በሰሜን ከኦሮሚያ እና ከሰሜን ምዕራብ ኮንታ ልዩ ወረዳ፣ በምስራቅና በደቡብ ከደቡበ ኦሞ እና ከቤንች ማጅ ዞን፣ በምዕራብ ከደቡብ ምዕራብ ሸካ ዞን ጋር ይዋሰናል። የአረቢካ ቡና ዋና መገኛ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ ቡና ምንጩና መገኛው በዴቻ ወረዳ ማኪራ በተባለ ቦታ መሆኑም ይነገራል። የኢትዮጵያ የቡና ዝርያ ምንጭ ሆኖ ይጠቀሳል። በዞኑ የሚገኘው ጥቅጥቅ ደን በኢትዮጵያ ካሉት ጥቂት የቡና ደኖች ውስጥ አንዱ ነው። የከፋ ዞን፤
የዞኑ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የአካባቢው ነዋሪዎች በተፈጥሮ ደን አካባቢ የሚኖሩና በአደን፣ በከሰል፣ በእንጨትና ሌሎች የባህላዊ ዕደጥበብ ዘርፍ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም፤ የከፋ ዞን ማህበረሰብ አባላት በአብዛኛው በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን፤ በደን አካባቢ አነስተኛ የእርሻ ማሳ ይጠቀማሉ። ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱ የኤክስፖርት ምርቶች መካከል በዋናነት ቡና በስፋት የሚመረትባት፣ የውሽውሽ ሻይ ልማት የሚገኝበት፤ ማር ምርት፤ ቅመማ ቅመም ወዘተ. በከፍተኛ ደረጃ ስለሚመረት በሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ዞኑ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።
ደን እና የተፈጥሮ ጫካ የከፍቾ ብሔረሰብ ኑሮ እና ማህበራዊ ህይወት አንድ አካል ነው። በከፋ ምድር ውስጥ ባሉት ጫካዎች በአብዛኛው የጫካ የተፈጥሮ ቡና ይበቅላል። ከዚህም በመነሳት በከፋ ጫካዎች ውስጥ የበቀሉና ተራብተው የሚገኙ ከአምስት ሺህ በላይ የቡና ዝርያዎች ይገኛሉ። ደን ለከፊቾ ህዝብ ሁሉም ነገሩ ነው። ማር፤ ኮረሪማ፤ ጥምዝ የተለያዩ የተፈጥሮ ፍራፍሬዎች፣ ቶጆ፣ ጋሮ ስራስሮች ወይም አኖ በከፋ ደን ውስጥ የሚገኙ ናቸው። እነዚህ የከፋ የተፈጥሮ ደኖችና ጫካዎች በከፊቾ ብሔረሰብ ባህል ከአባት ወደ ልጅ ሲወራረሱ የመጡ፤ እያንዳንዱ ዛፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ እና ባለቤት ያለው ነው። የዚህ የባለቤትነት ባህላዊ የደን እንክብካቤና አጠባበቅ “የኮቦ ስርአት” ተብሎ ይጠራል። የተፈጥሮ ሀብቱንና ደኑን ለመጠበቅ አስተዋጽኦ ካደረጉት ሀገር በቀል ዕውቀቶች አንዱ የኮቦ ስርአት ነው።
አካባቢው ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ልማት በማምጣት ለዘላቂ ልማት፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለባህል እሴቶች መጠበቅ የሚያበረክተውን ድርሻ ለማስቀጠል አሁን ላይ እንደ ችግር የሚስተዋሉት መሰናክሎች “ሳይቃጠሉ በቅጠል ሊባልለት ይገባል።” ይላሉ የአካባቢው ነዋሪዎች፤
ወይዘሮ መዓዛ አሰፋ በከፋ ዞን የቦንጋ ከተማ ነዋሪ ናቸው። “ዞኑ ራሱን ጠቅሞ ለሌሎችም እንዲተርፍ ከታሰበ መሰረታዊ የሆኑ ችግሮች ሊቀረፉ ይገባል። እንዳለው የተፈጥሮ ሀብት በኢንዱስትሪው በልጽጎ፤ ከፌዴራል መንግስት ጋር ትስስር ፈጥሮ እንዲሰራ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ሊደመጡ ይገባል። በርካታ ወጣቶች ሥራ አላገኙም፤ ቢያንስ ኢንቨስተር ተብሎ ገብቶ ደን ጨፍጭፎ ጣውላ ጭኖ ከመሄድ ያለፈ ኢንዱስትሪ ሊያስፋፋና አገርን ሊጠቅም የሚችል የኢንቨስትመንት ሥራዎች ትኩረት አላገኙም። ያልለሙ በርካታ አካባቢዎች አሉ። ህዝቡን ለመጥቅም እድሎችን ማመቻቸት ይገባል” ብለዋል። የአካባቢውን መሠረታዊ ችግር ከመፍትሄ ጠቋሚ ሀሳብ ጋር ሲሰነዝሩ፤
ወይዘሮ መዓዛ እንደሚሉት፤ በርካታ እናቶች በአቅራቢያቸው ህክምና ለማግኘት ስለሚቸገሩ በየመንገዱ ሲወድቁ ይታያሉ፤ ህዝቡን ሊታደጉ የሚችሉ የህክምና ጣቢያዎች መስፋፋት አለባቸው። አካባቢው በተፈጥሮው አረንጓዴ ቢሆንም፤ አቅሙን ወደ ገንዘብ በመለወጥ ረገድ ግን ሥራ እየተሰራ አይደለም። በወንዞችና በደኖች ላይ ተስማሚ ያልሆኑ ባዕድ ነገሮች ሲቀላቀሉባቸው ይታያል። ስለዚህም፤ ጠንካራ የአካባቢ ጥበቃ መሠረተ ልማት ያስፈልጋል። አረንጓዴ ልማቱን የሚደግፉ በርካታ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባት አለባቸው።
