የገዳ ስርዓት ዘመንን ተሻግሮ ለትውልድ ባስተላፈው መልካም ባህላዊ እሴት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ከሶስት ዓመታት በፊት በዓለም የማይዳሰሱ ቅርስነት ተመዝግቧል። በአሁኑ ጊዜ ድግሞ የገዳ አስተዳደር ስርዓትን በስርዓተ-ትምህርት ውስጥ በማካተት እንደ አንድ ትምህርት(ኮርስ) ለመስጠት ማቀዱን የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ይፋ አድርጓል።
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫላ አዎታ እንደሚገልጹት ዩኒቨርስቲው የገዳ ስርዓት ስርዓተ-ትምህርት ተዘጋጅቶለት ትምህርት ለመስጠት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል። ይህ ደግሞ ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች በየአካባቢያቸው ካለው የተፈጥሮ ሀብት አኳያ የምርምር ልቀት መስኮችን መለየታቸውን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፤ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲም ከምስረታው ጀምሮ የራሱን የልህቀት መስኮች ማለትም ግብርና፣ ማዕድንና አገር በቀል እውቀቶች ለይቶ እየሰራ ነው፡፡
እነዚህ የምርምር መስኮች ሲመረጡ መነሻ ምክንያቱ ደግሞ ዩኒቨርስቲው የሚገኘበት አካባቢ ያለውን የተፈጥሮ ሀብትና ባህላዊ እሴት ታሳቢ ያደረገ ነው። ዩኒቨርስቲው የሚገኝበት ምዕራብ ጉጂ ዞን ደግሞ በማዕድን ሰፊ ሀብቶች ያሉት እንደመሆኑ፤ በዚህ ላይ ዩኒቨርስቲው ትኩረት ሰጥቶ ምርምር ቢያደርግ የአካባቢው ማህበረሰብ ይጠቀማል። ለአገሪቱም በማዕድኑ ዘርፍ ጠንካራ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያደርጋል የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡
እንደ ዶክተር ጫላ ገለጻ፤ የዩኒቨርሲቲው ሁለተኛው የምርምር ልህቀት መስኩ ደግሞ ግብርና ሲሆን፤ ምዕራብ ጉጂ ዞን በቡና ምርት እና በእንሰሳት ሀብትም የታወቀ አካባቢ ነው። በመሆኑም በእነዚህ የግብርና ምርቶች ላይ የላቀ ምርምር በማከናወን የአካባቢውን ህብረተብ ተጠቃሚ ያደርጋል። የግብርና ምርቶቹም በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡
ሶስተኛ የምርምር ልህቀት መስኩ ደግሞ የአገር በቀል እውቀት ነው። የጉጂ አካባቢ በተለይም በገዳ ስርዓት የሚታወቅ ነው። ቀደም ሲልም ሆነ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ደረጃ የዲሞክራሲ ስርዓት ጉዳይ ትኩረት የሚሰጠው ነው። የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መነሻው ግሪክ ቢባልም፤ አፍሪካም የዲሞክራሲን ስርዓት ግንባታ ረገድ የራሷ አሻራና ስልጣኔ አላት። ከእነዚህ ስልጣኔዎች መካካል አንዱ የገዳ ስርዓት ነው። እንደ ኢትዮጵያዊያን ስናስብ ደግሞ የሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተለያዩ የስልጣኔ ቅርሶች እንዳሉ የሚታወቅ ነው። ከማይዳሰሱ ቅርሶች አንዱ ደግሞ የገዳ ስርዓት ነው። ይህ አስተዳደራዊ መዋቅር ባህላዊና ፖለቲካዊ እውቀት ለትውልድ የሚተርፍ በመሆኑም ነው ዩኔስኮ በቅርስነት የመዘገበው፡፡
