አዲስ አበባ፡- ሰላምንም ሆነ ፍትህን በአገር ላይ ለማስፈን መንግስት እጅና እግር የሚያገኘው ግብር መሰብሰብ ሲችል መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የታክስ ንቅናቄ ማብሰሪያ ፕሮግራም ትናንት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት የስልጣኔ እግሮችን ለማበርታትና እንቅፋቶችን ለማስወገድ ጠንካራ የፍትህ ሥርዓት ወሳኝ ነው፤ ሰላምንም ሆነ ፍትህን በአገር ላይ ለማስፈን ደግሞ መንግስት እጅና እግር የሚያገኘው ግብር መሰብሰብ ሲችል ነው። አለበለዚያ ለምልክት የተቀመጠ ምንም ማድረግ የማይችል ሽባ ነው ብለዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ሰርተን ለመኖር የሚያስችለን አገር ጸንቶ እንዲኖር ህግን የሚያስከብርና ሰላምን የሚያሰፍን መንግስት ያስፈልጋል፤ ይህንን እንዲሰራ ደግሞ አገራዊ የገንዘብ አቅም ያስፈልገዋል፤ ይህም አቅም በዋናነት የሚገነባው ከዜጎችና ከነዋሪዎች በሚገኝ ግብር ነው።
ግብር ቀላል ቢሆንም ለመንግሰት ግን እንደ ኦክሲጅን አስፈላጊ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አገርን ከፍ ለማድረግ ከሚያስፈልጉ ሶስት ቀላል ነገሮች መካከል ግብር አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። ላብ ደምን ያድናል እንደሚባለው ግብር ደግሞ የብዙዎቻችንን ህይወት ለመታደግ የሚያስችል አገራዊ አቅምን ይፈጥራል። ግብር ባለመክፈል በአገር ላይ ከሚደርሰው ኪሳራ በላይ በመክፈሉ የሚገኘው ስልጣኔ ለሁላችን ኪስ የማይጎዳና ርካሽ መሆኑን አመልክተዋል።
ዜጎች በሚከፍሉት ግብር መንግስት የመሰረተ ልማትን በማስፋፋት በተለይም የግል ዘርፉ ጠንካራና ተወዳዳሪ እንዲሆን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፤ ምክንያቱም ጠንካራና ተወዳዳሪ የሆነ የግል ዘርፍ ለዜጎች ሰፊ የስራ እድልን ከመፍጠሩም በላይ ትርፋማነቱን የሚያረጋግጥና ትልቅ የገቢ ምንጭ በመሆን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የስልጣኔ መገለጫዎች ከሚባሉት አንዱ የተስተካከለ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ፣ማህበረሰባዊ ደህንነት፣ የዳበረ የፍትህ ሥርዓት፣ የላቀ የእውቀትና የጥበብ አቅም፣ በምግብ ራስን መቻልና መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ለሁሉም ማዳረስ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እነዚህ ሳይቋረጡና ከደረጃቸው ሳይወርዱ ለማስቀጠል የሚቻለው ግብርን ለመሰብሰብ የሚያስችል ሥርዓትና አቅም ሲፈጠር ብቻ መሆኑን አብራርተዋል።
«ኢትዮጵያ እንድታድግ ፣ እንድት ሰለጥን፣ ሰላምና ደህንነቷ የተሟላ ሆኖ ለዜጎቿና ለነዋሪዎቿ መሰረታዊ ፍላጎቶችን በበቂ ሁኔታ ማቅረብ እንድትችል፤ ብሎም ድህነትን አሸንፋ ወደ ብልጽግና ጎዳና እንድትገሰግስ ከፈለግን ለግብር ያለንን ደካማ አመለካከት መቀየር ይኖርብናል። ግብር የሚያጭበረብር ሰው እንደ አራዳ መቆጠሩ ቀርቶ አገሩንና መንግስቱን የሚጠላ ፤ ስለ ራሱ ልጆች የዛሬና የወደፊት ህልውና ምንም የማይጨነቅ ሞኝ ተደርጎ ሊቆጠር ይገባል» ብለዋል።
ግብርን በወቅቱ አለመክፈል ፣በተጭበረበረ ደረሰኝ መነገድ ፣ ያለንግድ ፍቃድ መስራት፣ ባለስልጣናትን ተደግፎ በህገ ወጥ ንግድ ላይ መሰማራት ፣ግብርን መሰወር ፣የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲሁም ሙስናና ብልሹ አሰራር የግብር ሥርዓቱን በካቴና አስረውታል፤ ይህ ድርጊት የዜጎችን ደም መምጠጥ ስለሆነ ከዚህ ድርጊታችሁ ያለማንም ነጋሪ ውጡ ሲሉም አሳስበዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ግብር ለየትኛውም አገር ህልውና ማረጋገጫ መንግስታት የመረጣቸውን ህዝብ ጥያቄ የሚመልሱበት ነው ፤ ይህ የተሰበሰበ ግብር ደግሞ ለታለመለት አላማ በውጤታማነትና በብቃት ሲውል የህዝብ ጥያቄ ይመለሳል መተማመንም ይፈጥራል ብለዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ ደረጃው ይለያይ እንጂ በየትኛውም ዓለም መንግስት የታክስ ህግ ተገዢነትን ለማምጣት ፣ የታክስ አስተዳደሩን ፍትሀዊ ለማድረግ ሲጥር ግብር ከፋዩ ላለመክፈል በሚያሳየው ዳተኝነት አለ፤ አገራት ይህንን ለመፍታትና የታክስ አሰባሰባቸውን ለማሳደግ የተደራጁ የማህበረሰብ ንቅናቄዎችን በማድረግ ግብር የግል ገንዘብ ሳይሆን የአገርና የህዝብ እዳ መሆኑን ያስተምራሉ፤ በዚህም መንገድ የተጓዙ አገሮች ህዝባቸው ግብርን መክፈል ባህል፣ ስልጣኔና ኩራት አድርገው እንዲወስዱ ማስቻላቸውን አስረድተዋል።
እኛም ግብርን በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል አገሪቱ ውስጥ ለሚካሄዱ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር ስራዎች መፋጠን የበኩላችንን መወጣትና ለውጡን ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ማድረግ አለብን ያሉት ወይዘሮ አዳነች ይህንን ማድረጋችን ደግሞ ህዝቡ ለሚያነሳቸው የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ እንዲሰጥ ከማስቻሉም በላይ የሀብት ክፍፍሉ የተመጣጠነና ፍትሀዊ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።
የታክስ ንቅናቄ ማብሰሪያ ፕሮግራሙ ላይ ከ1 ሺ ያላነሱ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት የተገኙ ሲሆን ንቅናቄውን በፈቃደኝነት የሚደግፉና ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ ሰዎችም አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2011
በእፀገነት አክሊሉ