ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ዘመን ለኢትዮጵያ ጠበቃ በመሆን የተሟገቱትና በኢትዮጵያ ዙሪያ ስምንት መጽሐፍትን የጻፉት ወይዘሮ ሲልቪያ ፓንክረስት ያረፉት ከ59 ዓመት በፊት በዚህ ሳምንት መስከረም 17 ቀን 1953 ዓ.ም ነበር።
ወይዘሮ ሲልቪያ ፓንክረስት ሚያዝያ 27 ቀን 1874 ዓ.ም እንግሊዝ አገር ማንችስተር ከተማ ውስጥ ተወለዱ። ሲልቪያ ለኢትዮጵያ መቆርቆርና ድምጽ መሆን የጀመሩት ኢጣልያ 1927 ዓ.ም በኅዳር ወር መጨረሻ ወልወል በተባለ የኢትዮጵያ ምድር ላይ በፈጸመችው ወረራ ምክንያት ነበር።
የሞሶሎኒ ዓላማ ኢትዮጵያን በሙሉ ለመውረር መሆኑን በመገንዘብ ሲልቪያ በጊዜው የነበረው የመንግሥታቱ ማህበር በገባው ቃልኪዳን መሠረት፤ ኢትዮጵያን ከኢጣልያ ወረራ እንዲያድን ብዙ የአቤቱታ ደብዳቤዎች በመጻፍና ሕዝባዊ ስብሰባዎች በማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገው ነበር። ነገር ግን እንግሊዝና ፈረንሳይ ከኢጣልያ ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለመቀራመት በማሰፍሰፋቸው ወረራው እንዲቆም የቀረበውን ሀሳብ የደገፈ አገር አልነበረም።
ሲልቪያ ብዙ የአቤቱታ ደብዳቤዎችን ለእንግሊዝና ለሌሎች መንግሥቶችና እንደ ቢ.ቢ.ሲ፣ ዴይሊ ኤክስፕሬስ፣ ማንቸስተር ጋርዲያን፣ ዴይሊ ቴሌግራፍና ኒውስ ክሮኒክል ላሉ መገናኛ ብዙኃን በመጻፍ በኢትዮጵያ ላይ ስለ ተቃጣው የፋሺስት ወረራ ሰፊ ግንዛቤ እንዲገኝና ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ከፍተኛ ጥረት አድርገው ነበር።
ኢትዮጵያ በባሪያ ንግድ ትጠቀማለች በማለት ፋሺስቶች ያሰራጩ የነበረውን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ተቃውመው አጋልጠዋል።
ጸረ–ፋሺስት አቋም የነበራቸውን እነጆሞ ኬንያታን፣ ኤሚ አሽዉድ ጋርቪን (ጃሜይካ) እንዲሁም የሞሶሎኒ ተቃዋሚ የነበሩ ጣልያናዊ ታጋዮችን ጭምር በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲተባበሩ አድርገው ነበር። በጊዜው በለንደን የኢትዮጵያ አምባሳደር ከነበሩት ዶክተር ወርቅነህ እሸቱ ጋር በመተባበርና ከእቴጌ መነን ጋር በመጻጻፍ በኢትዮጵያ በኩልም ስለ ነበረው ሁኔታ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲፈጠር ያደርጉ ነበር። ለኢትዮጵያ ነፃነት የሚያደርጉትን ትግል እንዲያግዙ ታዋቂ ከነበሩ የእንግሊዝ ምሁራንና የፓርላማ አባሎች ጋር በቅርበት ሰርተዋል።
ኢጣልያ ወረራዋን ቀጥላ ከሞላ ጎደል ኢትዮጵያን በተቆጣጠረችበት ዘመን ለዓለም መንግሥታት ማኅበር፣ ለዊንስተን ቸርችል፣ ለእንግሊዙ ሊቀጳጳስ፣ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሩዝቬልትና ለሌሎችም ኃያላን የአቤቱታ ደብዳቤዎች ጽፈዋል።
በ1928 ዓ.ም “New Times and Ethiopia News” የተሰኘ ጋዜጣ አቋቁመው ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤ እንዲኖር አድርገዋል። ጣሊያን በአዲስ አበባ ብቻ 30 ሺህ ሕዝብ በመጨፍጨፍ የፈጸመው የጦር ወንጀል በይፋ እንዲታወቅ አድርገዋል። አጼ ኃይለሥላሴ የዲፕሎማሲ ጥረት ለማድረግ በስደት አውሮፓ በተጓዙበት ወቅት ለንደን ሲደርሱ በክብር ተቀብለው በየጊዜው ቃለመጠይቅ በማድረግ ባቋቋሙት ጋዜጣ አማካኝነት በነበራቸው ሰፊ ሕዝባዊ ቅቡልነት ንጉሠ ነገሥቱ ድጋፍ እንዲያገኙ አድርገዋል።
የዓለም መንግሥታት ማህበር ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ በሚወያይበት ጊዜ ጄኔቫ ድረስ እየተመላለሱ መልዕክተኞቹን በማነጋገር ኢትዮጵያ ለጊዜው በኢጣልያ ብትወረርም የማህበሩ አባልነቷ እንደተጠበቀ እንዲቆይ ደክመዋል።
ምሁራንን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን፣ የፓርላማ አባሎችንና የቤተ እምነቶች መሪዎችን በማስተባበር በርካታ አቤቱታዎችንና መግለጪያዎችን በስፋት በማሰራጨትና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን በማካሄድ የእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያ ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ እንዲቀይር ባደረጉት ያላሰለሰ የፖለቲካ ትግል እንግሊዞች የኢትዮጵያን አርበኞች ጦር ደግፈው የጣልያን ጦር ድል ተመትቶ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ኢትዮጵያ ከፋሺስት ኢጣልያ ነፃ ከወጣች በኋላ ቀጥሎ የገጠማት ችግር የእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ወይም ኤርትራን፣ ኦጋዴንንና ቦረናን ለመያዝ መወሰኑ ነበር። በዚህም ረገድ ሲልቪያ ከአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ጋር በመተባበር የእንግሊዝ መንግሥት እኩይ ዓላማ እንዲከሽፍ ለ14 ዓመታት ባደረጉት ጠንካራ ትግልና በኢትዮጵያ መንግሥት አልበገር ባይነት ውጥኑ ሳይሳካ ቀርቶ በ1946 ዓ.ም እንግሊዝ ኢትዮጵያን ለቃ ወጥታለች።
