እሁድ መስከረም 27 ቀን 2010 ዓ.ም የላሊበላ (ላልይበላ) ከተማ በተቆጡ ሰልፈኞች ተጥለቀለቀች። ሰልፈኞቹ ከያዙዋቸው መፈክሮች መካከል
“ታሪክ መስራት ካልቻልን ታሪክ እንጠብቅ!”፣
«ታሪክና ቅርስ እየፈረሰ አዲስ ታሪክ አይሰራም!»… የሚሉ ይገኙበት ነበር።
የላሊበላ ሕዝብ ጥያቄ ለአደጋ የተጋለጠው ታላቅ ቅርሱን በተመለከተ የመንግሥት ዝምታንና መለሳለስን ለመስበር ያለመ ነበር። በእርግጥም ጥያቄው በመንግሥት መሰማቱ የታወቀው እንደዋዛ በአንድ ጀምበር ነበር። ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ባለፈው ዓመት ለሥራ ጉብኝት ወደፈረንሳይ ባቀኑበት አጋጣሚ የሥልጣን ብቻ ሳይሆን የዕድሜ እኩያቸውን ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮንን አንድ ውለታ እንዲሰሩላቸው ተማጸኑ። ተማጽኖውም ለአደጋ የተጋለጠውን የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ጥገና ወጪ ፈረንሳይ ትሸፍን ዘንድ የሚጠይቅ ነበር። ጠ/ሚኒስትር ዐብይ በአንድ ወቅት “ለምኜ ይሳካልኛል” እንዳሉት ይህም ተሳካና ስምምነት ተገኘ።
እነሆ በፈረንሳዊያን የሙያና የገንዘብ እገዛ የላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስትያናትን ከአደጋ ለመታደግና ለመጠበቅ የሚያስችለው ፕሮጀክት መጀመሩ ሰሞኑን በይፋ ተበሰረ።
የፈረንሳይ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር የተመራው የልኡካን ቡድን በያዝነው ሳምንት በላሊበላ ጉብኝት አድርጓል። ለልኡካን ቡድኑ ከዚህ በፊት ስለተደረጉ ጥገናዎችና ስለ ወቅታዊ የቤተ- ክርስቲያናቱ ሁኔታም በባለሙያዎች ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል።
በሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ በዘርፉ የተለያዩ ባለሙያዎችን ያካተተ ልኡክም ወደ ኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ይመጣል። ይህም በቤተክርትያናቱ ላይ ያሉ ጉዳቶችንና የሚያስፈልጋቸውን ጥገና የመለየት ስራ የሚሰራበት የመጀመሪያው ክፍል እንደሚሆን ተጠቁሟል።
ስለላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ጥቂት ነጥቦች
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት በ12ኛው ክፍለ ዘመን በንጉስ ላሊበላ እንደተገነባ ይነገራል። ከአንድ ድንጋይ ተፈልፍለው የተሰሩ 11 ውቅር አብያተ ክርስትያናት በላሊበላ ይገኛሉ። ጎብኚዎች የአለምን የህንፃ ጥበብ ከፍ ያደረገ ሲሉ ይገልጹታል፤ ምክንያታቸው ደግሞ የውቅር ፍልፍል አብያተ ክርስቲያኑ የግንባታ ሂደቱ ከላይ ወደታች መሆኑ ነው።
የኢትዮጵያን ጥንታዊ የምህንድስና ጥበብ ያሳየ ነው ይሉታል፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን።
የላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስትያናትን ከአለት በመፈልፈል ያነፃቸው ከ11ዱ የዛጉዬ ነገስታት አንዱ የሆነው ቅዱስ ላሊበላ /1120 – 1197 ዓ.ም/ ነው። እነዚህ በአሰራር ጥበባቸው ዓለምን ያስደመሙና በመንፈሳዊ መዓዛ የተሞሉ አብያተ ክርስትያናት፤ ከኢትዮጵያን የጥበብ መኩሪያ እና ሃብትነት ባሻገር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በ1979 ዓ.ም የአለም ቅርስ ሆነው ተመዝግበዋል።
የቅዱስ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስትያናት፡- ቤተ ማሪያም፣ ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ ደናግል፣ ቤተ መስቀል፣ ቤተ ደብረሲና፣ ቤተ ጎለጎታ፣ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ አባ ሊባኖስ፣ ቤተ መርቆሬዎስ፣ ቤተ ገብርኤል ወሩፋኤል፣ ቤተ ጊዮርጊስ የተሰኙ ቤተ ክርሰትያናትን ይዟል። ቤተ ደብረሲና አልፎ አልፎ ቤተ ሚካኤል በመባል ይጠራል። የቅዱስ ላሊበላ መካነ መቃብር የሚገኘውም በዚሁ በቤተ ደብረሲና ነው። ይሄ ቤተክርስትያን ከቤተ ጎለጎታ ጋር ተያይዞ የታነፀም በመሆኑ (Twin Churches) ቤተ ሚካኤል ወጎለጎታ ተብሎ እንደ አንድ ስለሚቆጠር የላሊበላ አብያተ ክርስትያናት ቁጥር 10 ናቸው የሚልም አስተያየት አለ።
ቤተ ማሪያም የቅዱስ ላሊበላ የመጀመሪያ ስራ ስትሆን ታህሳስ 29 የልደት በዓልም በዚች ቤተክርስትያን ነው በድምቀት የሚከበረው። ቤተ መድኃኔዓለም በመጠን ከሁሉም የሚበልጥ እና “አፍሮ አይገባ” የተባለው መስቀል የሚገኝበት ነው። ቤተ ጊዮርጊስ የሚባለው ደግሞ በመስቀል ቅርፅ የታነፀ እና ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ ረቂቅ የኪነ ህንፃ ጥበብ የተከናወነበት ነው። ቅዱስ ላሊበላ እነዚህን አብያተ ክርስትያናት ለማነፅ ከ22 – 30 ዓመታት ፈጅቶበታል ይባላል።
ከ1512 – 1518 ኢትዮጵያን የጎበኘው የፖርቹጋል ቄስ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ /ላሊበላን የጎበኘ የመጀመሪያው አውሮፓዊ/ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “ስለ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስትያናት ስራዎች ብዙ ብፅፍ የሚያምነኝ ሰው መኖሩ በጣም ያሳስበኛል፤ያስጨንቀኛል። እስካሁን ያልኩትንም እንኳን ቢሆን “ውሸት ነው” የሚሉኝ። ነገር ግን የፃፍኩት በሙሉ እውነት ለመሆኑ በኃያሉ እግዚአብሔር ስም እምላለሁ። እንዲያውም ከዚህ በላይ ማለት ይቻላል። ሆኖም በቀጣፊነት ስሜ እንደማይነሳ ተስፋ አደርጋለሁ። ”
በላሊበላ ፍልፍል ዓብያተ-ክርስትያናት ላይ የተከሰቱ ችግሮች
የላሊበላ ፍልፍል አብያተ-ክርስትያናት ከስምንት ምዕተ ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ እንደመሆናቸው በቆዩበት ዘመን ለተለያዩ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ አደጋም የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ በመሆኑ በቅርሶቹ ላይ መጠነኛ ጉዳት መስተዋሉ አልቀረም።