“የማያለቅስ ልጅ አይጠባም” የሚለውን የአባቶች ብሂል ያስቀደሙት ሌላኛው የአካባቢው ተወላጅ አቶ ታዬ ነጋ፤ “በዞኑ የሚስተዋሉትን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አበክሮ ማቅረብ መፍትሄውን ለማፈጣን ይረዳል” ይላሉ። ችግሮችን አይቶ ማለፍ ሳይሆን ለመፍትሄው ሲባል ሁልጊዜም መጠየቅ እንደሚያስፈልግም ያብራራል። አቶ ታዬ አክሎም፤ በተለይ የከፋ የቡና ሙዚየም ከዚህ በፊት መገንባቱንና አሁን ላይ ግን በእንክብካቤ እጦት ምክንያት የሸረሪት ድር እያደረበት እንደሚገኝ አስታውሰው፤ መንግስት ጉዳዩን ቸል እንዳይለውም አስገንዝበዋል። የክልሉና የዞኑ አስተዳደሮች፤ እንዲሁም የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም ነው አቶ ታዬ የገለጹት፤
አቶ ታዬ፤ የከፋ ዞን እምቅ ሀብት ያለበት አካባቢ እንደመሆኑ እንደ መንገድ፣ ድልድይ፣ ውሃ፣ ደረጃውን የጠበቀ ሆስፒታልና የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችም በአግባቡ እንዳልተሟሉ በማመላከት መንግስት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም ጠቁመዋል። አካባቢው በቡና ልማት ብቻ ሳይሆን እንደ ሰሊጥና ስንዴ ያሉትን ሰብሎች በብዛት ለማምረት የሚያስችል እንደሆነና በተለይ በሁለቱ የሰብል ዝርያዎች እንደ ቡናው ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ቢዘረጉ ለአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ ለአገሪቷ የኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል። 12 ዓመታትን ያስቆጠረው የቦንጋ ውሃ ፕሮጀክትም ተግባራዊ እንዳልተደረገና ጉዳዩ አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሻም ጠቅሰዋል።
የከፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማስረሻ በላቸው እንደሚሉት፤ የከፋ ዞን በክልሉም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የበርካታ ህዝባዊ ፍትህ መገኛ ከመሆኑ ባሻገር የአገሪቱ ሳንባ ከሆኑና በመመናመን ላይ ካሉ ጥቂት ቅሬተ ደኖች መካከል ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃና በዩኔስኮ የተመዘገበ ከ700 ሺህ ሄክታር በላይ ጥቅጥቅ ደን የሚገኝበት ነው።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የከፋ ዞን አየር ንብረትና ጫካ የተለያየ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ላላቸው ተክሎችና ሰብሎች ምቹ በመሆኑ በአግባቡ ጥቅም ላይ ቢውል ከዞኑ አልፎ ለክልሉና ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት የሚችል እምቅ ሀብት ያለው ዞን ነው። ዞኑ በ12 የገጠር ወረዳዎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረ ሲሆን ህዝቡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰው ወዳድ፤ እንግዳ አክባሪ ከመሆኑ ባሻገር፤ አካበቢውን ማልማት የተካነበት የኑሮ ዘይቤ አለው።
