• የቤት ኪራይ አበል 18 ሺ ብር ሆነ
• የማይመልሱት የእጅ ተንቀሳቃሽ ስልክ እና ላፕቶፕ ኮምፒዩተር ተፈቀደላቸው
• መመሪያው ከነሀሴ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ የሚሆን ነው
አዲስ አበባ ፡- ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በየወሩ አሥራ ስምንት ሺ ብር የቤት ኪራይ አበል እንዲከፈላቸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወሰነ። በሌሎች ጥቅማጥቅሞች ላይ ማሻሻያ ያደረገ ሲሆን የማሻሻያ መመሪያው ከነሀሴ አንድ ቀን 2011 ዓ/ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።
የከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ለመወሰን ህዳር አንድ ቀን 1997 ዓ.ም የወጣውን መመሪያ ለማሻሻል የወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መመሪያ መሰረት የቤት ኪራይ አበል የሚከፈላቸው ከፍተኛ ኃላፊዎች መንግሥት የመኖሪያ ቤት ማቅረብ ካልቻለ ኃላፊው ቤት እስኪሰጠው ድረስ በየወሩ 18 ሺ ብር የሚከፈለው ይሆናል።
መንግሥት መኖሪያ ቤት ያልሰጣቸው ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች የቤት ኪራይ የሚከፈላቸው በየመስሪያ ቤቱ በጀት ተይዞለት መሆኑን የሚያብራራው መመሪያው ባልና ሚስት ሁለቱም ባለስልጣናት ከሆኑ ግን ጥቅሙ የሚሰጠው ለአንደኛው አካል ብቻ መሆኑን አመልክቷል።
ለከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ለሚመደብ ተሽከርካሪ ፍጆታ የሚውል በወር 245 ሊትር ናፍጣ ወይም 200 ሊትር ቤንዚን መሆኑን መመሪያው ጠቅሶ ለቤተሰብ ለሚመደብ ተሽከርካሪ ደግሞ 200 ሊትር ቤንዚን የሚሰጣቸው መሆኑ ተገልጿል። እንዲሁም ኃላፊው መኪናውን በአቅራቢያው የማያሳድር ከሆነም ተሽከርካሪውን ለማሳደር እና ኃላፊውን ለማምጣት የሚኖረውን ርቀት ታሳቢ በማድረግ ተጨማሪ ነዳጅ የመስሪያ ቤቱ ኃላፊ መፍቀድ የሚችል መሆኑን መመሪያው አመልክቷል።
ኃላፊው ለመኖሪያ ቤቱ ለሚጠቀመው ስልክ በየወሩ እስከ 200 ብር የስልክ ወጪ የሚከፈለው መሆኑን የጠቀሰው መመሪያው ለተንቀሳቃሽ ስልክ ለሚደረግ ግንኙነት የሚያስፈልግ የስልክ አገልግሎት ወጪ ከመስሪያ ቤቱ በመረጃ ተደግፎ በሚቀርብ ጥናት ለገንዘብ ሚኒስቴር በማቅረብ ማስወሰን የሚቻል መሆኑ ተብራርቷል። እንዲሁም የመንግሥት ኃላፊው ለሥራ የሚጠቀምበት ተመላሽ የማይሆን ተንቀሳቃሽ ስልክ እና ላፕቶፕ ኮምፒዩተር በመስሪያ ቤቱ ለአንድ ጊዜ ተገዝቶ የሚሰጠው መሆኑንም አስታውቋል።
የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ማለት ሚኒስትር፣ ሚኒስትር ዴኤታ፣ጠቅላይ አቃቤ ህግና ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ፣ ኮሚሽነርና ምክትል ኮሚሽነር፣ ዋና ዳይሬክተር እና ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤና ምክትል አፈጉባኤ እንዲሁም በእነዚህ ደረጃ የተሾሙ የበላይ ኃላፊዎች በጥቅማጥቅም መመሪያው የሚካተቱ መሆናቸው ተጠቅሷል።
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ ም
አልማዝ አያሌው