ከቅርሱ እድሜ አንጻር በቅርሱ ላይ የተለያዩ ጉዳቶች መታየት የጀመሩበት ትክክለኛ ወቅት ባይታወቅም የጎርፍ ፍሳሽ፣ የዝናብ ፍሳሽ፣ የጸሐይ፣ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ፣ የመሬት እንቅስቃሴ፣ ወዘተ. ተደማምሮ በቅርሶች ላይ የመሰንጠቅ እና ሌሎች ጉዳቶች ተስተውለውበታል።
ይባስ ብሎ በሀገራችን ባለው ቅርሶችን የመጠገን ልምድ አናሳ መሆን እና መሰል ተያያዥ ምክንያቶች ቅርሶች የከፋ ጉዳት ሳይደርስባቸው ለመታደግ ተጨማሪ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በቅርሶች ላይ እየተስተዋለ ያለው ጉዳት ከጊዜ ጊዜ እየከፋ በመምጣቱ ችግሩ በግልጽ በሚታይ ደረጃ ደርሷል።
የጥገናና እንክብካቤ ሥራዎች
ቅርሶቹ እየደረሰባቸው ካለው ችግር ለመታደግ የተሰሩ ስራዎችን በተመለከተ አርክቴክት ሳንድሮ አንጀሊኒ /Sandro Angelini/ እ.ኤ.አ. ከ1967 – 1970 ከሰራው በፊት ስለተሰሩ የጥበቃ እና እንክብካቤ ስራዎች የሚገልጽ የተጻፈ ሰነድ የለም።
ሆኖም ግን አንዳንድ የንድፍና የፎቶ መረጃዎች በቅርሶች ላይ የጥበቃና እንክብካቤ ስራዎች እንደተሰሩ የሚጠቁሙ መረጃዎች አልታጡም። ለምሳሌ፡-እ.ኤ.አ በ1880 ዓ.ም. በቤተ- አባ ሊባኖስ ላይ በዓለም አቀፉ ሞኑመንት ፈንድ እና በኢትዮጵያ የላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት ጥበቃና እንክብካቤ ኮሚቴ አማካይነት የጥገናና እንክብካቤ ስራዎች እንደተሰሩ አመላካች መረጃዎች ተገኝተዋል።
እ.ኤ.አ. ከ1920 እስከ 1958 ዓ.ም. የጽሑፍ ማስረጃዎችን ማግኘት ባይቻልም የተለያዩ የጥገናና እንክብካቤ ስራዎች እንደተሰሩ አመላካች መረጃዎች አሉ።
በዚህ ጊዜ የተሰሩ ስራዎች በዋናነት በዝናብ ወቅት ሰርጎ የሚገባውን ውኃ ለመከላከል የተሰሩ ሲሆኑ በጥናት ላይ ተመስርቶ በጥንቃቄ እንዳልተሰራ የተጠቀሙበት ቁስ ይጠቁማል።
እ.ኤ.አ. በ1920 ዓ.ም. አረብ /Arab/ በተባለ ምናልባትም የግብጽ ተቋራጭ በጣራዎች ላይ የጥገና ስራዎች እንደተሰሩ የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ።
በዚህ የጥገና ስራ የተካተቱትም ቤተ-ማሪያም፣ ቤተ- አማኑኤል፣ ቤተ-ጎልጎታ እና ቤተ-ደናግል ነበሩ።
እ.ኤ.አ. ከ1958-1959 ዓ.ም. በMinistry of Public Works አማካኝነት ሰባስቲያኖ ኮንሶሊ /Sebastiano Consoli/ በተባለ ኢንተርፕራይዝ የጥገና ስራዎች እንደተሰሩ የሚያመላክቱ መረጃዎች ተገኝተዋል።
ሌላውና በጥገናና እንክብካቤ ስራው ስለተሰራው ስራ የተሟላ የጽሑፍ ማስረጃ ዝርዝር ሪፖርት ተሰንዶ የተገኘበት እ.ኤ.አ. ከ1967 እስከ 1970 ዓ.ም. በዓለም አቀፉ ሞኑመንት ፈንድ እና በኢትዮጵያ የላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት ጥበቃና እንክብካቤ ኮሚቴ አማካይነት በአርክቴክት ሳንድሮ አንጀሊኒ የተሰራው ሠፊ የጥገናና እንክብካቤ ስራ ነው።
