አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርድ አባላት በሙሉ ጊዜ እንዲያገለግሉ መታቀዱን የህግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ ጽህፈት ቤት የምርጫ ቦርድ መልሶ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች፤ ከምሁራንና ከመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ትናንት በኢሊሌ ሆቴል ምክክር አድርጓል፡፡
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህርና ረቂቁን ያቀረቡት ዶክተር ሲሳይ አለማየሁ እንደገለጹት፤ ረቂቁ የምርጫ ቦርድን የሚመለከተው አዋጅ ቁጥር 532/99 ለማሻሻል የተዘጋጀ ነው፡፡ አዋጁ እንዲሻሻል ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት በመንግስት በኩል ምርጫ ቦርድን እንደገና ገለልተኛ፣ተዓማኒና ቀልጣፋ የስራ አፈጻጸም የተላበሰ ተቋም ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ለማቋቋም ባለው ፍላጎትና ከተለያዩ አካላት በሚነሳው ጥያቄ መሰረት ነው፡፡
በረቂቁ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል የአባላቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታ አንዱ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በቦርዱ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ አካላት በትርፍ ጊዜያቸው ያገለግሉ የነበረ ሲሆን፤ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ የቦርዱ አባላት በሙሉ ሰዓት ቦርዱን እንዲያገለግሉ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ይህም አባላቱ በቦርዱ ስራ ላይ የተሻለ ተሳትፎ ኖሯቸው በቋሚነት የሀገሪቱን ምርጫዎችና የህዝብ ውሳኔዎች ለማስፈጸም ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር ሲሳይ ማብራሪያ፤ ቦርዱ ምርጫን ከማስፈጸም በተጨማሪ የስነ ዜጋ ትምህርት መስጠት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መመዝገብና ማስተዳደር፤ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ የመራጮችን ምዝገባ የማካሄድ ስልጣን ይሰጠዋል፡፡ ቦርዱ እስካሁን እስከ ክልል ድረስ ቅርንጫፍ የነበረው ሲሆን፤ ከክልል በታች በምርጫ ክልል ደረጃ ጽህፈት ቤት እንዲደራጅና ስራውን የሚያስተባብሩ ሰራተኞች እንዲኖሩት ታቅዷል፡፡
ረቂቅ አዋጁ አባላቶቹ እንዴት እንደሚመለመሉ? ከሀላፊነታቸው እንደሚነሱ? ስልጣንና ሀላፊነታቸው ምን እንደሆነ? በዝርዝር ማስቀመጡን የገለጹት ዶክተር ሲሳይ፤ አዋጁ ተቋሙ በቂ በጀትና ጊዜ ኖሮት በነጻነትና በገለልተኝነት ማሰማራት የሚያስችል ማዕቀፍ እንዲኖር የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉት አንዳንድ ባለድርሻ አካላት አዋጁን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ ከፊት ከነበረው የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ አንጻር ሲታይ እጅግ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት አመራር አቶ ገብሩ በርሄ እንደተናገሩት፤ ረቂቁ በፊት ከነበረው አዋጅ ጋር ሲነጻጸር ሰፊ ልዩነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ገለልተኛና ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለ አድልኦ እንዲያገለግል የሚያስችል ቦርድ ለማቋቋም የሚረዳ ነው፡፡
ሆኖም ረቂቁ የተለያዩ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑን አንስተዋል፡፡ የቦርድ አባላት ብዛት አምስት ብቻ እንዲሆን ሃሳብ መቅረቡ ተገቢ አይደለም፤ በተለይም በምርጫ ወቅት በርካታ ስራዎች ስለሚሰሩ እነዚህን ስራዎች ለመስራት የሰው ብዛት ያስፈልጋል፡፡ የቦርዱ የስራ ዘመን ዘጠኝ ዓመት መሆኑም ተገቢነት የለውም፡፡ ቦርዱ ቢያንስ ሁለት ምርጫዎችን እንዲያስፈጽም ከዘጠኝ ዓመት በላይ ሊቆይ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያዊያን አንድነት ዴሞክራሲ ድርጅት አመራር አቶ አድማሱ ሀይሉ በበኩላቸው፤ ህገ መንግስቱ ሳይሻሻል አዋጁ እንዲሻሻል መደረጉ ተገቢ አይደለም፡፡ ህገ መንግስቱ ሳይሻሻል አዋጁ እንዲሻሻል መደረጉ ለውጥ ለማምጣት አያስችልም፡ በመሆኑም በቅድሚያ ህገ መንግስቱ የሚሻሻልበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከምርጫ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች ህጎችንም ለማሻሻል እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን፤ በህጎቹ ላይ ያሉትን ክፍተቶችና ችግሮች ከተለያዩ መስፈርቶች አንጻር እየተገመገሙ መሆናቸውንም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2011
በመላኩ ኤሮሴ