አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም እ.አ.አ በህዳር 2018 የኢትዮጵያን መንግስት ዋቢ በማድረግ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውስትራሊያና በአፍሪካ ይኖራሉ። እነዚህ ዜጎች ለሀገሪቱ ብልጽግናና እድገት እያደረጉት ያለው ተሳትፎ ግን ከቀን ወደ ቀን መሻሻሎች ቢኖሩትም ዛሬም በሚጠበቀው ደረጃ አይደለም። በመሆኑም ዳያስፖራው ማህበረሰብ ያለውን እውቀት፣ ሀብትና ልምድ ለሀገር ብልጽግና ለመጠቀም የተጠናከረ ስራ መስራት እንደሚጠበቅ ምሁራንና የሚመለከታቸው አካላት ያሳስባሉ።
“ኢትዮጵያዊ የማይገኝበት ሀገር የለም፤ እያንዳንዱ ዳያስፖራ ደግሞ ሁኔታዎች ከተመቻቹለት ለሀገሩ የሚያበረክተው የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በመሆኑም መንግስትና የሚመለከታቸው ተቋማት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ሳይቀዛቀዝ እንዲቀጥል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል” የሚሉት በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ዘላለም እጅጉ ናቸው። ዶክተር ዘላለም እንደሚያብራሩት፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሀገር ቤት ካለው በተሻለ ሀብት ለማፍራት፣ ለእውቅትና ለቴክኖሎጂ ቅርብ ናቸው። ይሄንን አቅም በተናጠል በግለሰብ ደረጃም ሆነ በቡድን በመሆን ወደ ሀገር ማስገባት ቢቻል ሀገሪቱን ለማበልጸግ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
ስለ ሀገር ብልጽግናና እድገት ሲታሰብ የተማረ የሰው ሀይል ቀዳሚው ጥያቄ ነው የሚሉት ዶክተር ዘላለም፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩ ብዙ ምሁራን ቢኖሯትም ሀገር ቤት ገብተው የሚያስተምሩት ወይንም ከሚሰሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የትምህርት እድልና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር የሚሰሩት ከቁጥራቸው አንጻር ጥቂቶች ናቸው ይላሉ። በመሆኑም፤ መንግስት የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግሩ እንዲስፋፋ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳስባሉ።
በአንጻሩ፤ “ብዙ መስራት የሚጠበቅበት ቢሆንም የውጭ ምንዛሬ በማስገኘቱ በኩል ያለው የዳያስፖራ ተሳትፎ ያሉበት ችግሮች እንዳሉ ሆኖ ከአመት አመት ለውጥ የሚታይበትና አበረታች ነው።” የሚሉት ዶክተር ዘላለም፤ ለዘመድ አዝማድ እየተባለ የሚላከው የውጭ ምንዛሬ በአንድ ወቅት ሀገሪቱ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ ልካ ከምታገኘው በላይ ደርሶ እንደ ነበር በመግለጽ ያን ያህል አስተዋጽኦ አበርክቷል የተባለው በመደበኛ መንገድ የገባው ነው። ከዚያ ያልተናነሰ፤ ምናልባትም የሚበልጥ ደግሞ በተለያየ መንገድ በጥቁር ገበያ የሚንቀሳቀስ እንዳለ ይጠቁማሉ። “ላኪዎቹ በተሻለ ወጪ ሀገር ቤት ማድረስ ከቻሉ ወደ ኢህጋዊ እንቅስቃሴ ሊገቡ አይችሉም” የሚሉት ዶክተር ዘላለም፤ ወደ መደበኛው መስመር ለማስገባትና ለመቆጣጠር በተለያዩ አለማት የግልም ሆነ የመንግስት ባንኮች ቅርንጫፍ መክፈት እንደሚጠበቅ፤ በሀገር ውስጥ ያለውንም ህገወጥ የውጭ ምንዛሬ የገንዘብ ዝውውር እንቅስቃሴ
.መቆጣጠር አሊያም ወደ ህጋዊ መስመር ሊገቡ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚጠበቅ ይጠቁማሉ።
በአጠቃላይም እንደ ህንድ ካሉ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር የዳያስፖራው ተሳትፎ ዝቅተኛና ብዙ መስራት የሚጠበቅበት ነው የሚሉት ዶክተር ዘላለም። ለዚህም ዳያስፖራው ለሚያደርገው ተሳትፎ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር በመንግስት ስር ያሉ ተቋማትን አሰራር ምቹ ማድረግ፤ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድን ጨምሮ ከዳያስፖራው ጋር የሚሰሩ ማህበራትና ተቋማትን ማበረታታት፤ ማስፋፋትና መደገፍ፤ እንዲሁም ዳያስፖራው በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እንዲያውቅና ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከሀገር ውጪ ያለው ማህበረሰብ የት በምን አይነት ሁኔታ እንዳለና ለሀገሪቱ እያደረገ ያለውንም አስተዋጽኦ እየተከታተሉ፤ እየመዘገቡና እየገመገሙ ማስቀመጥ የዳያስፖራው ተሳትፎ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