የገዳ ስርዓት አሁን ያለው ዘመናዊ የዲሞክራሲ ስርዓት ባልነበረበት ዘመን ህዝቦች እርስ በእርሳቸው ተከባብረው አብረው መኖር እንዲችሉ፣ የራሳቸው እሴት ኖሮቸው ራሳቸውን በራሳቸው እንዴት መምራትና ማስተዳደር እንደሚችሉ ያሳየና ሌሎችንም ባህላዊ እሴቶች ጭምር አካቶ ያያዘ ነው። እናም በዚህ ስርዓት ዙሪያ ላይ ጥልቅ በምርምር በማካሄድ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በዘርፉ ምርምር ማድረግና እውቀቱን ማስተማር ተገቢ ነው። የገዳ ስርዓት አሁንም ጥቅም ላይ እየዋለባቸው ተብለው ከሚጠቀሱት አካባቢዎች አንዱ ጉጂ ዞን ነው። ከዚህ የተነሳ ነው ዩኒቨርስቲው የአገር በቀል እውቀት የልቀት መስካችን ነው ብለን መርጠን እየሰራን ያለነው በማለት ዶክተር ጫላ የሚያብራሩት፡፡
እንደ ዶክተር ጫላ አገላለጻ፤ ስለ ገዳ ስርዓት ምርምሮች እንዲካሄዱ ስራዎችን ተጀምረዋል። ዩኒቨርስቲው የአገር በቀል እውቀትና ልማት የሚል ጆርናል በማዘጋጀት በመጪው ጥቅምት ወር ላይ ለማሳተም ጥረት እያደረገ ነው። የእነዚህ አይነት ጆርናሎች መታተምም ስርዓቱን ከማሳወቅ ባለፈ ዩኒቨርስቲው አገርና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያስችለዋል። እናም ዩኒቨርሲቲው ከምርምሩ ጎን ለጎን የመማር ማስተማሩ ስራ ያካሂዳል፡፡
ምክንያቱም ለአዲሱ ትውልድ የገዳ ስርዓት ማስተማር ቢቻል ኖሮ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በየቦታው የሚታዩት ከስነ ምግባር ያፈነገጡ ችግሮች አይከሰቱም ነበር። ስለዚህ የቀደሙ እሴቶችን ማስተማር ያስፈልጋል የሚል አቋም ተይዟል። በመሆኑም የገዳ ስርዓት በመሆኑ ዩኒቨርስቲው እንደ አንድ ትምህርት (ኮመን ኮርስ) እንዲሰጥ ወስኗል። ይህ ደግሞ በየዩኒቨርስቲዎች የሚያጋጥሙ የጸጥታ ችግሮችን ከማቃለል አኳያ የሚያግዝ ሲሆን፤ እነዚህ ወጣቶች እንደ ገዳ ስርዓት ያሉ ነባር የመካባባር፣ መቻቻልና አብሮ የመኖር የህዝብ እሴቶችን በቅጡ ቢገነዘቡት ኖሮ ይህ የጸጥታ ችግር አይፈጠርም፤ ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳ በቀላሉ ይፈታሉ።
ዶክተር ጫላ፣ ‹‹በአዲሱ ዓመት መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ ከዚህ በፊት ተቋርጦ የነበረው ‹የፍሬሽማን ኮርሶች› እንዲሰጡ ወስኗል። ይህን መነሻ በማድረግ የገዳ ስርዓት እንዴት አድርገንና በምን መልኩ ለወጣቱ እናስተምር በሚል ከዩኒቨርስቲው ሰኔት ጋር በተደጋጋሚ ተወያይተንበታል። የተማሪዎችና የማህበረሰቡ የፍላጎት ዳሰሳ ጥናትም አካሄደናል። በጥናቱ መስረት ፍላጎቱ መኖሩ ተረጋግጧል። እንደ ገዳ ያሉ ባህላዊ እሴቶች ለአገር ግንባታና ለዜጎች ባህሪ ቀረጻ በጣም ጠቃሚ ናቸው። ይህን ተከትሎ ስርዓተ ትምህርት ቀረጻ አዘጋጅተናል፡፤›› ሲሉም ነው የገዳ ስርዓትን በኮመን ኮርስነት ለመስጠት የተወሰነበትን አግባብ ያስረዱት።