ይህ የጥገናና እንክብካቤ ስራ ለመጀመሪያ ጊዜ የአብያተ- ክርስቲያናቱ ስትራክቸራል ችግሮች የተለዩበት ስራ ነበር።
የዚህ ጥገናና እንክብካቤ ፕሮጀክት ዋና ዓላማ የነበረውም አብያተ-ክርስቲያናቱ መጀመሪያ ወደነበሩበት ሁናቴ ለመመለስ ያለመና ከዚህ ቀደም በተሰሩ የእንክብካቤና ጥገና ስራዎች በዓለቶቹ ላይ የተጨመሩ በዓድ ቁሶችን ማስወገድንም ያካተተ ነው።
የፕሮጀክቱን ይዘት በተመለከተ አንጀሊኒ እራሱ እንዲህ ሲል በሪፖርቱ አካትቷል፤ ““…The guiding principle of this preservation effort is to safeguard the churches from further deterioration, remove false additions and to re-establish where aesthetically permitted the monolithic form and character that they once had …”
በአጠቃላይ በሳንድሮ አንጀሊኒ የተሰራው የጥገናና እንክብካቤ ስራ በሁሉም የላሊበላ ፍልፍል አብያተ-ክርስቲያናት ላይ የታየውን የመሰንጠቅ ችግርና የስትራክቸር እንቅስቃሴ የብረትና የመስታወት “ፊሸር ሜትር” በመጠቀም ጥቅል የሆነ ዳሰሳ የተሰራበት ነው።
እ.ኤ.አ. በ1986 ዓ.ም. ለቤተ-ማሪያም ጊዜያዊ መከላከያ ጣራ እንዲሰራለት ተደርጎ የነበረ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩም እ.ኤ.አ. በ1993 ዓ.ም. ለቤተ-አማኑኤልም ተሰርቶለታል።
ሌላው በላሊበላ ፍልፍል አብያተ-ክርስትያናት ላይ የተሰራው የጥበቃና እንክብካቤ ስራ ዛሬ ላይ በአምስቱ አብያተ- ክርስትያናት ላይ የምናያቸው አራት ጊዜያዊ የጣራ ከለላዎች ናቸው።
እነዚህ ጊዜያዊ ጣራዎች /Temporary Shelters/ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ባለው የትብብር ፖሊሲ አማካኝነት የአውሮፓ ህብረት በለገሰው የገንዘብ ድጋፍ የተሰሩ ናቸው።
ጊዜያዊ ጣራዎቹ የተሰሩት ለቤተ-ማርያም፣ ቤተ-መስቀል፣ ቤተ-መድኃኒዓለም፣ ቤተ-አማኑኤልና ቤተ-አባ ሊባኖስ ነው።
ጊዜአዊ ጣራዎቹ እንዲሰራላቸው የተደረጉትም በዝናብ ወቅት በቀጥታ በሚገባው የዝናብ ፍሳሽ ምክንያት በእጅጉ ለጉዳት ተዳርገው የነበሩ በመሆኑ ነው።
ጣራዎቹ የተሰሩትም በአብያተ-ክርስትያናቱ ስትራክቸርና በአካባቢው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት በማያደርስ እና መልሶ ለማንሳት በሚያመች መልኩ በተጠና ሁኔታ ነው።
ወደ ግንባታው ለመግባት የነበሩት ሂደቶች እንደተጠበቁ ሆኖ የጣራዎቹ ግንባታ እ.ኤ.አ. February 2007 ተጀምሮ February 2009 ዓ.ም. ማለትም ከሁለት ዓመታት በኋላ ተጠናቋል።
የጊዜያዊ ጣራዎቹ ግንባታ በሂደት ላይ ሳለ የዓለም ሞኑመንት ፈንድ እ.ኤ.አ. በ2008 ዓ.ም. ግምገማ ያደረገበት ሲሆን ከግንባታ በኋላም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመሬት ሳይንስ ት/ቤት በዶ/ር አስፋወሰን አስራት እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ተቋም በዶ/ር ኢሳያስ ገብረዮሐንስ በ2014 ዓ.ም. የክትትልና ግምገማ ስራ ተከናውኗል።
