ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲከተላቸው የነበረ ውን የዲዛይነርነት ፍቅር ማሳካት ችለዋል። እስከ ቻይና ድረስ ተጉዘውም ምርቶቻቸውን ለዓለም በማቅረብ ዝናን አትርፈዋል። በተለይም መልካቸው ላይ ለዛ ያለው አነጋገራቸው ሲታከልበት ጥሩ አምራች ብቻ ሳይሆን ጥሩ የማርኬቲንግ ባለሙያም አድርጓቸዋል።
የመግባባት ችሎታቸውን ተጠቅመው ያመረቷቸውን ምርቶችም በበርካታ የአፍሪካ አገራት ለማሻሻጥ እንዳልተቸገሩ ይናገራሉ። የሚያውቋቸው ደግሞ ጠንካራ ሰራተኛ መሆናቸውን እና ቁምነገር አዋቂ መሆናቸውን ይመሰክራሉ።
በሀገር ልጆች የተዘጋጁ አልባሳትን እና የቆዳ ምርቶችን በጥራት አቅርቦ እስከማስተዋወቅ የደረሰ ስራን ያከናውናሉ። በተለይ እራሳቸው በሚቀምሩት የዲዛይን ስራ በርካታ ደንበ ኞቻቸውን መሳብ ችለዋል። አሁን ላይ አስር የቆዳ መስፊያ እና ማዘጋጃ ማሽኖችን ይዘው ከእራሳቸው አልፈው ሰራተኞችን ቀጥረው እየሰሩ ይገኛል።
በቀጣይ ደግሞ የኢትዮጵያን ምርቶች በሰፊው ለዓለም ከማስተዋወቅ ባለፈ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የውጭ ምርቶችን እስከማስቀረት የሚደረስ አላማ ሰንቀው እየተንቀሳቀሱ ይገኛል። ወይዘሮ ጥሩወርቅ አሰፋ ይባላሉ የዛሬው እንግዳችን። ውልደትና እድገታቸው በደቡብ ኦሞዋ የቱሪስት መተላለፊያ ጂንካ ከተማ ነው። ቤተሰቦቻቸው በስራ ምክንየታት ወደጂንካ ጎራ ቢሉ የዛሬዋን ስራ ፈጣሪ ወልደው በዚያው ጥቂት ቆይተዋል። ወይዘሮ ጥሩወርቅም በልጅነታቸው ቦርቀው እና ከዕኩዮቻቸው ጋር ተጫውተው አድገዋል።
በልጅነታቸው ኔሪ የተሰኘው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው ዕውቀት መሸመቱን ሲያያዙት በወቅቱ የእጅ ስራዎችን መስራት እና ዲዛይኑ ላይ ማጤን ይፈልጉ እንደነበር ያስታውሳሉ። 8ኛ ክፍልን ጂንካ ከተማ ላይ እንደተማሩ ግን ወደሌላዋ የኢትዮጵያ ከተማ ማቅናታቸው አልቀረም።
አክስታቸው በደቡቧ ማዕከል ሀዋሳ ከተማ ላይ ጎጆ ቀልሰው ነበርና እርሳቸው ጋር ሄደው እንዲማሩ ቤተሰብ ላኳቸው። በሃዋሳም አዲስ ከተማ በተሰኘው ትምህርት ቤት ከ9ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ድረስ ሲማሩ አራት ዓመታትን አሳልፈዋል። 12ኛን ሲያጠናቅቁ ግን ተመልሰው ወደቤተሰባቸው ዘንድ ጂንካ አመሩ።
የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ውጤት ሳይታወቅም ወይዘሮ ጥሩወርቅ በአጋጣሚ የተገኘ ትዳር ውስጥ ገቡ። ባለቤታቸው ደግሞ ነጋዴ ነበሩና እርሳቸው ያቋቋሙት ወርቅ ቤት ውስጥ ወይዘሮ ጥሩወርቅ በሽያጭ ሰራተኝነት መስራት ጀመሩ። ሰራተኞችን በመቆጣጠር እና ንግዱን ፈር በማስያዝ መንቀሳቀሳቸውን ቀጥለዋል። ከሶስት ዓመታት የወርቅ ቤት ንግድ በኋላ ግን የጂንካው ህይወት አብቅቶ ከባለቤታቸው ጋር ለስራ ወደ ሀዋሳ አቀኑ።
በሀዋሳ ከተማ ዳግም ሲመለሱ ግን የጽህፈት እና ኮምፒውተር አገልግሎት ንግድ ለመጀመር ነበር ውጥናቸው። ሀዋሳ መሃል ፒያሳ ላይ የጽህፈት አገልግሎት የሚሰጥ አነስተኛ ንግድ ጀምረው መስራት እንደጀመሩ ጥሩ ማትረፍ ችለው ነበርና ንግዳቸውን እያስፋፉ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ እና ዋርካ የተሰኘው አካባቢ ስቴሽነሪ ሱቅ በመክፈት መስራት ችለዋል።
በወቅቱ ዘጠኝ ሰራተኞችን ቀጥረው ለበርካቶች የጽህፈት፣ የፎቶ ኮፒ እና ተዛማጅ አገልግሎቶችን ሰጥተዋል። በሃዋሳ ቆይታቸው ሶስተኛ ልጃቸውን እንደተገላገሉ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ለአዲስ ህይወት ጅማ ወደአዲስ አበባ መምጣት እንዳለባቸው ወስነዋል። እናም አዲስ አበባ ላይ በሚሊኒየሙ መጥተው ጎተራ ፔፕሲ የተሰኘው አካባቢ መቀመጫቸውን አድርገዋል።
ባለቤታቸው ደግሞ ቀድሞም ከወርቅ ንግዱ በተጨማሪ የኮንስትራክሽን ግንባታ ስራ ይሰሩ ነበርና ወይዘሮ ጥሩወርቅም ዘርፉን ለመቀላቀል ወስነዋል። እናም መዲናዋ ላይ ከባለቤታቸው የግንባታ ፈቃድ ውክልና ወስደው የኮንዶሚኒየም ግንባታዎችን ለመከወን ባለሙያዎችን ይዘው ጨረታዎች ላይ መሳተፍ ጀመሩ። እንዲሰሩ የተመደቡባቸውን የኮንዶሚኒየም ግንባታዎች በመከታተል እና ሰራተኞችን ተቆጣጥሮ በማሰራት አንድ ብለው የጀመሩት ግንባታ እስከ አምስት የደረሱ የኮንዶሚኒየም ህንጻዎችን እንዲገነቡ አስችሏቸዋል።
በአያት እና ቱሉ ዲምቱ ሳይቶች አራት ዓመታትን ሴትነታቸው ሳይበግራቸው ግንባታቸዎችን አካሂደዋል። በወቅቱ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ትዳራቸው ሊቀጥል ባለመቻሉ ከባለቤታቸው ጋር መለያየታቸው ግድ ሆነ። እናም የኮንስትራክሽን ስራውም ሲቀር ወይዘሮ ጥሩወርቅ ለተወሰኑ ጊዜያት የሚሰሩት ስላልነበራቸው አብዛኛውን ጊዜያቸውን ቤታቸው ውስጥ ያሳልፉ ነበር።
በቤት ውስጥ አብዛኛውን ጊዜያቸውም ማሳለፉን ያልመረጡት ወይዘሮዋ ስራን ሀ ብለው ለመጀመር አዲስ ሙያን መርጠዋል። የልጅነት ፍላጎታቸውን እውን ለማድረግ የዲዛይነርነት ሙያ ትምህርት ቤት ገብተው ጠንክረው መማራቸውን ተያያዙት። አንድ ትምህርት ተቋም ሁለት ዓመት ሌላው ጋር ደግሞ ስምንት ወር እያሉ የልብስ እና የቆዳ ስፌት እና ዲዛይን ሙያን አቀላጥፈው ተማሩ።
ለስራ ደከመኝ ማለትን የማይወዱት ወይዘሮዋ ታዲያ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ በጎን ደግሞ ሰባት ሺ ብር የሚያወጣ የልብስ መስፊያ ማሽን ገዝተው ስራ መጀመራቸው አልቀረም። ማሽኗን ይዘው ቤታቸው ውስጥ የሃገር ባህል ልብስ ሲያዘጋጁ ለቤተዘመድ እና ለጓደኞቻቸው ያቀርቡ ነበር። ገበያውን ሲያዩት ግን እራሳቸውን ችለው ቢሰሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ በማመን በአካባቢያቸው የሚገኝ ወረዳ ሄደው የመስሪያ ቦታ እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ አቀረቡ።
በወቅቱ ያለስራ የተቀመጠ ቦታ ነበርና ለወይዘሮ ጥሩወርቅ እንዲሰሩበት ሲሰጣቸው ጊዜ ባለማባከን በቀጥታ ስራቸውን ወደማስፋፋቱ ተሸጋገሩ። እራሳቸው የጀመሩት የልብስ ዲዛይን እና ስፌት ስራም እያደገ መጥቶ አራት ሰዎችን በመጀመሪያው ስድስት ወራት እንዲቀጥሩ እድል ፈጥሮ እንደነበር ያስታውሳሉ። በወቅቱ ደግሞ የቆዳ ቦርሳዎችን እና የተለያዩ ምርቶችን በጎን በማምረት ለገበያ ማቅረቡ ዋነኛ ስራ ነበር።
በስራ ላይ እያሉ ደግሞ በሱዳን የሚዘጋጅ የአምራቾች ኤግዚቢሽን መኖሩን ይሰሙና ባዛሩ ላይ ተሳትፈው ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ይወስናሉ። እናም ወደሱዳን አምርተው በእራሳቸው የተሰሩ አልባሳትን ሲያሳዩ የሱዳን ሸማቾች ግን በብዛት ትኩረታቸው የነበረው የቆዳ ምርቶቹ ላይ ነበር። በሱዳን ያለው የቆዳ ምርቶች ገበያ የሳባቸው ወይዘሮዋ ከጎረቤት አገር መልስ የሃገር ባህል ልብስ ስራውን ጋብ አድርገው ወደቆዳ ምርቶች ላይ ሙሉ ትኩረታቸውን አደረጉ። የቆዳ ምርቶችን ከባቱ እያስመጡ እራሳቸው በማዘጋጀት ጥራት ያላቸው ምርቶች መሸጡን ተክነውበታል።
በተለያዩ ጊዜያትም በዲዛይናቸው የተዋቡ የቆዳ ቦርሳ፣ ቀበቶ እና የተለያዩ ምርቶችን ወደሱዳን በመላክ ገበያቸውን ዓለም አቀፍ ማድረግ ችለዋል። ከሱዳን በተጨማሪ ቻይና ፣ ጂቡቲ እና ቦትስዋና በመጓዘ ምርቶችን እያስተዋወቁ ይሸጣሉ። በቤት ውስጥ የተጀመረው ምርት አሁን ላይ በመላው ዓለም እየተዳረሰ ይገኛል። በሳርቤት የሚገኘው ማምረቻቸው እራሳቸው እያሰለጠኑ ዕውቀታቸውን የሚያጋሯቸው ዘጠኝ ሰራተኞችን መያዙን ይናገራሉ።
አስር የቆዳ ምርቶች ማዘጋጃ ዘመናዊ ማሽኖችን ገጥመው ምርቶችን በየቀኑ ለገበያ ያቀርባሉ። ገበያ ከተገኘ በወር እስከ አንድ ሺ የሚደርሱ የሴት ቦርሳዎችን ማምረት እንደሚችሉ የሚገልጹት ወይዘሮ ጥሩወርቅ፤ የኢትዮጵያ ቆዳ ምርቶች በመላው ዓለም ተፈላጊ በመሆናቸው የገበያ አድማሳቸውንም ለማስፋት እያሰቡ መሆኑን ይገልጻሉ። በግል ጥረታቸው ባሳደጉት ስራ ገቢ እየተጠቀሙ የአገርንም ውጭ ምንዛሬ እያሳደጉ ናቸው። በየወሩ ከሚያገኙት ጠቀም ያለ ትርፍ በተጨማሪ ሁለት የቤት መኪናዎችን መግዛት እንደቻሉም ይናገራሉ።
በቀጣይ እቅዳቸው ደግሞ የተሻሻሉ እና በሰፊው ማምረት የሚያስችሉ ማሽኖችን በማስመጣት የቆዳ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ማምረት ነው። በተለይ ወደኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭ የቆዳ ምርቶችን ማስቀረት እስከሚቻል ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሰፊ የቆዳ ምርት ገበያ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል የሚሉት ወይዘሮዋ፤ የእርሳቸው ፍላጎት የሀገር ውስጥ ገበያን በማዳረስ ተወዳዳሪነታቸውን ዘርፈ ብዙ ማድረግ መሆኑን ያስረዳሉ።
ወደተለያዩ አገራት የሚላኩ ምርቶችን ጥራት ማሳደግ ስመ ገናና ፋብሪካ ገንብተው መስራት ደግሞ የረጅም ጊዜ እቅዳቸው ነው። ለእርሳቸው ስራ ከምንም በላይ ክቡር ነው። በመሆኑም በጠዋት ተነስተው ለምርት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማቅረብ ከሰራተኞቻቸው ጋር በጋራ ይሰራሉ። በዲዛይኑም ቢሆን ቤታቸው ውስጥ እንኳን ቁጭ በሚሉበት ወቅት ስራቸውን ለማዳበር መጣሩን አላቋረጡም። ነገር ግን ስራቸው አልጋ በአልጋ አለመሆኑን ሲያስረዱ የቆዳ ምርቶች ግብዓት እንደልብ አለመገኘቱ ለዘርፉ ስራ ፈታኝ መሆኑን አልደበቁም።
በተለይ ገበያ በሚበዛበት ወቅት ከፋብ ሪካዎች የሚመጣውን ቆዳ እስኪያገኙ ጊዜ እንዳያልፍባቸው ከመርካቶ ጭምር ግብዓት እየገዙ እንደሚሰሩ ይገልጻሉ። ይሁንና ያሉትን ችግሮች ተቋቁሞ መስራት ከተቻለ ውጤታማ ለመሆን እንደማይከብድ ነው የሚናገሩት። በተለይ ሴቶች በውስጣቸው ያለውን የስራ ፍላጎት በማጤን ወደተግባር ለመቀየር ማመንታት እንደማይኖርባቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ጥሩወርቅ የእርሳቸው የልጅነት ዲዛይነር የመሆን ፍላጎት አድጎ ወደቆዳው ኢንዱስትሪ እንደቀላቀላቸው ያስረዳሉ።
“ለስራ የተነሳሱ ልቦችን ከሰውነት አካላት ጋር በማጣጣም ንግድ ውስጥ አሊያም የተለያዩ ሙያዎች ውስጥ በመሳተፍ እራስንም ሆነ ሀገርን መጥቀም እንደሚቻል የእኔ ታሪክ ማሳያ ነው” ሲሉ ይገልጻሉ። ማንኛውም ስራ ትኩረት እና ፍላጎት ይጠይቃል። በየመሃሉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተቋቁሙ በጥንካሬ መስራት ከተቻለ በትንሹ የተጀመረ ስራ ትልቅ የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 3/2012
ጌትነት ተስፋማርያም