በሀገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የኮንስትራክሽን እንቅስቃሴ ተከተሎ የአርማታ ብረት ፍላጎት ከቀን ወደቀን እየጨመረ ይገኛል። በመንግሥትና በግለሰቦች ከሚከናወኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በግለሰብ ደረጃ ለሚሠሩ ቀላል የግንባታ ሥራዎች የአርማታ ብረትን የመጠቀም ፍላጎቱ ከፍ ብሏል። በአንፃሩ ጥቂት የማይባሉ የብረት ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች በሀገሪቱ ውስጥ መቋቋም ቢችሉም በዘርፉ ከሚታየው ውስብስብ ችግር ጋር በተያያዘ እጥረቱንም ሆነ የዋጋ ውድነቱን መታደግ አልተቻለም።
ሚስተር ሼል ኤች ቾ የኢኮስ ብረታ ብረት ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅና የኮሪያ በኢትዮጵያ ቢዝነስ ማህበር ሊቀመንበር ናቸው። ችግሩን እንዲህ ያብራራሉ። «በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው ማምረት ከሚችለው አቅሙ 30 በመቶውን ብቻ እያመረተ ይገኛል። በወር15 ሺ ቶን ማምረት ቢኖርበትም በአሁኑ ወቅት ከፍተኛው ወርሃዊ ምርት አራት ሺ ቶን ብቻ ነው። በዚህ ምክንያት አሁን እያመረትን ያለነው ለገበያውም ሆነ ልናመርት ከምንችለው ጋር የተመጣጠነ አይደለም። ወደ ኢንቨስትመንቱ የገባነው 900 ሚሊዮን ብር አውጥተን ነው። በመሆኑም ምርት ስንጀምር ብድር መክፈል ይጠበቅብናል፤ ማሽኖች በአግባቡ ባለመሥራታቸው የሚፈጠር ችግር አለ፣ የሠራተኛ ደመወዝ የግድ ነው። ማምረት ስንጀምር ዕቅድ የተያዘው በተጠናው የአዋጭነት ጥናት መሰረት አምርተን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸጥ ነበር። ነገር ግን በሙሉ አቅም መሥራት ባለመቻላችን እየተጎዳን ነው። በቂ ግብአት ባለ ማግኘታችን በአንድ ፈረቃ ብቻ ለመሥራትም ተገደናል የማምረቻ ወጪን ለመቀነስ መሠራት የነበረበት ግን በሦስት ፈረቃ ነበር። ከዚህ በፊት ብሔራዊ ባንክ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ብሎ የሚመድበው የውጭ ምንዛሬ ቢኖርም ወደ አስመጪዎቹ ያጋደለ ነው።» በማለት ነው ያጋጠማቸውን ተግዳሮት የገለፁት።
በምዕራፍ ሁለትም ከውጭ የሚገባውን ጥሬ ዕቃ በማስቀረት ቁርጥራጭ ብረቶችን በጥሬ ዕቃነት በመጠቀም ለማምረት ዕቅድ እንዳላቸው ይናገራሉ። በዚህም 500ሺ ቶን ብረት ለማምረት አቅደዋል። ይህንንም ለመሥራት በቂ ቁርጥራጭ ብረት በሀገር ውስጥ ስለማይገኝ 300 ሺ ቶን ያህል ቁርጥራጭ ብረት በዓመት ማስገባት እንደሚገደዱ ይጠቅሳሉ። ጥሬ ዕቃውን ለማምረት የሚገቡት ቁርጥራጭ ብረቶች ዋጋ ዝቅተኛ ስለሆነ ወደ ሥራ ሲገባ የውጭ ምንዛሬውን የበለጠ ማዳን እንደሚቻል ይናገራሉ። ፋብሪካውን አቋቋሞ በሀገር ውስጥ ማምረት ከተቻለ አገሪቱ ለብረት ምርት ግብአት ከምታወጣው ላይ 100 ሚሊዮን ዶላር ማዳን ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።
«ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ ከፍተኛ የማምረት አቅም ያላቸውን ፋብሪካዎች መገንባት ቢቻልም በውጭ ምንዛሬ እጥረት በሙሉ አቅም መሥራት ባለመቻሉ ከውጭ የሚመጣው ላይ ተንጠልጥሎ ለመኖር ተገደናል» የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ መሰረታዊ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን ሙሉጌታ ናቸው።
ሥራ አስኪያጁ እንደሚያብራሩት እንደ ሀገር ከተከሰተው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ባለፈ በብሔራዊ ባንክ በ2010 ዓ.ም ወጥቶ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው መመሪያ ለሥራቸው እንቅፋት ሆኗል። መመሪያው ለአስመጪዎችና ከውጭ ለመጡ አምራቾች ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን የኢንዱስትሪ ልማት ዋናው ግብ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን ማጠናከር መሆኑ በኢንዱስትሪው ፖሊሲ ተቀምጧል። ሁለቱም ለሀገር ውስጥ የሚያመርቱ ናቸው፡፡ ይህንንም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ለሌሎችም ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አሳውቀናል። ሆኖም ከብሔራዊ ባንክ ምንም ምላሽ ስላልተገኘ ችግሩ ቀጥሏል፡፡
ጥራትን በተመለከተ ለብዙዎቹ የብረታ ብረት ምርቶች አስገዳጅ የጥራት ደረጃዎች አሉ፤ የኢትዮጵያ የደረጃዎችና ተስማሚነት ኤጀንሲ ይሄንን እየሠራ ሰርተፊኬት ይሰጣል። ይሄን ሲሠራ ግን አምራቾቹና ማምረቻቸው በግልጽ የሚታወቅ ስለሆነ በየወቅቱ ቁጥጥር ይደረጋል። የድንገቴ ቁጥጥርን ጨምሮ ጥሬ ዕቃውን፤ የአመራረት ሂደቱን፣ ምርቱን ስለሚቆጣጠር ከደረጃ በታች ለማምረት ዕድሉ አይኖራቸውም። ከውጭ የሚመጣው የኮንትሮባንድና አንዳንዴ በህጋዊ መንገድም የሚገባው ላይ ተገቢው ቁጥጥር አይደረግም ። ይሄም በገበያ ውድድር ላይ የራሱን ተጽዕኖ አሳድሯል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኔትወርክ ለተሳሰሩ አስመጪዎች ተጠቃሚነት ሲባል የሚሠራ ሸፍጥ መኖሩን ጠቅሰዋል። ኢንዱስትሪዎቹ በዚህ ችግር ውስጥ ሆነው እንደሚያመርቱ እየታወቀ በመንግሥት በኩል ፍላጎቱ ምስጢር ተደርጎ ይያዝና በአንዳንድ ተቋማትና ፕሮጀክቶች ለይስሙላ ጨረታ ይወጣል። ኢንዱስትሪዎች በዛ ተወዳድረው የውጭ ምንዛሬ ጠብቀው ጥሬ ዕቃ አስገብተውና አምረተው ለማቅረብ የማይችሉበት የጊዜ ገደብ በጨረታ ሰነዱ ላይ ይቀመጣል። በሌላ በኩል መረጃው ቀድሞ የሚደርሳቸው ደግሞ ዕቃውን አስቀድመው ያስገባሉ፤ አንዳንዶቹ በእርግጠኝነት ጨረታው ወጥቶ ሂደቱ ሳይጠናቀቅ ምርት የሚያስገቡም አሉ።
በመሆኑም በመንግሥት በኩል በየወቅቱ ባህሪያቸው የሚቀያየረውን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እየተከታተሉ መቆጣጠር፤ የውጭ ምንዛሬንና የዋጋ ተመንንም በተመለከተ ታሪፎችን ለዓመታት ከማስቀመጥ ይልቅ እንደየወቅቱ ሁኔታ በማደስ ሕግን ማስከበር፤ አጠቃላይ ሂደቱንም ለመቆጣጠር ተከታታይነት ያለው በጥናት ላይ የተመሰረተ ፈጣን እርምጃ መወሰድ እንደሚገባ ይናገራሉ።
«በሀገሪቱ ዘጠኝ የውጭ ሀገር፣ አራት የሀገር ውስጥ እና አንድ በጥምረት የሚሠራ በድምሩ አስራ አራት የብረት ማምረቻ ፋብሪካዎች ቢኖሩም በከፍተኛ ደረጃ አመረቱ ሲባል የአቅማቸውን ሃያ በመቶ ብቻ ነው።» የሚሉት ደግሞ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፊጤ በቀለ ናቸው።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ሃያ በመቶ የሚደርስ ምርት የሚያመርቱትም የተወሰኑት ፋብሪካዎች ብቻ ለአጭር ጊዜ እንጂ በአብዛኛው እያመረቱ ያሉት አስር በመቶ ነው። እነዚህ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ማምረት ቢችሉ ከሦስት ሚሊየን ቶን በላይ ብረት በዓመት ማቅረብ ይችላሉ። የሀገር ውስጥ ፍላጎት ግን ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን አይዘልም። በዕቅድ ተቀምጦ የነበረው ግን በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ አድርጎ የጎረቤት አገራት ፍላጎት ስላላቸውና በየብስ ትራንስፖርት ማዳረስ ስለሚቻል የውጭ ምንዛሬ ማግኛ ተደርጎ ነው።
ከውጭ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር የእጥረት ብቻ ሳይሆን የተዛባና ፍትሃዊ ያልሆነ አሠራር መኖሩ ጭምር መሆኑን ይገልፃሉ። አገር በቀል ከሆኑት ኩባንያዎች መካከል ጥራት ያላቸውና የተሻለ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ብዙ ማምረት የሚችሉ ቢኖሩም በብሔራዊ ባንክ በኩል ከምን መነሻ እንደሆነ ሳይታወቅ ለውጭው ባለሀብት ብቻ ተነጥሎ ወረፋ ሳይጠብቅ የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኝ እየተደረገ ይገኛል። ለዚህ በተደጋጋሚ እንዲስተካከል ለብሔራዊ ባንክ በደብዳቤ ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ ማግኘት ግን አልተቻለም። ከአስራ አራቱም አምራቾች መካከል በየሩብ ዓመቱ እየተፈተሸ በሚያመርቱት ልክ መሰጠት የነበረበት ቢሆንም ሲሠራ የነበረው ግን በዘፈቀደ ነው። ለምሣሌ 60 ሺ ቶን ለሚያመርት ኩባንያ20 ሚሊዮን ዶላር ሲፈቀድለት 120 ሺ ለሚያመርተው የሀገር ውስጥ አምራች ደግሞ አራት ሚሊየን ዶላር ብቻ ይሰጠው እንደነበረ ለአብነት አንስተዋል።
ሌላው ችግር አንዳንድ አስመጪዎችም በተለያዩ ኮንስትራክሽኖች ስም ከቀረጥ ነፃ ብረቱን ያስገቡና ገበያ ላይ ይለቁታል። ይሄ ለተባለው ግንባታ ባለመዋሉ መንግሥትም ቀረጡን አጥቶ አምራቹም በስንት ልፋት ያመረተውን ብረት ዕኩል ይዞ ገበያ ሲቀርብ ዋጋው ስለማይመጣጠን ከጨዋታው ይወጣል። ከዚህ በፊት ሁለት መቶ ሺ ሰው በማይኖርበት ከተማ ሃምሳ ኢንተርናሽናል ሆቴሎች ይገነባሉ ተብሎ ከቀረጥ ነፃ የገባ ምርት ነበር። የቁጥጥር ሥርዓቱ ጠንካራ ባለመሆኑ ብረቶችን ወደ ክልል የመውሰድ፣ ከከተማ ዳርቻ አስቀወምጦ ሰው ሰራሽ ዕጥረት ይፈጠርም ስለነበር ኢንዱስትሪው ሲጎዳ መቆየቱን ገልፀዋል፡
እንደ ሀገር የብረት ማዕድን ለማውጣት የተጀመረ ሥራ ቢኖርም ከፍተኛ ገንዘብ፣ እውቀትና ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ በመሆኑ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም። በመሆኑም ለአርማታ ብረት «ደረጃ 40» ለሚባሉት መካከለኛ የህንፃና የመንገድ ግንባታዎች የሚከናወኑባቸውን ለማምረት ውድቅዳቂ ብረቶችን እንደ ጥሬ ዕቃ መጠቀም ይቻላል። በዚህ በኩል የተጀመሩት ሥራዎች ሲሳኩ ከውጭ የሚመጠው የጥሬ ዕቃ ፍላጎት ግዙፍ ግንባታዎች ለሚከናወኑባቸው «ደረጃ 60 እና 75» ለሚባሉት ብቻ ስለሚሆን የውጭ ምንዛሬውን ዕጥረት መቀነስ ይቻላል የሚል እምነት አላቸው።
ዘርፉ አሁንም በመንግሥት ትኩረት ሊሰጠው፣ ችግሮቹም ተለይተው መፍትሄ ማግኘት የሚገባው ዘርፍ መሆኑን ሳንጠቁም አናልፍም። በተለያየ መልኩ የሚሠራው ሸፍጥ፣ ኔትወርክ እና ሌሎች የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችም መታየት አለባቸው መልዕክታችን ነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