
ሰላምና ዴሞክራሲ ለብልፅግና መዳረሻ መንገዶች ናቸው። ባልበለፀገ ኢኮኖሚ ውስጥ ዘላቂነት ያለው ሰላምና ዴሞክራሲ ማስፈን አዳጋች ነው። ለዚህም ሲባል ነው በፅኑ መሰረት ላይ የቆመ፣ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ መገንባት ያስፈልጋል የሚባለው።
በብልፅግና ውስጥ ሰላምን ማረጋገጥና መጠበቅ፣ የዴሞክራሲ ባህልን ማጎልበት፣ ሀገራዊ አንድነት ማጠናከርና ማስቀጠል፣ ኢኮኖሚን በጠንካራ መሰረት ላይ ማኖር፣ ፍትህን ማረጋገጥና ሀገራዊ ክብርን መቀዳጀት እንዲቻል ሀገራዊ ልማት መሰረታዊ ጉዳይ ነው። የማንኛውም አገር ዓላማና ግብ እንዲሁም የሁሉም ህዝቦች ተስፋና ህልም የበለፀገ ኢኮኖሚ፣ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነው። ከዚህ አንጻር ከተመዘነ ከአርባ ዓመታት በላይ ያስመዘገበው የኢትዮጵያውያን ትግል እስካሁን በጠንካራ መሰረት ላይ አልቆመም።
ይህም ብቻ አይደለም። ለዘመናት የቆየው የዴሞክራሲ ጥያቄና ትግል ህዝቦችን ማዕከል ባላደረጉ ፍላጎቶችና የአገርን እድገት በማያረጋግጡ ትልሞች ለመዝለቅ በመሞከራቸው አብዛኞቹ ምኞት ሆነው ቀርተው እዚሀ ደርሰናል። የቅርቡ ሁኔታ ደግሞ ሰላማችንን አደጋ ላይ ጥሎታል። የሰላም መደፍረስ የዴሞክራሲን ጥያቄ ያዳፍናል። የህዝቦችን አንድነትም ያናጋል። የአገርንም እድገት ወደኋላ ይጎትታል፤ ለድህነትም ያጋልጣል። በአንጻሩ ህዝቦች በአንድነት ተባብረው የቆሙ እንደሆነ በመካከላቸው ንፋስ አይገባምና በዙሪያቸው ሰላም ይሰፍናል።
ሰላም ባለበት ሁሉ ሰክኖ ማሰብ ይቻላልና ስለእድገት መነጋገር፣ ስለየጋራ ጥቅም አጀንዳ አስቀምጦ መወያየት ይለመዳል። ይህ የሃሳብ ፍጭትና ተሰባስቦ የመነጋገር ልምድ በዋናነት የሚጠይቀው መደማመጥን ነው። የዴሞክራሲ ስርዓት የባህል ህንጸት ነው። በውስጡ ሰጥቶ መቀበልን፣ መከባበርን፣ ባይሰጡም የሰዎችን ሃሳብ እውቅና መስጠትን ይጠይቃል። ያስለምዳል። መነሻው የጋራ ጉዳይ ይሆንና ልዩነት የሚኖረው ጥቅሙን በማረጋገጫው አካሄድ ላይ ብቻ ይሆናል።
ለህዝባችን መለወጥና ለሀገራችን እድገት መትጋት ያላትን ተፈጥሮአዊ ሀብት በትክክል እንድትጠቀም ማድረግ ደግሞ ሀገሪቱ በሁሉም መስክ እያስመዘገበች ያለችውን ለውጥ በፅኑ መሰረት ላይ የቆመ እንዲሆን ያደርገዋል። የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት የተፋጠነ ማድረግ ወደ ብልፅግና ለምታደርገው ጉዞ ወሳኝ ከመሆኑም በላይ ለሀገሪቱ ህልውናም ጭምር መሰረታዊ ነገር ነው።
የሀገር ግንባታ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚቀጥል፤ በሀገራዊ አንድነት እሳቤ የሚፀና ነውና ሁሉም ዜጋ ሀገራዊ ሀላፊነቱን በትክክል እንዲወጣ ስለ ሀገር የሚያስብና ሀገሩን የሚወድ መሆኑ ይገባዋል። ሀገር ወዳድ ዜጋ ለሀገሩ ለውጥ ያለ እረፍት ይሰራል፤ ለብልጽግናዋም ይታትራል።
ለሀገር ልማትና ብልፅግና ወሳኝ ከሆኑ መሰረታዊ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ሰላም ነው።
የሰላም እጦት የእርስ በርስ አለመግባባትና ግጭት ወደ ኋላ የሚመልስና ውጤቱም አሉታዊ የሆነ መጥፎ ገጠመኝ ነው። ለሰላም መረጋገጥ ደግሞ መነጋገር፣ መደማመጥና በተሻሉና ሀገርን በሚለውጡ ገንቢ ሀሳቦች ላይ መግባባት ያስፈልጋል። አንዱ ወገን ሌላኛውን መውቀሱ፤ አንዱ ተነስቶ ሌላኛውን ለመጣል ማሰቡ ለሱም ምቾት አይፈጥርለትም። እንደ ሀገርም ተሸናፊነት ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን የችግሮቻችን መፍትሄ ያለው በእኛው እጅ ላይ ነው። ተቀራርበን በጉዳዮቻችን ላይ እንነጋገር፤ በምናነሳቸው ሀገራዊ ሁኔታዎች እንግባባ፤ በተለያዩ ሃሳቦች ላይ እንደራደር፤ ያኔ የገዘፈ የሚመስለን ልዩነታችን ይጠብባል ብሎም የሚለያየን ነገር ይቀረፋል። ልዩነታችን የሰፋ ቢሆን እንኳን አንደኛችን የሌላውን ተቀብለንና አክብረን በልዩነት ውስጥ በፍቅር እናድራለን።
የትኛውም ትውልድና አገር አንድ ዓይነት አመለካከት ብቻ ኖሮት አያውቅም። እንደማህበራዊ ውቅራችን ሁሉ አስተሳሰባችንም ይለያያል። ልዩነት በራሱ የተሻለና የነጠረ፣ ሀገርን ገንቢ፣ ብልፅግናን አቅራቢ ሃሳብ ለማመንጫት ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራል። በዚህ ላይ ሀገራዊ አንድነት ማጎልበትና ማህበረሰባዊ ግንኙነትን ማጠንከር ደግሞ ወደፊት በሀገር ደረጃ ሊደረስበት ለታቀደው የልማት ግብ ምቹ መደላደልን ይፈጥራል። ይህ ደግሞ አንዱና ዋነኛው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አንጓ ነው።
ዴሞክራሲ የሃሳብ ብዝሀነት መገለጫ ነው። ዴሞክራሲ መደማመጥንና ሆደ ሰፊነትን ማጎልበቻ ነው። ይህ ሁሉ የሚያሳየን ታዲያ፤ አገርን ወደብልጽግና ማማ ለማውጣት፤ በህዝቦች መካከል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ገንብቶ የህዝቦችን የስልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ፣ አንድነታቸው ህብረታቸው የጠነከረ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት የሚስተናገዱባት ዳር ድንበሯ የታፈረ፣ ሰላም የሰፈነባት አገር በመሻት ወይም በመሰጠት አለመገኘቷን ነው። ይልቁንም እንዲህ ያለችቱ አገር የምትገኘው በአዲሱ አገራዊ የመደመር እሳቤ አንድ አገራዊ ራዕይ ሰንቀን በጋራ ስንቆም ብቻ ነው።
እናም በአዲሱ ዓመት አዲስ አዕምሮ ሊኖረን አዲስ አስተሳሰብም ልንላበስ ይገባናል። የዘንድሮው አዲስ ዓመት ከቁጥር መጨመር በዘለለ በውስጣችን ለውጥ ተፈጥሮ ከቂም፣ ከጥላቻና ከዘረኝነት ጸድተን፤ በፍቅርና በይቅርታ ተሞልተን ለአገር ልማትና ብልጽግና፣ ለህዝቦች አንድነትና ልዕልና የምናስብበት፤ ይህንንም በተግባር ለመግለጽ የምንነሳበት ዓመት ሊሆን ይገባዋል። በስድስቱ የጳጉሜን ቀናት እንደአንድ አስበን በህብረት የተጋራናቸውን ጽንሰ ሃሳቦች በውስጣችን አሳድረን፤ ሰላምና ፍቅርን በመካከላችን አስፍነን ጠንካራና ዘላቂ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት እንነሳ!
አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም