አሜሪካና ኢራን ሆድና ጀርባ መሆን የጀመሩት ከበርካታ አስርት አመታት በፊት የአሁኑ የኢራን የለውጥ ኃይል ቴህራን ውስጥ የሚገኘውን የአሜሪካን ኤምባሲ ወርሮ በርካታ አሜሪካዊያንን ከአገተ ጊዜ ጀምሮ ነው። ኢራን እ.ኤ.አ በ2000 “የአለብኝን የኃይል እጥረትና የህክምና ችግር ለመፍታት” በሚል ምክንያት የኒዩክሌር ማብላያ ተቋም ከገነባች ወዲህ ደግሞ ኢራን ከምዕራባዊያንና ከእስራኤል ጋር ወደ ለየለት ወታደራዊ ፍጥጫ ገብታለች።
በዚህም አሜሪካ፣ እስራኤል፣ ሳዑዲ አረቢያና ሌሎች ምዕራባዊያን ሃገራት ኢራን የኒዩክሌር የጦር መሳሪያ ሰርታ አስከፊውን የአቶሚክ ቦምብ በእጇ ልትጨብጥ ነው ሲሉ ቴህራንን ይከስሳሉ። ቴህራን ግን ይሄን መሰሉን ክስ ፈጽማ አትቀበለውም።
በመሆኑም እስላማዊቷ ሃገር ኢራን የኒዩክሌር ግንባታዋን ለማቆም አሻፈረኝ ማለቷን ተከትሎ በምዕራባዊያኑ ሃገራት በተጣለባት ከባድ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ ሁለት እጆቿ ወደኋላ የፍጥኝ ተጠፍንጎ መፈናፈኛ አጥታ ትገኛለች።
በተለይ የፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማን ከስልጣን ጊዜ መጠናቀቅና መሰናበት ተከትሎ በጥቁሩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት እግር የተተኩት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራንን እንዳትራመድ በእግር ብረት አስረው፤ እንዳታይ በጥቁር መጋረጃ ጋርደው፤ እንዳትዳብስ ሁለት እጆቿን በካቴና ጠፍንገው፤ እንዳትተነፍስ አፏን ለጉመው አሳሯን እያበሏት ይገኛሉ።
በዚህም፤ ከሶስት ወራት በፊት ኢራን “ሁሉን ያጣሁ ጎመን” አልሆንም በማለት እ.ኤ.አ በ2015 የገባቀችውን የኑክሌር ስምምነት ወደጎን በመተው “ዩራኒየም የማበልጸግ አቅሜን በአራት እጥፍ አሳድጋለሁ” ማለቷን እና የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ሞሳድ ኢራን በቀጥታ አሊያም በተላላኪዎቿ በኩል በአሜሪካና በአጋሮቿ ላይ የከፋ ወታደራዊ የሽብር ጥቃት ልታደርስ እንደምትችል ለዋይት ሃውስ ባለ ስልጣናት ሹክ ማለቱን ተከትሎ አሜሪካ ዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን የተባለውን ግዙፍ የጦር መርከብና የፀረ ሚሳኤል መሳሪያዎች ከአያሌ ተዋጊ አውሮፕላኖችና ወታደሮቿ ጋር ወደ ፋርስ ባህረ ሰላጤ አጓጉዛ “ኢራን ሆይ ተመከሪ” ስትል ሰነብታለች።
ኢራንም የልዕለ ኃያሏን አሜሪካ ማስጠንቀቂያ ወደጎን በመተው በጃፓንና በሳኡዲ የነዳጅ ማመላለሻ መርከቦች ላይ የፈንጅ ጥቃት ፈፀመች። የኢራን ጠብ አጫሪ ድርጊትም በዚህ ሳያቆም ኢራቅ ባግዳድ ውስጥ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ በተላላኪዎቿ በኩል ለማጥቃት ሞክራለች። እንዲሁም “የኔ የነዳጅ ማመላለሻ መርከብ በአሜሪካን ታግቶብኛል” በሚል ሰበብ የእንግሊዝን የነዳጅ ማመላለሻ መርከብ አግታ ከእንግሊዝ ጋር ጦር መማዘዝ ቀርቷት ነበር።
ከዚህ ሁሉ የከፋውና የቀጠናውን ውጥረት ይበልጥ ያባባሰው እ.ኤ.አ ሰኔ 20/2019 በፋርስ ባህረ ሰላጤ በዓለም አቀፍ የአየር ክልል ውስጥ ሲበር የነበረን አንድ አሜሪካ ሰራሽ ሰው አልባ አውሮፕላን ኢራን በተወንጫፊ ሚሳኤል መትታ መጣሏ ነበር። አሜሪካ ሰላዩ አውሮፕላን ተመትቶ የወደቀው በዓለም አቀፍ የአየር ክልል ነው ብትልም ኢራን ሌላ ይዘት ያለው የመከራከሪያ ነጥብ ይዛ ብቅ አለች። በወቅቱ የኢራን ወታደራዊ ኃይሎች በሰጡት መግለጫ “አውሮፕላኑ የተመታው በኢራን አየር ክልል ውስጥ ነው” በሚል ከአሜሪካ ጋር በገቡት እሰጣገባ፤ ዓለም ዛሬ ነገ ወደ ለየለት ጦርነት ይገቡ ይሆን? ሲል በሰቀቀን ኪሎውን ሲቀንስ ሰነባብቷል።
ያም ሆነ ይህ ግን፤ ለወትሮውም ቢሆን ሰላም የጠፋበት የመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ‘በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ’ እንዲሉ በያዝነው ሳምንት ቅዳሜ እለት አመሻሽ ላይ በትልቁ የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋም ላይ ጥቃት በመድረሱ በቀጠናው ያለው ውጥረት ጦዟል።
222 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ የሚያወጣ ዘመናዊ የስለላ አውሮፕላኗን ያጣችው አሜሪካ አንዳች ወታደራዊ አፀፋ ለኢራን ልትሰጥ ትችላለች ተብሎ እየተጠበቀ ባለበት ማግስት ውጥረቱን የሚያባብስ ሌላ ጥቃት በአሜሪካዋ ወዳጅ ሳዑዲ አረቢያ ላይ መድረሱን ተከትሎ፤ ወትሮውንም አሜሪካ የእራሷን እና የወዳጅ ሃገራትን ሉዓላዊነትና ጥቅም ለማስከበር አጸፋዊ ርምጃ ልትወስድ ትችላለች የሚል ስጋት አጭሯል።
ውጥረቱንም ያባባሰው በየመን የሚንቀሳቀሱት እና በኢራን ድጋፍ የሚደረግላቸው የሁቲ አማጽያን በሳዑዲ የደረሰውን ጥቃት ያደረስነው እኛ ነን ቢሉም፤ አሜሪካ በበኩሏ ሳዑዲ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ ለማድረግ ጊዜ አልወሰደባትም። ጥቃቱን ተከትሎም የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝደንት ማይክ ፔንስ፤ “ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ የራሷን እና የወዳጅ ሃገራትን ሉዓላዊነትና ጥቅም ለማስከበር አስፈላጊ የሆኑ ርምጃዎችን ከመውሰድ ወደኋላ አትልም። በዚህ እርግጠኛ ሁኑ” ሲሉ ተደም ጠዋል።
የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ በበኩላቸው፤ ‘’የድሮውን ጥቃቱ ከየመን ስለመነሳቱ የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ የለም። ሁሉም መንግሥታት ኢራን በዓለም የኢነርጂ ምንጭ ላይ የሰነዘረችውን ጥቃት ማውገዝ አለባቸው’’ ለማለት ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር። እርሳቸውም ቅዳሜ ዕለት የሳዑዲ ነዳጅ ማውጫ ተቋማት ላይ ለተሰነዘረው የድሮን ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ አድርገዋል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ በበኩላቸው “ለጥፋቱ ማን ተጠያቂ እንደሆነ ስለምናውቅ አቀባብለን የሳዑዲ መንግሥት ምክረ ሃሰብ ምን እንደሆነ እየጠበቅን ነው” በማለት ወታደራዊ አማራጭ ከግምት ውስጥ እንደገባ አመላክተዋል።
በስም ያልተጠቀሱት የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን እንደተናገሩት፤ ዒላማ የተደረጉት 19 ቦታዎች እንደነበሩ እና ጥቃቱ የተሰነዘረው ከምዕራብ እና ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው፤ ጥቃቶቹ የተነሱባቸው ስፍራዎች በየመን የሁቲ አማጺያን የሚቆጣጠሯቸው ቦታዎች አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ ጨምረው እንደተናገሩት፤ የተገኘው መረጃ ጥቃቱ የተሰነዘረው ከኢራን ወይም ኢራቅ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል። ሁቲዎች ከዚህ ቀደም በሳዑዲ ምድር የነዳጅ ማምረቻና ማቀነባበሪያ ላይ ጥቃት አድርሰው ያውቃሉ። ነገር ግን ይህ ጥቃት በመጠኑ የገዘፈ እና በዓለማችን ከፍተኛ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ስፍራና በሌሎች የነዳጅ ማውጫ ቦታ ላይ የተፈጸመ ነው ብለዋል። በአንጻሩ ኢራን በፕሬዝዳንቷ ሐሰን ሮሃኒ በኩል የለሁበትም ያለች ሲሆን፤ “በየመን ሕዝቦች የተወሰደ አፀፋዊ እርምጃ” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ጥቃቱን ገልፀውታል።
በያዝነው ሳምንት ሰኞ ዕለትም አሜሪካ የለቀቀችው የሳተላይት ምስሎች፤ ቅዳሜ አመሻሽ ላይ ኢራን አደረሰችው ተብሎ ጣት የተቀሰረባት “ያልተጠበቀ” ጥቃት ያስከተለውን የጉዳት መጠን ያሳየ ሲሆን፤ ከኢራን ጋር አብረዋል ተብሎ የሚነገርላቸው የየመን ሁቲ አማፂያን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስደዋል። ነገር ግን አማፂያኑ ያለ ማንም ድጋፍ ይህንን ያህል ጥቃት፣ በዚህ ያህል ትክክለኛነት ያከናውናሉ መባሉ ለአሜሪካ አልተዋጠላትም።
አሜሪካ ይፋ ያደረገቻቸው የሳተላይት ምስሎች በነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማቱ ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት ያመለከተ ሲሆን፤ በሳዑዲ ላይ የተሰነዘሩት የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃቶች መሆናቸውን እና ሁሉም ዒላማቸውን መምታት አለመቻላቸውን የአሜሪካ የደህንነት ቢሮ መረጃ ጠቁሟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ሳዑዲ ላይ የተቃጡት የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃቶች መነሻቸው ከኢራን ስለመሆኑ ደርሼበታለው ስትል ማክሰኞ እለት ይፋ አድርጋለች። የአሜሪካ ባለስልጣናት የሳዑዲን ነዳጅ ማቀነባበሪያ ለመምታት ጥቅም ላይ የዋሉት የድሮን እና ሚሳዔል አይነቶችን ለይተናል። ጥቃቱ ከደረሰበት ስፍራ በሚሰበሰቡ ቁሶች ላይ የሚደረገው የፎረንሲክ ምርመራ ውጤት ኢራን እጇ እንዳለበት የማያወላውል መረጃ ማሳየታቸው አይቀሬ ነው ብለዋል።
ምክትል ፕሬዝደንት ማይክ ፔንስ “አሜሪካ ሁሉንም መረጃዎች እየመረመረች ነው” ካሉ በኋላ የውጪ ጉዳይ ቢሮው ኃላፊ ማይክ ፖምፔዎ “ምላሻችን ምን መሆን እንዳለበት ለመወያየት” ወደ ሳዑዲ አቅንተዋል ብለዋል።
በሌላ በኩል ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ባለስልጣን ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት፤ የሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማትን ዒላማ አድርገው ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱት ጥቃቶች መነሻቸው ከደቡባዊ ኢራን ነው። ጥቃቱ የተሰነዘረበት አቅጣጫ እና ስፋት ከግምት ውስጥ ሲገባ የሁቲ አማጽያን ፈጽመውታል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል።
የሁቲ አማጽያን ከዚህ ቀደም ወደሳዑዲ የድሮውን ጥቃቶችን አድርሰዋል፤ ሚሳዔሎችንም አስወንጭፈዋል። ይህን ጥቃት ግን የሁቲ አማጽያን ለመፈጸም የሚያስችል ቁመና የላቸውም። እንዲሁም፤ ጥቃቶቹ የተሰነዘሩት በየመን የሁቲ አማጽያን ከሚቆጣጠሩት ስፍራም አይደለም ብለዋል።
ኢራን በበኩሏ ከጥቃቶቹ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለኝም ስትል የቆየች ሲሆን፤ የኢራን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ በትዊተር ገጻቸው ላይ “አሜሪካ እውነቱን አምና መቀበል አልፈለገችም” ካሉ በኋላ፤ ይህን ሁሉ እሰጥአገባ ማስቆም የሚቻለው በየመን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ማስቆም ሲቻል ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል፤ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን አገራት (ኔቶ) ወታደራዊ ጥምረት የበላይ ኃላፊ ጄንስ ስቶልትነበርግ በበኩላቸው፤ በሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማት ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ የውጥረቱ መጋጋል እጅጉን እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል። ኢራን “ቀጠናውን እያመሰችው ነው” ሲሉም ከስሰዋል።
ጄንስ ስቶልትነበርግ “እንዲህ አይነት ለቀጠናው በአጠቃላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያለው ጥቃት ዳግመኛ እንዳይደርስ እንድንከላከል ጥሪ እናቀርባለን፤ ውጥረቱ እንዳይባባስም ከፍተኛ ስጋት አለብን” ሲሉ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል በሰጡት ቃለመጠይቅ ወቅት ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ሳዑዲ አረቢያ የዓለማችን ቁጥር አንድ ነዳጅ አምራች ሃገር ስትሆን በየቀኑ ወደ 7 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ወደ ውጪ አገራት የምትልክ ሲሆን፤ ሳዑዲ ላይ ጥቃቱ ከተሰነዘረ በኋላ የዓለማችን የነዳጅ አቅርቦት አምስት በመቶ ሲቀንስ ዋጋውም መጨመር አሳይቷል። የዘርፉ ባለሙያዎች እንዳሉት፤ ስፍራው ከደረሰበት ጉዳት ተጠግኖ ዳግመኛ ወደ ሥራ እስኪመለስ ሳምንታትን ይጠይቃል ብለዋል።
የሳዑዲ የኢነርጂ ሚኒስትሩ ማክሰኞ እለት እንደተናገሩት፤ በነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማቱ ላይ የደረሰው ጉዳት ተጠግነው ወደ ቀደመ የማምረት አቅማቸው በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ይመለሳሉ። ጥቃቱ በሰው ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም። ነገር ግን፤ ጥቃቱ የሳዑዲ አረቢያን ድፍድፍ ነዳጅ የማምረት አቅም በግማሽ መቀነሱን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2011
ሶሎሞን በየነ