በቅርብ ጊዜ የተከናወነው የጥገናና እንክብካቤ ስራ የተከናወነው በቤተ-ገብርኤል-ሩፋኤል ላይ ነው። ይህ የጥገናና እንክብካቤ ስራ የተሰራው በሁለት ምእራፎች ማለትም በዝግጅት ምእራፍና በትግበራ ምእራፍ ነው። የዝግጅት ምእራፉ እ.ኤ.አ. ከ2009 ዓ.ም እስከ 2013 ዓ.ም. ሲሆን በዚህ ምእራፍ የተሰራውን የጥናት ስራ ዩኔስኮና የዓለም ሞኑመንት ፈንድ ሲመሩት የፋይናንስ ምንጩ የተገኘው ከኖርዌይ መንግስትና ከዊልሰን ቻሌንጅስ ፈንድ ነው።
የፕሮጀክቱ ትግበራ ምእራፉ የተከናወነው ደግሞ እ.ኤ.አ. ከሴፕቴምበር 2012 ዓ.ም. እስከ ዲሴምበር 2015 ዓ.ም. ዩኔስኮ እና ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በነደፉት የጥገና እቅድ መሰረት ሲሆን ለትግበራ ምእራፉ የገንዘብ ድጋፍ የተገኘው ደግሞ ከአሜሪካ አምባሳደር ፈንድ ነበር።
እንደመሰናበቻ
በላሊበላ አብያተ ክርስትያናት መጠለያ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። እንደሚታወቀው መጠለያው የተከለለው በጊዜ ገደብ ነው። ይህ የጊዜ ገደቡ ካበቃ አመታት ተቆጥረዋል። በወቅቱ መጠለያው ጥሩ ጥቅም ሰጥቶ ሊሆን ይችላል፤ አሁን ግን ጉዳት ነው እየፈጠረ ያለው። ቅርሱ ከ10 ዓመታት በላይ ፀሐይና ዝናብ ሳያገኘው በመጠለያ የቆየ ነው። አሁን በድንገት መጠለያው ተነስቶ ለፀሐይና ለዝናብ ቢጋለጥ ጉዳት ማጋጠሙ አይቀርም። ስለዚህ ተገቢ ጥናት እና ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
ላሊበላ ልዩ ቅርስ ነው። ዛሬም አገልግሎት ያልተቋረጠበት ህያው ቅርስ ነው። በሙዚየም የተቀመጠ አይደለም። በሮቹ ላለፉት 800 ዓመታት እየተከፈቱ እየተዘጉ ነው። ለ800 ዓመታት የሰው እጅ ነክቶታል። እንደ ሌሎች በክብር የተቀመጡ ቅርሶች አይደለም ላሊበላ። አንዴ ከእጅ ከወጣ አይገኝም። ህዝቡም ሰላማዊ ሰልፍ የወጣው ለዚህ ነው። ለላሊበላ ህዝብ ቅርሱ እንጀራው ነው። ኑሮው ነው። የላሊበላ ቅርስ ለላሊበላ ህዝብ እስትንፋሱ ነው።
ይህን እስትንፋስ ለማስቀጠል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ብርታት የፈረንሳዮች ወደላሊበላ መምጣት ለቅርሱ ትንሳዔ መልካም ብስራት ሆኗል። ማን ያውቃል?!…በቅርቡ ደግሞ እድሳቱ ተጠናቅቆ እነዚያ በቁጣ ለሰልፍ አደባባይ የወጡ አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞችና እህቶች እንደገና ለምስጋና አደባባይ ይወጡ ይሆናል። (ማጣቀሻዎች፡- ህብር ኢትዮጵያ፣ ኢቲቪ፣ አማራ መገናኛ ብዙሃን፣ አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ ቢቢሲ አማርኛ…)
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 10/2012
ፍሬው አበበ