ወጣት ወሰኔ ታጠቅ በአራት ኪሎ አካባቢ የጀበና ቡና ትሸጣለች። ባለፈው ዓመት ብዙ ደስ የማይሉ ነገሮች እንዳጋጠሟት ትናገራለች። ሥራዋን በአግባቡ ለመስራት የማያስችሉ ነገሮች አጋጥሟት ነበር። በሀገሪቱ ውስጥ የነበረው ሰላም መደፍረስም አሳስቧት ነበር። ባለፈው ዓመት የነበሩ መጥፎ ነገሮች ካለፈው ዓመት ጋር አብሮ ይሄዳል የሚል እምነት አላት። በአዲስ ዓመት ነገሮች እንደሚስተካከሉ ተስፋ አድርጋለች። አዲስ ዓመት አዲስ ጥሩ ነገር ይዞ ይመጣል የሚል ተስፋ አላት። አዲስ ዓመት በመምጣቱ ደስ የሚል ስሜት እየተሰማት ነው።
በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያውያን ሰላም ፍቅር አንድነት ትመኛለች። ጽንፍ የወጣ ብሔርተኝነት የማይኖርበት፣ ታናሽ ታላቁን የሚያከብርበት፣ ዜጎች የሚዋደዱበት፣ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰርተው ራሳቸውንና ሀገራችንን የሚጠቅሙበት ዓመት እንዲሆን ትመኛለች። በአዲሱ ዓመት አምና የነበሩ ችግሮች እንዳይቀጥሉ ሁሉም የበኩሉን ሊሰራ ይገባል የምትለው ወሰኔ፤ እሷም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሥራዋን ጠንክራ በመስራት ራሷንና ሀገሯን ለመጥቀም እንደምትንቀሳቀስ ትናገራለች። በሥራዋ ውጤታማ መሆን ትሻለች። አቅሟ የቻለውን ሁሉ ለሀገሯ ለማድረግም ዝግጁ ነች። ከዚህ በላይ ራሷንና ሀገሯን እንድትጠቅም ድጋፍ ግን ያስፈልጋታል።
መንግሥት ወጣቱ ወደ ሥራ የሚገባበትን ሁኔታ ሊያመቻች ይገባል። በሥራ ዕድል ፈጠራ አካባቢ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችም መስተካከል አለባቸው። ለሥራ አጦች በተበጀተው በጀት ቤተሰብና ጓደኛ የመጥቀም አካሄድ በአዲሱ ዓመት ሊቆም ይገባል። ሁሉም ዜጋ እንደመሆኑ ለሁሉም ዜጋ ፍትሃዊ አገልግሎት መቅረብ አለበት። አሁን ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ የተመደበው ገንዘብ በተገቢው መንገድ ለወጣቶች እንዲደርስ ተገቢው ክትትል ሊደረግ ይገባል። እነዚህ ችግሮች የሚቀረፉ ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። የሕግ የበላይነትን ከማስፈን ረገድ የሚታዩ ችግሮችም መቀረፍ አለባቸው።
አዲስ ዘመን መስከረም 1 /2012
መላኩ ኤሮሴ