በእስራኤል ምርጫ አንድ ፓርቲ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት 120 መቀመጫዎች ባሉት የአገሪቱ ፓርላማ /ካንሴት/ 61 የመቀመጫ ድምፅ ማግኘት ግድ ይለዋል። ይህን ማሳካት ያልሆነለት ደግሞ ከሌሎች ተፎካካሪዎቹ ጋር ድምፁን በማስደመር ጥምር መንግስት ለመመስረት ይወስናል። ጠቅላይ ሚኒስትር መርጦም ለፕሬዚዳንቱ ያሳውቃል።
በፖለቲካ ጉዳይ ተንታኞች ዘንድ ያለ ጥርጥር በአገሪቱ ታሪክ ከታዩት የተለየና ከፍተኛ ትንቅንቅ የታየበት መሆኑ የተሰመረበት የዘንድሮ እስራኤል ምርጫም የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁና የቀድሞው የአገሪቱ ወታደራዊ ሃይል አዛዥ ቤን ጋንቴዝን ብርቱ ፉክክር አስመልክቷል።
ባሳለፍነው አመት ሚያዚያ ወር ላይ በተካሄደው ምርጫ አብላጫ ድምፅ በማግኘት አሸናፊ ሆኖ አገር ለመምራት ብቁ የሆነውን ፓርቲ ማሳውቅ አልቻለም። ይህን ተከትሎም አገሪቱ ከስድስት ወራት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ምርጫ ለማካሄድ ተገዳለች።
ሰሞኑን በተካሄደው ምርጫም በቀድሞው የአገሪቱ ወታደራዊ ሃይል አዛዥ ቤን ጋንቴዝ የሚመራው ሰማያዊና ነጭ ፓርቲ 33 ድምፅ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁና የቀኝ ዘመም ፓርቲያቸው (ሊኩድ ፓርቲ) ደግሞ 31 ድምፅ ማግኘታቸው ታውቋል። በአይማን አዳህ የሚመሩት የአረብ እስራኤል ፓርቲዎቹ 13 ድምፅ አግኝተዋል።
በሁለተኛው ምርጫም አሸናፊ ሆኖ አገር ለመምራት ብቁ የሆነውን ፓርቲ ማሳወቅ አልቻለም። ይህን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ከተቀናቃኛቸው ጋር ጥምር መንግስት ለመመስረት ጥያቄ ለማቅረብ ተገደዋል።
ባሳለፍነው አመት ሚያዚያ ወር ላይ እንደተካሄደው ምርጫ አብረን እንስራ ሲሉ የጠየቁትና ለኔታኒሁ እጃቸውን ቢዘረጉ ፊት ተነስተው በር የተዘጋባቸው ጋንቴዝ፣ አሁን ደግሞ ተራው የእኔ ነው በሚል ጥያቄውን ውድቅ አድርገውታል። ይሁንታቸውን ከለገሱ ደግሞ ፓርቲያቸው ከፍተኛ ወንበር እንደማግኘቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ኃላፊነትን መረከብ እንደሚፈለጉ አሳውቀዋል።
በእርግጥም አሁን ላይ በአረቡ አገራት ላይ የሚከተሉት ለዘብተኛ አቋም የአብዛኞቹን ድጋፍ እንዲያገኙ ያስቻላቸው ጋንቴዝ የተሻለ ድምፅ በእጃቸው አስገብተዋል። አገር ለመምረት ፍላጎት ያለው ማንኛውም የምርጫው ተወዳዳሪ ፓርቲ የሰውየውን ድምፅ መጋራት ግድ ይለዋል። ይሁን እንጂ ሁሉን ለመናገር ጊዜው ገና እንደሆነም ተጠቁሟል፡ የአገሪቱ ምርጫ ኮሚቴ ውጤቱ ገና ሙሉ አለመሆኑና የ14 ጣቢያዎች ድምፅ አለመካተቱን ያሳወቀ ሲሆን፤ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ግን 99 በመቶ የሚሆነው ድምፅ መቆጠሩን አስተጋብተዋል።
በአንጻሩ አንዳንዶች ‹‹ቀሪዎቹ ድምፆች ምርጫውን መገልበጥ ምንም አቅም አይኖራቸውም፤ ከፍተኛ ድምፅ በተቋደሱት ፓርቲዎች መካከል የጥምር መንግስት የመመስረት እድሉ አጠራጣሪ ነው፤ ክሰተቱም ለአስራ ሶስት ዓመታት የዘለቀውን የኔታኒያሁ የስልጣን ጉዞ ሊቋጨው ይችላል›› ሲሉ ተደምጠዋል።
ይህን ተከትሎም በርካታ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ተንታኞች የተለያዩ ዘገባዎችንና አስተያየቶችን አመላክተዋል። አሶሽየትድ ፕሬስ ፣ ከአመታት የፖለቲካ ዙፋን ንግስና በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እጣ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ ወድቋል ሲል አስነብቧል። በሃርቲዝ ላይ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ የሆነው ሲዮሲ ቬርቴር ወቅታዊ ሁኔታውን በመገምገም ኔታኒሁ ከእንግዲህ ወዲህ የአገሪቱን ምርጫ ለማሸንፍ ብቁ እንዳልሆኑ ጠቅሶ፤ታሪካቸውም መቋጫውን ማግኘቱን ተናግሯል።
የማሪቪ ዴይሊው ፀሀፊ፣ቤን ካስፒት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ዳግም በዙፋናቸው የሚቀጥሉበት እድል እጅግ አነስተኛ ነው ሲል አስነብቧል። ለረጅም አመታት በእስራእል ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በመፃፍ የሚታወቀው አን ሼን ፐፍር፣ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ከዚህ ቀደም እንደምናውቀው ሁሉም የሚፈሩትና የሚርዱለት የፈለገውን ለማድረግ የማይሳነው አይሆንም ሲል አስታውቋል።
የዎል ስትሪት ጆርናሉ ፀሀፊ ዶቭ ሊበር በበኩሉ፤ከአስርት አመታት የስልጣን ቆይታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ኔታኒያሁ የእስራኤልን የፖለቲካ አቅጣጫ መዘወር አቅሙን ተነጥቋል። ይህን ሁሉ ቀውስ ተሻግሮ በስልጣን ላይ ቢቆይ እንኳ ሃያልነቱን ተገፎ ነው አደባባይ የሚወጣው ሲል አስነብቧል።
እኤአ በ1996 በአርባ ሰባት ዓመታቸው የመሪነቱን ስልጣን የያዙት ኔታንያሁ ከአራት ዓመታት በኋላ ስልጣናቸውን ለኤሁድ ባራክ ማስረከባቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ከአስር ዓመታት ቆይታ በኋላም እኤአ በ29 ለሁለተኛ ጊዜ የአገሪቱ መሪ በመሆን ያለፉትን አስራ ሶስት ዓመታት በስልጣን ቆይተዋል።
ፖለቲካዊ እውቀታቸው ምጡቅ መሆኑ የሚመሰከረላቸውና በፍልስጤምና በኢራን ላይ ባላቸው ጠንካራ፣ ተጠራጣሪና ግትር አቋም የሚታወቁት የስልሳ ዘጠኝ ዓመቱ ኔታኒያሁ፤ በአገራቸው የፖለቲካ በተለይም የደኅንነት ጉዳይ ላይ እጅ አይሰጡም። አገርን መምራት የሚለካው የአገርን ሉዓላዊነትና ደኅንነት በማስጠበቅ መሆኑን አጥብቀው የሚያምኑት ኔታንያሁ፤ ይህ አቋማቸውም ከአረብ አገራት ጋር ሆድና ጀርባ ሆነው ዓመታትን እንዲዘልቁ አድርጓቸዋል።
በተለይ ባለፉት ወራት በአገሪቱ ፓርላማ የሰማያዊና የነጭ ፓርቲያቸው አብላጫውን ወንበር እንዲቆናጠጥ፣ በርካታ ተግባራትን ቅስቀሳዎችን በማድረግ አሸናፊ ለማድረግ አማራጮችን ከማስፋትና ከመቀመር ባይቦዝኑም የመሻታቸውን ማግኘት ግን አልሆነላቸውም። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ።
በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚያስረዱት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠረጠሩባቸው ሶስት የሙስና ወንጀሎች በምርጫ ቅስቀሳቸው ላይ ከባድ ፈተና ጥለውባቸው አልፈዋል። ያለፉትን ሁለት ዓመታትም የተለያዩ ምርመራዎች ሲካሄድባቸው ቆይቷል።በተጠረጠሩበት ወንጀል ፍንጮች ስለመኖራቸው ቢጠቆምም ተጨባጭ ማስረጃ ማግኘት ግን አልተቻለም። ኔታኒያሁም ቢሆኑ ከደሙ ንፁህ ስለመሆናቸው በመግለፅ ውንጀላውን መሰረተ ቢስና ስልጣናቸውን ለመገዳደር የተጠነሰሰ ሴራ እንደሆነ እያስገነዘቡ ሲሟገቱ ቆይተዋል።
ፖለቲካ ምሁራን፣ ከሙስናው ወንጀል ባሻገር ሌሎችም የውስጥና የውጭ ግንኙነት ደካማ አፈፃፀማቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከባድ ዋጋ እንዳስከፈላቸው ዋቢ በማድረግ ውጤቱም ለአስራ ሶስት ዓመታት የዘለቀውን ዙፋናቸውን እንደገረሰሰው በመጠቆም ‹‹ምርጫው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን መቋጫ ነው›› ሲሉ ተደምጥዋል።
ምንም እንኳን በኔታኒያሁ መሸነፍ የተደሰቱ የሚመስሉ ቢኖሩም፣አሁንም ቢሆን ጉዳዩ መቋጫውን አለማግኘቱን የሚያስረዱም በርካቶች ሆነዋል። ሰውየው እንዳይርቁባቸው የሚፈልጉ አገራት መኖራቸውም እርግጥ ነው። በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ለወጠናቸው እቅድ ስኬታማነት የጠቅላይ ሚኒስትሩ መኖር በእጅጉ የሚያስፈልጋት አሜሪካ ፍላጎቷም ሆነ ምኞቷ ሰውዬውን በስልጣን ማቆየት መሆኑ ነገሮችን የመገልበጥ አቅሙ ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚያስረዱም በርካታ መሆናቸው እየተገለጸ ነው።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሩቨን ሪቭሊን ውዝግቡን ፈር ለማስያዝ ፓርቲዎቹን በጠረጴዛ ዙሪያ አስቀምጠው ለማወያየት እቅድ ስለመያዛቸውም ተመላክቷል። ይሁንና በሁለቱ ተፋላሚዎች መካከል የተከሰተው የልዩነት አቋምና ግብግብ በቀላሉ ከመፈታት ይልቅ ሌላ ሶስተኛ ምርጫ እንዲካሄድ ሳያስገድድ እንደማቀር አስገምቷል።
የምርጫውን ውጤት ተከትሎ በርካቶች በዚህ መልክ የየቅል አስተያየታቸውን ቢያስቀምጡም ሁሉም ውዝግብ ግን በዚህ ሳምንት መቋጫውን የሚያገኝም ይመስላል።
የእየሩሳሌም ፖስት ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ጊል ሆፍማን ለኤቢሲ እንደገለጸው፤ ክብረ ወሰን የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ቆይታ ወደ መቋጫው የተቃረበ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምርጫ ፈተናቸውን ተሻግረው በስልጣን መቆየት ከቻሉ ግን አዲስ ታሪክ መፃፍ ይችላሉ። ከቀድሞው ዴቪድ ቤን ጉሪዮን በላይ በታሪክ የመጀመሪያና ብቸኛው እስራኤልን ለረጅም ዓመታት የመሩ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚለውን ክብር መቀዳጀት ይቻላቸዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 13/2012
ታምራት ተስፋዬ