አዲስ አበባ፡- በኦሮሞ ታሪክ እና በገዳ ሥርዓት ላይ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ጥናት ያደረጉት ኤርትራዊው ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ በኢትዮጵያ የታሪክ መዝገብ እና በኦሮሞ ሕዝብ ልብ ሁሌም እንደሚታወሱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የገዳን ዴሞክራ ሲያዊ ሥርዓት ለዓለም ላስተዋወቁት ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ የክብር ዶክትሬት ሰጠ። በወቅቱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ እንደገለጹት፤ ፕሮፌሰር አስመሮም በኦሮሞ ህዝብ ማንነትና ጥንታዊ ስልጣኔ ላይ አተኩረው ባከናወኑት ጥናት በኢትዮጵያ የታሪክ መዝገብ እና በኦሮሞ ሕዝብ ልብ ሁሌም ሲታወሱ ይኖራሉ።
እንደ አቶ ለማ ገለጻ፤ ዓለም አቀፋዊው ምሁር ፕሮፌሰር አስመሮም የዛሬ 45 ዓመት በሳይንሳዊ ትንተና ተመስርተው ስለገዳ ሥርዓት መጽሐፍ አሳትመዋል። ጥናቱም የገዳን ዴሞክራሲ ለዓለም ያስተዋወቀ ነው። በዚህ ሥራቸው ለዘመናዊ የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክና ባህል ጥናትና ምርምር የማዕዘን ድንጋይ የሚሆን ሥራ በማስቀመጥ የላቀ ድርሻ ካበረከቱ ምሁራን መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ የሕዝብ ባለውለታ ናቸው።እኝህ ምሁር በኦሮሞ ታሪክ፣ ባህል እና ፍልስፍና ላይ ባካሄዱት ሰፊ ምርምር፤ ባሳተሟቸው መጻሕፍት እና የገዳ ሥርዓትን ለዓለም በማስተዋወቅ ሁሌም ይታወሳሉ።
እንደ አቶ ለማ ገለጻ ፤ ፕሮፌሰሩ የገዳን ሥርዓት በማጥናት እና ወደ መጽሃፍ በመቀየር ድንቅ ተግባር ፈጽመዋል። ይህም የእርሳቸውን ትዕግስት፤ ጥንካሬ እና ቁርጠኝነት በላቀ ደረጃ የሚያረጋግጥ ነው። ይህ ተምሳሌትነታቸውም በትውልድ መወረስ ይገባዋል። የተጀመረው የገዳ ስርዓት ምርምርና ጥናት ከዳር እንዲደርስ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል።
ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ በበኩላቸው፤ በተሰጣቸው የክብር ዶክትሬት የተሰማቸው ደስታ ልዩ መሆኑን ገልጸዋል፣ በቀጣይ ጊዜያትም ስለኦሮሞ ባህል እና የገዳ ስርዓትን የሚተነትን መጽሐፍ ለማሳተም በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ ያለው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደ ገዳ ያሉ የማህበረሰቡ ባህላዊ ተቋማት ጥቅም ላይ መዋል እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እንደገለጹት፤ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ለፕሮፌሰር አስመሮም የክብር ዶክትሬት ለመስጠት ሲወስን በርካታ የባህል እና የታሪክ አስተዋጽኦአቸውን ተመልክቷል። ተመራማሪው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስተዋወቁት የገዳ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ለማህበረሰብ ዕድገትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያበረከቱት አስተዋጽኦም ከግምት ውስጥ ገብቷል። ገዳ ከአደጉት አገራት የዴሞክራሲ ሥርዓት የተሻለ መሆኑን በጥናት ያሳዩ ምሁር በመሆናቸው የክብር ዶክትሬቱ ይገባቸዋል።
ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ የተወለዱት በ1930ዎቹ ዓ.ም አስመራ ከተማ ውስጥ ነው። ዕድገታቸውም በቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር ውስጥ ሲሆን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በአሜሪካው ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በአንትሮፖሎጂ ትምህርት ዶክትሬታቸውን አግኝተዋል። በኦሮሞ ባህልና ታሪክ በተለይም በኢትዮጵያ እና ኬንያ ቦረና አካባቢዎች ትውፊቶች ላይ ከግማሽ ምዕተ ዓመት የዘለቀ ጥናት ሰርተዋል። ለጥናትና ምርምር የሚጋብዙ መጻሕፍትንም አሳትመዋል። ፕሮፌሰር አስመሮም ከረጅም ዓመታት በኋላ አዲስ አበባ ሲመጡም ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2011
በጌትነት ተስፋማርያም