ወጣት ምሩጽ ሀይሉ ቅድስተ ማርያም አካባቢ ነዋሪ ሲሆን አራት ኪሎ አካባቢ የሚገኘው ውሃና ፍሳሽ መስሪያ ቤት ባልደረባ ነው። 2011 ጥሩም መጥፎም ነበር። በዓመቱ የተከሰቱ አንዳንድ ነገሮች ደስታን የሚፈጥሩ ሆነው አልፈዋል። በግል ሕይወቱ በርካታ ጥሩ ሥራዎችን የሰራበት ስለነበር አስደሳች ዓመት ነበር። አንዳንድ በሀገሪቱ የነበሩ ነገሮች ደግሞ የሚያሳዝኑ ነበሩ። በተለያዩ ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ የነበሩበት ነው። ይህ የሚያሳዝን ነበር። አዲስ ዓመትን በአዲስ መንፈስ ለመቀበል ዝግጅት ላይ ነው። ለበዓሉ አስፈላጊ ግብዓቶችንም እያዘጋጀ ነው።
በ2012 በግል ሕይወቱም ሆነ በሀገር ደረጃ ብሩህ ተስፋ እየታየው እንደሆነ የሚናገረው ምሩጽ ብሩህ ዓመት እንደሚሆን ባለሙሉ ተስፋ ነው። ምክንያቱም አሁን ከሰላምም አንጻር የሚስተዋሉ ችግሮች እየተቀረፉ ናቸው። አንጻራዊ ሰላም እየታየ ነው። የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለው ሀገሪቷ ወደ ቀድሞ ሰላሟ ትመለሳለች የሚል ተስፋ
ሰንቋል።
አዲሱ ዓመት መልካምም ሆነ መጥፎ እንዲሆን የምናደርገው እኛ ዜጎች ራሳችን ነን የሚለው ምሩጽ፤ ሁሉም ዜጋ መልካም ከሰራ ሀገሪቷ መልካም እንድትሆን ይረዳታል። እኔ በራሴ ለራሴም ሆነ ለሀገሬ መልካም ነገሮችን ለማድረግ ዝግጁ ነኝ። ከዚህ ቀደምም ለሀገሬ አስተዋጽኦ ለማበርከት የጀማመርኳቸው ሥራዎች አሉ። በክረምት ወራት በበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ ስሳተፍ ነበር። ይህንን በበጋውም ወቅት ለማከናወን አቅጃለሁ። ከዚህ ቀደም በአቅሜ የምረዳቸው ሰዎች አሉ። እነሱን መርዳቴን እቀጥላለሁ። ራሴንም ከመጥፎ ነገሮች በመጠበቅ ለሀገር ራስ ችግር እንዳልሆን እጠነቀቃለሁ። የተሳሳቱ ሰዎችን እንዲታረሙ በመርዳት እሳተፋለሁ ብዬ አስባለሁ።
በአዲሱ ዓመት ለሀገሬ ከምንም በፊት ሰላም ነው የምመኘው። እኛም የምንኖረው ሰላም ሲኖር ነው። ለመኖር ብቻ ሳይሆን ሞቶ ለመቀበር ራሱ ሰላም ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር ሀገሬ ሰላም እንድትሆን፣ እንድትበለጽግ፣ አሁን ከሚታዩ ከመጥፎ ነገሮች የምንላቀቅበት፣ ጽንፈኛ ብሔርተኝነትና ጎሰኝነት የምንላቀቅበት እንዲሆን እመኛለሁ። ያለው ለተቸገረው የሚረዳበት፣ እንዲሁም ያለንን በማካፈልም ለሰዎች የምንደርስበት እንዲሆን እመኛለሁ። እኔም ለነዚህ ነገሮች የበኩሌን የአቅሜን እወጣለሁ ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን መስከረም 1 /2012
መላኩ ኤሮሴ