እሁድ መስከረም 21 ቀን 1978 ዓ.ም የወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ 46ኛ ዓመት ቁጥር 22 እትም “የፊልም ጣጣ” በሚል ርዕስ በፊልም ሥራ ወቅት የተከሰቱ ፈገግ ሚያደርጉ ሁለት ገጠመኞችን አስነብቦ ነበር።
የፊልም ጣጣ
ማናቸውም ተንቀሳቃሽ ፊልም በሚሰራበት ጊዜ የተለያዩ ችግሮችና እንቅፋቶች ሳያጋጥሙት ይጠናቀቃል ማለት ዘበት ነው። ችግር በሚፈጠርበትም ወቅት የፊልሙ ዲሬክተር ሥራውን ለተወሰነ ጊዜ ለማቋረጥ ይገደዳል። አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥሙት ችግሮች እንደ አየር ንብረት ለውጥና የመሪ ተዋንያን መታመም የመሳሰሉ ከበድ ያሉ ጉዳዮች ሲሆኑ፤ አልፎ አልፎ ግን በጣም ቀላል በሆኑ ምክንያቶች የተነሳ የፊልም ማንሳት ሥራዎች እየተስተጓጎሉ በአዘጋጆቹ ድርጅቶች ላይ ያልታሰበ ኪሳራ ይደርሳል።
ለምሳሌ ጥቂት ቆየት ባለ ዘመን ነው፤ አንድ ኩባንያ በአንድ ገበሬ እርሻ አጠገብ ፊልም በመሥራት ላይ ሳለ የገበሬው ዶሮዎች በኃይል እየተንጫጩ ሥራውን በማወካቸው ከቀትር በፊት መከናወን የነበረበት የፊልም ሥራ በሙሉ እንዲሰረዝ ተደረገና ድርጅቱ ባልታሰበ ኪሳራ ላይ ወደቀ። በዚህ ጊዜ የፊልሙ አዘጋጅ ችግሩን ለማቃለል ሲል በወሰደው እርምጃ ፤ ዶሮዎቹን በጠቅላላ በከፍተኛ ዋጋ ከገበሬው ላይ ገዝቶ በሙሉ ካስፈጃቸው በኋላ ሥራውን ቀጠለ።
በሌላ ጊዜ ደግሞ 41 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሆነበት “ክልዮፓትራ” የተሰኘው ፊልም በሚዘጋጅበት ጊዜ መሪ ተዋንያኑ ኤልዛቤት ቴይለርና ሪቻርድ በርተን አንዱን ትዕይንት በሚሰሩበት ክፍል ወለል ሥር ድመቶች ድምጽ እያሰሙ ይበጠብጣሉ። ድመቶቹ ተፈልገው እንዲወጡ ተደረገና ይኸው እስኪከናወን ድረስ የአንድ ሰዓት ጊዜ ባከነ። አንድ ሰዓት ያለሥራ በመባከኑም የ 17 ሺህ ዶላር ኪሳራ ደረሰ።
****************
አርብ ጥቅምት 20 ቀን 1957 ዓ.ም የወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ 24ኛ ዓመት ቁጥር 258 እትም ሮይተርስን ጠቅሶ “ተናካሽ ውሾችን በበርበሬ ማባረር ተጀምሯል” በሚል ርዕስ በአሜሪካን ቺካጎ ውሾችን ማባረሪያ አዲስ መላ ስለመገኘቱ አስነብቦ ነበር።
ተናካሽ ውሾችን በበርበሬ ማባረር ተጀምሯል
ትናንትና የቺካጎ ከተማ ፖስታ ቤት ሠራተኞች የውሻ ማባረሪያ መድኃኒት በፖምፕ እየነፉ ደብዳቤዎችን በየቤቱ ባደሉ ጊዜ የከተማ ነዋሪዎች በሙሉ ተደናግጠዋል። ይህን የውሻ ማስፈራሪያ ዘዴ ያመጡት የቺካጎው ፖስታ ቤት ኃላፊ ሚስተር ሐሪ ሴምራው ናቸው። የከተማው ፖስታ ቤት ሠራተኞች ደብዳቤዎችን በየቤቱ ሲያድሉ ብዙ ጊዜ በውሾች ተነክሰዋል።
ትናንትና እያንዳንዱ ፖስታ ቤት ሠራተኛ የመጣበትን ኃይለኛ ውሻ መልሶ ለማባረር የሚረዳውን የውሻ ማስፈራሪያ ይዞ ደብዳቤዎቹን በየቤቱ ሲያድል ውሏል። ውሾቹም ጭራቸውን ወደ መሬት እየሸጎጡ ሸሽተዋል። መርዝነት የሌለው ይህ የውሾች ማባረሪያ መድኃኒት የተሰራው ከበርበሬና ከነዳጅ ዘይት መሆኑ ተረጋግጧል።
(ሮይተርስ)
****************
ረቡዕ ታህሳስ 7 ቀን 1946 ዓ.ም የወጣው ሰንደቅ አላማችን ጋዜጣ 13ኛ ዓመት ቁጥር 35 እትም ዘመን የተባለውን በኤርትራ የሚታተም ጋዜጣ ጠቅሶ “አዲስ ጥርስ” በሚል ርዕስ አንድ አዛውንት ያጋጠማቸውን ያልተለመደ ክስተት አስነብቦ ነበር።
አዲስ ጥርስ
ዘመን የተባለው የኤርትራ ጋዜጣ በቁጥር 111 በወጣው ዓምዱ መቶ ዓመት የሞላቸው አንድ አረጋዊ አዲስ ጥርስ ማብቀላቸውን ለጋዜጠኞች እንደገለፁ ጽፏል። እኒህም አረጋዊ ሰው በምን ምክንያት ይህን ዕድል እንዳገኙ ቢጠየቁ፤ በባላገር በመኖር ካንዱ አገር ወዳንዱ በመዘዋወርና አየር በመለወጥ መሆኑን ለጋዜጠኞቹ አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 14 / 2012