አዲስ አበባ፡- በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በተለያዩ ዘርፎች ላቅ ያሉ እድገቶች መመዝገባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ትናንት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የ100 ቀን ግምገማችን በተለያዩ ዘርፎች ላቅ ያሉ እድገቶች መመዝገባቸውን አሳይቶናል ብለዋል።
ይሁንና የእድገት አቅጣጫችን ከፊታችን የበለጠ ሥራ እንደሚቀረን ያመለክተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ስንተገብራቸው የቆየነው የተቋም እና የሲቪል ሰርቪስ ለውጥ ሥራዎች የእድገት ጥረታችንን በመደገፍ ላይ ይገኛሉ ሲሉ ገልጸዋል።
የሕዝብ አገልግሎቱ ዘርፍ አዲሱን የማብቃት ባሕል እንዲያሳድግ እና ሌሎችም ውጤታማ እንዲሆኑ እንዲደግፍ እጠይቃለሁ ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ለሁለት ቀናት ተካሂዷል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በተያዘው በጀት ዓመት የ8 ነጥብ 4 በመቶ እድገት የማስመዝገብ ውጥን መያዙን ተናግረዋል።
በ2017 የመጀመሪያው 100 ቀናት ተግባራዊ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተሻለ የኢኮኖሚ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ማድረጉም ነው የተገለጸው። ይህም የተቀመጠው እድገት እንደሚመዘገብ አመላካች ነው ብለዋል ሚኒስትሯ።
በተለይ በወጪ ንግድ፣ በመንግሥት ገቢ ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በውጭ ምንዛሬ ግኝት የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል። ከወጪ ንግድ አንጻር በተለይ በወርቅ ወጪ ንግድ እጅግ ስኬታማ ሥራ መከናወኑን አብራርተዋል።
ለአብነትም በ2016 በጀት ዓመት ዓመቱን ሙሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን 4 ቶን ብቻ እንደነበር የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ብቻ 7 ቶን ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱን ተናግረዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በአጭር ጊዜ ውስጥ ምን ያህል ለውጥ ማምጣቱን አመላካች ስለመሆኑ አብራርተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ በበኩላቸው፤ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሰፊ ዝግጅት ተደርጎበት በመተግበሩ ስኬታማ ሆኗል። በአጠቃላይ ያለፉት ሶስት ወራት አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚመዘገብ ያመላከተ መሆኑን ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም