አዲስ አበባ፡- የመስቀል በዓል እአአ በ2013
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሳይንስ የትምህርትና የባህል ማዕከል (ዩኔስኮ ) በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበ ጀምሮ የቱሪስት ፍሰቱ
ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ የህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ተወካዩ አቶ ታሪኩ ነጋሽ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት መስከረም ወር በኢትዮጵያ ብዙ ቱሪስት የሚገኝበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተለይ በመስቀል በዓል ላይ የሚገኘው የቱሪስት ብዛት ከዓመት ዓመት ከፍ እያለ መጥቷል።
” የመስቀል በዓል ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል ከመመዝገቡ በፊት የቱሪስት ብዛቱ ብዙም አልነበረም” ያሉት አቶ ታሪኩ ለአብነትም እአአ በ2011 ላይ 183ሺ 800 እንዲሁም በ 2012 ላይ 191ሺ417 እንደነበር አስታውሰዋል። እኤአ 2013 የመስቀል በዓል የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ከተመዘገበ በኋላ ግን የቱሪስት ፍሰቱ በየዓመቱ እድገት ማሳየቱን አቶ ታሪኩ ጠቅሰው፤ በዓሉ በተመዘገበበት ዓመት የገባው ቱሪስት ብዛት 231ሺ 586 ሲሆን፤ በዓመቱ 268 ሺ 944 ደርሷል። በ2015 ደግሞ የቱሪስት ብዛቱ 298ሺ357 ነበር። ይሄው የቱሪስት ፍሰት እያደገ ሄዶም አአአ በ2016 ላይ 325ሺ 501 ወደ አገር ውስጥ ገብቷል። በ2017 ደግሞ 432ሺህ687 ከፍ ማለቱን ተናግረዋል። ይሁንና በ2018 በተለይ በአገሪቱ በነበረው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ቁጥሩ ወደ 384ሺ 615 ወርዷል። አሁንም ቢሆን ግን በቱሪዝሙ ዘርፍ ከፍተኛ የመንግስት ቁርጠኝነት በመኖሩ ከፍታውን ሊያስቀይረው እንደማይችል ገልጸዋል።
እንደ አቶ ታሪኩ ገለጻ፤ የመንግስት ቁርጠኝነት የቱሪስት ብዛቱን ብቻ ሳይሆን የቆይታ ጊዜንም ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የሌላ አገር ዜጎች አዲስ አበባን ሳይረግጡ እንዳያልፉና አንድ ቀን በአዲስ አበባ ቆይታቸው ተደስተው ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ሄደው እንዲጎበኙና የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ እድል የሚሰጥ ስራ ይሰራል፡፡ ሌላ ጊዜም መጥተው አገሪቱን በሚገባ እንዲያዩ ጉጉት ያሳድርባቸዋል፡፡
አዲስ አበባ ላይ የሚያርፍ ማንኛውም ቱሪስት እንዲደሰትና የቆይታ ጊዜውን እንዲያራዝም ለማድረግ እየተሰሩ ያሉት ሥራዎችም ከመንግስት ቁርጠኝነት የመነጩ መሆናቸውን የሚያነሱት አቶ ታሪኩ፤ የቤተመንግስቱ ለጎብኝዎች ክፍት መሆን፣ የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክትና ሌሎች ተግባራት አገሪቱ በቱሪዝም የምታገኘውን ገቢዋን እንድታሳድግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
ያለ ቱሪዝም ጥቅል የአገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ እንደማይቻል ጠቅሰው ከቤተመንግስት ጀምሮ ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩም ለዚህ ነው ብለዋል። አሁን ያለው የቱሪስት ፍሰት እድገት የበለጠ ለመስራት የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸው እያንዳንዱ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የሚሰሩ አካላት ይህንን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ወደ ውጤት መቀየር ላይ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ ም
ጽጌረዳ ጫንያለው