በስርዓተ ትምህርቱ ዙሪያ ላይ መምህራንን ብቻ ሳይሆን ስለገዳ የተመራመሩና የጻፉ እንዲተቹት ተደረጓል። በዚህ መሰረት ‹‹ኢንትሮዳክሽን ቱ ገዳ ሲስተም›› የሚባል ኮርስ ለተማሪዎች ለመስጠት ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀ ተናግረዋል። ይህ ኮርስ ዓላማው መሰረታዊ የገዳ እውቀት ማስጨበጥ ነው። ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሚመጡ ‹‹የኮመን ኮርሶች›› ጋር ተጣምሮ በመንፈቀ ዓመት የሚሰጡ ‹‹ክሬዲት አወር›› ደረጃን በጠበቀ መለኩ በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ጀምሮ ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች በሁለት ወይም በሶስት ክሬዴት አወር የሚሰጥ ይሆናል፡፡
ኮርሱን የመስጠት ሂደቱም በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይሁንታ ማግኘት አለማግኘቱን በተመለከተም፤ ትምህርቱ ለአገር ግንባታ፣ ሰላምና ልማት እስከጠቀመ ድረስ አዋጅ 1112/11 ዘንድሮ የወጣውና ከዚህ በፊትም የነበረው አዋጅ ጭምር ለዩኒቨርስቲዎች የትምህርት ፕሮግራሞችን የመቅረጽ ስልጣን እንደተሰጣቸው ነው ዶክተር ጫላ ያስረዱት። ከዚህ ባለፈ የገዳ ስርዓትን ማስተማር ኢትዮጵያን ይገነባል፤ የዲሞክራሲ ስርዓትን እንዳይናድና በህዝቦች መካካል ተከባብሮ በሰላም ለመኖር የሚያስችል መሆኑን፤ የዲሞክራሲና ሌሎች መልካም እሴቶች ከአውሮፓና ከምዕራቡ ዓለም መቅዳት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም ለአገር ዲሞክራሲ ግንባታ፣ ሰላምና ልማት የሚጠቅም አገር በቀል እውቀት እንዳላት ለማስተማርም እድል የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።
የገዳ ስርዓት በውስጡ አካቶ ከያዛቸው አንኳር ጉዳዮች ዲሞክራሲዊ አስተዳደር፣ እርቅ፣ መግባባትና ተከባብሮ መኖርና ለሽምግል ዋጋ መስጠት ናቸው። ለተማሪዎች በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ እውቀት ማስጨበጡ ኢትዮጵያ ውስጥ መቻቻል መከባበር፣ ችግር ሲፈጠር ደግሞ በውይይትና በእርቅ መፍታት የሚችል ትውልድ ማፍራት ያስችላል። የዚህ ድምር ውጤትም ለአገሪቱ ሰላምና ዕድገት የራሱ የሆነ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡
ይሄን አስመልክቶ በጀርመን አገር ዩኒቨርስቲ ኦፍ ጊሰን የትምህርት ፖሊሲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፊሰር ተስፋዬ ኩከመ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ስርዓተ ትምህርት እንደ ደካማ ጎን የሚወሰደው ከህዝቡ ባህል፣ ስነልቦና ብዝሃነት ጋር የተያያዘ አገር በቀል እውቀቶችን በስርዓት ትምህርት ውስጥ አለመካተታቸው ነው። በዚህ ረገድ ቀደም ሲል ከሃይማኖት የመነጨ ግብረ ግብ የሚባል ትምህርት ይሰጥ የነበረ ቢሆንም በኋላ እንዲቀር ተደርጓል። ይህም የትምህርት ስርዓት ቀረጻው አንዱ ድክመት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
