
አዲስ አበባ፡- በ2012 የትምህርት ዘመን በመላ አገሪቱ የመፅሐፍት ስርጭትን ለማወቅ የሚያስችል በቴክሎጂ የታገዘ አሰራር ተግባር ላይ እንደሚውል ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።የተለየ ጥያቄ ካልቀረበ በስተቀር በበጀት ዓመቱ መፅሐፍት የማተም ዕቅድ የለኝም ብሏል።
በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ትግበራ ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አስፋው እንደገለፁት፤ በ2012 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች የመፅሐፍ ስርጭት በአግባቡ መድረስና አለመድረሱን ለማወቅ የሚያስችል ቴክኖሎጂ እንደሚተገበር ጠቁመዋል።መንግስት የተማረ የሰው ኃይል ለማሳደግና የአገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለማቃለል ከፍተኛ በጀት በመመደብ የመፅሐፍት ህትመት እያከናወነ ነው።
ይሁንና በአንዳንድ ክልሎች የመጽሐፍ ስርጭቱ ደካማ በመሆኑ ተማሪዎች እንደሚቸገሩና የአገሪቱ ሃብት እንደሚባክንም በክትትል ተደርሶበታል ብለዋል።
በበርካታ ክልሎች መጽሐፍት በንብረት ክፍሎች አሊያም ደግሞ በማከማቺያ ስፍራዎች ለረጅም ጊዜ ተከማችተው በመቀመጣቸው የመንግስት ልፋት በታሰበው ልክ ስኬታማ እንዳይሆን አድርጎታል።በተጨማሪም ከላይኛው እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር ቅንጅታዊ አሰራር ባለመዘርጋቱ መጽሃፍ ስርጭቱ በሚፈለገው መልኩ መከናወኑን ለማወቅ እንዳላስቻለ ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።በመሆኑም አዲስ አሠራር መተግበር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ አቶ እሸቱ ገለፃ፤ የመፅሃፍት ስርጭትንም ለመከታተል የሚያስችል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መተግበር አስፈላጊ በመሆኑ በ‹‹ባርኮድሪደር›› በመታገዝ መፅሀፍቶቹ በተማሪዎቹ እጅ ስለመድረሳቸው ለማረጋገጥ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ እንደሚውል አረጋግጠዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ በየዓመቱ ከተማሪዎች ቁጥር አኳያ ስምንት በመቶ ጭማሪ እየተደረገ የመፅሃፍት ህትመት ሲከናወን መቆየቱን አስታውሰው፤ በዚህ ዓመት ግን የተለየ ጥያቄ እስካልቀረበ ድረስ አዳዲስ የመፅሃፍት ህትመቶች እንደከዚህ ቀደሙ እንደማይከናወኑ ገልፀዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶኤፍሬም ሽመልስ በበኩላቸው በ2012 በጀት ዓመት ለትምህርት ከደረሱ 7ነጥብ3 ሚሊዮን ህፃናት መካከል 6ነጥብ3 ሚሊዮን የሚሆኑት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ይጀምራሉ።2ነጥብ4 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ አንደኛ ክፍል የሚገቡ ናቸው።
1ነጥብ9 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ወይንም ከስምንተኛ ወደዘጠነኛ ክፍል ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።በመሆኑም እነዚህን የአገር ተረካቢ ህፃናት የሚያስፈልጋቻውን ድጋፍና የግብዓት አቅርቦት ማመቻቸት መንግስት ትኩረት የሰጠው ጉዳይ ነው።ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን የመማሪያ ግብዓቶች የማሟላቱ ሂደት በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ባለሙያው እንዳሉት፤ አዲሱ ትምህርት ፖሊሲን መሻሻል ተከትሎም በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ በሰፊው ይሰራል።በተለይም ደግሞ የዳስ ትምህርት ቤቶችን በዘመናዊ ህንፃዎች ለመቀየር ሚኒስቴሩና የክልል መንግስታት በቅንጅት እየሰሩ ይገኛሉ።በተጨማሪም በ2011 በጀት ዓመት አልፎ አልፎ ሲከሰቱ የነበሩ ግጭቶች
የመማር ማስተማር ሂደቱን ማስተጓጎላቸውን አስታውሰው፤ በዚህ በጀት ዓመት ችግሮቹን ለማቃለል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር መደረጉንና የተሻለ የትምህርት ዘመን ለማድረግ መታቀዱን ገልፀዋል።የተማሪ መፅሐፍ ጥምርታም በትምህርት ዘመኑ በተሻለ ሁኔታ እንደሚከናወንና ይህንንም ለመከታተል የሚያስችሉ ዘመናዊ አሰራርና ቴክኖሎጂን ማዕከል ያደረጉ ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷው በሰፊው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ እቅድ መሠረት መስከረም12 ቀን 2012 ዓ.ም በመላ አገሪቱ ትምህርት የሚጀመርበት ሲሆን፤ በሁሉም ሥፍራዎች መምህራን ሥራ እንዲጀምሩ አቅጣጫ መቀመጡን ገልፀዋል።በበርካታ የአገሪቱ ስፍራዎችም የተማሪዎች ምዝገባ እየተጠናቀቀ መሆኑን አቶኤፍሬም አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር