በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ፤ ለዓመታት የአልጋ ቁራኛ የሆነች አንዲት ባለፀጋ ሴት ነበረች። ሴትዮዋ አልጋ ላይ ሆና የቤቱን አጠቃላይ ክንውን ትቆጣጠራለች። የቤተሰቡ ልብሶች ታጥበው የሚሠጡት በመኝታ ቤቱ መስኮት አቅጣጫ ባለው ገመድ ላይ ነበር፡፡ ሴትዮዋ ታጥበው የተሠጡትን ልብሶች በመኝታ ቤቱ መስኮት መስታወት እያየች ሠራተኞቹን ልብሶቹ በደንብ እንዳልፀዱ ትጨቀጭቃቸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ጊዜ ሰራተኞች እየለቀቁ ይሄዳሉ። የቤቱ አባወራም ሰራተኛ በማመላለስ እስከመሰላቸት ደርሶ ነበር።
ከዕለታት በአንዱ ቀን ባለቤቷን አስጠርታ በስራ ላይ የነበረችውን ሰራተኛ ልብስ ማፅዳት ስለማትችል እንዲያባርራትና አዲስ ሰራተኛ እንዲያመጣላት ትጠይቀዋለች። በሁኔታው የተሰላቸው ባል እንድትባረር የተፈረደባትን ሰራተኛ ያስጠራና «ስራሽን በትክክል ባለመስራትሽ ልትባረሪ ነው። በሌሎች ሙያ ጎበዝ እንደሆንሽ ባለቤቴ መስክራልሻለች። ነገር ግን ልብስ አፅድቶ ማጠብ ባለመቻልሽ እንዳባርርሽ አዛኛለች። ያን የመሰለ የቤት ውስጥ ሙያ እያለሽ እንዴት ልብስ ማጠብ ያቅትሻል?»በማለት ይጠይቃታል።
ሠራተኛዋ ከዚህ በፊት በሰራችባቸው ቤቶች ልብስ በማፅዳት ላይ ቅሬታ ተነስቶባት አያውቅም። እንደውም ምስጋናዎች ነበር የሚቀርብላት። አሁን ግን በሚገባ ብታጥብም አሰሪዋን ልታስደስት አለመቻሏ አስጨንቋታል። ምክንያቱን በመመርመር ላይ ሳለች አንድ ሀሳብ ብልጭ ይልላታል። አሰሪዋ የምታይበትን መስኮት ስታየው ለብዙ ጊዜ ባለመፅዳቱ ቆሽሾ ነበር። ያለ የሌለ ጉልበቷንና ብልሃቷን ተጠቅማ የመኝታ ቤቱን መስኮት መስታወት አፀዳችው፡፡
በማግስቱ አሰሪዋ ከእንቅልፏ ከመንቃቷ በፊት በጠዋት ተነስታ የቤቱን ልብስ ሁሉ አጥባ አሰጣችው። ሴትዮዋ እንደ ልማዷ ታጥበው የተሠጡትን ልብሶች በመኝታ ቤት መስኮት በኩል አየቻቸው። ሰራተኛዋን አስጠርታ ‹‹ዛሬ ልብሶቹን በደንብ አጽድተሻቸዋል፤ እስከዛሬ ይሄን ችሎታሽን የት ደብቀሽው ነው?›› በማለት ጠየቀቻት። ሠራተኛዋም ሀሳቧ እንደሰመረላት በመረዳት‹‹ልብሶቹን ያፀዳሁት ከወትሮ በተለየ መንገድ አይደለም፡፡ በተለየ መንገድ ያፀዳሁት ግን መስታወቱን ነው›› ብላ የመስኮቱን መስታወት አሳየቻት፡፡
ብዙዎቻችን ነገሮችን የምናይበት የህሊና መስታወት አስተሳሰባችንን ይገድበዋል። ነገሮችን የምናይበት መንገድ ባለመስተካከሉና ባለመለወጡ የምናየው ነገር በሙሉ እንደለመድነውና ከነበረው ያልተለየ ሊመስለን ይችላል፡፡ አስተሳሰባችን ከነገሮች ጋር እንዲለወጥ ማድረግ የምንችለው እይታችንን ስናስተካክልና አዳዲስ ነገሮችን ለመቀበል በሚኖረን ፍላጎት ልክ ነው። ትክክለኛ አስተሳሰብ የነበረውን ነገር በነበረበት እንዲቀጥል ብቻ መፈለግን ይቃወማል። ምክንያቱም ነገሮች በጊዜ ሂደት መለወጥ ይኖርባቸዋል። አዳዲስ ፍላጎቶችና አዳዲስ አስተሳሰቦችም ወደ ትክክለኛነት የሚመሩ መንገዶች ይሆናሉና።
