አዲስ አበባ፡- በደቡብ ብሄሮችና ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አንዳንድ ዞኖች እያነሱ ያሉት የክልል እንሁን ጥያቄ የክልሉ መንግስት እያስጠና ባለው ጥናት በአግባቡ ታይቶ ምላሽ የሚሰጠው መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የሲዳማን የክልል የመሆን የዘመናት ጥያቄ የክልሉ መንግስት ተቀብሎ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ማድረጉን ተከትሎ በአንዳንድ የክልሉ ዞኖች ተመሳሳይ ፍላጎት ጨምሯል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎችም ጥያቄያችን ምላሽ አያገኝም በሚል ስጋት ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ተበራክተዋል፡፡ ይሁንና የክልሉ መንግስት አስቀድሞም ቢሆን እነዚህ ጥያቄዎች ሊመጡ እንደሚችሉ በመገንዘብ ጥናቱ ሁሉም ህዝብ በሚያማክልና በሚጠቅም መልኩ ምላሽ እንዲሰጥ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
የክልሉ መንግስትም የሲዳማን የክልልነት ጥያቄውን ተቀብሎ የሌሎቹን ደግሞ በጥናት ለመመለስ መታሰቡ የፍትሃዊነት ጥያቄ አያስነሳም ወይ? ተብለው ተጠይቀው ሲመልሱ፣ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ለዘመናት የቆየና ቀድሞ በነበሩ አመራሮች ሲገፋ የኖረ በመሆኑ እንዲሁም ክልሉን የሚመራው ገዢ ፓርቲም ጥያቄው የህዝብ መሆኑን አምኖበት ህዝበ ውሳኔ እንዲሰጥበት ውሳኔ ማስተላለፉን አስረድተዋል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ እንደከዚህ ቀደሙ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ አፍኖ ለመቀጠል አዳጋች ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፣ ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ አንፃር ህዝቦች ያዋጣል የሚሉትን ሃሳብ ማዳመጥ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱም ውሳኔው ተወስኗል ብለዋል፡፡
የሲዳማን ያህል ጎልቶ ባይወጣም ተመሳሳይ ጥያቄ በሌሎቹም አካባቢዎች ይነሳ እንደነበር አስታውሰው፤ ይሁንና በስፋት ጥያቄው እያየለ የመጣው የድርጅቱ ጉባኤ ከወሰነ በኋላ ሲሆን፣ የጉባኤውም ውሳኔ ለሁለት ዓመት ስራ ላይ የሚውል በመሆኑ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
«በህገመንግስቱ መሰረት ለምክር ቤቱ ጥያቄ ከቀረበበት እለት ጀምሮ ባለው አንድ ዓመት ውስጥ ህዝበ ውሳኔ መደረግ አለበት ብሎ ያስቀምጣል፡፡ አመቱ ሊያልቅ ጥቂት ወራት እና ብዙ ስራዎች ደግሞ ይቀራሉ፡፡ በህገመንግስቱ ጭምር በጊዜ ገደብ የተገደበ በመሆኑ ነው ቶሎ ወደ ስራ መግባት ያስፈለገው» ብለዋል፡፡
በመሆኑም ህዝበ ውሳኔውም የሚመለከተው የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ብቻ መሆኑንና የሌሎቹ ጥያቄ ግን በጥናቱ ለአስተዳደርና ለመልማት በሚመች መልኩ እንዲመለስ ይደረጋል ብለዋል፡፡ አተገባበሩም የህዝቡን ሙሉ ፍላጎትና ፍቃድ መሰረት ያደረገ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
ከመብት አንፃር የክልልነት ጥያቄ ትክክል መሆኑን ጠቅሰው፣ ነገር ግን ለህዝቦች የሚሻለውና የሚጠቅመው አደረጃጀት በጥናት ሊመለስ የሚገባና ይህንንም ህዝብ ባሳተፈና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ለመመለስ እንደ ድርጅት አቋም መያዙን አስረድተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህና በሌሎችም ወቅታዊ ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ለዝግጅት ክፍሉ የሰጡትን ዝርዝር ምላሽ በዛሬው የፖለቲካ አምዳችን ገጽ 11 ማግኘት እንደምትችሉ መጠቆም እንወዳለን፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2018
ማህሌት አብዱል