የሰው ልጅ ህይወት በጊዜ የተቀመረ ነው። ይህንን ጊዜ በሚገባ ለመጠቀም የተዘጋጀ ሰውም ዘመኑን በሥርዓት ዋጅቶ ይጠቀምበታል። የተገዛ ጊዜም፣ የተወጠነ ይፈፀምበታል፤ ውጤት ይለካበታል፤ አሰራር ይመዘንበታል፤ አያያዝ ይታይበታል። ድክመትና ጥንካሬ ይፈተሽበታል።
ይህንን ደግሞ በወጣትነት ዘመን ነቅተው ሲጓዙበት ለኋለኛው ብቻ ሳይሆን ላሉበት ዘመን ጠቃሚነቱ አያጠያይቅም። መልካም መልካሙን ፍሬ ለማጨድ ይጠቀሙበታል፤ በመልካም መንገድም በጊዜ ውስጥ ይጓዙበታል።
ታዲያ፣ መልካም ወጣቶች፣ ደስታቸውን ፍለጋ በጣላቸው ነገር ላይ የሚይደገፉ፣ የሚፈልጉትን መልካም ለማግኘት በማንም ላይ የማይደነፉ፣ ከራሳቸው ይልቅ በሌላ እጅ የደስታቸውን ቁልፍ የማያስቀምጡ፣ ለመልካምነት የሚሯሯጡ ባለብሩህ አእምሮ ናቸው።
ስለዚህ በትናንት ማንነታቸው ሳይሆን ዛሬ ባለው እውነትና እምነት ለመጓዝ ነው የሚነሱት። ዛሬን የሚዋጅና ዛሬን የሚያደንቅ ሰው፣ ለነገ ማሰቡ አጠያያቂ አይደለም።
ሁልጊዜ እንደምለውና ስናገረውም መልካም ነገር ወደውስጤ የሚፈስሰው፣ ነገን አስቦ መስራት ዛሬን በአስደናቂ ሁኔታ መፈጸም ነው። እንዲያውም የዛሬ መልካም ጅማሬ የነገ ግማሽ ፍፃሜ ነው።
አንድ መሐንዲስ መሬት ላይ የሚያውለውን የግንባታ ሥራ ክፍሎች በሚገባ ከነደፈ በኋላ፣ ግንባታው ሲጀመር ምን የት ጋ፣ እንደሚያርፍና ግንባታው ተቀጣጥሎ ወደተፈለገው ግብ እንደሚደርስ ያውቃል። ለዚህ እያንዳንዱን ብረት፣ እያንዳንዱን ኩንታል ሲሚንቶ፣ እያንዳንዱን ኪሎ ሚስማር፣ እያዳንዱን የሰው ኃይል፤ እያንዳንዱን የግንባታ ቁስ ጥንካሬና ዘላቂነት በሥርዓት በማጤን ሁሉም ሀብት ለተገቢው ዓላማ መዋሉን በማረጋገጥ ያሰራዋል፤ ያከናውነዋል።
ነገውን ወረቀቱ ላይ ጽፎና ዝርዝር አፈጻጸሙን አስቀምጦ ስለተነሳ ለማከናወን ሲፈልግ ከመሰረት እስከላይኛው ግንባታ ድረስ በቅርብ አፈፃፀሙን ይከታተላል።
በትውልድ ላይ የምንሰራው ሥራ ሁለገብ የመሆኑን ያክል በጊዜ ውስጥ የተለካ ነው። የትናንት አባቶቻችን ዘመን የፈቀደውን ሁሉ አድርገውና እንዳቅማቸው አከናውነው ሃገር አስረክበውናል። የእነርሱ ሚና የጸናችና በዓለምአቀፍ ደረጃ ዳር ድንበሯ የተከበረ፣ ሉዓላዊነቷ የታወቀች ሃገር ከመሰረታዊ እውቀት ጋር ማስረከብ ነበረ፤ አድርገውታል።
ቀጣዮቹ አባቶች መሬት ላይ ከምንሰራው ሥራ ይልቅ በአእምሮ ላይ የሚሰራውን ሥራ ትኩረት በማድረግ ያለፉትን አርባ አምስት ዓመታት አሳልፈናል። አሁን በ30ኛው የእድሜ ጠገግ ውስጥ እና ከዚያ በታች ላሉት የሰራናቸውን ሥራዎች ስናስብ ከመንገድና የኃይል አቅርቦት እድገት ውጭ የሚያመረቃ ሥራ ተሰርቷል ማለት አይቻልም ።
