜ የራሱ የሆነ ዋጋ ያለው መሆኑን አጥቼው አይደለም።እንደዚያ ቢሆን ኖሯማ ከሀብትና ከባለጸግነት ይልቅ ጥበብን በመምረጡ ከሁሉም በላይ ጥበብ የተሰጠው አራት ዓይናው ጠቢብ ንጉሥ ሰለሞንም “ለሁሉም ጊዜ አለው” ባላለ ነበር።
በእርግጥ በህይወት ጎዳና ላይ ማንኛውም የዕድሜ ክልል የራሱ የሆኑ አወንታዊና አሉታዊ ገፅታዎች አሉት።“ልጅነቴ፣ ልጅነቴ ማርና ወተቴ” የምትለዋን መዝሙር ደግመን ደጋግመን ዘምረን ብናድግም በወጣትነት የዕድሜ ክልል ላይ ስንደርስ በሚሰማን ትኩስ የህይወት ኃይልና የአሸናፊነት መንፈስ ያለምንም ፍርሃትና ማቅማማት የፈለግነውን ነገር ሁሉ በድፍረት ስናደርግና አንዳንዴም ተሳክቶልን ጀብዱ ስንፈፅም በወጣትነታችን ከልብ መደሰታችን አይቀርም።
ሁሉንም ነገር በስሜት ከማድረግ፣ ከችኩልነትና ከግብታዊነት ወጥተን ክፉና ደጉን አመዛዝነን ወደ ምንወስንበት ደረጃ ተሸጋግረን፤ ለአቅመ አዳምና አቅመ ሔዋን ደርሰን፣ ለወግ ለማዕረግ በቅተን፤ ተድረንና ተኩለን ከልጅነት አልፈን ልጅ ወልደን ማሳደግ ስንጀምር ደግሞ አብሮ የሚመጣው ድርብርብ ኃላፊነት ቢከብደንም ኃላፊነታችን የምንወጣ፣ አስተዋዮችና አዋቂዎች ለመሆን በመብቃታችን አዲስ ደስታን ይፈጥርልናል።
እንደዚሁ የጎልማሳነት ዘመናችንን ጨርሰን ወደ ሽምግልና ደረጃ በምንደርስበት ጊዜ አቅማችን እየተዳከመ በመሄዱ ምክንያት እንደ ልባችን ሰርተን የፈለግነውን ነገር በፈለግነው ሰዓት ማግኘት ባለመቻላችንና የልጆቻችን እርዳታ ወደ መጠበቅ በመሸጋገራችን ቅር መሰኘታችን አይቀሬ ይሆናል።ይሁን እንጂ ክፉንም ደጉንም አሳልፈን፣ ሁሉንም አይተን በረጂሙ የዕድሜ ዘመናችን ባካበትነው ሰፊ የህይወት ልምድና ዕውቀት ክብርና ሞገስን አግኝተን፣ መካሪና አስተማሪ፣ ሸምጋይና አስታራቂ ለመሆን በመታደላችን በዚህም እንደሰታለን።በዕድሜያችን ምክንያት ህብረተሰባችን አክብሮን አርዓያና መሪ አድርጎ ሲሾመን እውነትም ዕድሜችን ፀጋችን መሆኑን እንረዳለን።በዚህም ደስ እንሰኛለን።
እንዲያውም ሐቁ ይህ ቢሆንም፤ በማንኛውም የዕድሜ ክልል ላይ መሰራት የሚችሉ ነገሮች ቢኖሩም “ለሁሉም ጊዜ አለው” እንዳለው ጠቢቡ አንዳንዶቹ ግን የግዴታ ዕድሜን መሰረት አድርገው መከናወን የሚገባቸው ተግባራት አሉ።በሌላ አነጋገር የግድ በዚያ የእድሜ ክልል ውስጥ ካልተደረጉ በስተቀር ተመልሰው ሊገኙ ባለመቻላቸው የሚቆጩ ይሆናሉ ማለት ነው።ይህንንም ኢዱኬት ኢንስፓየር ቸንጂ ድረ ገጽ “በወጣትነት ዘመን ካልተደረጉ በስተቀር በስተ እርጅና ዘመን ሊያስቆጩ ይችላሉ” ብሎ ከዘረዘራቸው ነገሮች መካከል ለአብነት ሁለቱን ብቻ በማሳያነት ወስደን የ “ለሁሉም ጊዜ አለውን” ትክክለኛነትና ተገቢነት እንመልከት፡፡
ለምሳሌ አንድ የማያውቁትን ወይንም የአፍ መፍቻ ያልሆነ እንግዳ ቋንቋ ለመማር የህጻንነት የዕድሜ ክልል ተመራጭ መሆኑን በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።ዕድሜ እየገፋ በሄደ ቁጥር ቋንቋን ለመማር አዳጋች መሆኑንም የቋንቋ ምሁራን ይገልጻሉ።በአንፃሩ የህጻንነት የዕድሜ ክልል በተፈጥሮው ቋንቋ ለመማር አመቺ በመሆኑ ከአፍ መፍቻችን ሌላ ሌሎች ቋንቋዎችን በፍጥነትና በቀላሉ መልመድ ወይም መማር እንችላለን።
እናም በልጅነታችን ከራሳችን ቋንቋ ውጭ ሌሎች የምንፈልጋቸውን ቋንቋዎች ብንማር ቋንቋ ዘመናችን ከላይ የተጠቀሰው ድረ ገፅም በስተእርጅና ከሚቆጩ ነገሮች መካከል አንዱ ከአፍ መፍቻ ቋንቋችን በተጨማሪ ሌላ ቋንቋ ለመማር አለመሞከራችን መሆኑን መለክታል።
ምክንያቱ ደግሞ ቀደም ብሎ እንደተገለጸው ዕድሜችን ከገፋ በኋላ ቋንቋ ለማማር መሞከር ከውጤታማነቱ ይልቅ ልፋቱ ያመዘነ ስለሚሆን ነው።በመሆኑም ያለፈው አልፏልና ልጅዎ ከአፍ መፍቻው ሌላ ቋንቋ እንዲማርና እንዲያውቅ ፍላጎት ካለዎት ጊዜው አሁን ነውና እንዲማር ያድርጉት ኋላ ላይ በስተእርጅና ከሚመጣ “የተምሬ ቢሆን” ቁጭትና ፀፀት ያድኑታልና፡፡
እንደዚሁ አንድ በጣም የሚፈልጉትን ነገር ማድረግ ፈልገው ነገር ግን በማህበረሰብ ወግና ቀኖና ታጥረው ወይም በምን ይሉኝ ፍርሃት ምክንያት ሳያደርጉት በመቅረትዎ ባመለጥዎት ነገር ተቆጭተው ያውቃሉ? አዎ የሚፈልጉትን ነገር ያለ ምንም ይሉኝታና ፍርሃት ለማድረግ ትክክለኛ ጊዜው የወጣትነት ዕድሜዎ ነበር! ምክንያቱም ወጣትነት በትኩስ ኃይል የምንሞላበትና “የእሳትነት ባህሪ” የሚገለጽበት እንደ መሆኑ መጠን የምንፈልገውን ነገር ለማድረግ ያለ ገደብ ፍላጎታችንና ስሜታችን የምንገልጽበት ዕድሜ ስለሆነ ነው፡፡
“ጥሩ ነው ወጣት መሆን ገንዘብ ባይኖርህ ጤና ይኖርሃል፣ መልክ ባይኖርህ ጉራ ይኖርሃል፣ ደስታ ባይኖርህ ንዴት ይኖርሃል፣ ፍቅር ባይኖርህ ተስፋ ይኖርሃል፣ ዕውቀት ባይኖርህ ጉራ ይኖርሃል፣ መጨቆን ቢበዛብህ ሪቮሉሽን ታነሳለህ…መኖር ቢያስጠላህ ወይም ቢያቅትህ ራስህን ትገድላለህ።ሰው ባያውቀውም ቅሉ ታሪክ ይኖርሃል፣ ወጣት ነህና!” የሚለው የጋሽ ስብሐት አባባልም ነገሮች የሚደረጉባቸው የራሳቸው ውስን የጊዜ ክልል ያላቸው መሆኑን ከፍ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
ወጣትነት ለፈለጉት ነገር ሞትም የሚደፈርበት የዕድሜ ክልል በመሆኑ የፈለግነውን ነገር የማድረግ ዕድላችን ከፍተኛ ነው።እናም በወጣትነትዎ ሳያደርጉት በመቅረትዎ በእርጅና ዘመንዎ “ምናለበት አድርጌው ቢሆን” ብለው ከሚቆጩባቸው ነገሮች መካከል ምናልባትም በብዙዎች ዘንድ የሚከሰተውና ዋነኛው ይኸው የፈለጉትን ነገር የማድረግ ፍራቻና ይሉኝታ ነው።
