
ቦንጋ፡- በመንግስት የአስተዳደር ስርዓት የከፊቾ ህዝብ ከውይይትና ምክክር ባለፈ መምራት ብቻ ሳይሆን መመራትንም በተግባር ያሳየና ለዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር ፍልስፍና ምሳሌ የሆነ ህዝብ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ከከፋ ዞን ማህበረሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት እንደተናገሩት፤ የከፋ የፍትህ ሥርዓትና የመንግስት አስተዳደር የሚበልጥ ብሄር፣ የሚያንስ ብሄር፣ የሚበልጥ ማንነት፣ የሚያንስ ማንነት፣ የሚበልጥ ባህል የሚያንስ ባህል አለመኖሩን ያሳየ፣ ኢትዮጵያዊነቱን የተገነዘበ መሆኑን ተናግረዋል።
ምክክር፣ ንግግርና ውይይት ያዳበረው ማህበረሰቡ በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊመሰከርለት የሚችል ስራን ተግቶ መስራትና አካባቢን ማልማት የሚያውቅ ትጉህ ህዝብ መሆኑን ተናግረዋል።
የከፋ ህዝብ ከሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮ ጋር መኖርን ያዳበረ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ለሌሎች ማህበረሰቦች ሰፊ ልምድ ሊሆን የሚችል እንደሆነ ተናግረዋል።
እንደአገር ያለብን ችግር የሚፈታው አፈሩን በማልማትና አንድነትን በማጠናከር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይ የከፊቾ ብሄር አፈሩን አልምቶ ተፈጥሮን በመንከባከብ ረገድ ያለው ጥንካሬ ምስክርነትን ያስገኘለት መሆኑንና ለአንድነቱም ከቀደምት ታሪኩ ከአጎራባች አካባቢዎች ጋር ተዋልዶ በአንድነት በመኖር የአገር አንድነት ፋይዳን ቀድሞ የተረዳ ህዝብ ነው ብለዋል።
በውይይት መድረኩ የልማትና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን በተመለከተ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልፀው፤ የክልል የመዋቅር ጥያቄን በተመለከተ ደግሞ ጥያቄው በአንድ ጊዜ የሚመለስ አለመሆኑንና ዞኑ ከክልሉ ጋር በመመካከርና ጉዳዩ በሚገባ ተጠንቶ ህዝቡ ካመነበት ለፌዴራል መንግስት ከባድ እንዳልሆነ፤ ነገር ግን ክልል በመሆን ጥያቄ ውስጥ የሚወሰዱ እርምጃዎች ጥንቃቄ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቀዋል።
የከፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው፤ የከፊቾ ህዝብ የተለኮሰው የአንድነት ችቦ ብርሃን እንዲሰፋ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ በለውጡ ማግስት በአገሪቷ አንዳንድ ችግሮች እየተስተዋሉ ቢሆንም የከፋ ዞን አልፎ አልፎ ለሚታዩ ውዥንብሮች ራሱን ያላጋለጠ መሆኑንና ወደፊትም ከመንግስት ጎን በመቆም ለውጡን እንደሚያስቀጥል ተናግረዋል።
አቶ ማስረሻ አያይዘውም አካባቢው በአረንጓዴ ልማት እምቅ ሀብት ያለው ቢሆንም በርካታ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ያሉበት መሆኑን ጠቁመው፤ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ማዕከል መሆን የሚችል አካባቢ ቢሆንም ሀብቱን በአግባቡ ሊጠቀምበት ያልቻለ ነው ብለዋል፡፡ ሲንከባለሉ የመጡ ሁለንተናዊ ችግሮችም በመንግስት በኩል መፈታት አለባቸው ብለዋል።
ትናንት በቦንጋ ከተማ በተደረገው ውይይት ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳና፣ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2012
አዲሱ ገረመው