የአሜሪካው 35ኛ ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በአንድ አጋጣሚ “ ሁሉም ሸማች ነው፤ በግሉም ሆነ በመንግስት ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች በአወንታዊም ሆነ በአሉታዊ አግባብ ጥቅሙ የሚነካ በሌላ በኩል የሸማቹ ውሳኔ በግሉም ሆነ በመንግስት ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል ነው። “ ሲሉ ሸማች በኢኮኖሚው ፣ በፖለቲካውና በማህበራዊ እርካቦች የተቆናጠጠውን ከፍታ አመላክተዋል።
ከዚህ የፕሬዝዳንቱ ትርጓሜ ሁለት አበይት ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል። የመጀመሪያው አንተም ፣ አንችም፣ እኔም ሁላችንም ሸማች መሆናችንን። ሻጩ ሸማች፣ ሸማቹ መልሶ ሻጭ ይሆናል። ሁለተኛውና ትልቁ መልዕክት በሸማቹ ፣ በሻጩ እና በመንግስት መካከል ያለውን ሚዛናዊ እና ፍትሐዊ ግንኙነት ነው።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1986 ይፋ የሆነው የሸማቾች ጥበቃ ሕግ “ ማንኛውንም ሸቀጥ ወይም አገልግሎት የሚገዛ ሸማች ነው። “ በማለት ይተረጉማል ። ይህ ኬኔዲ “ ሁላችንም ሸማች ነን። “ ካሉት ጋር ይቀራረባል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም የታተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ ሸማችን ጠበብ አድርጎ፣” እህልን ለንግድ ሳይሆን ለምግብነት የሚገዛ በላተኛ።
“ ሲል ይበይነዋል። የአገልግሎት ሸመታውን በዘነጋ መልኩ። የእንግሊዘኛው ሜሪያም ዌብስተር መዝገበ ቃላት ደግሞ ቅንብብ አድርጎ “ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን የሚገዛ ሰው “ (a person who buys goods and services.) በማለት ይተረጉመዋል። ሸማችነት ሸቀጥንም አገልግሎትንም እንደሚያካትት ባረጋገጠ ምሉዕ ብያኔ።
ወደ ሀገራችን ስንመጣ በሸማቹ፣ በሸቀጥና አገልግሎት ሻጭ እና በመንግስት መካከል ያለው ግንኙነት የተዛባ፣ ኢፍትሐዊ፣ መርህ አልባ እና ኢዴሞክራሲያዊ ነው። መንግስትም ሆነ ሻጭ የየራሳቸውን ፍላጎትና ጥቅም ለማስከበር ይተጋሉ እንጂ ለሸማቹ ያን ያህል ደንታ የላቸውም ማለት ይቻላል። በተለይ መንግስት በ “የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው “ አባዜ ሻጭ ላይ የሚፈጥራቸው ማናቸውም ጫናዎች መዳረሻቸው ሸማቹ እንደሆነ እያወቀ እንኳ ጫናውን ቀለል ለማድረግ አያስብም።
ከለውጡ በፊት በነበሩ አስርና ከዚያ በላይ ተከታታይ አመታት የተመዘገበው “ ዕድገት “ መንግስት ከፍተኛ ካፒታል በማፍሰስ ዕውን ያደረገው ስለነበር እና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሊጎርሰው ከሚችለው በላይ ስለነበር ለተከታታይ አስር እና ከዚያ በላይ አመታት የዋጋ ግሽበቱ በሁለት አኀዝ ሲቀጥል አይቶ እንዳለየ በቸልታ አልፎታል።
የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አኀዝ ለማውረድ የማክሮ ኢኮኖሚ በተለይ የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያ ቢያደርግ ያስመዘግብ የነበረውን ባለሁለት አኀዝ ኢኮኖሚያዊ “ ዕድገት “ ስለሚገታውና ፖለቲካዊ ነጥብ ስለሚያስጥለው ሕዝቡን በዋጋ ግሽበት አለንጋ ማስገረፍን መርጧል። የታክስ ፖሊሲውም ሸማቹን ለተደጋጋሚ ታክስ የሚዳርግ ከመሆኑ ባሻገር ሻጩ ላይ የሚጣል ታክስ ግብር የማታ ማታ እንደ ትኩስ አሎሎ ወደ ሸማቹ የሚወረወር መሆኑን እያወቀ በዚሁ የተዛባ ፖሊሲው ገፍቶበታል።
የግብር መሰረቱን ከማስፋት ይልቅ በተወሰኑ የግብር ዘርፎች ላይ የሙጥኝ ማለትን መርጧል። ባለዝቅተኛ ኑሮውን በተለይ የመንግስት ሰራተኛውን በተደራራቢ ግብር ጀርባውን እያጎበጠ በዚሁ ዜጋ ስም በተገኘ ብድር በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚገቡ ባለፀጋዎች የግብር፣ የታክስ እፎይታ ጊዜ ይቸራል። ሕዝብ የቆጠበው ገንዘብ ሳይቀር ማኑፋክቸሪንግን እና ግብርናን ለማበረታታት በሚል ያለ መያዣ የሀገርን ሀብት እንደ ጠላት ገንዘብ በታትኖታል።
ልማት ባንክ በተለይ በጋምቤላ ክልል “በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ‘ ባለሀብቶች ‘ “ ብትን ብትን ያረገውን በቢሊዮን የሚቆጠር የሀገር ገንዘብ ያስታውሷል። ከእነዚህ “ ተበዳሪዎች “ ብዙዎቹ ዛሬ እምጥ ይግቡ ስምጥ አይታወቅም። የተሰወሩት ብድሩን ሳይመልሱ ብቻ አይደለም። አንዳንዶቹ ለእርሻ የተሰጣቸው መሬት ላይ የነበረውን ደን መንጥረው ጣውላ እና ከሰል ቸርችረው ጭምር መሰወራቸውን ለሚሰማ ያማል።
የሸቀጥ፣ የአገልግሎት ሻጩ ደግሞ በበኩሉ መንግስት የጣለበትን ሁሉንም የግብር፣ የታክስ ዕዳ እንዳለ ወደ ሸማቹ ያስተላልፋል። ብዙኀኑ የቆጠበውን ገንዘብ ከባንክ ሲበደር የሚከፍለው ወለድ ሳይቀር በተዘዋዋሪ ከብዙኀኑ ከሸማቹ በእጅ አዙር በንግድ ስም ይቀበለዋል። ስለሚከራየው ሱቅ፣ የገበያ አዳራሽ፣ ቢሮ ዋጋም አይጨነቅም። ከሸማቹ እንደሚሰበስበው እርግጠኛ ነዋ።
በገበያ ሰንሰለቱ ለተሰገሰጉ ደላላዎች ስለሚከፍለው ኮሚሽን አያሳስበውም አስልቶ ሸማቹ ላይ ይጥለዋላ። ወደ ውጭ ልኮ ስለሚሸጠው ቡና፣ የቅባት እህል፣ የፋብሪካ ውጤት፣ ወዘተ . ዋጋ መውረድ አይጨነቅም። ከስሮ ሽጦ በሚያገኘው የውጭ ምንዛሬ በአስመጭ ስም በሚያስገባው ሸቀጥ ለዚያውም ጥራቱ እዚህ ግባ በማይባል በሳምፕል በተመረተ መናኛ ሸቀጥ ከ100 እስከ 1000 በመቶና ከዚያ በላይ በማትረፍ ወደ ውጭ ሲልክ የከሰረውን በእጅ አዙር በብዙ እጥፍ የሸማቹን ጉሮሮ አንቆ ይቀበላል።
በሀገሪቱ የትርፍ ሕዳግ የሚባል ነገር አይታወቅማ። በአለማችን የትርፍ ሕዳግ የሌላትም ሆነ በነፃ ገበያ ስም ስግብግብ ነጋዴ እንደ ፈለገ የሚፈንጭባት፣ የሚፋንንባት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ትቀራለች?
የነፃ ገበያ አባት በሚባሉት ምዕራባውያን እንኳ በማንኛውም ሸቀጥና አገልግሎት ላይ የትርፍ ሕዳግ ተጥሎበት እያለ እኛ በመንግስት ቸልተኝነት አሳራችንን እናያለን። በተለይ ከጥቂት አመታት ወዲህ የተከሰተው የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት፣ ቀማኛ የንግድ ስርዓት የሕዝቡን ታጋሽነት፣ ቻይነት በእጅጉ እየተፈታተነው ይገኛል። ሸማቹ በስግብግብ ነጋዴዎች እና ሕገ ወጦች በቁም ሲገፈፍ መንግስት መከላከል ሲገባው ችላ ማለትን መምረጡ ወቅታዊው የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።
በግብር ከፋዩ ዜጋ ገንዘብ ድጎማ በሌለ የውጭ ምንዛሬ የሚገባ ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳር፣ መድሀኒት፣ ወዘተ . ሳይቀር ለስግብግቦች በአንድ ጀምበር መክበሪያ ሲሆን ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እግሩን የሚጎትትበት ምክንያት ለብዙዎቻችን እንቆቅልሽ ሆኖ ቀጥሏል።
ባለፉት 27 ዓመታት በነፃ ገበያ ስም እንደ ኢትዮጵያውያን ሸማቾች ፍዳውን ያየ አሳሩን የበላ ሸማች የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ስነ ምግባር የጎደላቸው ስግብግብ ነጋዴዎች፣ አገልግሎት አቅራቢዎች እና ከሻጩና ከሸማቹ ድምር ቁጥር የሚበልጡ ደላላዎች ጋር በማበር ሸማቹን በኑሮ ውድነት በችጋር እየጠበሱት ነው።
መንግስት በነፃ ገበያ ስም ስግብግብ ነጋዴውን እና ደላላውን ስድ መልቀቁ፣ አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ ማለፉ ግንባር ፈጥረው ሊባል በሚችል ሁኔታ ሸማቹን ቁም ስቅሉን እንዲያሳዩት የፈቀደ አስመስሎታል። ይቅርታ ይደረግልኝና የሸማቾችን መብት ለማስከበር በመንግስት የተቋቋመው አካልም ይሁን በሸማቾች የተመሰረተው ማህበር (በእርግጥ) ምን እየሰሩ እንደሆነ ግልፅ አይደለም።
ስለሆነም በመላው አለም እንደሚደረገው የሸማቹን መብት እና ጥቅም የማስከበር ጉዳይ ለመንግስት ብቻ በመተው ዘላቂ እና ስርነቀል ለውጥ ስለማያመጣ ሸማቹ መብቱን፣ ጥቅሙን፣ ጤንነቱን የሚያስጠብቅለት ጠንካራ፣ ሀቀኛ ሀገር አቀፍ የሸማቾች ማህበር ሊያቋቁም ይገባል። ማህበሩ የሸቀጥና የአገልግሎት ሸማቹን መብትና ጥቅም የሚያስከብር ብቻ ሳይሆን ግዴታውንም ሆነ ኃላፊነቱን የሚያስገነዝብ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ማህበሩ የነፃ ገበያ ውድድርን ከማበረታታት ባሻገር፣ እውነተኛ የገበያ መረጃዎችን ለሸማቹ ለማድረስ ያግዛል። ከዚህ በተጨማሪም ያልተገባ የንግድ ውድድርን ለመከላከል አስተዋጾ ይኖረዋል።
አለም አቀፉ የሸማቾች ጥበቃ ሕግ ሸማቾች የመምረጥ፣ መረጃ የማግኘት፣ የመደመጥ፣ የመካስ፣ የጤነኝነት፣ የተሟሉ መሰረታዊ ፍላጎቶችን፣ አማራጭ አገልግሎትና ሸቀጣሸቀጦችን፣ ስለሸቀጦችና አገልግሎቶች አጠቃቀም መረጃ የማግኘት፣ ወዘተ መብት እንዳላቸው ያትታል። የሸማቾች ጉዳይ አለም አቀፍ አጀንዳ ነው ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1985 ስለ ሸማቾች መብት ጥበቃ ባወጣው እና አባል ሀገራት እንዲተገብሩት ጭምር በሚያሳስበው ሕግ ሀገራት፣ መንግስታት የሸማቾችን መብት ፣ ጥቅም የሚያስከብሩ አሰራሮችንና አደረጃጀቶችን የመዘርጋት ኃላፊነት እንዳለባቸው ያሳስባል። ከእነዚህ ውስጥ የሸቀጦችን እና አገልግሎቶችን ደረጃ ከጥራት፣ ከጤና አንጻር ማውጣት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
እንደ ቀብድ
የሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበርን ማቋቋም አስፈላጊነት ላይ ልዩነት ይኖራል የሚል ስጋት ስለሌለኝ ማህበሩ በቀጣይ ሲቋቋም ሊያተኩርባቸው ይገባል ብዬ የማምንባቸውን እና በአለማችን ከሚገኙ መሰል ማህበራት የቃረምኋቸውን ነጥቦች በቀብድነት ላስጨብጥ።
1ኛ. የሚቋቋመው ማህበር የሸማቾችን ጥቅምና መብት በዘላቂነት ለማስከበር፣ ለማስጠበቅ ታማኝ ጠበቃ፣ ተሟጋችና ድምፅ ሆኖ ሊያገለግል ይገባል።
2ኛ. ሸማቾች መብታቸውን፣ ጥቅማቸውንና ደህንነታቸውን ለማስከበርና ለማስጠበቅ እንዲችሉ ማህበሩ የማብቃት ግንዛቤ የመፍጠር ኃላፊነት አለበት።
3ኛ. ማህበሩ የሸማቾችን መብት ጥቅም እና ደህንነት የሚያስከብሩ የፖሊሲ ሀሳቦችን በማመንጨት ለመንግስት የማቅረብ አደራ አለበት።
4ኛ. ማህበሩ ለብቻው ውጤታማ ሊሆን ስለማይችል ከግሉ ዘርፍ፣ ከሚዲያው፣ ከባለድርሻ አካላትና ከመንግስት ጋር በቅንጅት መስራት ይጠበቅበታል።
5ኛ. ማህበሩ ቀጣይነት ላለው ሸማችነት በሚዛናዊነትና ፍትሐዊነት መስራት እንዲሁም አሰራሩ ግልፅና ገለልተኛ ሊሆን ይገባል።
እንደ መውጫ
የሀገራችን ሸማች በተመጣጣኝ ዋጋ፣ ጥራት ያለው፣ ጤንነቱ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ሸቀጥ አገልግሎት አማርጦ፣ አወዳድሮ የመሸመት መብት ቢኖረውም እውን ማድረግ ባለመቻሉ ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ተዳርጎ ይገኛል። ለኑሮ ውድነት፣ ለጤና ጠንቅ ለሆኑ ሸቀጦች እና ጥራት በጎደላቸው ሸቀጦች ጤናው እየታወከ ይገኛል።
ከሁሉም በላይ በሸማቹ፣ በሻጩና በመንግስት መካከል ያለው ግንኙነት የተዛባ፣ ኢፍትሐዊና ኢዴሞክራሲያዊ መሆኑ በተለይ ሸማቹን ሁል ጊዜ ተበዳይ፣ ተገፊና ተጠቂ አድርጎታል። በአዲሱ አመት የሚቋቋመው የሸማቾች ማህበር ይህን የተዛባ ግንኙነት የሚያስተካክልና የተነጠቀውን መብትና ያጣውን ጥቅም የሚያስመልስ ይሆናል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ። አዲሱ አመት የሸማቹ መብት እና ጥቅም የሚከበርበት ብሩህ አመት ይሁንልን።
አዲስ ዘመን መስከረም 12/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳይን)