አዲስ አበባ፡- በገቢ አሰባሰብ ላይ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ስርዓትን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን የገቢዎች ሚንስቴር አስታወቀ፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር ትናንት ‹‹ግዴታዬን እወጣለሁ መብቴን እጠይቃለሁ›› በሚል መሪ መልእክት ታህሳስ 12 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄደውን አገር አቀፍ የማህበረሰብ ንቅናቄ አስመልክቶ በጽህፈት ቤቱ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አበቤ እንዳመለከቱት፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው ግብረ ሃይል ወደ ስራ ከገባ አንድ ወር አስቆጥሯል፡፡ ግብረ ኃይሉ የታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡
ወይዘሮ አዳነች እንደገለጹት፤ በገቢ አሰባሰብ ላይ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመፍታት በቅድሚያ የፖሊሲ እና አስተዳደራዊ ማሻሻያ ማድረግ ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የማሻሻያ ተግባራቱን ስራ ላይ ለማዋል በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የገንዘብ ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርን፣ የገቢዎች ሚኒስቴርን፣ ብሔራዊ ባንክን እና ብሄራዊ ፕላን ኮሚሽንን ያካተተ ሲሆን ከተቋቋመ ጀምሮ በርካታ የታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ስርዓትን የሚያሻሽሉ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡
‹‹የምንሰበስበው የገቢ መጠን እየቀነሰ መጥቶ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት 10 ነጥብ 7 በመቶ ላይ ደርሶ ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገሮች ጭምር ግርጌ ላይ እንድንቀመጥ አድርጎናል›› ያሉት ሚኒስቴሯ ለዚህም በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ሚኒስቴሯ ገለጻ፤ ሀገሪቱ ውስጥ ተፈጥረው የነበሩት ስር የሰደዱ ችግሮች እና የግብር ሰብሳቢውና የታክስ ፖሊሲ አውጪው ድክመት ሰፊውን ቦታ ይይዛሉ፡፡ የውጭ ንግድ መቀዛቀዝ፣ የተደራጀ ሌብነት፣ የታክስ ስወራ፣ ማጭበርበር እና በኮንትሮባንድ ወንጀሎች ዙሪያ የሚታዩ ጥፋቶች ታክለው የግብር ስርዓቱን በማጥበባቸው ህቡዕ ኢኮኖሚ በመስፋፋቱ ገቢ እየቀነሰ መጥቷል፡፡
ትክክለኛ ግብርን በወቅቱ አሳውቆ አለመክፈልም ሌላው ተግዳሮት መሆኑን የሚገልጹት ሚኒስትሯ፤ ለዚህ በምክንያትነት የሚጠቀሰው ዜጎች ለግብር ያላቸው ግንዛቤ ማነስ፣የእኔነት ስሜት ማጣት፣የታማኝነት መውረድ፣የማህበራዊ ልዕልና መጥፋት፣ የሞራል ዝቅጠት እና የመሳሰሉት ናቸው ይላሉ፡፡ በተጨማሪም ግብር የመክፈል ባህላችን አለመዳበሩ፣ ተጠቃሚው ህዝብ በደረሰኝ አጠቃቀም ዙሪያ ልምዱ አናሳ መሆኑ እንዲሁም ያለደረሰኝ የሚከናወን የትኛውንም አይነት ግብይት መፈጸም በራሱ ላይ ስርቆት እንዲፈጸም መፍቀድ መሆኑን ያለመረዳትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ይገልጻሉ፡፡
ሚኒስትሯ እንደገለጹት፤ ችግሮቹ ዘርፈ ብዙ እንደመሆናቸው መጠን በተሟላ ሁኔታ መፍታት ይቻል ዘንድ ሁሉም ዜጋ ባለቤት ሆኖ የሚሳተፍበት የታክስ ሀገራዊ ንቅናቄ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ሀገሩን እና ህዝቡን አክብሮ በንጹ ልቦና እና ፍጹም ታማኝነት ግብሩን በወቅቱ የሚከፍል ማህበረሰብን መፍጠር ዓላማ ያደረገው ይህ ሀገራዊ የለውጥ ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ይከፈታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2011
በየትናየት ፈሩ