ለእግሮቹ ጫማ ያላማረው፣ ታርዞ ያልለበሰ፣ ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ እየሰጠ እርሱ ያልተቋደሰውን የቀለም ገበታ ለልጁ አዕምሮ የቸረ ቤተሰብ ሕይወቱ ሊለወጥ የሚችለው የአብራኩን ክፋይ በማስተማሩ እንደሆነ ስለሚገነዘብ ልጆቹ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲቀላቀሉ ደስታው ወደር የለውም። ይሁን እንጂ አንዳንዴ የሕይወት ጎዳና የታሰበውና የታቀደው ቀርቶ ትምህርቱን አጠናቅቆ የታለመውን ዕውን ያደርጋል የተባለው ያልተጠበቀ ዕንቅፋት ገጥሞት ከአላማው ሊሰናከል ይችላል።
ይህን መሰል ድንገተኛ ችግር አጋጥሞት ካሰበው እንዳይደርስ በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የተወሰኑ የትምህርት አካላት የተፈፀመበትን በደል ለተቋማችን ያደረሰን የዛሬው የፍረዱኝ ባለጉዳያችን ተማሪ አዱኛ ዘማርያም ነው። እኛም ከተማሪው አንደበት ያደመጥነውን አቤቱታ፣ የሰነድ ማስረጃዎችና ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጋር በጉዳዩ ላይ ያደረግነውን ቆይታ እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ከአንደበቱ
ተማሪ አዱኛ በአርሲ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና ትምህርት ክፍል የሦስተኛ ዓመት ተማሪ እንደሆነ ይናገራል። ሆኖም ወደ አራተኛ ዓመት ለመግባት የሚያስፈልገውን የመጨረሻ የተማሪዎች መመዘኛ ፈተና ተፈትኖ ጨርሶ በተጋባዥ የውጭ መምህራን መፈተን የነበረበትን መመዘኛ በሕመም ምክንያት ሳይወስድ ያመልጠዋል። ለዩኒቨርሲቲው ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ይህንኑ የገጠመውን ችግር በመጥቀስ ፈተናውን እንዲፈተን በደብዳቤ መጠየቁን ያስታውሳል።
የኮሌጁ ኮሚቴ ተሰብስቦ ፈተናውን በውስጥ መምህራን እንዲፈተን እንደተፈቀደለት የሚናገረው ተማሪ አዱኛ፤ መምህራኖቹን ሲጠይቅ ግን ለተጋባዥ መምህራን ክፍያ የሚታሰብ በመሆኑ ለእነርሱ ይከፈል የነበረውን ብር እንዲፈትኑ ለተወሰኑት የውስጥ መምህራን እንዲከፈላቸው የሚል ተያያዥ ጥያቄ መነሳቱን ያስረዳል። ጉዳዩን አብራርቶ በድጋሜም በደብዳቤ ኮሌጁን ይጠይቃል። ኮሌጁም ጉዳዩን ወደ ዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ይመራዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትም ጉዳዩን ተመልክተው ደብዳቤ የፃፉ ሲሆን፤ የጤና ሣይንስ ኮሌጅ ዲኑ ደብዳቤውን መሠረት በማድረግ ፈተናውን እንዲፈተን ይጽፉለታል። ይሁን እንጂ የሚመለከታቸው አካላት እንደማይፈትኑት ያሳውቃሉ። የተቋሙ የበላይ ፕሬዚዳንት የወሰኑት ውሳኔ ተፈፃሚ ባለመሆኑና ቀን እየገፋ መሄዱ ያሳሰበው ተማሪ አዱኛ ተመልሶ ወደ ፕሬዚዳንቱና የሚመለከታቸው አካላት ዘንድ ሲያመራ ፈተናውን እንደተፈተነ ይገለጽለታል።
ሳይፈተን እንደተፈተነ የተገለፀለት ፈተና ግርታን የፈጠረበት ተማሪ አዱኛ፤ ውጤቱን እንዴት እንደሞሉትም እንደማያውቅ ነው የሚያስረዳው። በዚህ ያላበቃው ችግርም የተፈተነውን የጽሑፍ ፈተና ስምንት ነጥብ አንድ ቢያመጣም የተሞላለት ግን አምስት ነጥብ አንድ በሚል እንደሆነ በኀዘን ይናገራል። በዚህ መልኩ የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች (ኮርሶች) ላይ ያስመዘገባቸው ውጤቶቹ ተቀንሰው እንደተመዘገቡለት ይገልፃል። ለሕመሙ አሳማኝ የሆነ የሕክምና ማስረጃ እንዳለውና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና ሌሎች የተቋሙ አስተዳደር አካላት እንዲፈተን የወሰኑትም ይህን ተመልክተው እንደሆነ ያስረዳል።
ውጤቱ በዚህ መልኩ እንዲቀንስ በማድረግ ደግሞ እንዳይማር ብሎም ከዩኒቨርሲቲው እንዲወጣ አንዳንድ የዩኒቨርሲቲው መማር ማስተማር አካላት እንዳሰቃዩት ይናገራል። በዚህ መልኩ አምስት ወራት እንደሞላውም ነው የሚገልፀው። ችግሩን በየደረጃው ቢያቀርብም ምንም ዓይነት መፍትሔ ሊያገኝ አልቻለም።
ከባህርዳር ከተማ ቲሊ ከተባለች አካባቢ ለትምህርት የወጣው ተማሪ አዱኛ፤ ከዩኒቨርሲቲው በመውጣቱ የሚያርፍበት ቤትም ሆነ የሚመገበው ነገር እንዳልነበረው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተረድተው ብር እንደሰጡትና እንደተባበሩትም ያስረዳል። የሰጡት ገንዘብ በአሁኑ ወቅት አልቆ በቤተ ዕምነት ውስጥ ለመጠለል እንደተገደደ ነው የሚገልፀው።
የትምህርት ክፍሉ እንደማይፈተን ከወሰነበት በኋላ ከግቢው ለመውጣት እንደተገደደ የሚገልፀው ተማሪ አዱኛ፤ ከግቢው እንዲወጣ ሲደረግ እንኳ ሰብዓዊነት በጎደለው መንገድ እንደሆነ ይናገራል። ዩኒቨርሲቲው ለመማር ማስተማሩ እንዲያግዛቸው በሚል ለተማሪዎች የሰጠው ታብሌት ሳይቀር በተቋሙ የፀጥታ አካላት ተቀምቶ እንደተባረረም ነው የሚያስረዳው።
ማንኛውም ተማሪ ፈርሞ የተረከበውን ንብረት በአግባቡ ለሚመለከተው አካል መመለስ እንዳለበት ቢታመንም በእርሱ ላይ የተፈፀመው ግን ከዚህ የተለየና ተገቢነት የጎደለው ድርጊት ነው ሲልም ይተቸዋል። በወቅቱም የፀጥታ አካላቱ ኃይለ ቃል የተሞላባቸውና አስነዋሪና ፀያፍ ስድቦችን ሲያወርዱበት የያዘውን የድምጽ ማስረጃ ከፍቶ አስደምጦናል። ከዚህ በተጨማሪም በእጁ ላይ የሚገኙ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን ሰጥቶናል።
ሰነዶች
ተማሪ አዱኛ ዘማርያም በቀን 05/09/2011 ዓ.ም ለአርሲ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ያስገባው ማመልከቻ አንዱ ነው። ተማሪው ለአስተዳደሩ ባስገባው ደብዳቤ፤ በዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዓመት የሕክምና ተማሪ መሆኑን ገልፆ፤ ባጋጠመው የጤና እክል ምክንያት የተማሪ መመዘኛ የጽሑፍ ፈተናውን ከሕመም ጋር ሆኖ እንደምንም ቢጨርስም ሕመሙ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰበት በመሄዱ የቃል መመዘኛ ፈተናውን መፈተን እንደማይችል ለጤና ሣይንስ ኮሌጁ አስተዳደር እንዲሁም ለትምህርት ክፍሉ (ዲፓርትመንት) አሳውቆ እንደነበር ያብራራል።
ምንም እንኳ በወቅቱ የገጠመውን አጣብቂኝ ለዩኒቨርሲቲው የቅርብ የትምህርት ክፍሉ ቢያሳውቅም ሕመሙ ግን እያዞረ የሚጥል በመሆኑ ከሕክምና በተጨማሪ በዕምነቱ ፀበል ሲከታተል ይቆያል። በዚህም የጤና እክሉ ሙሉ በሙሉ ባይሻለውም የተሻለ ለውጥ በማየቱ ያመለጠውን መመዘኛ ፈተና በድጋሚ እንዲፈተን መጠየቁን ተማሪ አዱኛ በማመልከቻው አብራርቶ ጽፏል። ይሁን እንጂ ያመለጠውን የቃል (ኤክስተርናል ኦራል) መመዘኛ ፈተና ‹‹ባጀት የለንም›› በማለት ትምህርት ባስተማሩት መምህራኖቹ እንዲፈተን ተፈቅዶለት ነበር። በመጀመሪያ ቀንም የፋርማኮሎጂ ፈተና ይፈተናል።
በመመዘኛ ፈተናው ወቅት ያጋጠሙትን ችግሮች በማስረዳት ከእርሱ እኩል ወደ ዩኒቨርሲቲው የተቀላቀሉ ተማሪዎች ከተፈተኑት ፈተና ጋር ሲነፃፀር የእርሱ ፍትሐዊ አፈታተን እንዳልነበረ ለጤና ሣይንስ ትምህርት ቤት አሳውቆ ሕጋዊ በሆነ መልኩ መመዘኛውን እንዲፈተን በተደጋጋሚ ጠይቆ ምንም ዓይነት ምላሽ ማግኘት እንዳልቻለ በማመልከቻው ማስፈሩ ይነበባል። ጥያቄውን ባነሳባቸው ወቅቶች ሁሉ አግባብነት ያለው መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ምላሹ ለእንግልት የዳረገው እንደሆነም ነው ያስቀመጠው።
ጥያቄውን ካነሳ ከሁለት ወራት በላይ ማስቆጠሩን በመግለጽ፤ መፍትሔ ግን እንዳልተሰጠው በጽሑፉ ማስፈሩ ይታያል። ሁኔታው በጤናው ላይ ካጋጠመው ችግር ጋር ተዳምሮ ሊቋቋመው ከሚችለው በላይ የሆነ ሥነልቦናዊ ጫና ያሳደረበት በመሆኑ ትምህርት ከሚጀመርበት 05/09/2011 ዓ.ም አስቀድሞ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ መፍትሔ እንዲሰጠው መጠየቁን ለተቋሙ ያስገባው ማመልከቻ ደብዳቤ ያሳያል።
ተማሪው በቀን 05/09/2011 ዓ.ም ለአርሲ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ባስገባው ማመልከቻ ጀርባ የተቋሙ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች በጉዳዩ ላይ እንደመሩ መመልከት ችለናል። በዚህም ለዋና ሥራ አስፈፃሚ በሚል የተመራው ጽሑፍ ተማሪው መመዘኛ ፈተና በተጋባዥ መምህር ካልሆነ ሆነ ብለው ያስተማሩት መምህራኖች ይጎዱኛል በማለቱ ጉዳዩ ከትምህርት ክፍሉ (ዲፓርትመንቱ) አቅም በላይ ስለሆነ ውሳኔ እንዲሰጥበት መጠየቃቸውን ያመለክታል።
ለአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት በዚሁ ማመልከቻ ጀርባ ላይ በእስኪርቢቶ በተፃፈው ሌላኛው ጽሑፍ ደግሞ ተማሪው በወቅቱ ከጭንቀት የተነሳ በተጋባዥ መምህራን መፈተን እንዳልቻለ በመጥቀስ፤ በመነጋገር በውስጥ መምህራኖች እንዲፈተን መደረጉን ያስረዳል። ሆኖም ግን ይህ ቢደረግም ተማሪው በደል እንደተፈፀመበት በማንሳቱ ጉዳዩ በአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት በኩል እንዲታይለት ተጠይቋል።
ለአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በተደረገው ምሪት ላይም ጉዳዩ ተጣርቶ መፍትሔ እንዲያገኝ የሚል ሲሆን፤ ለጤና ሣይንስ ኮሌጁም የቀረበ ተመሳሳይ ጥያቄ በጀርባው ላይ ከሚታዩት ጽሑፎች መካከል ይገኝበታል። በስተመጨረሻ ለአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት በሚል በሰፈረው ጽሑፍ የጤና ሣይንስ ኮሌጁ በተጠየቀው መሠረት ተወያይቶ መልስ ወይንም ውሳኔ በጽሑፍ ማሳወቅ ቢገባቸውም ምንም ውሳኔ ሳይሰጡ ወረቀቱን እንደመለሱላቸው መግለፃቸው በማመልከቻ ደብዳቤው በስተጀርባ የተቋሙ የተለያዩ ክፍሎች በጉዳዩ ላይ የተጻጻፉትን በመመልከት መረዳት ይቻላል።
የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት በመዝገብ ቁጥር 2-18/111/11 በቀን 27 ሰኔ 2011 ዓ.ም የተማሪውን ጉዳይ አስመልክቶ ለጤና ሣይንስ ኮሌጁ የላከው ደብዳቤ ሌላው የተመለከትነው ሰነድ ነው። በሰነዱ፤ ተማሪ አዱኛ በሕመም ምክንያት የተማሪዎች መመዘኛ ፈተና እንዳመለጠው ጠቅሶ በቀን 14/10/2011 ዓ.ም ባቀረበው ማመልከቻ መፍትሔ እንዲሰጠው መጠየቁ ተመላክቷል። ስለሆነም የጤና ሣይንስ ኮሌጁ የጤናውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት በድጋሚ ፈተናውን ወስዶ ወደ ትምህርቱ እንዲመለስ ገልፀው፤ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዱጉማ አዱኛ ማሳሰባቸው ይነበባል።
የዩኒቨርሲቲው የጤና ሣይንስ ኮሌጅ ለፋርማሲ ትምህርት ክፍል ለሕክምና ላቦራቶሪ ሣይንስ ትምህርት ክፍል በቀን 10/11/2011ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር አ/ዩ/ጤ/ሳ/ኮ/31/271 ወጪ አድርጎ የላከው ደብዳቤ በተማሪ አዱኛ እጅ ከሚገኙ ሰነዶች ውስጥ ይገኛል። በደብዳቤው ተማሪው በድጋሚ መመዘኛ ፈተናውን እንዲፈተን የተጠየቀ ሲሆን፤ ጉዳዩንም ከመነሻው ያብራራል። በዚህም ተማሪው በሕመም ምክንያት ሳይፈተን ቀርቶ በCAC ስብሰባ ላይ በመወያየት በውስጥ ፈታኞች እንዲፈተን ተወስኖ ከተፈተነ በኋላ የሚጠበቀውን ውጤት ሳያስመዘግብ ቀርቷል።
በቀን 27/10/2011 ዓ.ም በደብዳቤ መዝገብ ቁጥር 2-18/111/11 ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት በተላከ ደብዳቤ ተማሪው ያለበትን የጤና ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት በድጋሚ ፈተናውን እንዲወስድ መወሰኑን ያትታል። በመሆኑም በትምህርት ክፍሉ የወደቀውን ፈተና በድጋሚ ከውጭ በሚመጡ ፈታኞች እንዲፈተን ያሳስባል።
የዩኒቨርሲቲው ጤና ሣይንስ ኮሌጅ በ16/11/2011 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር አ/ዩ/ጤ/ሳ/ኮ/31/456/2011 ወጪ የሆነው ደግሞ የፋርማሲ ትምህርት ክፍል ለዋና ሥራ አስፈፃሚ የላከው ደብዳቤ ነው። በደብዳቤው ተማሪው ከሌላ ዩኒቨርሲቲ መምህር ተጠርቶለት እንዲያስፈትኑት መታዘዛቸውን በመግለጽ፤ ጉዳዩ በCAC በመያዙ በደብዳቤ ፈተናውን እንዲፈትኑ መደረጉ የሥራ ሒደቱን ያልጠበቀ እንደሆነ ተችቶታል። በመሆኑም መጀመሪያ የCAC ውሳኔ ተጠናቅቆ የተማሪው ውጤት በዩኒቨርሲቲው አሠራር እንዲዳኝ በትምህርት ክፍሉ አቅጣጫ መቀመጡን በማብራራት ለዋና ሥራ አስፈፃሚ ምላሽ እንደተላከ ደብዳቤው ያመለክታል።
በቀን 13/12/2011 ዓ.ም
ተማሪ አዱኛ ለአካዳሚክ
ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት
ጽሕፈት ቤት ለችግሩ
መፍትሔ እንዲሰጠው የጠየቀበት
ደብዳቤ ሌላው ሰነድ
ነው። በማመልከቻው ያጋጠመውን
ችግር
ገልጾ፤ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት እንዲፈተን ብሎም የጤና ሣይንስ ኮሌጁ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ለሚመለከተው የትምህርት ክፍል ፈተናውን እንዲፈተን በደብዳቤ ቢጠይቁም የሚመለከተው የትምህርት ክፍሉ ግን እንደማይፈትኑት እንዳሳወቁት በአቤቱታው አካትቶ በመጻፍ መፍትሔ እንዲሰጠው እንደጠየቀ በማመልከቻ ደብዳቤው ይነበባል።
ተማሪው በቀን 02/01/2012 ዓ.ም የጻፈው ማመልከቻ ሌላው ሲሆን፤ በዚህ ደብዳቤ ላይ ያጋጠመውን ችግርና መፍትሔ ለማግኘት የሔደበትን ርቀት አብራርቷል። ስለ ፈተናውና ውጤቱ እንደተቀነሰበት የጠየቀው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ሳያገኝ እንዴት እንደሆነ ባላወቀው ሁኔታ በተቋሙ የፀጥታ ጥበቃ ሥራ ላይ የተሠማሩት ፖሊሶች ቅጥር ግቢውን ለቅቆ እንዲወጣ እንዳደረጉት ያብራራል። ለዚህ ድርጊት ምክንያት ቢጠይቅም ሳይመለስለት መታወቂያውን እንደተቀበሉት፣ ዩኒቨርሲቲው የሰጠውን ታብሌት መውሰዳቸውንና በመተኛ ክፍሉ (ዶርም) ውስጥ የሚገኘውን ሳጥን (ሎከር) ቁልፍ እንደሰበሩበት እንዲታወቅለት መጻፉ ይታያል።
ዩኒቨርሲቲውስ ምን ይላል?
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዱጉማ አዱኛ፤ ጉዳዩን እንደሚያውቁት ነው የሚናገሩት። ተማሪው በተቋሙ በሕክምና ዘርፍ ተማሪ እንደነበረና እንደተባረረም ይገልፃሉ። ጉዳዩን በተመለከተ መፍትሔ እንዲሰጠው ለእርሳቸው ጠይቆ ከሬጅስትራር፣ አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተርና የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት በየደረጃው ችግሩ ትኩረት ተሰጥቶት መታየቱን ይገልፃሉ። በዚህም ማስረጃውና ያስመዘገባቸው ውጤቶች ሲታዩ ያለ አግባብ በግቢው እንደቆየ መደምደሚያ ላይ ተደርሷል ይላሉ።
አንድ ተማሪ በዩኒቨርሲቲው ሕግና ደንብ እንዲሁም አገራዊ የትምህርት መመዘኛ አንፃር ብቁ ሆኖ ካልተገኘ ግቢውን ይለቃል። ይሁን እንጂ የተማሪ አዱኛ ጉዳይ ለምን እንደተለየና የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በሮችን ያንኳኳበት ምክንያት ግልጽ እንዳልሆነላቸው ነው የሚገልጹት። ተማሪ አዱኛ ውጤቱ ሲታይ (F) ያለው በመሆኑ ውጤቱ ካልሞላ መቀጠል አይችልም። ይህም እንደ ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ የተቋሙም ሕግና ደንብ ነው።
ተማሪ አዱኛ የመጀመሪያ ጥያቄው መመዘኛ ፈተናው እንዳመለጠው ሳይሆን ውጤቱ እንደተቀነሰበት የሚያሳይ ነበር። ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ መልቀቃቸው በአዱኛ የተጀመረ አዲስ ሁነት ሳይሆን የነበረና የሚኖር ነው። በአንድ ትምህርት ወይንም በምክንያት ተማሪ አይባረርም የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ተማሪ አዱኛ ከሌላ ዩኒቨርሲቲ ተዛውሮ የገባና ወደ ሦስተኛ ዓመት የሚሸጋገር በመሆኑ አሠራሩን እንዲሁም የተፈተነውን ፈተና ጠንቅቆ ያውቃል ባይ ናቸው።
በአንድ ወቅት ግን ያለአግባብ ያለፈበትና መምህራኖቹ ተማሪውን ለማገዝ ከነበራቸው ቅንነት ደጋግመው መመዘኛ ፈተና ይሰጡት እንደነበር ጉዳዩን ለማጥራት በተደረገው ጥረት መታወቁን ይናገራሉ። ይህም እያንዳንዱ ማስረጃ በአግባቡ ተቀምጧል። ለዚህም የሕክምና የትምህርት ክፍሉ፣ እርሱ ይማርበት የነበረው የትምህርት ክፍል፣ መምህራኖቹ፣ የኮሌጁ ዲን እማኞች ናቸው። በተቋሙ የጤና ሣይንስ ኮሌጅ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የሚመራ ሲሆን፤ ይህ ሁሉ ታልፎ አካዳሚክ ጉዳዮችና ሬጅስትራር ሁሉ በጋራ ሆነው ጉዳዩን በልዩ ትኩረት አጣርተዋል።
የዩኒቨርሲቲው የሴኔት ሕግ፣ በተለያዩ ሕግና መመሪያዎች መሠረት ውጤቱ በቂ ወይንም አጥጋቢ
ባለመሆኑ ቢባረርም ለምን መገናኛ ብዙሃን ድረስ መሄድን ምርጫው እንዳደረገ ግልጽ አለመሆኑን ያሳውቃሉ። እኛም ታዲያ ይህ ከሆነ እርስዎ ለምን በደብዳቤ አዘዙ ስንል ጥያቄ አቀረብንላቸው።
ፕሬዚዳንቱ በምላሻቸው፤ ደብዳቤው ጉዳዩ እንዲታይለት የሚል እንደነበር አስታውሰዋል። ነገር ግን ስህተት ነበር ይላሉ። ተማሪው ለምን ይመላለሳል? በሚል እንደጻፉ በመግለጽ፤ ይህም ምንም ማለት እንዳልሆነና በዩኒቨርሲቲው ሕግና ደንብ መመሪያ መሠረት ፈትኑት የሚል እንደነበር ያብራራሉ። ይህንን እንደ መነሻ ተጠቅሞ ወደ ተለያዩ አካላት ቢወስደውም እርሳቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት እንጂ አካዳሚክ ጉዳዮችን ሕግና ደንብ እየጣሱ እንደማይሰሩም ይገልጻሉ። ኃላፊ በመሆናቸውም ሕግ ጥሰው ተማሪው ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ እንደማይችሉም ነው የሚናገሩት።
ጉዳዩ እንዲጣራና እልባት እንዲያገኝ እንጂ የተሠራው ሥራ ትክክል አይደለም በሚል ደብዳቤ አለመጻፋቸውን በመግለጽ፤ በዚህ መሠረት ተጣርቶ ምላሽ እንደተሰጠ ያብራራሉ። በወቅቱ ግን ተማሪ አዱኛ ችግሩ ምንም እንዳልታየለት ሲያቀርብ እርሳቸውንና የሥራ ባልደረቦቻቸውን የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ቢያሳስታቸውም በቆይታ ግን ተቋሙ ችግሩን ለመፍታት በቁርጠኝነትና በልዩ ትኩረት ሁኔታውን ለማጥራት ባደረገው ሙከራ ጥያቄው ተገቢ እንዳልሆነ በበቂ ምላሽ ማረጋገጥ መቻሉንም ይናገራሉ።
በትምህርቱ ባገኘው ውጤት የተባረረ በመሆኑ እንጂ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ወደተሳሳተ መንገድ ማምራቱ እንደሚያስጠይቀውም ይገልፃሉ። ይህ ስህተቱ ሳይበቃ ወደተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ማቅናቱም ወደ ትምህርት ገበታ አይመልሰውም። ተማሪው በአንድ የትምህርት ዓይነት (ኮርስ) ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች አጥጋቢ ውጤት ስላላገኘ የተባረረ በመሆኑ ሊመለስና በትምህርት ገበታው ላይ ሊቀመጥ እንደማይችል ይጠቁማሉ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 14/2012
ፍዮሪ ተወልደ