የባህል ህክምናዎች፣ ፍልስፍናዎች፣ ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ሁኔታዎች የመሳሰሉ አገር በቀል አስተሳቦችና ዕውቀቶች የተካተቱበት ስርዓት ትምህርት መስጠቱ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው የሚገልጹት ፕሮፊሰር ተስፋዬ፤ እንደ ገዳ ሁሉ ሌሎችም የአገረሰብ እውቀቶች በዩኒቨርስቲዎች የትምህርት ስርዓት ውስጥ ተካተው ቢሰጡ ጥቅም እንዳላቸው ይገልጻሉ። ለምሳሌ የኮንሶ የእርከን ስራ በአካባቢ ጥበቃና ልማት ትምህርት ውስጥ ተካቶ ቢሰጥ በአገሪቱ ተጨባጭ ማሳያ ከመሆኑም በላይ ተማሪው የራሱን አገር በቀል እውቀት ለማሳደግ እንደሚቀለው ያስረዳሉ። እነዚህ አገር በቀል እውቀቶች በሌሎች አካባቢዎች ለማስፋፋትና እንዳይጠፉ ለማድረግም እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡
እንደ ፕሮፊሰር ተስፋዬ ገለጻ፤ የዩኒቨርስቲዎች ዋና ስራ እውቀት ማመንጨት፣ ማስተማርና ምርምር ማድረግ ነው። አገር በቀል የሆኑ እውቀቶችና ቴክኖሎጂዎች መሰብሰብና ማደራጀት ያስፈልጋል። በምርምር ተቋማት አገር በቀል እውቀቶችና ቴክኖሎጂዎች በበቂ ደረጃና ጥልቀት ከተደራጁ በኋላ ከዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታ በማያያዝ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላፍ ነው ትምህርቱ ለተማሪዎች የሚሰጠው።
በዚህ መነሻነት የዩኒቨርስቲዎች አገር በቀል እውቀቶችን በፕሮግራም ቀርጸው ለተማሪዎች ትምህቱን መስጠታቸው የሚበረታታ ተግባር ነው። ከዚህ አኳያ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ የገዳ ስርዓትን በኮርስ መልክ ለተማሪዎች መስጠቱ ጥሩ ጅምር ነው። ሆኖም በኢትዮጵያ ውስጥ የገዳ ስርዓት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካባቢዎችና ብሔረሰቦች ሌሎች አገር በቀል እውቀቶችና የአስተዳደር ስርዓቶች ስላሉ እነዚህ እውቀቶች እኩል ትኩረት ተሰጥቷው በተደራጀ መልኩ በአገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ ተካተው ቢሰጡ መልካም መሆኑንም ነው ፕሮፌሰር ተስፋዬ የመከሩት፡፡
የገዳ ስርዓት በኢትዮጵያ የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት ዘንድ ባሕላዊ አስተዳደራዊ ስርዓት ሆኖ ለዘመናት እውቀትን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሸጋገር ያገለገለ ነው። የገዳ ስርዓት በማኅበረሰቡ ውስጥ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ፣ እና የግጭት ማስወገጃ ስርዓቶችን ያቀፈ እና በተጨማሪም የሴቶችን ሰብዓዊ መብት በማስከበር ረገድም ከፍተኛውን ሚና መጫወቱን የታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ።
የገዳ ስርዓት የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት ሞራላዊ እሴቶች ተጠብቀው ከትውልድ ትውልድ እንዲተላላፉ እና ባሕላዊ መስተጋብሮች እንዳይጠፉ ዓይነተኛ አስተዋጾ አድርጓል። የገዳ አስተዳደር አምስት ደረጃዎች ያሉትና በአንድ አባገዳ የሚመራ ሲሆን፣ በየስምንት ዓመቱም በዴሞክራሲያዊ ባህላዊ አሰራር አዲስ መሪ አባገዳ ይሰየማል። በገዳ አስተዳዳሪነት የተመረጡ አባገዳዎችና በእርከን የተሾሙ የአገር ሽማግሌዎች በኦዳ ዛፍ ጥላ ስር በመሰባሰብ ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ። የሕብረተሰቡን ባህልና ቶፊቶች የመጠበቅ ኃላፊነቶችን እንደሚወጡ መረጃዎች ያስረዳሉ።
አዲስ ዘመን መስከረም 12/2012
ጌትነት ምህረቴ