ሁሉም ሰው በአንድ ወቅት ሕፃን ነበር፤ ያ የተፈጥሮ ሂደት ነው። በአካልም ሆነ በአዕምሮ ለጋ ሙሉ በሙሉም በሰዎች (በወላጅ ወይንም በአሳዳጊ) ጥበቃ ሥር ሆኖ ማደግን የማያውቅ የሰው ፍጡር የለም።
“ክፉና ደግ መለየት የማይችሉ ህፃናት ገና በለጋ ዕድሜያቸው ካልተቃኑ በወደፊት ህይወታቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ማስከተሉ የማይቀር ነገር ነው” ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች፤ የዕድሜ ደረጃ የአንድ ሰው ሁለንተናዊ ዕድገት መሠረት የሚጣልበት መሆኑን ሲያጠይቁ፤ ህፃናት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የሚደርሱባቸውን ጥቃቶች ለመከላከልም ሆነ ራሳቸውን ለመጠበቅ በአካልም ሆነ በአዕምሮ ዝግጁ እንዲሆኑ ከፍተኛ የሆነ የአስተዳደግ ክትትል እንደሚያስፈልጋቸውም ይናገራሉ።
የማኔጅመንት ባለሙያና በቤተሰብ ህይወት አማካሪ የሆኑት አቶ ቃለክርስቶስ ኃይሉ እንደሚሉት፤ የህጻናት ማንነት የሚቀረጸው ባደጉበት ማህበረሰብ ውስጥ ነው። ልጆች በሚያድጉበት ጊዜ በአንድ ቤት ውስጥ የተለያየ አስተሳሰብ ሲኖር ያንን አስተሳብ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተጨማሪ አስተሳሰቦችን ሊያስተናግዱ ይችላሉ። የሀሳብ ልዩነቶች ለህጻናት በሚመጥን መልኩ መሆን አለባቸው። ህጻናት በቤተሰብ ውስጥ ሊያዩት የሚገባው አስተሳሰብ የጋራ የሆኑ እሴቶችን ሊያንጸባርቁ የሚችሉትን ነው። በውጭ ሊያከብሩት የሚገባውን ነገር በቤት ውስጥ ሊያገኙም ይገባል። በበጎ መልኩ የተቀነበበ የሀሳብ ብዝኃነቱን ቤት ውስጥ ማግኘት የሚችሉ ህጻናት ንጹህ ህሊናና ጽዱ አዕምሮ ኖሯቸው ማደግ ይችላሉ። ሲያድጉም የተለያዩ አስተሳሰቦችን ማስተናገድ የሚችሉ ይሆናሉ። ሲያድጉ ሌሎችን እንዲያከብሩ የሚያደርግ ድልድይ መስራት ያስፈልጋል። በመሆኑም፤ በቤት ውስጥ የሚንጻበረቁ አስተሳሰቦች የአንዱን ኮናኝ የአንዱን የበላይ የሚያደርግ ሳይሆን በመከባበርና መደማመጥ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት።
ጤናማ ሀሳብ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ማህበረሰብ አካባቢያችን የተቀበለው መሆኑን የሚናሩት አቶ ቃለክርስቶስ፤ የጤናማ አስተሳሰብ ፍልስፍና በህብረተሰቡ ውስጥ በእምነትም በመንፈሳዊ አስተምሮም ተቀባይነት ያገኘ መሆኑንና በህግ ከተደነገገው የሥነ ምግባር መር ጋር የማይጻረሩ ናቸው በማለት፤ መነሻቸውም ማህበረሰቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ እነዚህን እውቅና ያገኙ በጎ ምግባራትና እሴቶች በህጻናት አዕምሮ ውስጥ እንዲሰርጹ ማድረግ ቀዳሚው ተግባር እንደሆነ ይገልጻሉ። ታዳጊዎች ይህንን እንዲገነቡ ደግሞ ቤተሰብ አስቀድሞ ነገሩን መገንዘብ እንዳለበት ይመክራሉ።
ወይዘሮ ገነት የማነ በትምህርት ተቋማት ዙሪያ የትምህርት ባለሙያ ናቸው። “ቤተሰብ ልጁን በስነ ምግባር፤ በተለያዩ ስልቶች እንደሚገነባው ሁሉ ቅብብሎሹ ግን እስከ ትምህር ቤተ ደረጃ ድረስ መሆን ይኖርበታል፤ ሲሉ የትምህርት ተቋማትና የቤተሰብ ትስስር መጉላት እንዳለበት ያስገነዝባሉ። በተለይም ለህጻናት ምቹ ሆኖ ማደግ ትምህርት ቤቶች ለህጻናት ከሚያስፈልገው ሥነ ልቦናዊ የአስተዳደግ ዘዴ ባሻገር በቁሳዊ ነገሮች ላይም ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ይናገራሉ።