ጠቢቡ “ለሁሉም ጊዜ አለው” ማንኛውም ነገር የሚደረገው “በተወሰነ የጊዜ ክልል ውስጥ መሆኑን” ለማመልከት እንጅ እኛ እንደምናደርገው ነገርን ሁሉ ለጊዜ እየሰጡ፤ በጊዜ እየተመሩ መኖር ይገባል ማለቱ አይደለም።“ጊዜ ይመልሰው” እያሉ ሁል ጊዜ በቀጠሮ መኖር አይደለም “ለሁሉም ጊዜ አለው” የሚለው ቃል ትርጉም።ይህን ለመረዳት ቃሉን እንደ ጠቢብ ሆኖ በጥበብ ማስተዋል ይገባል።
በመጽሐፈ መክብብ ምዕራፍ ሦስት ቁጥር አንድ ላይ የተቀመጠው የጠቢቡ ሰለሞን ቃል እንዲህ ነው የሚለው፤ “ለሁሉ ዘመን አለው፤ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው”። የእንግሊዝኛውን ትርጉም ወስደን ብንመለከተው ደግሞ ቃሉ ምንን ለመግለጽ ታስቦ እንደተጻፈ በማያሻማ መንገድ ተቀምጦ እናገኘዋለን።“To everything there is a season, and a time to every purpose under the heaven”(ሰረዙ ከራሴ የተጨመረ) ነው የሚለው።“ለሁሉም ጊዜ አለው” የሚለውን ዓረፍተ ነገር ትክክለኛ ትርጉም የተሸከሙት በእንግሊዝኛ ትርጉሙ ውስጥ ያሰመርኩባቸው ሁለቱ ቃላት ናቸው።ይህም የቃሉ ትክክለኛ ትርጉም “ማንኛውም ነገር( purpose) የሚደረገው በተወሰነ የጊዜ ክልል( season) ውስጥ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
“ለሁሉም ጊዜ አለው” ለሚለው ቃል እኛ የሰጠነው ትርጉም ግን ከእውነታው በእጅጉ የራቀ ነው።ምክንያቱም እኛ ለሁሉም ጊዜ አለው ስንል ማናቸውንም ተግባሮቻችን በተሰጠን የጊዜ ክልል ውስጥ ከማከናወን ይልቅ ጊዜ ይሰራልን ይመስል “ጊዜው ሲደርስ ሁሉም ይሆናል” ወይም “ጊዜ ይሰጣል፣ ጊዜ ይነሳል” እያልን ጊዜን ሰጭ ነሽ አድርገን በራሳችን ላይ መሾማችን ነው።ይህ ደግሞ አላዋቂነት የፈጠረው ከንቱ ጊዜ አምላኪነት ነው።ማድረግ የሚገባነን ነገር በወቅቱ ካላደረግን በስተቀር መመለክ የሚገባው እውነተኛው አምላካችን ፈጣሪ ራሱ ሺህ ዓመት ብንጠብቀው የምንፈልገውን ነገር ሊሰጠን አይችልም።
ሰው ያልዘራውን አያጭድምና! ሰው የሚሆነውም አስተሳሰቡንና አመለካከቱን ነው፤ የሆንነውና የምንሆነው ነገር ሁሉ በራሳችን ምርጫ የተፈጠረና የሚፈጠር ነው፤ ዕጣ ፋንታችንንም የምንጽፈው በገዛ እጃችን ነው፤ ነጻ ፈቃድ ማለትም ይኸው ነው።ፈላስፋው ሞንቴስኩ እንዳለው በዚህ ዓለም ላይ በየቦታው ራሱን የእስር ሰንሰለት ውስጥ ቢያገኘውም ሰው በተፈጥሮው ነፃ ሆኖ ነው የተወለደውና!
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 14 / 2012
ይበል ካሳ