ባህላዊ እሴቶች በትምህርት ስርዓት ውስጥ ተካተው አለመሰጠታቸው መጤ ባህሎች እንዲስፋፉ፣ መከባበርና መቻቻል እንዲጠፋ፣ ሀገራዊ አንድነት እንዲላላና የጋራ እሴቶች እየተመናመኑ እንዲሄዱ በር ከፍቷል። በመሆኑም ችግሩ እንዳይቀጥል ሀገራዊ እሴቶችን በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ በማካተት ከአውሮፓውያኑ የትምህርት ስርዓት ጋር አጣምሮ ማስተማር እንደሚያስፈልግ ምሁራን ይናገራሉ።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ የታሪክና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አብዱ መሀመድ እንደሚናገሩት፤ መልካም አስተዳደር ከመልካም አስተሳሰብ ይመነጫል፣ መልካም አስተሳሰብ ደግሞ ከመልካም ሰው። ስለዚህ መልካም ሰውን ለማፍራት መልካም በሆነ በባህል እሴት የተገነባ ስርዓተ ትምህርት ያስፈልጋልና አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ይህንን አካቶ መስጠት ይገባል። እስካሁን ይህ ባለመሆኑ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አፍሪካም ጭምር እየተወቀሰች መሆኑን ያነሳሉ።
አፍሪካም ሆነች ኢትዮጵያ የራሷ ባህል ፣ወግና ማንነት የሚታይበት የትምህርት ሥርዓት የላቸውም። ይህ ደግሞ የአውሮፓውያኑ የትምህርት ሥርዓት ተገዢ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው የሚያነሱት ዶክተር አብዱ፣ አገሪቱ ባህላዊ እሴቷን በስርዓተ ትምህርት አካታ እያስተማረች አለመሄዷ በአመለካከትም ሆነ በሌሎች ተግባራት የአውሮፓውያን አስተሳሰብ አራማጅ አድርገዋታል።
ባህላዊ እሴቶች ተትተው ትኩረት ለአውሮፓውያን የእውቀት ቅመራ ሆኗል። ከባህል እሴቶች ያፈነገጠ ስርዓት እንዲገነባም እድል አመቻችተዋል። ስለዚህ በትምህርት ስርዓት ውስጥ ባህላዊ እሴቶቻችንን አካተን እናስተምር የሚለው ሀሳብ የዘገየ ቢሆንም መተግበሩ ይጠቅማል ይላሉ።
እንደ ዶክተር አብዱ ገለጻ፤ ከቅኝ ግዛት ትምህርት ለመላቀቅ፣ በማህበረሰብ መካከል የነበረውን የመከባበርና መቻቻል መገለጫ ወደ ነበረበት ለመመለስ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም እውቀት እንጂ ሁከት ፈጣሪ እንዳይሆኑ ለማስቻል ባህላዊ እሴቶች በትምህርት ስርዓት ውስጥ አካቶ መስጠት ያስፈልጋል።ይህም የአስተሳሰብና የሞራል ድህነትን ለማጥፋት ይጠቅማል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሶሾሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ካንሲቴ ዴለቦ በዶክተር አብዱ ሀሳብ ይስማማሉ። አንድ ማህበረሰብ የሚሰራው የሚገለጸው በባህላዊ እሴቱ ነውና አሁን ባለው ደረጃ በውጪ ባህል መሰራቱ የሰው አገር እንጂ የአገርን ባህልና ታሪክ የሚያውቅ ትውልድ እንዳይፈጠር አድርጓል። በመሆኑም ባህላዊ እሴት በትምህርት ውስጥ ማካተቱ ለነገ መባል የለበትም ይላሉ።
ባህላዊ እሴት ከማህበራዊ እሴት ግንባታ ባሻገር የሚታዩ ናቸው። ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ፖለቲካን ለመገንባት፣ ሰላምን ለማረጋገጥ ወዘተ የማይተካ ሚና አላቸው። ነገር ግን እኩልነት፣ ዴሞክራሲ፣ ነጻነትና መሰል ነገሮች ጀማሪዎቹ ብንሆንም ከእኔ የውጪው ይበልጣል በሚል መርህ ከትምህርት ስርዓታችን ጀምሮ የውጪ ናፋቂነት ተጠናውቶናል ። ይህ ደግሞ በአስተሳሰብ ቀኝ እንድንገዛ እንዳደረገ ይናገራሉ።
“ከባህላዊ እሴቶች መካከል የገዳ ስርዓት አንዱ ነው፣የገዳ ስርዓት ዴሞክራሲዊ አስተዳደር፣ እርቅ ፣መግባባትና ተከባብሮ መኖርን ወዘተ ይይዛል” የሚሉት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫላ አዎታ ናቸው። እንደነዚህ አይነት ባህላዊ እሴቶች በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ቢካተቱ ተማሪዎች በጉዳዮቹ ዙሪያ ሰፊ እውቀት እንዲጨብጡ ያስችላል። ይህ ደግሞ መቻቻል፣ መከባበር፣ ችግር ሲፈጠር በውይይትና በእርቅ መፍታት የተለመደ እንዲሆን ያደርጋልና ጊዜ አይሰጠው ይላሉ።
ለአገሪቱ ሰላምና ዕድገት መምጣት የራሱ የሆነ ጉልህ ሚና የሚጫወት ከባህላዊ እሴት ውጪ ምንም ሊሆን እንደማይችል የሚናገሩት ዶክተር ጫላ፤ በስርዓተ ትምህርቱ ዙሪያ መምህራንን ብቻ ሳይሆን ስለገዳ የተመራመሩና የጻፉ እንዲተቹት ተደርጎ ‹ኢንትሮዳክሽን ኢን ቱ ገዳ ሲስተም›› የሚል ኮርስ በ2012 ለተማሪዎች ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም ‹‹የአገር በቀል እውቀት›› በሚል አንድ የትምህርት ኮርስ የተለያዩ ባህላዊ እሴቶች እንደሚሰጡ የሚያነሱት አቶ ካንሲቴ፤ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ከተለያየ አካባቢ የመጡ በመሆናቸው እነዚህ ትምህርቶች ያስፈልጓቸዋል። ለዚህ ደግሞ አዲሱ ፍኖተካርታ መልካም ጅማሮ ነው። ነገር ግን በዚህ መቆም እንደሌለበትና ባህላዊ እሴቶች እንደየአካባቢው ሁኔታ እየታዩ በትምህርት ስርዓት ውስጥ ሊካተት እንደሚገባ ይናገራሉ።
ባህላዊ እሴቶችን መጠበቅ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ካንሲቴ፤ችግር ሲገጥም ብቻ ለማስታወስ መነሳት ሳይሆን ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲያመጡ ማድረግ ላይ መሰራት አለበት ይላሉ። ምን አለን የሚለውን ማለየትና ወደ ተግባር መግባት እንደሚገባም ያስረዳሉ።
ሰዎች መጀመሪያ የራሳቸውን አካባቢ ማወቅ ሲችሉ ነው አገርን ከዚያም ዓለምን ሊያውቁ የሚችሉት የሚሉት ደግሞ ዶክተር ጫላ ናቸው። አሁን በአገሪቱ እየተደረገ ያለው ዓለምን ማሳወቅ እንጂ አገርን ማሳወቅ አይደለም። ስለሆነም ባህላዊ እሴቶችን በትምህርት ስርዓት ውስጥ በማካተት እያንዳንዱ ዜጋ ስለ አካባቢውና አገሩ እንዲያውቅ ማድረግ እንደሚገባ ይገልጻሉ።
ባህላዊ እሴቶች በትምህርት ስርዓት ውስጥ ተካተው እንዲሰጡ መንግሥት የመጀመሪያውን ኃላፊነት ይውሰድ ቢባልም የሚተገብረው አካል ከሌለ አሁንም ችግሩ ይቀጥላል። ስለሆነም ቤተእምነቶች ለእምነቱ ተከታዮች ማስተማር፣ወላጆችም በኢትዮጵያዊነት ባህላዊ እሴት የተገነባ ልጅን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። ማህበራትም ባህላዊ እሴቶችን ሊያጎሉ የሚችሉ ተግባራትን መከወን እንዳለባቸው ይናገራሉ።
አሁን እያጋጨን ያለው የባህሪ ድህነት እንጂ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ችግር ብቻ አይደለም። በመሆኑም ከእስካሁኑ ተምሮ ችግሩን ለመንቀል መስራት ያስፈልጋል። ለዚህም ከታችኛው ክፍል ጀምሮ ብሔሩ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነቱ እየተነገረው እንዲያድግ የትምህርት ስርዓት ውስጥ ባህላዊ እሴቶችን አካቶ ማስተማር ሁነኛ መፍትሄ እንደሆነ ያነሳሉ።
ዶክተር አብዱ ደግሞ፤ ለኢትዮጵያ ችግር ኢትዮጵያዊ መፍትሄ ማበጀት ፤ በባህላዊ እሴት የተቃኘ የትምህርት ስርዓት መፍጠር ያስፈልጋል። ባህላዊ እሴቶች ልዩነትን እንደሚያጠቡ፤ የሀሳብ የበላይነትን እንደሚያሰፉ፤ ለመወያየት ጊዜ እንደሚሰጡ አምኖ በመቀበል ወደሥራ መግባት መቻል አለበት። ሊሂቃኑ ከማስተማር መማር ይቅደምን መተግበር አለባቸው።
አስተማሪው መጀመሪያ የሚያስተምረውን ተረድቶ ትኩረት ለባህላዊ እሴቶቻችን መስጠት ከቻለ ደካማ ተማሪ አይኖርም። ይህ ደግሞ ባህላዊ እሴቶቻችን ያመጣሉ ተብሎ የሚታሰበውን ጠቀሜታ ግብ እንዲመታ ያደርጋል የሚሉት ዶክተር አብዱ፤ አርዓያ የሚሆኑ መምህራንም በየዘርፉ ሊፈጠሩ እንደሚገባ ይናገራሉ።
ባህል ተለዋዋጭ ነውና ከጊዜው ጋር አብሮ መለወጥ ስለሚገባም አገራዊ የባህል አቢዮትን በዲጅታል የባህል እሴት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ። የዜግነት ትምህርት በቴክኖሎጂ አማካኝነት መማር፣ ስለ አገር ነባራዊ ሁኔታም መረዳትና ባህልን አዲሱ የባህል ህይወት መርህ ማድረግ እንደሚገባም ያስረዳሉ።
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የግብረገብ ትምህርት እያንዳንዱ ልጅ ይማራል። ስለኢትዮጵያዊ ባህልና ስርዓትም በሚገባ እየተነገረው ዩኒቨርሲቲ ይደርሳል። ሆኖም የሃይማኖታዊ ትምህርት ነው በሚል በደርግ የፖለቲካ ርዕዮት ውድቅ ሆኖ ሥነምግባሩ ዝቅ ያለ ዜጋ ተገነባ። ባህላዊ እሴቶች ኋላ ቀር ናቸው መባልም ጀመሩ። በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ ወደባህላችን እንመልከት የሚለው ቢመጣም ከስም ያለፈ እንዳይደለ ዶክተር አብዱ ይናገራሉ።
ሦስቱም ምሁራን እንደሚሉት፤ ባህላዊ እሴቶች በትምህርት ስርዓት ውስጥ ማካተት ካልተቻለ ዜጎች ማንነታቸውን፣ አካባቢያቸውን፣ አገራቸውን ሳያውቁ ያድጋሉ። ዓለምን የመረዳታቸው ምጣኔም ይቀንሳል። የሌሎች አገራት ባህል አራማጅም ይሆናሉ። ዜጋ ጠፋ ማለት ደግሞ አገር እንደ አገር የመቀጠሏ ሁኔታ አጠያያቂ ይሆናል።
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ ም
ጽጌረዳ ጫንያለው