
አዲስ አበባ፡- በመንግሥት ተቋማት እና በአገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የልማት ስራዎች ላይ ህብረተሰቡ ክትትል እያደረገ ጥብቅ የማህበራዊ ተጠያቂነት ስራውን እንዲያጠናክር ተጠየቀ።
የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ሦስተኛ ምዕራፍን መጀመር አስመልክቶ ትናንትና በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ ሲካሄድ ከተለያዩ አካባቢዎች የተገኙ የማህበራዊ ተጠያቂነት የህብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም የአቅም ማጎልበት ኤክስፐርት ወይዘሮ መስከረም ግርማ እንደገለጹት፤ ማንኛውም አካል አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት ከህብረተሰቡ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ ማህበራዊ ተጠያቂነትን ማጠናከር ያስፈልጋል። ትግበራ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ሦስትም በመላ ኢትዮጵያ በሚገኙ 300 ወረዳዎች ላይ እየተተገበረ ይገኛል።
እንደ ወይዘሮ መስከረም ገለጻ፤ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ደግሞ የወረዳዎቹን ቁጥር 500 በማድረግ ህብረተሰቡ በአካባቢው ስለሚከናወኑ የልማት ስራዎች እና አገልግሎቶች መሻሻል ተገቢውን ጥያቄ እንዲነሳ ህብረተሰቡ ላይ ይሰራል። የማህበራዊ ተጠያቂነትን በወረዳዎቹ በማሳደግ የአገልግሎቶች ማሻሻል፣ የመረጃ ተደራሽነት፣ የገጽ ለገጽ ውይይቶች እና ህብረተሰቡ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን የአገልግሎት ማሻሻያዎች ላይ እንዲሳተፉ ይደረጋል።
በተለይ መሰረታዊ በሚባሉ አምስት ዘርፎች ማለትም በውሃ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና እና የገጠር መንገድ ዘርፎች ላይ የህብረተሰቡ ፍላጎቶች እና ስራዎች ስለመጣጣማቸው በየጊዜው ውይይቶች በማድረግ የማስተካከያ ሃሳቦች እንዲነሱ ፕሮጀክቱ ዓላማ አድርጓል።
ከዚህ በተጨማሪ ፕሮጀክቱ ግጭት በሚነሳባቸው አካባቢዎች የአገልግሎት መጓደል እና የመሰረተ ልማት ውድመት ሲያጋጥም ህብረተሰቡ በምን መልኩ አገልግሎት ማግኘት አለበት በሚሉ ጉዳዮች ላይ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ ይከናወናል።
በኦሮሚያ ክልል ጅማ አርጆ አካባቢ የማህበረሰብ አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ተወካይ የሆኑት መምህርት አልማዝ የበላይእሸት እንደገለጹት፤ በመንገድ፣ በውሃ ፣ በጤና እና በተለያዩ ዘርፎች የሚከናወኑ ግንባታዎችን በተመለከተ የማህበራዊ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ህብረተሰቡ የበለጠ ጥያቄ ማንሳት አለበት።
በዋናነት ደግሞ የልማት ስራዎቹን የሚያከናውኑን የመንግስት ተቋማት እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ስለሚያከናውኑት ሥራ ጥራት እና ፍጥነት በተመለከተ ማህበራዊ ተጠያቂነታቸው መጠናከር አለበት።
እንደ መምህርት አልማዝ ከሆነ፤ ከዚህ ቀደም በተተገበሩት የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮጀክቶች አማካኝነት ህብረተሰቡ በተለያዩ ግንባታዎች ላይ ማስተካከያዎችን በማንሳት እና ስለመብቱ እንዲጠይቅ ሰፊ ግንዛቤ ያስፈልጋል።
በፕሮጀክቱ ሦስተኛ ምዕራፍ ደግሞ በበለጠ ህበረተሰቡን ስለ ማህበራዊ ተጠያቂነት በማስተማር ስለ መንግሥት አገልግሎቶች እና የልማት ተቋማት ግንባታዎች መሻሻል የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የማህበራዊ ሃላፊነት እንዲጠናከር ያግዛል።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማህበራዊ ፍትህ ጉዳዮች ተወካይ ወይዘሮ ረቢቱ በዉሶ በበኩላቸው፣ በፕሮጀክቱ አማካኝነት በተለይ በውሃ እጥረት የሚሰቃዩ ዜጎችን ስለልማት ስራዎች አስፈላጊነት እና የአገልግሎት ሰጪዎችን ተጠያቂነት በተመለከተ ለህብረተሰቡ በተገቢው መንገድ መልዕክት ይተላለፋል።
ግንዛቤውን የያዘው ህብረተሰብ ደግሞ ለምን አልተሰራም ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ ግንባታ በሚደረግበት ወቅት በአግባቡ እና በሚፈለገው ጊዜ እንዲሰራ በመጠየቅ ጥብቅ ማህበራዊ ተጠያቂነትን እንዲኖር ያደርጋል። በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች እና አገልግሎቶች ከማህበረሰቡ ፍላጎት ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ የተጠናከረ ጥረት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2012
ጌትነት ተስፋማርያም