ምድሩ በአደይ አበባ ተውቦ፤ ሰማዩ ከሉን ገፍፎ ተስፋ ሰጪ ብርሀን የሚታይበት፣ በወፎች ጥዑም ዜማ የታጀበ አዲስ ቀን የሚበሰርበት፣ ተስፋ የሚሰነቅበት አዲስ አመት ለኢትዮጵያና ለኢዮጵያውያን ልዩ ነው። ይህች ለምለምዋ ሀገር ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ውበት ታጅባ ዘመንዋን የምትሻገርበት ነው። ተፈጥሮ ያስዋባት ማህፀን ለምለምዋ ምድር ኢትዮጵያ አዲስ ተስፋ ሰንቃ አዲስነትን ናፍቃ አዲስ ዘመኗን ጀመረች። ዘመኗን በራስዋ ስሌት የምትቀምር የውብ ባህል ባለቤት ሀገር ኢትዮጵያ አዲስ ዘመኗን በብሩህ ተስፋ ተቀበለች።
ሀገራዊ ለውጥ ተናፋቂ በዘመን ቅማሬ የሚታሰበው ለውጥ ተጠባቂ ነውና በአዲሱ አመት የሚታሰበው በጎ ለውጥ ሀገርም ህዝብም የሚናፍቀው ነው። በዘመኑ መታደስ ውስጥ እኛነታችን ይገኝ? ወይስ እኛ ቀድመን ታድሰን አዲሱን ዘመን እንቀበል? የዘመን መለወጥ ነው ሰዎችን የሚለውጠው? ወይስ ሰዎች ናቸው ዘመንን የሚለውጡት? የዘመን ለውጥ ግንባር ቀደም ተዋናዩ ሰው፤ አሻጋሪው ደግሞ ጊዜ ነውና የለውጡን ሂደት ማን ይምራው ለሚለው ሃሳብ አፅንዖት መስጠት ይገባል።
ወጣት ሀብታሙ ዱጉማ የስነ ልቦና ባለሙያ መምህር ነው። ዘመንን አዲስ የሚያደርገው የኛን የአዲስነትና የለውጥ ፍላጎት መሆኑን ያስረዳል። ባልተለወጠ አስተሳሰብ ውስጥ የዘመን መታደስ ፍሬ አልባ እንደሆነ የሚያስረዳው ሀብታሙ፤ የዘመን ተሀድሶ በሰዎች ለውጥ እና የአስተሳሰብ አድማስ ስፋት ልክ የሚደምቅ መሆኑን ይናገራል።
ባለሙያው ከዘመን ቀድሞ የሰው አስተሳሰብ መለወጥና መቅደም የሚገባው ዋንኛ ጉዳይ መሆኑን ያምናል። የሰው ልጅ በለውጥ ላይ ተገኝቶ በጊዜ ዑደት የሚቀያየረውን ዘመን መምራትና መለወጥ የሚገባው መሆኑንም ያምናል። የተሻለ ዘመን ላይ ለመድረስ የተሻለ ሃሳብ ወሳኝ ነው የሚለው ሀብታሙ፤ በአስተሳሰብ ከተለወጥን የዘመኑን ለውጥ ማድመቅ የሚቀልል መሆኑን ይናገራል።
አዲሱ ዓመት የተሻለ ለውጥ ለማምጣት መንገድ ሊሆን የሚችልና እራስን ለለውጥ ማዘጋጃ መንገድ ሊሆን እንደሚገባው የሚገልፀው ባለሙያው ሀብታሙ፤ ለውጥ በራሱ በሰዎች አጠቃላይ ሁኔታ የሚመራ እንደመሆኑ መጠን የወቅት መለዋወጥ አሊያም ደግሞ የዘመን መቀያየር ከሰዎች ሁለንተናዊ ለውጥ ጋር ካልተጣጣመ ለውጥነቱ ዋጋ ያጣል።
ዘመን የሚታደሰው ሰዎች ሲታደሱ መሆኑን የሚናገረው ሀብታሙ፤ እራስን ለለውጥ አዘጋጅቶ አዲስ ዘመንን መቀበል በአዲስ ለውጥ ላይ ለመገኘት የሚረዳ መሆኑን ይጠቁማል። እንደ ሀገርም አዳዲስ የለውጥ ሃሳብ ለመቀመርና ለውጥ ለማምጣት በአስተሳሰብና በአመለካከት ተለውጦ መገኘት የሚገባ መሆኑን ያስረዳል።
አለምነህ ፀጋ የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያ ነው። ሁለተኛ ዲግሪውን በማህበረሰብ ሳይንስ ያጠናቀቀው አለምነህ የለውጥ መሰረቱ ሰዎች መሆናቸውን ይናገራል። የዘመን ለውጥ በራሱ ምንም ነው የሚለው አለምነህ የቁጥሩ መቀያየር በሰዎች መለወጥ ውስጥ የማይለካ ከሆነ ውጤት አልባ መሆኑን ያስረዳል። እንደ አለምነህ፤ ለውጥ የሚለካው በሰዎች በጎ አስተሳሰብ እና በዚያ በጎ እሳቤ ውስጥ በሚፈጠሩ በጎ ተፅዕኖዎች ነው ።
ዘመንን ሰዎች በፈለጉት መልኩ ሊሰሩት፤ የተሻለና የለውጥ መንገድ ሊያደርጉት እንደሚችሉም ያስረዳል። አዲስ አመት በሰዎች ስነ ልቦና ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር የሚያምነው አለምነህ፤ ሰዎች ዘመኑ በራሱ አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል የሚል እምነት በውስጣቸው ያሳድራል። ነገር ግን፤ “የጊዜውን ለውጥ የሚመሩት እራሳቸው ሰዎች ናቸው።” በማለት ሃሳቡን ይገልፃል። ዘመንን በሚፈልገው መልኩ የሚሰራው ሰው ነውና እራሱ ቀድሞ ተለውጦ ዘመኑን ካልቀየረ የወቅቱ መለዋወጥ ብቻ ትርጉም አልባ መሆኑን ያስረዳል። ከዘመን መቀየር ጋር የሚታሰቡ ትልልቅ ሀገራዊ ለውጦችን በተሻለ ደረጃ ለመምራት ማህበረሰባዊ ለውጥ ትልቁ መሰረት መሆኑንም ያምናል።
አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም
ተገኝ ብሩ