
- በጥቅምት መጀመሪያ የሙከራ ኃይል ሊያመነጭ ነው
- ከመሬት 70 ሜትር ከፍታ ያለው ውሃ በግድቡ ተሞልቷል
- ውሃው በ12ነጥብ 4 ኪሎሜትር ዋሻ ውስጥ ያልፋል
አዲስ አበባ፤- 254 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው የገናሌ ዳዋ ኤሌክትሪክ ኃይል ግድብ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚያስችለው ውሃ በግድቡ በመሙላቱ በጥቅምት መጀመሪያ የሙከራ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በገናሌ እና ዳዋ ተፋሰሶች በጉጂ እና ባሌ ዞኖች መካከል እየተገነባ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ስራ ሲጀምር 254 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አለው።
በአሁኑ ወቅት በግድቡ ለተተከሉት ሶስት ተርባይኖች ማንቀሳቀሻ የሚሆነው እና ከግድቡ የታችኛው ወለል አንስቶ 70 ሜትር ከፍታ የሚደርሰው ውሃ በመሙላቱ በጥቅምት ወር መጀመሪያ የሙከራ ኃይል ማመንጨት ይጀመራል።
እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ፤ በግድቡ እንዲገባ የተደረገው ውሃ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንኛዎች ታሪክ ረጅሙ በሆነው እና 12 ነጥብ 4 ኪሎሜትር በሚረዝመው የኮንክሪት ዋሻ ውስጥ አልፎ ነው ተርባይኖቹን የሚያንቀሳቅሰው።
በአሁኑ ወቅትም ዋሻው በውሃ ተሞክቶ የፍተሻ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል። እስከአሁን ድረስ ያለውሃ እና በእርጥበት አማካኝነት በተደረጉ የተርባይን ፍተሻዎች የተሳካ ውጤት ተገኝቷል።
ሶስቱ ተርባይኖችም በሙሉ አቅም ሲሰሩ እያንዳንዳቸው 84 ነጥብ 7 ሜጋ ዋት ማመንጨት እንደሚችሉ የተናገሩት አቶ ሞገስ፤ ግድቡም ጥቅምት ላይ የሙከራ ኃይል ማመንጨት ሲጀመርም የሚመረተው ኤሌክትሪክ በይርጋለም እና ወላይታ ሶዶ ከተሞች አድርጎ አዲስ አበባ የሚገኘው ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ቋት እንዲገባ እና ወደሚያስፈልጉ አካባቢዎች እንዲሰራጭ እንደሚደረግ አስረድተዋል።
የገናሌ ወንዝን ተጠቅሞ የተሰራው ግድቡ በአካባቢው ተፈጥሮ ምክንያት በየካቲት ወር እና ከሰኔ ጀምሮ በሁለት ወቅቶች የክረምት ዝናብ እንደሚያገኝ የገለጹት አቶ ሞገስ፤ በቀጣይ ጊዜያት ከ100 ሜትር በላይ ውሃ ይዞ መስራት የሚችል በመሆኑ ለኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ስራ ሲጀምር የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በቴክኒክና ሙያ ለተመረቁ ወጣቶች እና መጠነኛ ሙያ ላላቸው ሰዎች የተለያዩ ስራዎችን ለመስጠት ውይይት ተደርጓል።
ህብረተሰቡም ከካሳ ክፍያ አወሳሰን ጀምሮ የመለየት ስራ በማከናወን በቀጣይ የአካባቢው ማህበረሰብ ከኤሌክትሪኩ ኃይል ተጠቃሚ በሚሆንበት መንገድ ላይ ከተቋሙ ኃላፊዎች ጋር ገንቢ ውይይቶችን ሲያደርግ እንደቆየ አስታውሰዋል።
እንደ አቶ ሞገስ ከሆነ፤ ከአዲስ አበባ 630 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የገናሌ ዳዋ 3 የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ግንባታው የተጀመረው መጋቢት 2003 ዓ.ም ላይ ነው። ከየካቲት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ለግድቡ የሚሆን ውሃ ሙሌት ሲካሄድ ቆይቷል። ቀሪ ስራዎች የሚቀሩት ግድቡ 451 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያለው ሲሆን ግንባታው በቻይናው ሲጂጂሲ ድርጅት እየተከናወነ ይገኛል።
ለግድቡ ወጪ የኢትዮጵያ መንግስት 40 ከመቶ ሲሸፍን የቻይናው ኤግዚም ባንክ ደግሞ 60 በመቶ የሚሆነውን ፋይንናንስ አቅርቧል። እንደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ፤ በገናሌ ወንዝ ላይ እንዲሰሩ ከታቀዱ ፕሮጀክቶች መካከል ከገናሌ ሶስት ግንባታ በዘለለ ገናሌ አራት እና አምስት የአሌክትሪክ ማመንጫዎችን ግንባታ ለማስጀመር ጨረታ ወጥቷል።
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2012
ጌትነት ተስፋማርያም