እ.አ.አ በ2018 በዓለም ዙሪያ ከ63 በላይ ጋዜጠኞች መገደላቸውን ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን (Reporters Sans Frontières – RSF) የተባለው ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋም ይፋ አድርጓል፡፡ አሟሟቱ ያስነሳው ዓለም አቀፍ ውዝግብ አሁንም ድረስ ያልበረደውን ሳዑዲ አረቢያዊውን ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂን ጨምሮ በዚህ ዓመት ከተገደሉት ጋዜጠኞች መካከል ከግማሸ በላይ የሚሆኑት ሆን ተብሎ ታስቦ በተፈፀመ ጥቃት እንደተገደሉ የተቋሙ ሪፖርት ያመለክታል፡፡
ተቋሙ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው ዓመታዊ ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፣ ጋዜጠኞቹ የተገደሉት ሙያዊ ተግባራቸውን እያከናወኑ በነበሩባቸው ጊዜያት ነው፡፡ ከጋዜጠኞቹ በተጨማሪም በሙያቸው ጋዜጠኛ ያልሆኑ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችም ሕይወታቸው እንዳለፈና አጠቃላይ የሟቾች ቁጥርም ከ80 እንደሚበልጥ ገልጿል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት የ15 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የተጋረጠ ከባድ አደጋ እንደሆነ ተቋሙ አስታውቋል፡፡ የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት አስር ዓመታት በዓለም ዙሪያ የተገደሉት ጋዜጠኖች ቁጥር ከ700 በላይ እንደደረሰም ተቋሙ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የተቋሙ ስራ አስፈፃሚ ክሪስቶፍ ዴሎር ‹‹የኃይማኖት ሰዎችን ጨምሮ ፖለቲከኞች፣ ባለሀብቶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ለጋዜጠኞች ያላቸው ጥላቻ በተጨባጭ በርካታ መጥፎ ውጤቶችን እያስከተለ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የሳዑዲ አረቢያዊው ጀማል ኻሾግጂ እንዲሁም የወጣቱ ስሎቫኪያዊ ጋዜጠኛ ጃን ኩያክና የፍቅረኛው ግድያ የመገናኛ ብዙኃንና የሃሳብ ነፃነት ጠላቶች የተጓዙበት ርቀት ማሳያ ነው›› ብለዋል፡፡
መቀመጫውን ፓሪስ ያደረገው ይህ ዓለም አቀፍ ተቋም አፍጋኒስታን፣ ሶርያና ሜክሲኮ ለጋዜጠኞች እጅግ አደገኛ ከሆኑ አገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት እንደሚጠቀሱ ገልጿል፡፡ ባለፈው ሰኔ ወር በሜሪላንድ፣ አሜሪካ በሚገኘው የ‹‹ካፒታል›› ጋዜጣ (Capital Gazette) መስሪያ ቤት ላይ በተከፈተ የተኩስ እሩምታ አምስት የጋዜጣው ሰራተኞች መገደላቸው ለወትሮው በመገናኛ ብዙኃን ነፃነት በምትታወቀው ልዕለ ኃያላኗ አሜሪካ ላይ ጥያቄ አስነስቶባታል፡፡
ከዚህ ባሻገርም በዓመቱ በዓለም ዙሪያ ከ348 በላይ ጋዜጠኞች እንደታሰሩና ይህም ባለፈው ዓመት ከታሰሩት ጋዜጠኞች እንደሚበልጥ የተቋሙ ሪፖርት ያሳያል፡፡ ከታሰሩት ጋዜጠኞች መካከል ደግሞ የአብዛኞቹ አሳሪዎች ቻይና፣ ግብፅ፣ ቱርክ፣ ኢራንና ሳዑዲ አረቢያ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ በተቋሙ ሪፖርት መሰረት፣ ቻይና 60፣ ግብፅ 38፣ ቱርክ 33፣ ኢራንና ሳዑዲ አረቢያ እያንዳንዳቸው 28 ጋዜጠኞችን በማሰር ቀዳሚዎቹን ስፍራዎች ይዘዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ ታስረው የነበሩ ጋዜጠኞች ቁጥር 326 እንደነበር ያስታወሰው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጋዜጠኞችን ጉዳይ የሚከታተልና መብቶቻቸውንም የሚያስከብር ራሱን የቻለ አማካሪ እንዲኖረው ጥሪ አቅርቧል፡፡
