
በኦሮሚያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ይከበራል
አዲስ አበባ፡- የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን የብሄር ጥላቻንና መካረርን በማስቀረት ህገ መንግሥቱን በአከበረ መልኩ እንዲከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ። 14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ እንደሚከበር ተገለጸ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ትናንት በአምባሳደር ሆቴል ባደረገው የዕቅድ ውይይት ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም እንዳሉት 14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው።
የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ህገ መንግሥቱ በፀደቀ በ25ኛ ዓመት የሚከበር መሆኑ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል ያሉት ወ/ሮ ኬሪያ የብሄር ጥላቻንና መካረርን በማስቀረት ህገ መንግሥቱን ባከበረ መልኩ መከበር እንዳለበት አሳስበዋል።
በአመለካከት ልዩነቶች ሳቢያ በሚፈጠሩ ችግሮች ህዝብ ሰለባ እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት አፈ ጉባኤዋ በዓሉ ይህንንና መሰል ችግሮችን ለማስቀረት በሚያስችል መልኩ መከበር እንደሚኖርበት ገልጸዋል።ከዚህ ቀደም በተከበሩ አስራ አንድ የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል አስፈላጊነት ዙሪያ ጥናት መደረጉን የገለጹት ወይዘሮ ኬሪያ የጥናቱ ድምር ውጤት “በማንነታችን ሳንሸማቀቅ በአደባባይ እንድናከብር ያደረገን በዓል ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” የሚል እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ሌላኛው በውይይቱም ከተነሱ ጉዳዮች መካካል 13ተኛውን የብሔር ብሔረሰብ እና ህዝቦች ቀን በዓል አካበበርን በመገምገምና ጠንካራ እና ደካማ ጎኑን በመለየት ለ14ተኛ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን እንደ ግብዓት ለመጠቀም በሚል ሀሳቦች በውይይት ተስተናግደዋል፡፡
በተጨማሪ ለውይይት ከቀረበው ሀሳብ አንዱ የመሪ ቃል አማራጮች ሲሆን ይህም ህገ መንግስታችን ለሰላም እና ለአገራዊ አንድነት ፣የህግ የበላይነት ለዘላቂያዊ ሰላምና ለአገራዊ አንድነት እንዲሁም ህገ መንግስታዊ ቃል ኪዳን ለዘላቂያዊ ሰላማችን ሲሆን በቀረቡት የመሪ ቃል ምርጫ ላይ በተወያዮቹም ሀሳብ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ሆኖም ግን ስምምነት ላይ ባለመደረሱ የመሪቃል መረጣው ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በውይይት መድረኩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ህዳር 29ቀን 2012 ዓ.ም በሚከበረው 14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ዝግጅት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የዘንድሮው 14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ህገ መንግስታዊ መከበር እና ሀገራዊ አንድነትን ታሳቢ አድርጎ እንደሚከበርም ተናግረዋል። አፈጉባኤዋ አክለው እንዳሉት የተሰጣቸው ጊዜ አጭር በመሆኑ እና ስፖንስር ማፈላለግ ስላልቻሉ ለክልሉ ምክር ቤት በማቅረብ ለበዓሉ የሚሆን በጀት እንደተፈቀደላቸውም ጨምረው ገልጸዋል።
13ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በብዝሀነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ መከበሩ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ ም
አብርሃም ተወልደ