ሥራ ወዳድነት በብዙ መልኩ ይገለጻል፡፡ ዝቅተኛ የሚባሉ ስራዎችን ከመስራት ጀምሮ ያለ እረፍት በትጋት እስከመስራት፤ ይሄ ግን በብዙዎቻችን ላይ አይታይም፤ የስራ መረጣ ለብዙዎች የእንጀራ መግፊያ ነው። ጥቂቶች የስራ ክቡርነት የገባቸው ግን ስራን ሳይንቁ ሰርተው፣ ራሳቸውን አሻሽለው ትልቅ የሚባለው ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
የዛሬው የህይወት እንዲህ ናት እንግዳችን የስራ ክቡርነትን የተረዱ ስራን ሳይመርጡና ሳያማርጡ ዝቅ ብለው የሰሩ ሰው ናቸው፡፡ ‹‹ ስራ የማይንቀው ልጅ›› እየተባሉ እስከመጠራት ደርሰዋል፡፡ የጫማ ማሳመር (ሊስትሮ)፣ ሱቅ በደረቴ፣ ሎተሪ አዟሪነት፣ ጥበቃ፣ አስተናጋጅነት፣ እንቁላልና ዶሮ መነገድ …ስራ ሁሉ ሞክረውታል፡፡ ቤተሰባቸው ያለባቸውን የኑሮ ችግር ለማላቀቅም ጥረው ግረዋል።
ከዛሬው እንግዳችን ዲያቆን አደራጀው አዳነ ጋር ያደረግነው የህይወታቸውን ቅኝት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
‹‹ እያያ›› ለመልካም ተግባር የወጣ ስም ዲያቆን አደራጀው ተወልዶ ያደገው በጥንቷ የስልጣኔ ከተማ ጎንደር ውስጥ ነው። ቀበሌ 4 ልዩ ስሙ አራዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ1976ዓ.ም በወርሓ መስከረም የአደይ አበባ በሚፈነዳበት፣ ዘመድ ከዘመድ በሚገናኝበት የአዲስ አመት መጀመሪያ ለቤተሰቦቹ የደስታ ምንጭ ሆኖ ቤተሰቡን ተቀላቀለ።
በእነ አደራጀው ቤት የሚበላ ባይጠፋም የልጅ ባህሪ ከውጪ ያለን መፈለግ ነውና አደራጀውም በልጅነት እድሜው በአካባቢው አጠራር ‹‹ገረጋንቲ›› ተብሎ የሚጠራውን ዳቦ እየበላ ነው ያደገው። ይህ ስም የወጣለት ዳቦው ጥቁር ሆኖ ለመብላት በጣም የሚያስቸግር ስለነበረ ነው። እናም በአራዳ አካባቢ የተወለደ ህጻን ሁሉ ይህቺን ሳይቀምስ ቀርቶ እንደማያውቅ ይናገራል።
አደራጀው በዚህ ዳቦ ሱስ ተይዞ ስለነበር ከእናት ከአባቱ ሳይቀር ሳንቲም እየወሰደ ገዝቶ ይመገባል። ከዚያ አልፎም እናት በአካባቢው ታዋቂ ስለነበሩ ሳንቲም ላኩልኝ ብላለች እያለ በመቀበል ዳቦና ከረሜላ በመግዛት ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ይበላ እንደነበር ያስታውሳል።
በተለይም የአንድ ቀኗ ተግባሩ እንዲህ ሲል ያስታውሳታል። “75 ሳንቲም ከጎረቤት ለእናቴ ሙገድ መግዢያ አምጣ ተብዬ ነው” ብሎ የተቀበለውና ዳቦውን ገዝቶ የበላበት ነው። እናም በወቅቱ አበዳሪዋ በበራፋቸው ላይ ያልፉ ስለነበር ለምን ሳንቲሙን እንደፈለጉት እናቲቱን ይጠይቃሉ። እናትም ይህንን እንዳላሉ ይገልጻሉ ልጃቸውን በመጥራት ይጠይቁታል።