“የዳያስፖራው ለሀገር ብልጽግና እያደረገ ያለው ተሳትፎ ከሚጠበቀው አንጻር አመርቂ ባይሆንም በየጊዜው ለውጥ አለ። በተለይ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጉብኝት ተከትሎ የተጀመረው መነሳሳት ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ነው” የሚሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የዳያስፖራ ተሳትፎ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ባዬ ናቸው። ዳይሬክተሩ እንደሚያብራሩት፤ ባለፈው አመት በአውሮፓና በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካነጋገሯቸው በኋላ አበረታች ለውጥና መነቃቃት እየታየ ይገኛል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በፊትም ዳያስፖራው በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች እየተሳተፈ ቢሆንም አብዛኛው እንቅስቃሴ ፖለቲካን መሰረት አድርጎ ጎራ በመለየትና በመነታረክ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በመቀበል ሀገር ውስጥ በመግባት የተለያዩ ስራዎች በመስራት ላይ የሚገኙትም በርካቶች ናቸው።
ይህም ሆኖ አሁንም የዳያስፖራውን ተሳትፎ የሚገዳደሩ ተግዳሮቶች አሉ። ለምሳሌ ዳያስፖራው ገንዘብ ወደ ሀገር ውስጥ ለመላክ በስፋት ህጋዊ የገንዘብ ማስተላለፊያ ዘዴዎችን ሲጠቀም አይታይም። ለዚህ ደግሞ ከግንዛቤ ባለፈ ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ስለነበሩ ነው። የመጀመሪያው ተደራሽነት ነው። በተለያዩ የአለም ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ የሚላክባቸው በቂ ህጋዊ የገንዘብ አስተላላፊ ባንኮች የሉም። በሁለተኛ ደረጃ ያሉትም ቢሆኑ ከጥቁር ገበያው ጋር ሲነጻጸሩ የአገልግሎት ክፍያቸው ውድ በመሆኑ በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ በአረብ ሀገራት የሚገኙ ዜጎች ገንዘባቸውን የሚልኩት ሰው በሰው እያፈላለጉ ነው።
በመሆኑም፤ በኤጀንሲው በኩል በአንድ ወገን ገንዘቡ በህጋዊ መንገድ መንቀሳቀሱ ለላኪዎቹ ዋስትና እንዳለው፤ በሌላ በኩልም በህጋዊ መንገድ ገንዘብን ማንቀሳቀስ የሀገር ልማትንና ብልጽግናን መደገፍ በመሆኑ ይህንን ተረድተው በተቻለ አቅም ወደህጋዊ መስመር እንዲገቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ ነው። የሀገር ውስጥ ባንኮችም በአለም አቀፍ ደረጃ ገንዘብ ከሚያስተላልፉ ተቋማት ጋር አብረው ለመስራት የጀመሩትን እንቅስቃሴ የመደገፍ ስራ ይሰራል።
ዳይሬክተሩ በእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንም ሲያብራሩ፤ አንዳንድ ግለሰቦች ራሳቸው ተሰባስበው በመደራጀት ሀገር ቤት ገብተው ያላቸውን እውቀትና ልምድ የሚያስፋፉ አሉ። በቅርቡ በአብዛኛው በአሜሪካ ተቀማጭ የሆኑና ከአውሮፓም የተውጣጡ ምሁራን “ተስፋ” የሚባል ድርጅት መስርተው በነሀሴ ወር ለሲቪል ሰርቪሱ በተለያዩ መስኮች የአቅም ግንባታ ስልጠና በነጻ ሲሰጡ ቆይተዋል። በአሜሪካ የሚኖሩ ሀኪሞችም ነጻ የህክምና አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ለጥቁር አንበሳና ለቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችንም አበርክተዋል።
“ባጠቃላይ፤ እስካሁን በስፋት እንደሚስተዋለው ዳያስፖራው በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የላቀ ተሳትፎ እንዲኖረው ለማስቻል በመንግስትም በኤጀንሲውም በኩል እየተሰራ ይገኛል።” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለይ ሀገር ቤት ከገቡ በኋላ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ውጭ ላሉትም ጥሩ መልእክት እንዲያስተላልፉ ለማስቻል ዳያስፖራዎች አንዳንድ ማነቆዎች ሲገጥሟቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት የመፍታት ስራ ይሰራል። ለዚህም በኤጀንሲው በየክልሉ የተቋቋሙት የዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ። በተጨማሪም በውጪው አለም በምን ደረጃ ምን ያህል ኢትዮጵያዊ እንዳለ ማወቁ ተሳትፎውን ለማጠናከር መሰረት ቢሆንም እስካሁን ግን ትክክለኛው እንደማይታወቅ በመጠቆም ለዚህም በቅርቡ የዳያስፖራ ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ከመንግስት በየመንደሩ የሚከናወኑትን የጥቁር ገበያ እንቅስቃሴ መቆጣጠር፣ እንዲሁም የመንግስትም ሆነ የግል ባንኮች ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚገኙባቸው ሀገራት ቅርንጫፍ ቢሮዎች እንዲከፍቱና የአገልግሎት ክፍያ ዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርጉ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። በተመሳሳይ ዳያስፖራው ለልማትም ሆነ ለበጎ ፈቃድ ወደ ሀገሩ ሲመጣ የሚገጥሙትን ችግሮች እየተከታተሉ በመቅረፍና ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ለሀገሩ ልማትና ብልጽግና የሚያደርገውን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክር ማድረግ ከእያንዳንዱ የመንግስት የስራ ሃላፊ የሚጠበቅ ይሆናል።
አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም
ራስወርቅ ሙሉጌታ