ከፋሺስቶችና ከኮሎኒያሊስቶች ጋር በመታገል ካስገኙት ከፍተኛ ውጤት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ፓርላማ እንዲሻሻልና ኢትዮጵያውያን ሴቶች በአገራቸው የፖለቲካና የማኅበራዊ ጉዳዮች ያላቸው ተሳትፎ እንዲጠናከር በማሳሰብ ለአጼ ኃይለ ሥላሴ በጽሑፍ ሀሳብ አቅርበዋል። የልዕልት ፀሐይን ሆስፒታል ለማሠራት ገንዘብ አሰባስበዋል። ሃያ መጽሐፍትን የጻፉ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ ትኩረታቸውን ኢትዮጵያ ላይ ያደረጉ ስምንት መጽሐፍትን በመጻፍ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ፣ ባህልና ሥልጣኔ ቀሪው ዓለም ሰፊ ግንዛቤ እንዲያገኝ አድርገዋል።
ሲልቪያ በ1948 ዓ.ም በ74 ዓመታቸው ከልጃቸው ከሪቻርድ ፓንክረስት ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኑሯቸውን በአዲስ አበባ በማድረግ ከእርሳቸው እጅግ አስደናቂ አበርክቶ በተጨማሪ ልጃቸው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ የልጅ ልጃቸው አሉላ ፓንክረስትና ቤተሰቦቻቸው በሙሉ ኢትዮጵያን ያለመታከት እንዲያገለግሉ ምክንያት ሆነዋል። ወደኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት “ኢትዮጵያ ነፃነቷን ካገኘች አገልግሎቱ አብቅቷል” በማለት እንግሊዝ አገር አቋቁመው የነበረውን ጋዜጣቸውን እንዲቋረጥ አድርገው ኑሯቸውን በኢትዮጵያ በማድረግ “Ethiopia Observer” የተሰኘ ጋዜጣ አቋቁመዋል።
ሲልቪያ ፓንክረስት ለኢትዮጵያን ድምጽ በመሆን 20 ዓመታት ሙሉ ላደረጉት ተጋድሎ በአዲስ አበባ አንድ መንገድ በስማቸው እንዲሰየም ተደርጎ ነበር። አጼ ኃይለሥላሴም ለሲልቪያ ፓንክረስት በጻፉት ደብዳቤ ለእርሳቸው የነበራቸውን ከፍ ያለ አድናቆትና ለኢትዮጵያ የዋሉትን ውለታ ታሪካዊነት ገልጸውላቸው ነበር። ልጃቸው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት “Sylvia Pankhurst, Counsel for Ethiopia” በተሰኘው መጽሐፍ ለኢትዮጵያ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ጽፈውላቸዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ተጠምቀው ወለተ ክርስቶስ የሚል ስመ ክርስትና ያገኙት ወይዘሮ ሲልቪያ በተወለዱ በ79 ዓመታቸው መስከረም 17 ቀን 1953 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ አርፈው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ንጉሳውያን ቤተሰቦች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ዲፕሎማቶች በተገኙበት በታላቅ ክብር በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል።
ኪዳኔ ዓለማየሁ “ወይዘሮ ሲልቪያ ፓንክረስት እንግሊዛዊቷ የኢትዮጵያ ጀግና” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ለዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ምንጭ ባደረግነው ሰፋ ያለ መጣጥፍ ሲልቪያ ካበረከቱት አገልግሎት አንጻር ተጨማሪ መታወሻዎች ሊቆምላቸው ይገባል በማለት በስማቸው ትምህርት ቤት አሊያም የምርምር ማእከል አንዲቋቋም ሀሳብ አቅርበዋል። በተጨማሪም አሁን ያለውም ሆነ የወደፊቱ ትውልድ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ስለ ሲልቪያ ፓንክረስት ተጋድሎና ታዋቂ የሆኑት ምሁር ልጃቸው ሪቻርድ ፓንክረስት ያበረከቱት አስተዋጽኦ በአማርኛና በሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ተጽፎ እንዲሠራጭ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 14 / 2012
የትናየት ፈሩ