እርሱም ገንዘቡን ማጥፋቱን ተናግሮ ከዚህም በፊት እንዲህ ያደርግ እንደነበር ያስረዳል። በጊዜው እናት በጣም ቢናደዱም ወዲያው አልመቱትም። ጎረቤታቸውን ይቅርታ ጠይቀው ከሰደዱ በኋላ ገላጋይ በሌለበት በበርበሬ ነበር ያጠኑት። ‹‹አለንጋዋም ብትሆን ዛሬ ድረስ ፊቴ ላይ አለች›› ይላል። ይሄ ነው በእንቁላሉ መቅጣት ማለት∷ ከዚያ በኋላ ግን ይህ ተግባር ቆመ፤ ከሰፈር ጓደኞቹ እንዳይገጥም በሚልም በቀጥታ ወደ ቄስ ትምህርት ቤት ተላከ። የግብረገብ ትምህርት መሰረታዊ ነገር ነውና ስርዓት ያለው ልጅ ሆኖ ማደጉን ይናገራል።
አደራጀው የመጀመሪያ ፍላጎቱ ካህን መሆን ነበርናም በቄስ ትምህርት ቤት መግባቱን ወዶታል። ግን ከጓደኞቹ መለየቱ ደግሞ በጊዜው በጣም አሳዝኖት ነበር። በእርግጥ ከዚህም ሌላ መሆን የሚፈልገው ጋዜጠኝነት ነው። ምክንያቱም ግጥም ይጽፋል፤ የንባብ ክህሎቱም በጣም የተዋጣለት ነው። ቀልድም ቢሆን በደቂቃዎች ውስጥ ፈጥሮ የማቅረብ አቅም አለው።
ከዚያም አልፎ ድምጹ ያምራልና ሚኒሚዲ ከእርሱ ውጪ ማንም ባያቀርብ ይባልለታል። የማንኛውንም ቋንቋ በትክክል በማዳመጥ ዳግመኛ በሚኒሚዲያ ትርጉሙን እንኳን ባያውቀው ከዜና ላይ አድምጦ ዜና ያቀርብ ነበር። በዚህም መምህራን ሳይቀሩ የሚያደንቁት ልጅ ነው። አብረውት ከሚማሩት ውስጥ በአማርኛ ንባብ የተሻለ መሆኑም ሌላ የልጅነት ምኞት እንዲኖረው አድርጎታል። ይህም የአማርኛ መምህር መሆን ነበር።
የዛሬው ዲያቆን አደራጀው ከሥራ የሚተርፈው ጊዜ ባይኖረውም ለደቂቃም ቢሆንም ጊዜውን ማሳለፍ የሚወደው ከትልልቅ ሰዎች ጋር ነው። በዚህም መካሪ፤ ሰዎችን አክባሪ፤ ዝምተኛና ታዛዥ ልጅ እንዲሆን አስችሎታል። ከዚያ ባለፈም ተጨዋችም አድርጎታል። ይህ ደግሞ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ከገባ በኋላ በተለያዩ መድረኮች ላይ ተዋናይና ግጥም አቅራቢ እንዲሁም የመድረክ መሪና ሌሎች ሥራዎችን እንዲሰራም ተመራጭ አድርጎታል።
በልጅነቱ በጨዋታ ብዙ ጊዜ አሳልፎ እንደማያውቅ የሚናገረው አደራጀው፤ ብዙ ጊዜውን የሚያሳልፈው የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት፤ ቤተሰቡን በቻለው መጠን በመደገፍ እንደሆነም አጫውቶናል። አደራጀው በሰፈር ልጆች ተወዳጅ ልጅ ነው። በዚህም ‹‹እያያ›› በሚል ቅጽል ስም ይጠሩታል። ለዚህ ስም መነሻቸው ደግሞ እርሱን ልክ እንደታላቅ ወንድማቸው አድርገው መውደዳቸው፤ ያላቸውን በብዛት መስማታቸውና እርሱን መከተላቸው ነው።
