አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት ተግባር ላይ በተሰማሩና ህጋዊ ፈቃድ በሌላቸው ኤጀንሲዎች ላይ ተገቢውን ርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ ።
ቢሮው በዘርፉ ከተሰማሩ ኤጀንሲዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
አቶ ካሳ ስዩም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ስምሪት አገልግሎት ማስፋፊያ ዳይሬክተር እንደገለጹት፤ በህጋዊ መንገድ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ከሚንቀሳቀሱት ድርጅቶች ይልቅ የህገወጦቹ ቁጥር ያሻቀበ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በአሁኑ ጊዜ ህጋዊ ፈቃድ የተሰጣቸው 454 ኤጀንሲዎች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ በሥራ ላይ የሚገኙት 303 ብቻ ናቸው። ይሁን እንጂ፤ መንግሥት ባደረገው ጥብቅ ቁጥጥር በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ሥፍራዎች ቢሮ በመክፈት ያለምንም ፈቃድና ህጋዊ እውቅና በመስራት ላይ የሚገኙ 995 ህገወጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች መኖራቸውን አረጋግጧል።
ቢሮው ለሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ፈቃድ ሲሰጥ ቅጥርን፣ ሥራ ፈጠራን፣ ዕድገትና ስልጠናን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ እስካሁንም ወቅታዊና ታማኝ የሥራ ገበያ መረጃ በመስጠት ጊዜና ጉልበት ቆጣቢ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። ይህ በመሆኑም ባለፉት ሦስት ዓመታት በውስን ህጋዊ ኤጀንሲዎች ብቻ በተደረገው ጥናት ለ54 ሺህ 624 ሰዎች የሥራ ዕድል ለማመቻቸት ተችሏል።
በውይይት መድረኩ በተለይም የሠራተኞችን ቅጥር አስመልክቶ በአንዳንድ ኤጀንሲዎች አሰራር ላይ ቅሬታዎች ተነስተዋል። ከተሳታፊዎች በቀረበው አስተያየት በጥቂት ኤጀንሲዎች ብልሹ አሰራር የበርካቶች ስም መጠልሸት እንደማይኖርበት ተገልጿል። ህገወጥ አሰራር ተከትለው በርካቶችን ለችግር በሚዳርጉ ኤጀንሲዎች ላይ ርምጃ ሊወሰድ ይገባል ያሉት ተሳታፊዎች፤ በቢሮው በኩል የሚስተዋሉ የቁጥጥር ክፍተቶች እልባት ሊበጅላቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2011
መልካምስራ አፈወርቅ