የፈጠራ ሥራ፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ አንድን ሀገር ወደተሻለ እድገት ለማሻገር የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ::ኢትዮጵያም ይህን በመገንዘብ ተቋምዓዊ መመሪያ በማዘጋጀት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ በመስራት ላይ ትገኛለች::በዚህ ረገድም ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሳይንስ አካዳሚ የተሻለ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ እንዲሰራ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ወጣቶች ሳይንስ አካዳሚ ወጣቶችን ለፈጠራ ሥራ የሚያነሳሳ ድጋፍ በማድረግ ባለፉት ጊዜያቶች የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ውድድር በማዘጋጀትም መነሳሳትን እየፈጠረ ይገኛል፡፡አካዳሚው ፈረንሳይ ሀገር ከሚገኘው የአፍሪካ የሳይንስ እድገት ማሕበር አ.ፕ.ሳ. (APSA) ጋር በመተባበር ‹‹አፍሪካውያን ወጣቶችን ለፈጠራ ሥራ እናበረታታ በሚል መሪ ቃል›› ከኅዳር 28 እስከ ታኅሳስ 1ቀን 2011ዓ.ም ‹‹አፕሳ ቻሌንጅ›› የተሰኘ የሳይንስና የቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ ውድድር አካሂዷል::
የውድድሩ ዓላማ ወጣቶች ዘላቂ የልማት ግቦችን መሰረት በማድረግ በአካባቢያዊ፣ በማህበራዊ፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ በጤና ወይም በየትኛውም የማህበረሰብ የኑሮ ሁኔታ ላይ መፍትሄ የሚያመጡ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት የአፍሪካዊያንን ችግር በአፍሪካዊያን ለመፍታት እንዲቻል ታሳቢ ያደረገ ነው::እንዲሁም አንዱ ከሌላው በመማር ልምድ እንዲያገኙበት የሚያስችል ነው፡፡
ከዕለቱ የውድድሩ ተሳታፊዎች አቶ እርቅይሁን እስከመቸ እና አቶ ይወድስ ዳኜ ከ18 የአፍሪካ ሀገሮች ከቀረቡ 120 ፕሮጀክቶች ውስጥ የአስራአንድ ፕሮጀክቶች የመጨረሻ ዙር ውድድር መካከል ለመሆን ችለዋል።የፈጠራ ስራቸውም ባህላዊ የሽመና ዘዴን በዘመናዊ የተካ ሲሆን፣ በኮምፒውተር ፕሮግራም በመታገዝ ነው መሳሪያውን የሰሩት፡፡ምንም አይነት የሰው ሀይል ሳያስፈልግ ሦስት እና ከዚያ በላይ የሆኑ የሽመና ማሽኖችን ባንዴ በኮምፒውተር በመቆጣጠር ምርት እንዲሰጡ የሚያስችል የፈጠራ ስራ ነው የሰሩት።
ዘመናዊው የፈጠራ መሳሪያ ምርት እና ጥራትን በመጨመር፣ የሰው ሀይልን በመቀነስ፣ አላስፈላጊ ወጭን እና ድካምን የሚያስቀር ነው። እንዲሁም የሀገራችንን ባህላዊ አልባሳትን ምርት እና ጥራቱን ከፍ ለማድረግ ያስችላል፡፡ይህ ደግሞ በተፈለገው መጠን ለሀገር ውስጥም ለውጭ ገበያም ለማቅረብ ይረዳል፡፡በተለይ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት በሀገር ኢኮኖሚ ላይም ድርሻ ያበረክታል። መሳሪያው ሙሉ ለሙሉ የተሰራው ከእንጨት እና በአካባቢ በቀላሉ ከሚገኙ ጥሬ ዕቃዎች ነው። የሽመና መሳሪያውም ከሙሉ ዋስትና ጋር ለገበያ ሲቀርብ 5ሺ ብር ዋጋ የተተመነለት መሆኑን የፈጠራ ባለቤቶቹ ያስረዳሉ።
ሌላው ከጓደኛው ጋር በመሆን በሰራው ፈጠራ ለመጨረሻው ዙር የደረሰው ተወዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ግርማ ከሰው ሽንት ጠቃሚ ንጥረነገሮችን በማስቀረት ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ ነው ያዘጋጁት፡፡ተወዳዳሪው ስለ ፈጠራው እንዳብራራው ያዘጋጀው ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ በአካባቢ፣ በዕፅዋት፣ በእንስሳት እንዲሁም በሰው ላይ የጎንዮሽ ጉዳት እንደማያስከትል አረጋግጧል፡፡እርሱ እንዳለው በተለይ ከተሞች በሽንት ይበከላሉ። ነዋሪዎች በብክለቱ ለተለያየ የጤና ችግር ይጋለጣሉ፡፡የፈጠራ ስራው በተግባር ላይ ሲውል የአካባቢ ብክለትን በማስቀረትም የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
ሽንት አካባቢን ከመበከል ወደ ገቢ ምንጭነት በማዋል በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገባውን ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ በመተካት ወጭን በቀላሉ መቀነስ ይቻላል፡፡በተጨማሪም የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም በኬሚካል የሚዘጋጀውን ማዳበሪያ ለማስቀረት ያግዛል። ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ የሚናገረው አቶ ዮሐንስ የእርሻ መሬትን ከኬሚካል ነጻ እንዲሆን ከማገዙ በተጨማሪ በቀላሉ ከሀገር ውስጥ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ይረዳል፡፡
በውድድር መድረኩ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሹመቴ ይግዛው እንደተናገሩት እንዲህ ያሉትን የፈጠራ ስራዎች በማበረታታት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ይቻላል፡፡እርሳቸው እንዳሉት ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለሳይንስ አና ቴክኖሎጂ አዲስ አይደሉም። በዓለም የሚታወቁ በባህላዊ መንገዶች በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡አዳዲስ ጽንሰ ሀሳቦችን በማመንጨትም ችግር የለባቸውም፡፡ዋናው ችግር ወደ ተግባር መቀየር ላይ ነው፡፡የፈጠራ ክህሎት ያላቸውን በመደገፍና ክትትል በማድረግ በሀገር ደረጃ የፈጠራ ሥራ እንዲጎለብት በተለይ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን በማበረታታት የተጠናከረ ሥራ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
እንደነጃፓን፣ ቻይና ሲንጋፖር የመሳሰሉት ሀገሮች የትናንት ታሪካቸውን ቀይረው ኃያላንና ያደጉ ሀገራት ተርታ ላይ መመደብ የቻሉት ለፈጠራ ሥራ ትኩረት በማድረጋቸውና ወጣቱን በማበረታታቸው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ሳይንስ አካዳሚ ኤክስኪዩቲቨ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ በበኩላ ቸው እንዲህ ያለው ውድድር በፈጠራ ባለሙያዎች መካከል ፉክክር የሚፈጥር ከመሆኑ በተጨ ማሪ የአፍሪካ ሀገራት ያሉባቸ ውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በፈጠራ እንዲፈቱ እንደሚያግዝ ተናግ ረዋል፡፡ ማእዕከላቸው የፈጠራ ባለሙያዎ ችን በማበ ረታታት የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
ችግሮችን በመፍታት እና አይነተኛ መፍትሄ በመስጠት ለአንድ ሀገር ቁልፍ ሚና ይጫ ወታሉ:: የፈጠራ ሥራ በአንድ ሀገር ፈጣን ዕደገት እንዲመጣ፣ ኋላቀርነት እና ድንቁርናን በማላ ቀቅ በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያስችላል::
የአፍሪካ የሳይንስ እድገት ማሕበር (አ.ፕ.ሳ.ሳ) ሳይንስን፣ ቴክኖሎጂንና የፈጠራ ስራን በማበራታት አፍሪካዊያን ወጣቶች በፈጠራ ስራ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ብሎም አፍሪካን የፈጠራ መዲና የማድረግ ዓላማ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ከዕለቱ መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል፡፡ማህበሩ ወጣት አፍሪካዊያን ጠንክረው በመስራት ለችግሮቻቸው መፍትሄ የሚሆኑ ሳይንሳዊ የሆኑ የፈጠራ ስራዎችን በማስተዋወቅ የነገዋን የበለጸገች አፍሪካን እውን በማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ማህበሩ አደራ ጥሎባቸዋል፡፡
ታሪክ እንደሚነግረንና አሁንም በተጨባጭ እንደምናየው የፈጠራ ስራዎች፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በዓለማችን ላይ ባደጉ ሀገሮች እና በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች በተጨባጭ ልዩነት ፈጥረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2011
ሰሎሞን በየነ