ብዙ ጊዜውን ቤተክርስትያንም በማሳለፉም ቄሴ የሚሉት ልጆች እንደነበሩ የሚያነሳው ባለታሪኩ፤ አደራጀውም የሚለው ስሙም በምክንያት እንደወጣለት ይናገራል። ደርግ ከገባ በኋላ እርሱ ሲወለድ ብዙ ነገሮች መደራጀትና መረጋጋት በመጀመራቸው አባቱ ሁሉ ነገር ፈርጁን ያዘ ሲሉ አደራጀው እንዳሉትም አጫውቶናል።
ችግር ያላቆመው ትምህርት በቄስ ትምህርቱ እስከ ዳዊት ደግሟል፤ ድቁናም ተምሯል። በዚህም እስከዛሬ ድረስ ከመጠሪያ ስሙ ፊት የሚቀመጠውን የማዕረግ መጠሪያ ዲያቆን የሚለውን ክህነት እንዲያገኝ ሆኗል። በተጨማሪም ፊደላትን ገና በልጅነቱ ልቅም አድርጎ እንዲያውቅ ረድቶታል። ከዚያ በቀጥታ ወደ ዘመናዊ ትምህርት የገባ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው ጻዲቁ ዮሐንስ ትምህርት ቤት ነው።
ዘጠኝና አስርን ለመማር ደግሞ እድገት ፈለግ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወይም በአካባቢው አጠራር አሸዋ ሜዳ የገባ ሲሆን፤ ጊዜ አግኝቶ በሚገባ ባያነብም በትምህርቱ ግን በጣም ጎበዝ ተማሪ ነበረ። ይህ ደግሞ በመምህራኑ፣ በተማሪዎቹም ሆነ በቤተሰቦቹ ልዩ አክብሮት እንዲሰጠው አድርጎታል። በተጨማሪም እስከ ኮሌጅ ድረስ አለቃና የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የክፍል አስተባባሪ እንዲሆንም አስችሎታል።
አደራጀው፤ ከአስረኛ ክፍል ነበር ወደ የሰርተፍኬት የመምህራን ስልጠና ‹‹ቲቲአይ›› የገባው። ምክንያቱ ደግሞ በዚያ እያለ ሥራ ሳይመርጥ እየሰራ ቤተሰቡን ይደጉም ነበር። እርሱ ያንን ማድረግ ካልቻለ ደግሞ ቤተሰቡ ባለበት ለመቀጠል ያዳግተዋል። አባት በደን ጥበቃ ብቻ የሚያገኙት ገቢ ቤተሰብን ሙሉ አድርጎ ለማስቀጠል እጅግ ከባድ ነው። ስለዚህም ከእኔ ምርጫ የቤተሰብ ይቅደም በሚል እስከ 12 መማርን ትቶ ደሴ ቲቲአይ ለመማር ተወዳደረ።
ውጤቱም መልካም ነበርና ተቀባይነቱን አገኘ። ይህንን ሲያደርግ ማንም አልደገፈውም። ምክንያቱም በመምህርነት ተቀጥሮ የሚሄድበት ቦታ ርቀት ይኖረዋል። እርሱ ደግሞ ያደገውም የተወለደውም ከተማ ስለሆነ አይወጣውም ብለው ስለሚያምኑ እንዲተወው አስገደዱት። ቢሆኑም በሀሳቡ የማይደራደረውና በአቋሙ የሚጸናው አቶ አደራጀው፤ ሀሳቡን አጽንቶ ለአንድ ዓመት በደሴ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ለመማር ጓዙን ጠቅልሎ ተነሳ። በዚያም በችግር ውስጥ ራሱን አሳልፎ ትምህርቱን ተከታትሎ ለምረቃ በቃ።
ሰርተፊኬቱን ይዞ ሥራ ከጀመረ በኋላም ቤተሰቡን እያገዘ መማሩን ያላቋረጠው አደራጀው፤ የፖሊሲና እስትራቴጂ ስልጠና ለወር ያህል ወስዶ ወደ ጃናሞራ ወረዳ መካነ ጽዮን ትምህርት ቤት ገባ። እዚያም እየሰራ ከሰርተፊኬት ለመውጣት ከ300 በለይ ኪሎ ሜትር እየተጓዘ ዲፕሎማ በርቀት ቅድስተማሪያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በቋንቋ ተምሮ አጠናቀቀ። ከዓመታት ቆይታ በኋላም የመጀመሪያ ዲግሪውን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በቋንቋ ትምህርት ተከታትሏል። ይህንንም ሲመረቅ መማርን አላቆመም። ይልቁንም በሌላ ዘርፍ ለመማር አድማስ ዩኒቨርሲቲ ተመዘገበ። በማኔጅመንት ትምህርትም ተመረቀ።
መማር የሚወደው አደራጀው፤ ከሁሉም ቦታ በከፍተኛ ውጤት ነበር የሚመረቀው። ይህ ደግሞ ሁሌም ተማር እንደሚያሰኘው ይናገራል። በዚህም ይመስላል ብዙ ዓመት ሳይፈጅ መንግስት እድሉን ስላመቻቸለት በስነጽሁፍ ትምህርት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪውን የያዘው። በጥቅሉ በኑሮ ፈተና ውስጥ ሆኖ ባለሁለት ዲግሪና ባለአንድ ማስተር የመሆኑ ምስጢርም ይህ ትምህርት ወዳድነት እንደሆነ ያስረዳል። አሁን እንደቀደመው ብዙ ፈተና ስለማይኖርበት መማርን እንደማያቆም ይናገራል።
ሥራ ወዳድነት አብዛኛው የልጅነት ዕድሜው በስራ ያሳለፈበት ነው። ኦቾሎኒና ከረሜላ በመሸጥም ነው ሥራ የተጀመረው። ርቀት ድረስ በመሄድ ደግሞ ወታደሮች የሰፈሩበት አካባቢ ላይ የሲጋራ ንግዱን ከትምህርት በኋላ ያጧጡፋል። ከዚያም አልፎ ሎተሪ ያዞራል። ግን የሚያገኘው ገንዘብ ብዙም አልነበረም።
እንደውም ለመጀመሪያ ጊዜ ለዚያውም ክረምት ላይ ቀን ሙሉ ሲሰራ ውሎ 200 ብር ነው ያገኘው። ይህ ደግሞ ሌሎች ሥራዎችን እንዲሰራ እንዳደረገው ይናገራል። ለአብነት ለእህቶቹ ካርቶን በካርቶን የሆነ አነስተኛ ሱቅ በበር ላይ የከፈተው በዚህ እንደነበር ያስታውሳል። ሆኖም ባላቸው ደግነት ብዛት አከሰሩት።
አደራጀው ሁሌ መስራት አንድ ቀን ከፍ ያደርጋል ብሎ ያምናል። እናም ቀኑን በጥናት ሳይሆን በሥራ ያሳልፋል። ስራ ሲባል ደግሞ እየመረጠ አይደለም። በእርሱ እምነት በሰው ላይ መጥፎ ነገር ማድረግ አይሁን እንጂ እኔን ከችግሬ ካነሳኝ የማልሰራው ስራ የለም ብሎ ያምናል። ስለዚህም ከኪሳራ በኋላ ራሱን ለማንሰራራት ሰዎች በብዛት በሚሰበሰቡበት ቦታ በመሄድ ሊስትሮ ይጠርጋል። ግን ትርፋማነቱ እምብዛም ነበር። እናም ከሦስት ወር በላይ በዚህ ሥራ ላይ አልቆየም።
‹‹ይህንን ሁሉ ስራ እንድሰራ ያደረገኝ የቤተሰቤ የኑሮ ሁኔታ ነው የሚለው ዲያቆን አራጀው፤ አባቱ የፓርክ ጠባቂ እናቱ ደግሞ የቤት እመቤት ናቸውና ቤቱ ብዙ ጊዜ ጎዶሎ ይሞላበታል። ስለዚህ በአባት ደመወዝ ብቻ የማይሞላውን ቤት ለመሙላት ሲል የማይሞክረው ሥራ እንዳሌለ ይናገራል። አደራጀው ስራ ወዳድ ያደረገው የአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ እንደነበርም ይናገራል። ምክንያቱም ለጉብኝት የሚመጣው የቱሪስት ብዛት በተለያየ መንገድ ገንዘብ እያገኘ ቤት እንዲሞላ አስችሎታል።
‹‹መቀመጥ መቆመጥ ነው›› ብሎ የሚያምነው ዲያቆን አደራጀው፤ ከቂጥህ መርፌ ተቀምጧል እንዴ እስኪባል ድረስ ይሰራ እንደነበር ያስታውሳል። በተለይ ምንም አይነት ሱስ የሌለበት በመሆኑ ያለውን ገንዘብ በአግባቡ እንዲጠቀም ረድቶታል። ለቤተሰቤ የሚለው ሀሳብ እንዲበረታም አግዞታል። አደራጀው ሎተሪ እያዞረ ብቻም አልነበረም፤ ሱቅ በደረቴም ሰርቷል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ብዙ እቃዎችን በአንድ ጊዜ ለመያዝ መቸገሩ ነው። ስለዚህ በካርቶን አድርጎ ሁሉንም በአንድ ላይ በመሰብሰብ አራዳን ብቻ ሳይሆን ገጠራማውንም ክፍል ይደርሳል።
ወገራ ወደሚባል ወረዳ በመሄድም እንቁላል በርካሽ ያመጣና ፋና ለሚባል መዝናኛ ክበብ ያከፋፍል እንደነበር የሚናገረው አደራጀው፤ ገቢው እየጨመረለት ሲሄድ ዶሮ ቤት ውስጥ ለማርባት ሞክሮ እንዳልተሳካለት ያስታውሳል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ እንብላውና እንሰጥሃለን የሚለው የቤተሰቡ ማታለያ ነበር።
የሎተሪ ውለታ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈጣን ሎተሪ በሚሸጥበት ጊዜ ብዙ ገንዘብ ማግኘት ችሎ ነበር ዲያቆን አደራጀው። እናም በዚህ ገንዘብ ስራዎቹን ማስፋት ጀመረ። መቆጠብና ለራሱ መማሪያም ማስቀመጥ የቻለው በሎተሪ ሽያጭ በመሆኑ ሎተሪ ለእኔ ባለውለታዬና ለዚህ ያበቃኝ ነው ይላል። ግን በሎተሪ ስራ መውጫው ቀን ሲደርስ ብዙዎቻችን እንጨነቅ የነበረውን ነገር መቼም አረሳውም ባይ ነው።
ምክንያቱም ካልተሸጠ ኪሳራ አለው። እናም ብዙ ጊዜ ጠጅና ሻይ ቤት እንዲሁም ጠላና ምግብ ቤቶች በመዘዋወር ለመጨረስ እንጥራለን። እንደውም ብዙ ጊዜ የምጠቀመው ዘዴም ነበረ። ፈጣኗን ወደሰዎች ፊት መወርወር። ከዚያ ይህማ የእኔ እድል ነው ይሉና ይገዙናል። እስከ አዘዞ ድረስ 12ኪሎ ሜትር በመጓዝ ይህ ተግባር ቀጥሏል።
ዲያቆን አደራጀው እነዚህን ስራዎች ብቻ አልነበረም እየሰራ የተማረው። የሆቴል አስተናጋጅም ሆኖ ሰርቶ ያውቃል። ለያውም ምሽት ቤቶች (ናይት ክለብ) ውስጥ። ይህንን እንዲያደርግ ያስገደደው ደግሞ የአባቱ ሞት ሲሆን፤ ትልልቅ ወንድሞቹ በቅርብ ባለመኖራቸው የተነሳ ግዴታ ቤቱን የመደገፉ ሁኔታ በእርሱ ጫንቃ ላይ አረፈ። በተጨማሪም እርሱም ቢሆን መማርና የበለጠ ለቤተሰቡ መድረስ አለበት። ስለዚህም ራሱንና ቤተሰቡን ከማስተዳደር ባለፈ ለትምህርት ቤት ወጪው ራሱ ሰርቶ ራሱ የመሸፈን ግዴታም አለበት።
በእርግጥ እናቱም ቢሆኑ ለስራ አልቦዘኑም። ጠላ እየሸጡ ቤቱን ይደጉማሉ። በጠላ ብቻ ማንን ከችግር አወጣ ብሎም የሆቴል መስተንግዶ በ47 ብር በወር እየተከፈለው ይሰራ ነበር። ምሽት ቤቶች ላይ ካሸር ሆኖ ሲሰራ ደግሞ ብዙ ችግሮችን ተጋፍጦ እንዳለፈም ይናገራል። ይህ ሁኔታው በጋውን ተሻግሮ ክረምት ወቅት ላይ ሲደርስ ይበልጥ ይጠነክራል። ራሱን በስራም ይወጥራል።
ግማሽ ቀን በሆቴል አስተናጋጅነት ከሰራ በኋላ፣ ከዚያ መልስ ለሚወደውና ውለታ ሰርቶልኛል የሚለውን ሎተሪ ማዞሩን ይቀጥላል። ከዚያ ሱቅ በደረቴውን፣ የቀረውን ደግሞ ለምሽት ቤት ካሸርነቱ እያዋለ በቀን 22 ሰዓት ያህል በስራ እንደሚያሳልፍ ያነሳል።
‹‹ የምሽት መዝናኛ ክለብ ትምህርት ቤቴ ነበር›› የሚለው እንግዳችን፤ ሰው እየጠጣና እየተደሰተ እኔ ደብተር ይዤ አጠና ነበር። ምክንያቱም እቤት ብሄድ ይህንን ማድረግ አልችልም። እናም ሰክሮ የሚደበድበኝና መጠጥ እላዬ ላይ የሚደፋብኝ ብዙ ነበር። በማይመለከተኝ ሁሉ ለምን አላስተናገድከኝም ብሎ የሚጣላኝ እንዲሁ ይበዛል። ግን አላማ አለኝና አይረብሸኝም። አሁን ብዙ ነገር ባይም አዲስ ነገር መስሎ አይሰማኝም።
አደራጀው ከዚያም ሲወጣም ማረፍን አይፈልግም። የጥበቃ ስራም ይሰራ ነበር። ሱቆቻቸውን እየጠበቀ፤ ትምህርቱን እያጠና እንዲሁም ወቅታዊ ነገሮችን በየጊዜው እየተከታተለ ከስራ ራሱን ሳይነጥል ይውላል፤ ያድራል።
ማህበራዊ ሃላፊነት ጃናሞራ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰርተፍኬት ተመርቆ በመካነ ጺዮን ትምህርት ቤት በሀላፊ መምህርነት በተመደበበት ወቅት ነበር ማህበራዊ ሃላፊነት እንዳለበት አምኖ መስራት የጀመረው። ትምህርት ቤቱ በ1974 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን፤ ተማሪው ብዙ ቢሆንም ክፍሉ ግን ሁለት ብቻ ነበር። እናም ይህ ያሰቀቀው ባለታሪኩ፤ ማህበረሰቡን በማስተባበር ክፍሎች እንዲበዙ ከማድረጉም በተጨማሪ ለመምህራንም የሚሆን ቤት ማሰራት ችሏል።