በ2018 የሳዑዲ አረቢያዊው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ግድያ አነጋጋሪ እንደሆነው ሁሉ፣ ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ ከተገደሉት ጋዜጠኖች መካከል በመስከረም 2017 በደቡባዊ ሕንድ ካርናታካ ግዛት፣ ባንጋሎር ከተማ የተፈፀመው የታዋቂዋ ጋዜጠኛ የጎሪ ላንኬሽ ግድያ እንዲሁም በግንቦት ወር 2017 በሰሜን ምዕራባዊ ሜክሲኮ ሲናሎዋ ግዛት በሰሜን ምዕራባዊ ሜክሲኮ ሲናሎዋ ግዛት የተገደለው የ50 ዓመቱ ሜክሲኳዊው ጋዜጠኛ ሃቪየር ቫልዴዝ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት የሳቡና ሕንድና የሜክሲኮ መንግሥታት ከጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች ከባድ ወቀሳዎችን እንዲያስተናግዱ ያደረጉ ግድያዎች ነበሩ፡፡
በመስከረም 2017 በደቡባዊ ሕንድ ካርናታካ ግዛት፣ ባንጋሎር ከተማ የተፈፀመው የታዋቂዋ ጋዜጠኛ የጎሪ ላንኬሽ ግድያ ዓለም አቀፍ ቁጣ ቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ጎሪ ላንኬሽ አክራሪ/ቀኝ ዘመም የሒንዱ ብሔርተኞችን በተመለከተ በምትፅፋቸው አወዛጋቢና በሳል ጽሑፎቿ ትልቅ ዝናና ክብር ያተረፈች ጋዜጠኛ ነበረች፡፡ ሕንድን ጨምሮ በመላው ዓለም ታዋቂ ለሆነውና ‹‹ዘ ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ›› (The Times of India) ለተባለው ጋዜጣ ሰርታለች፡፡ ‹‹ፍርሃት አልባዋና ተናጋሪዋ ሰው›› በመባል ትሞካሽ የነበረችውና ለዴሞክራሲና ለፕሬስ ነፃነት ትታገል እንደነበር የተነገረላት ጎሪ ላንኬሽ፣ ‹‹ፋሺስታዊና ኮሚኒስታዊ ባህርይ አለው›› ብላ በግልፅ ከተቸቺው ከህንድ ገዢ ፓርቲ (BJP) አባላትና ከሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ሆድና ጀርባ ከሆነች ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል ሲባል ነበር፡፡
በሌላ በኩል የ2011 የሲ.ፒ.ጄ (Comm ittee to Protect Journalists – CPJ) ዓመታዊ የፕሬስ ነፃነት ሽልማት (Press Free dom Award) አሸናፊ የነበረው ሜክሲኳዊው ጋዜጠኛ ሃቪየር ቫልዴዝ፣ አደንዛዥ እፅ በሜክሲኮና በአካባቢው አገራት ላይ እያደረሰ ስላለው ጥፋትና ማኅበረሰባዊ ቀውስ ላይ ያተኮሩ በርካታ የምርመራ ዘገባዎችን፣ ጽሑፎችንና መጽሐፍትን የፃፈ ስመጥር ጋዜጠኛ ነበር፡፡ በእነዚህ ስራዎቹም በሜክሲኮ እጅግ ዝነኛና የተከበረ ጋዜጠኝ እንደነበርም ይነገርለታል፡፡
በተለይ ሴት ጋዜጠኞች በሙያቸው ምክንያት የሚደርስባቸው ጥቃት ያሳሰበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሴት ጋዜጠኞችን ከፆታዊ ትንኮሳ፣ ጥቃትና ብዝበዛ የሚከላከል የውሳኔ ሃሳብ በኅዳር 2017 ማፅደቁ የሚታወስ ነው፡፡ የመብት ተሟጋች ድርጅቶችም ጋዜጠኞች በስራቸው ምክንያት ለሚደርስባቸው ጥቃት መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ከለላና ጥበቃ እንዲሰጧቸው ግፊት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በ2018 ከተገደሉት ጋዜጠኞች መካከል ባለፈው መስከረም ወር ቱርክ ወደሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ቆንስላ ገብቶ ያልተመለሰው የ‹‹ዘ ዋሺንግተን ፖስት (The Washington Post)›› ጋዜጣ አምደኛ የነበረው ጀማል ኻሾግጂ ግድያው አሁንም ድረስ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እያወዛገበ ይገኛል፡፡ የአሜሪካን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን በአንድ ወገን አንጋፋዎቹን ሴናተሮች ጨምሮ አብዛኞቹን የአገሪቱን የምክር ቤት አባላትን ደግሞ በሌላ ወገን አሰልፎ እያነታረካቸው ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2011
አንተነህ ቸሬ