የዘመኑ የመንፈስ ወረራ አባቶችን በወቀሳ ማሳነስ ነው። ገበሬውን መሬቱን ነጥቀው፣ ማሳውን ዘርፈው፣ ለስቃይ አሳልፈውት፣ እጁን ቆርጠውት፣ ጡት “እንትን” አድርገው የሚሉ ትርክቶች እያሰማንና እያስወገዝን የረባ ሃሳብ ትውልዱ ውስጥ ሳንጨምር ትናንትን ዛሬ እንድንኖር በማድረግ ላይ ስንባዝን ኖረናል።
ድርጊቱ ተፈጸመም አልተፈጸመም፤ መለኪያው ዘመኑ ነበር መሆን ያለበት። በጊዜ ውስጥ ያልተለካ እይታ ሸውራራ ነው። ይልቅ በዲሞክራሲያዊ አገዛዝና “ፍትህ ለሁሉም” በሚባልበት ዘመን ላይ እስር ቤቶችን የምድር ሲዖል ያደረጉ በዳይ ወንድሞቻችንን እና ታላላቆቻችንን እንውቀስ። እርሱም ሲበዛ ደግሞ “የሞኝ ዘፈን ሁሌ አበባዬ” እንዳይይመስልብን እሰጋለሁ።
“ያለፈውን ጊዜ ሳስታምመው ፣
እህህን ብቻ ነው፤ የማተርፈው።” እንዲል ገጣሚው ።
ስለበደሉት፣ ስላሰቃዩትና እንደ (“ኦሽዊትዝና ዳቻው” የሂትለር የአይሁድ ማሰቃያ ስፍራዎች ናቸው) እንስሳ አድርገው ወንድሜን ስላኮላሹት ሰዎች ሳስብ የሚያመኝን ያህል ስቃዩን እሽሩሩ ካልኩት ግን፣ ወደነገ እንዳልራመድ ወደፊት እንዳልጓዝ፣ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ የለውም። የተፈፀሙት ግፎች ለታሪክ እይታ ተቀምጠው ወደ ነገ ለመስፈንጠር በእርቅ መንፈስ መነሳት ነው፤ ያለብን።
ይቅርታ ከምድራዊ የሥጋ ፍላጎት ከፍ ማለትና የረቀቀ ሰማያዊነት ነው፤ እግዚአብሔር ብዙዎቻችን ይቅር ብሎ በምህረት እጁ የማይገባንን ሰጥቶን እንጂ ቆሞ የሚያስኬድ ንጽህና ስላለን አይደለም፤ የኖርነው። ስለዚህ ይቅርታ ስናደርግ የበለጠ ይቅር የምንለው ራሳችንን ነው። ይቅርታ ያደረግንለት ሰው ይቅር አልነውም አላልነውም እውነተኛ ስሜቱን እና ትርጉሙን አንረዳም።
ወደዛሬዎቹ ወጣቶችም ስንመጣ፣ እርስ በእርሳችሁ ይቅር መባባላችሁ እናም የፍቅር ሰዎች መሆናችሁ ጊዜያችሁን ፣በሚገባ ለመጠቀም ከመርዳቱም ሌላ አቅም አባካኝ ከሆነ ድርጊትም መታቀባችሁ ድንቅ ነው። ምክንያቱም ያ፣ ጉልበት፣ ያ፣ አቅም ለዛሬ መልካምና በጎ ተግባራት ይውላልና። የትናንቶቹ ልጆች፣ ዛሬ እናንተ የሌሎችን ተናጣቂና አስጨናቂ፣ ተደባዳቢና ጎረቤትና ሰፈር አንገብጋቢ ሳትሆኑ የምትመላለሱበት መንገድ ተናፋቂ የምትነኩት ሥራ አንጸባራቂ፣ ለሌላው አርዓያ የሚሆንና የምታስመኩ ነው የሚሆነው።
ማንም ቢሆን ዛሬ ወሮባላዎች፣ በሰው ሥቃይ ተደሳቾችና የወንድማችሁን ቅስም ሰባሪ፣ የወላጆቻችሁን ሥም በክፉ አስጠሪ አያደርጋችሁም። ይልቅስ በመልካም ህይወታችሁ የታረማችሁ፣ ጉልበታችሁ ለበጎነት የተገራ፣ ሚዛናዊ አስተሳሰባችሁ መሪያችሁ የሆነ፣ የጎረቤት መከታ፣ የሰፈር አለኝታ፣ የአካባቢያችሁ የምርጥነት ሀሌታ ናችሁ።
