አዲስ አበባ፡- በተወለዱ በስልሳ አምስት አመታቸው ታህሳስ አስር 2011 ዓ.ም ያረፉት ጋዜጠኛ፣ ተርጓሚ እና ደራሲ ግርማ ለማ የቀብር ሥነሥርዓት ትናንት የስራ ባልደረቦቻቸው፣ወዳጅ ዘመዶቻቸውና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት አዲሱ ገበያ በሚገኘው እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።
ጋዜጠኛ ግርማ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህዝብ አስተዳደር በከፍተኛ ማዕረግ በዲግሪ የተመረቁ ሲሆን፣ ‹‹የንጉሱ ገመና›› ከተሰኘው መፅሐፍ በተጨማሪ ‹‹የካህሊል ጅብራን ምርጥ ስራዎች›› የተሰኘ የትርጉም ስራ ለአንባቢ አቅርበዋል፡፡ ለህትመት ያልበቁ አምስት ያህል የትርጉምና የራሳቸው ወጥ ስራዎችም ነበሯቸው፡፡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ‹‹እንዲህ ቢሆንስ››፣ ‹‹ድሮና ዘንድሮ›› እንዲሁም ‹‹ሃሳብ አለኝ›› የተባሉ አምዶች አዘጋጅ፤ የ‹‹ዘመን›› መፅሄት መስራች እና የአምድ አዘጋጅም ነበሩ፡፡ በተጨማሪም ‹‹አፍሮዳይት›› እና ‹‹ዛቬራ›› በተሰኙ መፅሄቶች ላይ በዋና አዘጋጅነት ሰርተዋል፡፡
በ‹‹አዲስ አድማስ›› ጋዜጣ ላይ ‹‹ታቦት ፍለጋ›› በሚል ርዕስ በተከታታይ ይወጡ የነበሩ የግርሃም ሃንኮክ ትርጉም ስራዎችንም ያቀርቡ ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮ ቻናል›› ጋዜጣ ላይ በ ‹‹ማህደር›› አምድ ይሰሩ የነበሩት ጋዜጠኛ ግርማ በሬዲዮ ፋናም በተለያዩ የስራ ሃላፊነት አገልግለዋል።
ባለሙያው ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ የትርፍ ሰዓት ስራዎቻቸው ሲሆኑ በመደበኛነት የሰው ሀብት አስተዳደር (Human Resource Management) አማካሪ ነበሩ፡፡ በህይወታቸው የመጨረሻ ዓመታትም በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ጽሑፎችን ያቀርቡ ነበር፡፡ ጋዜጠኛ ግርማ በቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት በምስራቅ እዝ የወታደራዊ ፖለቲካ ክፍል ሃላፊ ሆነው በሻለቃ ማእረግ አገራቸውን ያገለገሉም ነበሩ።
የአንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ጸሐፊ፣ ደራሲና አማካሪ የነበሩት ግርማ ለማ ሥርዓተ ቀብር ያስፈፀሙት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አመራሮችና ሰራተኞች ናቸው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2011