ዞኑ ሦስት ነባር ህዝቦችን፤ ማለትም ከፊቾን፣ ናኦን እና ጫራን መያዙን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፤ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች በጋራ ተዋድደውና ተከባብረው የሚኖሩበት ሥፍራ መሆኑንና የከፋ ዞን ህዝቦች ከዛሬ አንድ ሺህ ዓመት በፊት ጀምሮ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ በተለያዩ ሦስት ስርዎ መንግስታት ሲተዳደሩ የቆዩ፤ ለዘመናዊ የመንግስት የአስተዳደር ሥርዓት ሲጠቀሙ የመጡና አገሪቷ ምድረ ቀደምት እንድትባል ያስቻሏት መሆኑንም ገልጸዋል። ሆኖም፤ ህዝቡ ተፈጥሮ የለገሰችውን ለምለም ስነ ምህዳር ለብልጽግና መነሻ ቢሆንለትም ትኩረት በማጣቱ ለበርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጠም ጭምር እንደሆነ ይናገራሉ። በዞኑ የመንገድ፤ የውሃና ሌሎች መሠረታዊ የሆኑ መሠረተ ልማቶች ችግር እየተስታወለበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዋና አስተዳሪው እንደሚሉት፤ ዞኑ በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በክልሉ እንደ አንድ አግሮ ፕሮሰሲንግ ማዕከል መሆን ቢችል በቂና እምቅ ሀብት ያለው በመሆኑ በኢኮኖሚ ማበልጸግ ይገባል። የተፈጥሮን ገጸ በረከት እድል በአግባቡ መጠቀም ሲቻል፤ ሀብቱን በሥራ ላይ ባለመዋሉ በርካታ ወጣቶች የስራ እድል ተነፍገው ይገኛሉ። እድሎችንና ተግዳሮቶችን በመለየት መንግስት ለዞኑ አስፈላጊ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን መመለስ ይኖርበታል። ከዚህ ቀደም ተጠይቀው ነገር ግን ምላሽ ሳያገኙ እየተንከባለሉ የመጡ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በዚህ ዘመን ላይ ምላሽ ይሻሉ።
በቅርቡ ወደ ከፋ ዞን አቅንተው የአካባቢውን ማህበረሰብ ያወያዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ፤ “መጥፎ ነገር የጎደለውን ለመሙላት ሌላ ማጉደሉ ነው። እስከተዋደድንና እስከተደመርን ድረስ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር የጎደሉ ነገሮች ይፈታሉ” በማለት ለአካባቢው ማህበረሰብ ተስፋ ሰጥተዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ ከልማት ጋር ተያይዘው የተነሱ የውሃ፣ የመንገድና የሆስፒታል ጥያቄዎችን በሚመለከት ሙሉ መረጃዎችን በመያዝ ፌዴራል መንግስት ማድረግ የሚችላቸውንና በበጀት ውስጥ መካተት የሚገባቸውን ጉዳዮች ይመለከታል። በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁ በጀት የተያዘው ለመንገድ በመሆኑ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች አዳዲስ መንገዶችን ጨምሮ ነባሮቹም እንደሚስተካከሉ መገንዘብ ይገባል። ምንም እንኳን በትምህርትና መሰል አገልግሎቶች ላይ በአገሪቷ ሰፊ ስራ እየሰራ ያለው በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ቢሆንምና ከመንግስት የሚበጀት ገንዘብ ባይኖረውም ከድጋፍ የሚገኙውን ሀብት በመጠቀም በሌላ አካባቢ የተጀመረውን ሥራ የከፋ ዞንንም ታሳቢ ተደርጎ ይሰራል።
“ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞም አቅም ያላቸውና አካባቢውን የሚቀይሩ ኢንቨስተሮችን እናመጣለን። ነገር ግን፤ ኢንቨስተር ማለት መሬት የሚቀማ ስላልሆነ ወጣቶች ሊታገሱ ይገባል። በቡና ንግድ የዓለምን ገበያ የተቆጣጠሩት አገራት ከኢንቨስትመንት በሚገኝ ካፒታል አማካኝነት ነው። ይህንን ታሳቢ በማድረግም አቅም ያላቸው፤ ማልማት የሚችሉና ተጠቅመው የሚጠቅሙ ሰዎችን ማምጣት ያስፈልጋል። ሲመጡ ግን የኢትዮጵያን ገጽታ በሚያጠፋ መንገድ ሀብታቸውን መቀማት እንዳይሆን ወጣቶች አበክረው ሊሰሩበት ይገባል። ይህ የስራ አጥ ወጣቶችን ቁጥር ከመቀነስ አልፎ የግል ባለሀብቱንም ያበረታታል” ሲሉም ልማቱ ሊያድግ የሚገባበትን አቅጣጫ ጠቁመዋል። ከማህበረሰቡ በተነሱ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይም የፌዴራል መንግስት ከዞኑ አስተዳደርና ከክልሉ አመራር ጋር በመሆን በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2011
አዲሱ ገረመው