ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአገራችን ኢኮኖሚ አቅሙ እየተንገራገጨ እንደሆነ መንግሥትም ሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በመሆኑም ኢኮኖሚው አሁን ካለበት ችግር ተላቆ አገሪቱ የምትፈልገው የእድገት ደረጃ ብሎም የብልፅግና ማማ ላይ እንድትቀመጥ የለውጥ አመራሩ የአዕምሮ ድምር ውጤት የሆነውን ’’ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ‘ ተግባራዊ አድርጓል።
ለመሆኑ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማለት ምን ማለት ነው? የሚሉና ሌሎች ከማሻሻያው ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን በማንሳት ከገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እነሆ…
አዲስ ዘመን፡- የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለምን አስፈለገ? ኢኮኖሚው ውስጥ የነበሩት ዋና ዋና ችግሮች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ኢዮብ፡- ባለፉት ዓመታት በሀገራችን በተመዘገበው ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል። በተለይም በመሰረተ ልማት እና በሰው ሃብት ልማት በርካታ ውጤቶችን አግኝተናል። ነገር ግን ኢኮኖሚው ከተግዳሮቶች ነጻ አልነበረም። በርካታ ተግዳሮቶች ገጥመውናል። በተለይም መዋቅራዊ ሽግግር በማምጣት ረገድ፣ የግሉ ሴክተር ኢኮኖሚው ውስጥ የሚገባውን ሚና እንዲጫወት እንዲሁም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ፍትሃዊነትን በተመለከተ በርካታ ችግሮች ነበሩ።
በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የገጠመን የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ከፍተኛ ተግዳሮት ነበር። እንግዲህ ማሻሻያው ያስፈለገው እነዚህን ተግዳሮቶች በመቅረፍ ኢኮኖሚውን በቀጣይነት በማሳደግ ነገር ግን እጥረቶቹን በመቅረፍ አሳታፊ ዘላቂና ሁሉንም የሚጠቅም ሥራ የሚፈጥር ኢኮኖሚ ለማምጣት ነው ማሻሻያው ያስፈለገው።
አዲስ ዘመን፡- ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተባለበት ምክንያት ምንድን ነው?
ዶክተር ኢዮብ፡- ሀገር በቀል የተባለው በዋነኝነት የሀገራችንን ችግር የምናውቀው እኛው ስለሆንን ለችግራችን መፍትሄ ማምጣት ያለብን በራሳችን እሳቤ ከሚል ነው። በተለይም ደግሞ የመደመር እሳቤ ሀገር ውስጥ ያለውን ጥሪት (የሰው ሀብት፣ እውቀት፣ ገንዘብንና ካፒታል) አሟጠን በመጠቀም የኢኮኖሚውን ሙሉ አቅም ሥራ ላይ ማዋል አለብን የሚል እሳቤ ስላለ እይታው ከውስጥ መሆን አለበት፣፤ የውስጣችንን ጥንካሬና ድክመት ለይተን ማውጣት ያለብን ራሳችን ነን፣ ለገጠመን ችግር ደግሞ መፍትሄ ማምጣት ያለብን ደግሞ እኛው ነን የሚል እሳቤ ስላለው ነው ሀገር በቀል የሚል ስያሜ የተሰጠው።
አዲስ ዘመን፡- በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የሚያከሄዱት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አብዛኛውን ጊዜ ከብሪቶን ውድ ተቋማት (የዓለም ባንክና የአለም የገንዘብ ድርጅት) ቀጥተኛ ወይም ተዘዋዋሪ ተጽዕኖ ነጻ እንደማይሆን ምሁራን ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት የኢኮኖሚና የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ተከትሎ ችግሮች ውስጥ ሲወድቁ ታይቷል። በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ሀገር በቀል ማሻሻያ ከውጭ ጫና ምን ያህል ነጻ ነው ማለት ይቻላል?
ዶክተር ኢዮብ፡- የእኛ ማሻሻያ ልዩነቱ ሀገር በቀል ነው። ሀገር በቀል ማለት ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት የተዘረጋ የማሻሻያ ፕሮግራም ነው። ሀገር በቀል ማለት ጠቃሚ ሀሳቦችን ከየትኛውም ዓለም አንወስድም ማለት አይደለም። አሜሪካም ቻይናም በየትኛውም ዓለም ጠቃሚ ሀሳብ ካለ የሪፎርሙ ማሻሻያ አካል ሆኖ ይገባል።
ለምሳሌ ስለዲጂታል ኢኮኖሚ የምናወረው በዚህ ማሻሻያ የኤሺያ ሀገራት በቅርብ ትልቅ ውጤት ያገኙበት ነው። በሌላ በኩል ስለቱሪዝም ስኬት ነው የምናወረው። በቱሪዝም ትልቅ ዉጤት ያገኙ በርካታ የአፍሪካ ሀገራትም አሉ። መልካም ነገሮችን ከአውሮፓም ፣ ከአሜሪካም፣ ከዓለም ባንክም ከሁሉም እንወስዳለን። ነገር ግን ትልቁ ልዩነቱ የራሳችንን የማሻሻያ ፕሮጀክት ቀርጸን በዚህ መልኩ አግዙን ነው ያልናቸው።
እስካሁን ድረስ ጫና አልፈጠሩብንም። እንዲያውም በአጠቃላይ የራስን ችግር በራስ ለይቶ ማቅረብና ችግሮችን አንጥሮ ማውጣት እንዲሁም የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በዚሁ መንገድ ሙሉ በሆነ መልኩ ማመላከት በጣም ትልቅ ስኬት ነው። የልማት አጋሮችም ይህ አንድ እርምጃ ነው ብለው ነው ያነሱት እንጂ ሌላ ቅሬታ አልሰማንም። በእርግጥ ኢትዮጵያ የሄደችበትን አካሄድ እጅጉን የማወደስ ነገር ነው የሰማነው። የሚያለያዩን ነገር ካለ እንለያያለን። ዋናው ነገር ሀገር በቀል መሆኑ ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው።
ለእኛ እስከሆነልን ድረስ ማንኛውንም የማሻሻያ ሀሳብ ተግባራዊ እናደርጋለን። የሚጠቅመንን ሀሳብ እንወስዳለን። የማይጠቅመንን ደግሞ አይጠቅመንም ብለን እንመልሳለን ማለት ነው። ይህኛው ግን እኛው ቀርጸነው፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዳሉት ብሩህ አዕምሮ ባላቸው ኢትዮጵያዊያን የተቀረጸ የማሻሻያ ሀሳብ ነው። እስካሁን ድረስ የልማት አጋሮቻችን ከማወደስና ከማድነቅ ባለፈ ምንም አይነት ትችት ሲያነሱ አልሰማንም።
አዲስ ዘመን፡- ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ማክሮ ኢኮኖሚያዊ፣ መዋቅራዊ እና ዘርፎችን የተመለከቱ ማሻሻያዎች አቅፎ እንዲይዝ ተደርጎ የተዋቀረ መሆኑ ይገለፃል። ሦስቱንም ቢያብራሩልን?
ዶክተር ኢዮብ፡- እነዚህን ሦስቱንም እንደ አንድ አንዱንም እንደ ሦስት አድርጎ መመልከት ጥሩ ነው። ሦስት እግር እንዳለው በርጩማ ነው። ለመቆም ሦስቱም በጣም አስፈላጊ ናቸው። አጠቃላይ ማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ሸማቹንም፣ የኢንቨስተሩንም፣ የመንግሥትንም፣ የግሉን ዘርፍ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ውስጥ ያሉ ተዋናዮችን በሙሉ በኢኮኖሚው ላይ እምነት እንዲያሳድሩ፣ ስለነገ እንዲያስቡ፣ ሰርተው ለመክበር እንዲያቅዱ የሚያደርጋቸው ነው።
የተረጋገጠ የማክሮ ኢኮኖሚ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ዛሬ የምትሰራው ሥራ፣ ዛሬ የምታካብተው ንዋይ ነገ ውጤታማ ይሁን አይሁን፣ ነገ ይሻሻል አይሻሻል እርግጠኛ መሆን አትችልም። ያንን ማረጋገጥ በጣም ወሳኝ ነገር ነው። ጤናማ የልብ ምት፣ ጤናማ የአይን እይታ፣ ጤናማ መተንፈስ እንዳለው ሰው አድርገህ አስበው። ያ የሲስተሙን ጤናማነት ነው የሚያሳየው። በሌላ በኩል ደግሞ መዋቅራዊ ሆኑ ነገሮች አሉ። መዋቅራዊ የሆኑ ነገሮች ኢኮኖሚውን ተብትበው እንደያዙ ነው ማሻሻያው ያሳየው።
ሊሰራ እያሰበ ፈቃድ ለማሳደስ ወራትና ዓመታት የሚፈጅበት አንድ ወጣት ወይም ሊበደር እያሰበ ለመበደር ያልቻለ ኢንቨስተር፤ በሀይል አቅርቦት ችግር አስፈላጊውን ምርት ማምረት ያልቻለ አምራች ወይም በአጠቃላይ በውጭ ም ምንዛሬ እጥረቱ ምክንያት ከአቅሙ 20 ወይም 30 በመቶ ብቻ እየሰራ ያለ አምራች ወይም ነጋዴ ያለውን አጠቃላይ አቅም አሟጦ እንዲያወጣና ውጤታማ እንዲሆን በየቦታው የተቀመጡ ጉቶዎችን ማውጣትና መዋቅሩን ማስተካከል ያስፈልጋል። አጠቃላይ የቢሮክራሲውን እሳቤ መቀየርን ጨምሮ ማለት ነው። ነገር ግን እነዚህን አድርገህ በየዘርፉ ያለ ደግሞ ዘርፍ ተኮር የሆኑ ችግሮችን ለቅመህ አውጥተህ ማስተካከል ካልቻልክ ደግሞ ማሻሻያው ሙሉ አይሆንም።
እነዚህን ሁሉ አድርገህ ግን ዘርፉን እንዳያድግ የያዙ ለምሳሌ የቱሪዝም ተወዳዳሪነት፣ የቱሪዝም መዳረሻ ከማልማት ጋር የተያያዙ ነገሮች እንዲሁም ግብርናን የተመለከትን እንደሆነ የግብርና ግብዓቶች አቅርቦት ጥራት ጋር ተያይዘው ያሉ ነገሮችን ወይም ግብርናውን ከማዘመን ጋር ያሉ ግብዓቶችን ከማሟላት ጋር ተያይዘው ያሉ ነገሮችን ካላሟላ ስርዓቱ ቢኖር አጠቃላይ ስርዓቱም ውጤታማ ቢሆን የዚያ ዘርፍ ችግር ደግሞ ካልተፈታ ዘርፉ ውስጥ ያለው አቅም ሊወጣ አይችልም ማለት ነው።
ለዚህ ነው እንግዲህ ተናቦ፣ ተቀናጅቶ፣ ተሰላስለው እነዚህ ማሻሻያዎች ወጥነት ባለው መልኩ መተግበር ያለባቸው። እነዚህን ሙሉ በሆነ መንገድ አንድ እይታ አይተህ ስትተገብራቸው ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን አቅም አሟጦ ለማውጣትና ሥራ ለመፍጠር፣ እድገቱን ለማስቀጠል እና ሀገሪቱንም ወደ ብልጽግና ጎዳና እንድትሄድ ለማድረግ ትልቅ መደለድል የሚፈጥር ማሻሻያ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ማለት ምን ማለት ነው?
ዶክተር ኢዮብ፡- ማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት በተለያየ መንገድ ይገለጻል። የውጭ መዛባትና የውስጥ መዛባት እንለዋለን። ውስጥ መዛባት የምንለው ገቢና ወጪ አለመመጣጠንን ነው የሚያመላክተው፤ የውጭ መዛባት የምንለው ደግሞ አጠቃላይ ሀገሪቷ የሚያስፈልጋት የውጪ ምንዛሬና ያላት በጣም የተለያየ ሲሆን ያንን የሚዛን ጉድለት እንለዋለን። ነገር ግን በአጠቃላይ ሚዛኑን ያልጠበቀ ሲሆንና ወደ አንዱ ያጋደለ ሲሆን፤ ለምሳሌ በርካታ የዕዳ ጫና ሲኖር፣ የወጪ ንግድ በጣም ደካማ ሆኖ የገቢ ንግዱ ግን በጣም የሰፋ ሲሆን ሚዛኑ እየሰፋ ሄዶ ጭራሽ ወደ መዛባት ደረጃ ይደርሳል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ማሻሻያው ሁሉንም የሀገሪቱን ህዝቦችና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ይገለፃል። በምን መልኩ ነው የሁሉንም የሀገሪቱ ህዝቦች በተለይ የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረገገጥ የሚረዳው?
ዶክተር ኢዮብ፡- አንዱ ኢኮኖሚያችን እጥረት የነበረው ዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ነው። ኢኮኖሚያችን በሚፈለገው መጠን በቂ ሥራ አልፈጠረም። በተጨባጭም በእይታም ከፍተኛ የሆነ የተጠቃሚነት ጉድለት አለ የሚል እሳቤ ስለነበረ ይህንን ለማስተካከል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በአመዛኙ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አቅም እንዴት አሟጥጬ ልጠቀመው ከሚል ስለሚነሳ ይህ ደግሞ ያለንን ሀብት ከቱሪዝም፣ ከግብርና፣ ከማኑፋክቸሪንግ እንዲሁም የሰው ሀይልን ጨምሮ ሌሎች ዘርፎችን እንዴት አስተባብረንና አቀናጅተን፣ አንድ ላይ ደምረን እንዴት አድርገን አስተባብረን ውጤታማ የሆነ ኢኮኖሚ እድገት እናምጣ ስለሚል እይታው ራሱ ሰው ላይ ያተኮረ ነው የሚሆነው።
የሰው ፍላጎት ላይ ያተኮረ ከመሆኑ አንጻር የሰው ልጆች ያላቸውን እውቀት አሟጠው እንዲያወጡ፤ ይህ ማለት ወጣቱ በተማረው መጠን የሥራ እድል እንዲያገኝ ወይም ደግሞ ሊነግድ ባሰበው ስፋት ነግዶ ማትረፍ እንዲችል፤ ሊያመርት ባሰበው አቅም ማምረት እንዲችል የሚያደርግ ነው። ስለዚህ ትልቁ ልዩነቱ ሰው ያለውን አቅም አሟጦ እንዲያወጣ እድል የሚፈጥር የኢኮኖሚ ማሻሻያ ነው።
እሳቤው ራሱ መንግሥት ሥራ ፈጣሪውን፣ አምራቹንና፣ ፈጣን ጭንቅላት ያላቸውን ለፈጠራ ሀሳብ የሚያመች ከባቢ የመፍጠር እሳቤ ስላለው ሥራ መፍጠር ትልቅ ለውጥ ነው የሚያመጣው። በእያንዳንዱ ዘርፎች በግብርናው፣ በቱሪዝሙ፣ በአምራቹም ዘርፍ ያለውን እምቅ ሀይል አሟጠን ለመጠቀም የሚያስችል ነው። ሥራ መፍጠርና የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የማሻሻያው ቁልፍ ትኩረት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ማሻሻያ ምቹ የቢዝነስ ከባቢ ለመፍጠር ይረዳል ተብሏል። እንዴት አድርጎ ነው ምቹ የቢዝነስ ከባቢን ለመፍጠር የሚረዳው?
ዶክተር ኢዮብ፡- ይህ ትልቅ ለውጥ ነው። በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት መንግሥት በኢኮኖሚ ውስጥ ትርጉም ያለው ሚና የተጫወተ ቢሆንም በዚያው ልክ የግሉ ዘርፍ ያለውን ሙሉ ሀይል አውጥቶ እንዲሰራ የሚያበረታታ አልነበረም። በግልጽ በግሉ ዘርፍና በመንግሥት መካከል ከፍተኛ የሆነ የመጠራጠር ስሜት ነው የነበረው። ቢሮክራሲያችንም ከማበረታታትና ከመደገፍ ይልቅ መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህ ምክንያት አጠቃላይ የቢዝነስ ድባቡ ለቢዝነስ የማያመች ሆኖ ቆይቷል። ሥራ የሚሰራ አንድ ሰው ብታወራ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢዝነስ መስራት ከባድ ነው የሚል እሳቤ ነው ያለው። ይህ ማሻሻያ ያንንም ችግር በደንብ የለየ ነው።
ይህንን ችግር በዚሁ ልንተወው አይገባም፤ ትንሽ ሥራ ካልሰራ የሚታትረውንና አዲስ በስራ ሊፈጥር የሚሞክረውን ወጣት፣ ኢንቨስት ለማድረግ ሀብት ይዞ የሚመጣውን ኢንቨስተር፣ ወይም ሀገር ውስጥ ያለውን ሀገራዊ ባለሃብት፤ ሥራ ሰርቶ ሀብት አትርፎ ለራሱም፣ ለቤተሰቡም ለሀገሩም የሚተርፍ እንዲሆን ማድረግ አንዱ ግብ ነው ብሎ ይጀም ራል።
ስለዚህ እይታው ኢትዮጵያ ቢዚነስ የሚሰራባት፣ ሰዎች ሰርተው የሚከብሩባት ሀገር መሆን አለባት፣ ቢዝነስ መስራት ሀጢያት አይደለም የሚል የተለየ እይታ አለው። ከዚህ አንጻር የቢዝነስ ድባቡን ከስር መሰረቱ ለመቀየርና ለኢንቨስትመንትና ለስራ ፈጠራ አመቺ እንዲሆን የማድረግ አስተሳሰብ አለው።
አዲስ ዘመን፡- ማሻሻያው የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ላይ ከዚህ በፊት ከነበረው የበለጠ ድርሻ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው ማለት ነው?
ዶክተር ኢዮብ፡- በትክክል። በአጠቃላይ የግሉን ዘርፍ አቅም አሟጦ መጠቀም ላይ ያተኮረ ነው። የግሉ ዘርፍ ሰፊ ነው። ጥቃቅን እርሻ ያለው ገበሬው ኩታ ገጠም እርሻ በመጠቀም አቅሙን አንድ ላይ ደምሮ፣ አከማችቶ የበለጠ ምርታማና አትራፊ መሆን አንዲችል ምቹ ድባብ መፍጠር፤ በሌላ በኩል የግሉ ዘርፍ የሚነግደውንም የሚያመርተውንም ሁሉንም ሰርቶ መክበር እንዲችል ያንን አስተሳሰብ ማምጣት ነው። ሰዎች ወደ ሥራ ፈጠራ እንዲገቡ፣ ያላቸውን እውቀት አጠራቅመው ትልቅ አቅም መፍጠር እንዲችሉ የማድረግ እሳቤ አለው። ግሉ ዘርፍ ላይ በጣም ያተኮረ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደምም መንግሥት የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ላይ ያለውን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ እየሰራ እንደነበር ሲገልጽ ነበር። ማሻሻያው ከዚህ ቀደም ከነበረው በምን ይለያል?
ዶክተር ኢዮብ፡- ከዚህ በፊት ከነበረው ትልቅ ልዩነት አለው። የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከዚህ ቀደም በግሉ ዘርፍና መንግሥት መካከል የነበረውን መጠራጠር ስሜት ይቀይራል። በጣም በመቆጣጠር ላይ ያተኮረ፤ ቋጠሮ መቋጠር ላይ ያተኮረ ነበር ቢሮክራሲው። እና ያንን ልክ አይደለም ከማለት ይጀምራል። ይሄ ትልቅ ለውጥ ነው። አንድ ነጋዴ አዲስ ሀሳብ አምጥቶ የተሻለ የምርት አቅርቦት ማቅረብ ከቻለ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ህጋዊ ሆኖ ገብቶ መስራት ከቻለ በጣም ጠቃሚ ነው።
ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የሚሰማራው ኦፕሬተር ወይም ጉሊት ምትነግደው ቸርቻሪ ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው። ይህ መበረታታት ነው ያለበት ፣ መደገፍ ነው ያለብን፤ ሰዎች ወደ ቢዝነሱ እንዲገቡ እናበረታታ እንጂ ፈቃድ ለማውጣት ወራትና ዓመታት ሊፈጅባቸው አይገባም የሚል ነው። ተግባርና ቃል ይለያያል ማለት ነው። በቃል ደረጃ ለዓመታት የግሉ ዘርፍ ሞተር ነው ሲባል ቆይቷል። በተግባር ግን ወደ መሬት ወርደህ ስታየው ፈቃድ ለማውጣት ይሁን፣ ለመስራት ይሁን በአጠቃላይ አዲስ ሀሳብ ለማምጣት ከባድ እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ነው።
አዲስ ዘመን፡- የውጭ እዳ መቀነስም የዚሁ ማሻሻያው አንድ ግብ ነው። እንዴት አድርጎ ነው በማሻሻያው የውጭ እዳ መቀነስ የሚቻለው?
ዶክተር ኢዮብ፡- ማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቱ አንዱ መገለጫ እየጨመረ የመጣ ከፍተኛ የእዳ ጫና መኖሩ ነው። ይህ ደግሞ የሀገራችንን የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት በእጅጉ የሚሸረሽር ነው። በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቱ ለኢኮኖሚ ጤናማነቱም አሳሳቢ ስለሆነ ይህንን መከላከል የግድ ነው የሚሆነው።
የእዳ ጫና ስናነሳ ደጋግመን እንደምናነሳው ከአጠቃላይ ሀገር ውስጥ ምርት መቶኛ ያለው ድርሻ ከፍተኛ ሆኖ አይደለም። ትልቁ ችግር የመክፈል አቅማችን ነው። የመክፈል አቅማችንን በጣም የጎዳው የውጭ ንግድ አፈጻጻማችን በጣም ደካማ መሆን ነው። ሁለተኛው ደግሞ የተበደርነው ብድር እና ተበድረን የጀመርናቸው ፕሮጀክቶች በጊዜ ባለማለቃቸው ባሰብነው ፍጥነት ውጤታማ ሆነው እዳውን ሊያስከፍሉን አልቻሉም።
ስለዚህ የዕዳ ጫናውን ለማቃለል አንዱ ትልቁ ትኩረት የምንበደረው ነገር ውጤታማ ነገር ላይ እንዲውል ማድረግ ነው። ሌላኛው የብድሩን ምንጭ አይነት መቀየር ነው። ማለትም ከፍተኛ ወለድና በአጭር ጊዜ የሚመለሱ ብድሮችን ትተን የረጅም ጊዜ ችሮታና አነስተኛ ወለድ ያላቸው ኮንሴሽናል ሎንስ የሚባሉትን ለይቶ ለመጠቀም ነው። ሌላው ደግሞ ወጪ ንግዳችን ላይ በጣም አጠንክረን በመስራት የወጪ ንግዱና አጠቃላይ የውጭ ሚንዛሬ ፍሰቱ፤ ይህን ስንል ከማዕድኑም፣ ከአገልግሎቱም ከቀረጡም ያለብንን እዳ በፍጥነት ለመክፈል የሚያስችለንን አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ቁመና መፍጠር ማለት ነው። ይሄ ነው ትኩረቱ የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡-ይህ መሆኑ ለብድር ዕዳ ቅነሳ እንዴት እገዛ ያደርጋል?
ዶክተር ኢዮብ፡- ይሄ አንደኛ ሲያስፈልገን መበደር የምንችል እንዲሆን በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለንን ታማኝነታችንን ያሻሽላል። ሁለተኛው የተዛባውን ማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን ያስተካክላል። ሦስተኛ እይታችንን ይቀይራል። ተበድረን የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች ጨክነን መጨረስ አለብን፤ የምንበደረው ለውጤት መሆን አለበት፣ ያለፈውን ክፍተት ማስተካከል አለብን የሚል እሳቤ ይዞ ስለመጣ በአጠቃላይ ከአጠቃላይ የእዳ ጫና ቅነሳ ረገድ የሚኖረው ማሻሻያ ከዚህ ረገድ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ምን ያህል ውጭ ብድር ነው ያለባት፤ በማሻሻያው ምን ያህሉን ለመክፈልስ የታቀደው?
ዶክተር ኢዮብ፡- ብድር የሚገለጸው አጠቃላይ ሀገራዊ ገቢ ያለው መቶኛ ድርሻ ነው። የውጭ ብድር የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት 31 በመቶ አካባቢ ነው። 31 በመቶ ማለት በጣም ከፍተኛ የሚባል አይደለም። 60 በመቶ፣ መቶ በመቶ እንዲሁም 200 ፐርሰንት ያለባቸውም አሉ። ትልቁ ነገር የመቶኛ ድርሻው ሳይ ሆን የመክፈል አቅም ነው።
የውጭ እዳ ቅነሳ እናደርጋለን ስንል ይህንን በሦስት ዓመት ውስጥ ከፍለን እንጨርሳለን አይደለም። አንዳንዶቹ ብድሮች የረጅም ጊዜ ብድሮች ናቸው። የብድር ስብጥሩን ብታየው ኮንሴሽናል የምንለው ለ10፣ ለ15 ወይም ለ20 ዓመት የምትበደረው አይነት ብድር አለ። ኮሜርሻል ብድሮች አሉ። ብድር መበደር የአንድ ኢኮኖሚ ጤናማነት መገለጫ ነው። መበደር በራሱ ችግር የለውም። ትልቁ ነገር በዚህ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ የተበደረችውን ብድር የምትመልስ የኢኮኖሚ ቁመና ያላት ሀገር አድርጎ መገንባት ነው ትኩረቱ እንጂ ያለውን ብድር በሙሉ ከፍሎ መጨረስ አይደለም።
ነገር ግን ባለፈው ሦስት ዓመት ብቻ ሳይከፈሉ የቆዩ በርካታ ብድሮች እንዲከፈሉ ተደርጓል። ባለፈው ዓመት ብቻ ለብድር ክፍያ ያወጣነው ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ነው። በጣም የተከማቸ ብድር የመክፈል ሥራ እንደተሰራ ያሳያል። ብድር የመክፈል ስራው እንዲሁ ይቀጥላል። ዋናው ትኩረታችን በሦስት ዓመት ውስጥ ብድር ከፍለን እንጨርሳለን ሳይሆን የብድር ጫናው እንዲስተካከል ነው። ብድር አጠቃላይ ካለው የውጭ ንግድና በየዓመቱ ከሚከፈለው ብድር አንጻር ነው።
አሁን 45 እስከ 50 በመቶ የሚሆነው ከወጪ ንግድ የሚገኘው የውጭ ሚንዛሬ ግኝት ለብድር ክፍያ የሚውል ነው። ይህንን ማውረድ ማለት ነው። የውጪ ንግዱን ከፍ አድርገን፤ ብድሮቹን ደግሞ አሸጋሽገን በ20 ወይም በ30 በመቶ የውጭ ምንዛሬ የሚገለጽ እንዲሆን ማድረግ ነው። ውጭ እዳ መቀነስ ማለት ያንን ማስተካከል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ማሻሻያው በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ያልቃል ተብሎ ነው የሚጠበቀው ?
ዶክተር ኢዮብ፡- ይህ የሦስት ዓመት የማሻሻያ ፕሮግራም ነው። በሦስት ዓመት ውስጥ በአጠቃላይ ያስቀመጥናቸውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን፣ የመዋቅር ማሻሻያውን፣ የዘርፍ ማሻሻያውን ጨርሰን ኢኮኖሚውን ጠንካራ መደላድል ላይ ከገነበን በኋላ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አራት ወይም አምስት ትላልቅ ኢኮኖሚዎች አንዷ እንድትሆን ይሠራል፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የእድገት አቅም ተሟጦ ወጥቶ የብልጽግና ጅማሮ የሚያደርግ በጣም መሰረታዊ የሆነ የማሻሻያ ስራ ነው።
እይታችንን፣ ፍላጎታችንና እሳቤያችንን በሙሉ የሚቀይር ነው የሚሆነው። ችግሮቹ ከተቀረፉና በየቦታው የተጣሉትን በርካታ ሀብቶች ማከማቸት ከቻልን ወደ ውጤት ካመጣነው የዚህ ሀገር ኢኮኖሚ በጣም ትልቅ የማደግ አቅም ያለው ስለሆነ ህዝቡ የአድገቱ ተጠቃሚ ስለሚሆን ቀጣይነት ባለው መልኩ የኢኮኖሚ እድገቱን ማስቀጠል ይቻላል። አጠቃላይ 10 ዓመት እይታ እንዳለ ሆነ ፕሮግራሙ ለሦስት ዓመታት የሚተገበር የማሻሻያ ፕሮግራም ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለማሻሻያው ምን ያህል በጀት ነው የሚያስፈልገው?
ዶክተር ኢዮብ፡- የማሻሻያውን ወጪ በተመለከተ ከልማት አጋሮች ጋር እንነጋገራለን። ይህን ያህል ያስፈልጋል ብለን አልገለጽንም። ባለፈው ከልማት አጋሮች ጋር ስንነጋገር አንዳንዶቹ በራሳቸው እስከ 10 ቢሊየን ብር ሊያወጣ ይችላል ብለው የገመቱ አሉ። እኛ አጠቃላይ እሳቤ ግን የሀብት ፍላጎቱ ከሀገር ውስጥም ከውጪም የሚመጣ ስለሆነ ከእያንዳንዱ የልማት አጋር ጋር ስለምንነጋገር አሁን ቁጥሩን ባልገልጽ እመርጣለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ኢዮብ፡- እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን መስከረም 8 / 2012
መላኩ ኤሮሴ