አደራጀው ይህ ባህሪው ህዝብ ወዳድነትንአጎናጽፎት እንደነበር ያነሳል። በዚህም ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ሊለቅ ሲል ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ እንዳይለቅብን ብሎ በማመልከቱ አስቀርቶታል። ከዚያ በሦስተኛ ዓመቱ ከትምህርት ቤቱ በእርሱ ምርጫ ሳይሆን በትምህርት መምሪያው አማካኝነት ወደ ‹‹አሰንዳ›› የሚባል ትምህርት ቤት ተቀየረ።
በዚያም ቢሆን መስራትን የሚወደው እንግዳችን ይህንኑ ተግባሩን አስቀጠለ። በአንድ ወር ውስጥም ወንዝ ዳር የነበረ ትምህርት ቤት ከነበረበት ቦታም አስነስቶ ቀበሌ ገበሬ ማህበሩ አካባቢ እንዲቀርብ ካደረገ በኋላ በተሻለ ሁኔታ እንዲገነባ ማህበረሰቡን አስተባበረ።
ይህንን ሥራውን ያየው የወረዳው የትምህርት መምሪያ አሁንም ከወር በኋላ አንስቶ ዛቅልጣ የሚባል ቀበሌ እንዲሰራ መደበው። በዚህም ሁለት ተጨማሪ ክፍል እንዲሁም ስድስት ክፍል የመምህራን መጠለያ በህብረተሰብ ተሳትፎ ካሰራ በኋላ ተነሳ። ድብል የሚባል ቦታም ተወሰደ።
አሁንም ማህበረሰብ ማገልገል ተግባሩ የሆነው እንግዳችን፤ እንደ ዛቅልጣው ሁሉ እዚህም ያንኑ ሥራውን ደገመው። ግን በቦታው ብዙ መቆየት የለበትም የወደቁትን ማንሳት ይኖርበታል ብሎ የሚያምነው ትምህርት መምሪያው አሁንም አንስቶ ወደሌላ ሥፍራ ቀየረው። እዚህም እንደዚያው እያደረገ በመቀጠሉ የበለጠ ይጠቅመናል በሚል የአመራርነት ስልጠና እንዲወስድ ወደ ብርሸለቆ ተላከ።
ከስልጠና በኋላ ግን በመምህርነት ሳይሆን የወረዳው የህዝብ ተሳትፎ አደረጃጀት ምክትል አማካሪ በማድረግ ወረዳው ላይ ነው የተቀመጠው። ከሁለት ዓመት የስራ ቆይታ በኋላ ደግሞ ወደ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በሙያ ዘርፍ የቱሪዝም ልማትና ፕሮሞሽን ኦፊሰር ሆኖ ተቀጠረ። በዚህም ደረስጌ ማሪያምና መሰል ቅርሶች እንዲተዋወቁና ጥገና እንዲደረግላቸው በማድረግ ዙሪያ ብዙ ስራዎችን መስራት ቻለ። ቀጣይም ወደ ጎንደር ተወስዶ በዚሁ ዘርፍ መስራት ቀጠለ። እርሱም ሙያውን ወዶት በዚሁ ዘርፍ ላይ እየሰራ ይገኛል።
ሽልማት ከማህበረሰብ ጀምሮ የምስጋናና የምስክር ወረቀቶች በየጊዜው እንደሚሰጡ የሚናገረው አቶ አደራጀው፤ ለእኔ ልዩ ሽልማቶቼ ሦስት ናቸው ይላል። በክላስተር ብዙ ስራዎችን በመስራቱ ምርጥ ሰራተኛ በሚል በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አማካኝነት ሳምሶናይት ቦርሳና የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል። ዞን መምሪያ ባህልና ቱሪዝምም እንዲሁ ኮከብ ሰራተኛ በሚል በተደጋጋሚ እስካሁን ድረስም ሞባይል ሲሸልመው ቆይቷል።