ስለዚህ ትናንትን ሊያኖራችሁ የሚፈልግ ግብዝ እንኳን ቢኖር የምንኖረው ዛሬን ነው፤ ብላችሁ ነው የምትመልሱለት። የምንኖረው ለነገ ነው በሉት፤ አዎ፣ እንኳንስ ነገና ከርሞን፣ የሚቀጥለው አፍታ ሰዓት በውስጡ ስለሚያመጣው ነገር ደንታ አልነበራችሁም፣ አሁን ግን ነገ የሚያሳስባችሁ፣ መጪው ሰዓት የሚቆረቁራችሁ ዘላለማዊነት የሚናፍቃችሁ፣ ወድቃችሁ የነበራችሁበትን ዝቅጠት የተገነዘባችሁ ምርጦች ሆናችኋል። ምክንያቱም ዘመናችሁ በይቅርታ መዓዛ ታውዷልና። ማንም በትናንት ሰብዕናችሁ ሊጎትታችሁ ቢፈልግ አትጎተቱለት።
አሁን፣ ክፋትን ስትተውትና መንደር- ገነንነታችሁ ሲከስም ጋባዣችሁ ሊበዛ፣ ውድቀታችሁን ለማፋጠን አስመሳይ ድግሶች እዚህም እዛም ሊደገስላችሁ ይችላል፤ አሁን ግን ትናንትን አልኖርም፤ ከትናንቴ የተማርኩትን የድካም መከራ ዛሬዬ ላይ አምጥቼ እርምጃዬን በገዛ እጄ የምገታ ሰው አይደለሁም በሏቸው፤ ጨፈቃ ቆርጠው ሰው ላይ እንጨፍር ለሚሏችሁ የደሃ አጥር እንጠርበት በሏቸው። ግንዲላ ጎትተው እየፈለጥክ ሰው ፍለጥበት ለሚሏችሁ ፣ ጠርቡን የአረጋውያን ቤት እንጠግንበት ብላችሁ መልሱላቸው።
ወደ አፍሪካ ደቡብ አቅጣጫ፣ ደቡብ አፍሪካን የስደት መዳረሻ ለማድረግ፣ ወደሰሜን አቅጣጫ አውሮፓና አሜሪካንን የስደቱ ማብቂያ ለማድረግ፤ ዓይና አውጣ ባሪያ ፈንጋዮች (የስደት ደላሎች) ምቹ ምድር በአፋር፣ በሆሳዕና በሰሜን ጎንደር መውጫ፣ የሚርመሰመሱበትና፣ ሰው ከሐገሩ ይልቅ ባዕድ አምላኪ፣ ዕድገቱን ከበለፀጉት ሰፈር ናፋቂ እንዲሆንና በስደት ትልልፍ ላይ ህይወቱን ለበረሐ ጊንጥ፣ ለንዳድ ረመጥና ለኩላሊት ሽያጭ እንዲያውለውም ለማድረግ የሚሰራባቸው ስፍራዎች ናቸው።
ይሁንናም ትናንትን እንኑር ካላልን ዛሬ ይሄ አይደገምም፤ ትናንትን የሙጥኝ ካላልን ዛሬ ይሄን በትውልዱ ልብ ላይ አንጭንም። የተሻገርን እኛ፣ ያሻገርን እኛ፣ ያስተላለፍን እኛ፣ ከየምስራቹ ይልቅ መርዶ ነጋሪ እኛ የሆንበት ይሄ አካሄድ ማብቃት አለበት።
እኛ ወጣቶቻችን በክብር ወጥተው በፍቅር እንዲመለሱ እንጂ እንደ ወንጀለኛ ወጥተው እንደውሻ ደማቸው ደመ-ከልብ ሆኖ የሚቀርበት አዙሪት እንዲያበቃ ነው፤ መሻት ያለብን።
መፀለይ ካለብን፣ ለስደት ስኬት እንጸልይ፤ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለንግድና ለተግባቦት፣ ስኬት ሳንታክት እንፀልይ፤ ለብሔራዊ እርቅና ፍቅር፣ ለህዝብ ተዋህዶና ተዋድዶ መኖር፣ እንጂ ትናንትን በህመም እያሰብን ዛሬን እያጠፋን ለመኖር፤ የደላላ ፀሎት አንፀልይ፤ ይህን መሰሉ ፀሎት ለግለሰቡም ለሐገርም አይበጅም።
ልብ ለምትሉ ወጣቶች ትናንት በህይወታችሁ ምዕራፍ ላይ የተጻፈ መጽሐፍ ነው፤ ትናንትን መኖር አይገባችሁም አልናችሁ እንጂ ከትናንት ክፉና ደካማ የሕይወት ገጽ አትማሩም አታነቡም አላልንም። እንዲያውም ትናንት የዛሬ ኑሯችሁ ምርጥ መማሪያ ነው፣ ይሁንናም እያፈራችሁ የምትሸማቀቁበት የገልቱዎች ገመድ ግን አይደለም።
እናንት የዛሬ ወጣቶችም፣ ያንን ስታደርጉም፣ በመልካምነት ዛሬ ስትነሱ፣ ሃገር የተነሳችባቸውን ክብሯን የማስጠበቅ እርምጃዎች ለማስቀጠል የምትነሱ ብሩካን እንጂ ተሽመድምዳችሁ የምትወድቁ ተስፋ ቢሶች አትሆኑም ።
በሃገሬ ወጣቶች ተስፋ አለን፣ ትናንት በተሰበረ ህይወት በተመላለሳችሁ የዛሬዎቹ መልካም ወጣቶች ብርቱ ተስፋ አለን። ምክንያቱም የሚናፍቃችሁ ክፋት፣ የሚያምራችሁ ጡዘት፣ የምትንሰፈሰፉለት የትናንት ጉዳት የለም። ከቀረም የቀረባችሁ፣ የቀረላችሁ ነገር ነው!!
ትናንትን ያልተማረበት ሰው ዛሬም የሚደግመው እርሱኑ ነው፤ ማንም ሰው በምድር ላይ የሚያመነጨው አዲስ ክፋት የለም፤ ክፋት አዙሪት ነው። ደግሜ እላችኋለሁ። ሐሜቱ ትናንት የጣፈጠለት የመሰለው ሰው ዛሬን የሚደግመው በአዙሪትነት ነው። ነፍስ ማጥፋት በሉት፣ ዝርፊያ በሉት፣ አመንዝራነት፣ ጥላቻ፣ ሰብቅ፣ መልኮቹና ስያሜዎቹ ቀየር እያሉ መጡ እንጂ፣ የተሰራ ኃጢያት ሁሉ በኦሪትም ዘመን ነበረ፤ ዛሬም አለ። የተለወጠ ሰብዕና ብቻ ነው፤ እነዚህን እርኩሰቶች የማይደግመው።
በየትኛውም ሥፍራ ላይ ሁኑና ይህንን እስቲ አስቡ፤ ለዛሬ ካቀድኩት ምን ሰራሁ? ከትናንት የቀረኝ ምን ነበረ? ለነገ ላሳልፈውስ የማይገባ ምንድነው ብላችሁ ጠይቁና ራሳችሁን ታዘቡ።
ከማንኛውም ሰው፣ የምንረከበው ነገር የእኛ ብቻ እንደሆነ ከቶውን አናስብ፣ ዛሬ ብንወስድም ነገ ሰጪዎች ልንሆን እንደሚገባን እንዘጋጅ። ከመቀበል ይልቅ ሰጭነትን የሚያስብ ልብ ይኑረን። ሰውን ምን ይገድለዋል? ቢባል “ለእኔ ብቻ “ ማለቱ ነው የሚባለው፤ አለምክንያት አይደለም። ስለዚህ አንዳች እውቀት ስትጨብጡ፣ ለታናናሾቻችሁ፣ ለሚመጣው ትውልድ አሻራ ማንጠሪያ እንጂ ለራሳችሁ ብቻ እንዳልሆነ አስቡ።
ዛሬ ወደ ነገ ራዕይ የመድረሻ ድልድይ ነው፤ “ጊዜህን ጨፍርበት”፤ “ጊዜሽን (ውበትሽን) ተጠቀሚበት” ፣ እንደሚሉት የወረተኞች ምክር ጊዜያችንን ተጠቅመን የምንጥለው ተራ የክብሪት ቀፎ ሳይሆን የትውልድ ጅረት መሸጋገሪያ የከበረ ድልድይ ነውና፤ ድልድዩን በስጦታዎቻችን እንገንባ።
የኢትዮጵያን ትናንት፣ ለዛሬ መነሻ፣ ለነገ መድረሻ እንድናደርገው ምኞቴ ነው፤ አበቃሁ፤ እስከሳምንት መልካም ሳምንት ይሁንላችሁ!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 10/2012
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