ቀደም ባሉት ጊዜያት የነበረን አተያይ ለውጥ ካላመጣን በአዲስ አስተሳሰብ ልንተካው ይገባናል። ተፈጥሯዊው ለውጥ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ የሚለዋወጥ ቢሆንም፤ የሠው ልጅ አመለካከት ግን በግል ፈቃዱ መለወጥ የሚችል እንደሆነ ይታመናል፡፡ ስለ አንድ ነገር ያለንን አመለካከት በተለያየ አቅጣጫ ማየት ከቻልን በየእለቱ አዳዲስ ነገሮችን መቀበልና በተግባር ማረጋገጥ እንችላለን።
ሴትዮዋ ያየችበት መንገድ ሲቀየር ነው ያየችው ነገር የተቀየረው፡፡ አስተያየታችን ሲቀየር የምናየው ነገርም በዛው ልክ ይቀየራል፡፡ በአንድ ነገር ላይ የተለያዩ ተቃራኒ ሃሳቦች እንዳሉ ማሰብ ከጀመርን ለውጦችን ፈጥነን ለመቀበል እንችላለን። ከነበረን የተሳሳተ አስተሳሰብ ተላቀን ከለውጥ ጋር መለወጥ እንጀምራለን፡፡ አይተን መመልከት ካልጀመርንና ሠምተን ማዳመጥ ካልቻልን አዳዲስ ነገሮችን ለመቀበልና ትክክለኛ ወደሚባለው መንገድ ለመሄድ ይከብደናል፡፡
የአስተሳሰብ ለውጥ በሕይወት ላይ ከፍተኛ ትርጉም አለው፡፡ ትርጉሙ ከራስ አልፎ ለዓለም የሚተርፍ ይሆናል፡፡ በራሳችን ከታጠረው ነባር አስተሳሰብ ወጥተን ዓለምን ስንቃኛት ዛሬ ከትናንት የተሻለ እንደሆነ እንረዳለን። በለውጥና በአዳዲስ አስተሳሰብ ያልተቃኘ ዓለም፣ ያልተመረመረ ማንነት እና ያልጠራ እይታ የዛሬና የነገውን እውነታ ያዛባል፤ በአሮጌው አስተሳሰብ ታጥሮ፤ አሮጌ ሆኖ ይቀራል።
አዲስ አስተሳሰብ ወደ አንድ እውነት ለመድረስ በሚደረገው ጉዞ ላይ ቁልፍ ቦታ አለው፡፡ ዓለማችን በየጊዜው አዳዲስ አስተሳሰብን ትፈልጋለች። ምክንያቱ ዛሬ ከትናንት የሚሻሉ በርካታ ነገሮች ይዞ እንደሚመጣ ይታመናልና። ነገ ደግሞ ከዛሬ የሚሻሉ አዳዲስ ነገሮች ይኖሩታል።
ሀገርም የሚገነባው በአዳዲስ አስተሳሰቦች ነው፤ በተሻለና ለጠንካራ ሃሳብ የተገዛ ሀገር ጉዞው የተሳለጠና ከዘመናዊው ዓለም ጋር የተዋሀደ ይሆናል። በአዲስና በመለወጥ መንገድ ለመጓዝ የቆረጠ ትውልድ አንድነቱን ያፀናል እንጂ አይከፋፈልም፤ እርስ በርሱ በመተባበር ያድጋል እንጂ ተከፋፍሎ አይወድቅም፡፡
ከአረጀውና ካፈጀው አስተሳሰብ ጋር የሙጥኝ ብሎ አብሮ አያረጅም። በመሆኑም ካለፉት መልካም ነገሮችን ወስደን፤ ከአዳዲሶቹ አስተሳሰቦች ጋር አዋህደን ለለውጥ መነሳት ይኖርብናል። አዳዲሶቹን አስተሳሰብ ለመቀበል ደግሞ የልቦናችንን መስታወት መወልወል በቂያችን ይሆናል። ያኔ ከዛሬ አሻገረን ብሩህ ነጋችንን የማየት እድል ይኖረናል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2011