ቤተሰብ ኖሮ መጋባት መልካም ቢሆንም ሳይኖር መጋባት ግን እንደሀጢያት መቆጠር አለበት ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ኑሮ የተሻለ የሚሆነው ምንግዜም በስራ ሲደገፍ ነው። እናም እኔም ባለቤቴን ስመርጣት ሀብትና ንብረቷን አይቼ አልነበረም። ሰርተን ቤታችንን እንሞላዋለን ብዬ ስላሰብኩ።
በእርግጥ ይህም ቢሆን የድሃ ቤተሰብ ልጅ አልነበረችም። መስራትና መለወጥም የምትወድ ናት። እናም ይህ ባህሪዋ ተመችቶኛል። በተመሳሳይ ስልጣነ ክህነቴን ትጠብቅልኛለች ብዬ ያመንኳት ስለሆነች ምርጫዬ ሆናለች ይላል የባለቤቱን አመራረጥ ሲያነሳ።
በስራ ላይ እያለ ብዙ የሚቀርባቸው ሴቶች ነበሩ፤ ከእርሱ ጋር እንዲሆን የሚመርጡትም እንዲሁ። እናቱም ቢሆኑ በአንድ በኩል የእከሌ ዘር ጥሩ ነው ይሉት ነበር። ግን እርሱ ዓይኑ ያረፈባት እርሷ ብቻ ነች። ይህ ደግሞ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ይላል። ትውውቃቸው በአበልጁ አማካኝነት ነው። እናም ዛሬ የአንድ ሴትና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ለመሆን በቅቷል።
መልዕክት ከዲያቆን አደረጃው ‹‹የሰው ልጅ በስራ እንጂ በሌላ መፈተን አለበት ብዬ አላምንም። ወጣት ሆኖ የሚለምን በጣም ያናድደኛል። ምክንያቱም ጉልበትና አቅሙ አለው። የማይሰራ ደግሞ ማደግም መለወጥም አይችልም። ስለዚህ ሰዎች ከእኔ ቢወስዱ ብዬ የማስበው ስራ ሳይንቁ መስራትን ነው። የስራ ተነሳሽነት ትልቅ ቦታ እንደሚያደርስ መማር ቢችሉ መልክም እድል ይገጥማቸዋል›› የሚለው ዲያቆን አደራጀው፤ ለእኔ የወረደ አስተሳሰብ እንጂ የወረደ የሚባል ስራ የለም የሚል እምነት አለው። እናም የወረደ በሚል እንዳንወርድ ስራ አንናቅ ይላል።
‹‹እኔ አሁንም ውጤታማ ነኝ፤ የተሻለ ደረጃ ደርሻለሁ ብዬ አላምንም። ለማህበረሰቡም ያለኝን ያህል አገልግያለሁ የሚል እምነት የለኝም። ብዙ መስራት ይጠበቅብኛል›› የሚለው እንግዳችን፤ መድረስ ካለብን ደረጃ ላይ ለመድረስ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል።
ቁርጠኛና ለራሳችን ታማኝ መሆንም ይጠበቅብናል። ተስፋ ሳይቆርጡ ለእኔ ብቻ እኖራለሁ ሳይሉ የምንኖረው ለእኛ ነው በሚል መስራት መቻልም ከሁሉም በላይ ያስፈልጋል ምክሩ ነው። እኛም ብዙ ከመናገር መማር ይቅደም ነውና ነገሩ ከጥቂቱ ሀሳቦቹ ብዙ ውሰዱ በማለት ለዛሬ በዚህ አበቃን። ሰላም!!
አዲስ ዘመን መስከረም 11/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው