
አዲስ አበባ፡- የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የጡረታ ቁጠባን ለግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ በማቅረብ የበጀት ጉድለት ማሟያ ማድረጉን ከቀጠለ መንግሥት ችግር እንደሚገጥመው አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳባ ኦሪያ፤ የመንግስት ሰራተኞች ቁጠባ 76 ቢሊዮን ብር ቢደርስም በገቢ ማስገኛ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ በማዋል ኤጀንሲውን ተጠቃሚ በማያደርግ ሁኔታ ለበጀት ጉድለት ማሟያ እንዲውል መደረጉ ቁጠባው ተዳክሞ መንግሥት ችግር ላይ ሊወድቅ እንደሚችል አሳስበዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ በኤጀንሲው የማቋቋሚያ አዋጅ የጡረታ አቅድ ቁጠባን በተመለከተ ገንዘብ ሚኒስቴር መመሪያ በማውጣት ለኢንቨስትመንትና ለቦንድ ሽያጭ እንደሚውል የሚደነግግ ቢሆንም፤ ሚኒስቴሩ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ኢንቨስትመንት ለማካሄድ መመሪያ ባለማውጣቱ በአዋጅ የተሰጠውን ሥራ አልሰራም።
በአዋጁ መሰረት ቁጠባውን በወለድ ለኢንቨስትመንት እንዲውልና ገቢ እንዲያገኝ አልተደረገም፡፡ ሂደቱ ከወቅቱ የብር የመግዛት አቅም መቀነስ ጋር ተያይዞም መንግስትን ችግር ላይ ይጥለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ‹‹ ባለፉት ስድስት ዓመታት ባደረገው ጥናት የብር የመግዛት አቅም በየዓመቱ በአማካይ 13 በመቶ ቀንሷል። ይህ ማለት የቁጠባ አቅዱ ገንዘብ በወል የመግዛት አቅሙ በየዓመቱ 13 በመቶ ይቀንሳል ማለት ነው። ይህም ጡረተኞች ከጊዜው ጋር የሚሄድ ክፍያ እንዳይፈፀምላቸው ያደርጋል›› ብለዋል።
መንግስት የቁጠባ አቅዱን ለበጀት ማሟያ ማድረጉን አቁሞ ባንኮች በሚያበድሩበት ወለድ መጠን በጥናት ተለይተው አዋጭ ለሆኑ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ማበደር ካልቻለ ቁጠባው ስለሚዳከም በጡረታ ፋይናንስ አስተዳደር ውስጥ መቀጠል ስለማይችልና እዳ ውስጥ ስለሚገባ ከበጀቱ አውጥቶ ለመክፈል እንደሚገደድ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ የጡረታ ቁጠባውን የበጀት ጉድለት ማሟያ ማድረግ የአስተዳደር ችግር ስለሆነ መንግስት እጁን ከማህበራዊ ዋስትና ቁጠባ ፋይናንስ ላይ መሰብሰብ አለበት፤ ይህ ካልሆነ ግን ሠራተኛው በዋስትናው ላይ እምነት እንዲያጣ ያደርጋል ብለዋል።
ከማህበራዊ ዋስትና የሚሰበሰበው ገንዘብ የአገራዊ ቁጠባ አካል ነው፡፡ ቁጠባው ለበጀት ጉድለት ማሟያ ሳይሆን ለዋስትና መዋል አለበት። ሰራተኞች ግብር ከፍለው ለዋስትና የቆጠቡትን ገንዘብ ለበጀት ማሟያ ማዋል ሁለት ጊዜ ግብር እንዲከፍሉ ማድረግ በመሆኑ ትክክል እንዳልሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
‹‹ዛሬ ለጡረተኞች እየከፈልን ያለነው ገንዘብ ከወቅቱ የኑሮ ሁኔታ ጋር አይሄድም። ይህን ማሻሻል የሚቻለው የጡረታ አቅዱን ቁጠባ አዋጭነቱ ለተረጋገጠ ኢንቨስትመንት በማበደር ከፍተኛ የወለድ ገቢ በማግኘት ነው። ይህን ማድረግ ከተቻለ የዛሬ ሠራተኞች የነገ ጡረተኞች የተሻለ ክፍያ እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል። የአቅዱን ቁጠባ ማስተዳደር ያለበትም ኤጀንሲው ነው›› ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ኤጀንሲው የማሻሻያ ጥናቱን አጠናቅቆ ለሥራ አመራር ቦርዱ አቅርቧል፤ መንግስት ማሻሻያውን ሲቀበል የጡረታ ፈንዱን በምን ላይ ማዋል አንዳለበት አሰራር ይዘረጋል። ይህን ለማድረግ በማሻሻያው የኤጀንሲው አሰራር፣ መዋቅሩና አዋጁ መቀየር አለበት። ይህ ከሆነ የመንግስት ሰራተኞች ጡረታ
ቁጠባ ባንኮች በሚያበድሩበት ወይም በተወሰነ ደረጃ ዝቅ ባለ መልኩ በማበደር ለኢንቨስትመንት ይውላል፤ ኤጀንሲውም ከፍተኛ ወለድ ያገኛል ።
ኤጀንሲው በ2011 በጀት ዓመት 22 ቢሊዮን ለመሰብሰብ አቅዶ 26ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ሰብስቧል። ከዕቅዱ በላይ አራት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ጭማሪ የመጣውም ሦስት ሺ141 አሰሪ መስሪያ ቤቶች መዋጮ በመሰብሰባቸው፣ ምርመራ በማድረግ ያልከፈሉት እንዲከፍሉ አስተዳደራዊ ርምጃ በመውሰድ፣ ማስጠንቀቂያ በመስጠትና ክስ በመመስረት ከ320ሚሊዮን ብር ውዝፍ ውስጥ 40 በመቶ ገቢ መደረጉና የልማት ድርጅቶች የደመወዝ ጭማሪ በመኖሩ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
በዘንድሮው በጀት ዓመት 10 ተቋማትና አምስት የተቋማት ኃላፊዎች መክሰሳቸውን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በኃላፊዎች ላይ ክስ በመመስረቱ ለውጥ መምጣቱን፣ በአንዳንድ ቦታዎች የመንግስት መዋቅር ላይ የህግ ተፈፃሚነት መሸርሸሩን፣ባልከፈሉት ላይ ምርመራ ተደርጎ እንዲከፍሉ ሲነገራቸው ‹‹አንፈርምም›› በማለት የጡረታ መዋጮ ለማስከፈል በድርድር ችግሩን ለመፍታት እንደሞከሩ ፣ አንዳንድ ተቋማት ክፈሉ
ሲባሉ ስራ ለማቆም እንደሚፈልጉ ወይም የመንግስትን አገልግሎት ስለሚያቆሙ ለችግሩ እልባት ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩም እንደሆነም ተናግረዋል።
በ2011 በጀት ዓመት ኤጀንሲው ካለው 76 ቢሊዮን ብር ለመንግስት የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ አንድ በመቶ ወለድ በማቅረብ 782 ሚሊዮን ብር የወለድ ገቢ አግኝቷል። ይህን ገንዘብ ባንኮች ከሚያበድሩበት ወለድ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው።
የግልና የመንግስት ባንኮች የሚያበድሩበት ወልድ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት በዝቅተኛው ወለድ ዘጠኝ ነጥብ አምስት በመቶ ሲሆን፤ ከፍተኛውና እስከ 25 ዓመት የሚደርሰው የረጅም ጊዜ ወለድ ደግሞ 18 ነጥብ ስድስት በመቶ ነው። ኤጀንሲው ያለውን 76 ቢሊዮን ብር ቁጠባ ለአጭር ጊዜ ቢያበድር ከፍተኛ ወለድ ያገኝ እንደነበር የባለሙያዎች ማብራሪያ ያስረዳል።
በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ዝግጅት ክፍሉ የጠየቃቸው የገንዘብ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሀጅ ኢብሳ “ምላሽ የለኝም ብሏል ብለህ” ጻፍ በማለት ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን ጋዜጠኛው ጆሮ ላይ ዘግተዋል።
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 6/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