ልጆች የ“እችላለሁ” መንፈስ በውስጣቸው እንዲዳብር በሚገባቸው ነገር ማስተማር እንደሚያስፈልግ የሚመክሩት ወይዘሮ ገነት፤ “ትምህርት ቤት ግልጽ ሆነው በተዘጋጁ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች መደራጀት እንዳለበትና፤ በክፍል ውስጥ የሚገኙ ዕቃዎች ቦታቸውን በአግባቡ ካገኙ ክፍሉ ምንጊዜም ለሕፃናት መልክና ሥርዓት ያለው ሆኖ እንዲታያቸው ይሆናል” ይላሉ። ይህና መሰል ምቹነት ያላቸው ሁኔታዎች ልጆች በሁሉ ነገር ምጡቅ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።
ወይዘሮ ገነት፤ “የግብረ ገብነቱ እሳቤ ደግሞ ከቤተሰብ አልፎ በትምህርት ቤት ውስጥ ሊዳብር ይገባል። የትምህርት ተቋማት በተለይ መልካም እሴቶችን ማስተማር ብቻ ሳይሆን እንደ ባለቤትነት መያዝ ይኖርባቸዋል። ቤተሰብ የሚመክረውን ካልኖረው ልጆች ሊኖሩት እንደማይችሉት ሁሉ፤ ትምህርት ቤቶችም የሚያስተምሩትን በተግባር ማሳየት ይኖርባቸዋል። የእያንዳንዱ ትምህርት ተቋም ማህበረሰብ ለተማሪዎች የሚመጥን መልካም አርዓያነታቸውን መግለጥ አለባቸው። የሥነ ሥርዓት ደንቦችን ከቀረፅን በኋላ ለተግባራዊነታቸው በአቋማችን መፅናት ይጠበቅብናል። አለበለዚያ ማስተማሩ ብቻውን ለውጥ አያመጣም” በማለት ያብራራሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የሕፃናት ባህሪይ ትክክለኛ መስመር እንዲይዝ የመምራትና አቅጣጫ የማሳየት ጉዳይ ነው። በመሆኑም ልጆች ትምህርት ቤት የሚሄዱት ሊማሩ እንጂ ሊፈረድባቸው አይደለም። ሌላ ሰው ለመሆን ከመማቀቅ መውጣት አለባቸው። ፈተናዎች አለማወቅን የሚያሳዩ መሆን የለባቸውም። ህጻናት ራሳቸውን እንዲያገኙ መፍቀድም ይገባል።
በግለሰብ ደረጃ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ሰብለ ሀይሉ በበኩላቸው፤ የሰው ልጅ በህይወቱ ስኬታማ ይሆን ዘንድ ወሳኝ የሆኑት አዕምሮን የማጽዳት ተግባራት ሲሆኑ፤ ይህም ከህጻንነት ዕድሜ ጀምሮ ሊሠራ የሚገባው ነው። በተሰማሩበት የህይወት ደረጃ አስተሳብን ማጽዳትና ስሜትን መረዳት ቤተሰባዊ ከሆነው የኑሮ ደረጃ ይጀምራል። ሰው ከቤተሰብ ጀምሮ የራሱን ማንነት ሊያዳብር ይገባዋል። በቤተሰብ የሚዘራውን መልካምነት የሚያዳብረው ደግሞ ትምህርት ቤትና አካባቢ ነው ይላሉ።
ወይዘሮ ሰብለ እንደሚሉት፤ የራስን ማንነት ከሚጎዱ ነገሮች መካከል አንዱ መልካም ያልሆነ ቤተሰባዊ ግንኙነት ነው። ስድብ፣ ክርክር. ጭቅጭቅና መሰል አሉታዊ ጉዳዮች በቤት ውስጥ ሲስተዋሉ ልጆች ይህንን እኩይ ባህሪይ ይዘው ከማደጋቸው ባሻገር የበታችነት ስሜት እንዲሰማቸውም ያደርጋል። በመሆኑም በፍርሀት፤ በጥርጥሬና በስጋት ሊያድጉ ስለሚችሉ ከሁሉ በላይ ፍቅር መስጠት ያስፈልጋል።
“ዓይናችንን ብንገልጥ በምንኖርበት አካባቢ በቀላሉ እንደ ባህልና ልምድ የተቀበልናቸው በርካታ የሰውን ልጅ ህልውና የሚያቃውሱ ብዙ ድርጊቶችን እናገኛለን። ጉዳዩን በእኔነት መንፈስ በመመልከት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት” ብለዋል ወይዘሮ ሰብለ፤
አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲሱ ገረመው